ሰላማዊትውቤ
ቡና የሚቀመሰው ጣዕሙንና ጥራቱን ለመለየት ብቻ አይደለም። በዓለም የቡና ገበያ ከፍተኛውን የሽያጭ ዋጋ እንዲያስገኝ በማሰብም ጭምር ነው። ሆኖም ጥራቱ ጣዕሙን ጣዕሙ ደግሞ ጥራቱን የሚወክል እንደመሆኑ የሚያወጣው ዋጋ በነዚሁ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ይመሰረታል። ያለጥራትና ጣዕም ስለ ዋጋ ማውራቱም የማያዋጣ አለመሆኑ ግልፅ ነው።
በዓለማችን ብሎም በሀገራችን የሚደረጉ የቡና ቅምሻ ውድድሮች እነዚህን ሁለት ነጥቦች መሰረት አድርገው ነው የሚካሄዱት።
ይሄ ደግሞ ብልህነት የተላበሰና ዘመናዊ አሰራር ከመሆኑ ባሻገር በቡና ገበያ የቀረበ ቡና ተመራጭ ዋጋ እንዲያገኝ ያስችላል። ጥራቱን ለማረጋገጥ መልኩን ብቻ ማየት በቂ አይደለም። ቀምሶ በማጣጣም ጣዕሙን መለየት ያስፈልጋል።
እንዲህ ያለው የቡና ጥራት ማረጋገጫ ሂደት ቡና አምራቹ የልፋቱን ዋጋ እንዲያገኝ ያስችለዋል። ኢትዮጵያ የቡና ጥራትን በጣዕም ውድድር ወደ ማረጋገጥ ሥራ የገባችው ገና በቅርብ ጊዜ በመሆኑ ተሞክሮው በመዳበር ላይ ይገኛል።
ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ሀገር ሆና፣ በግልና በማህበራት አማካኝነት በሥፋት ቡና ለዓለም ገበያ እያቀረበች እንዲሁም እውቅናን እንድታተርፍ ሰፊ ቁጥር ያለው ቡና አምራች አርሶ አደሮችና ባለሀብቶች ያሉባት ከመሆኗም አኳያ የቡና ጣዕም እያረጋገጡና እያወዳደሩ ለገበያ ማቅረብ ላይ ፈጥና አለመግባቷ ሊያነጋግር ይችላል።
ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገራችን በተካሄደ የምርጥ ቡና ቅምሻ ውድድር ኢትዮጵያ አሸናፊ ለመሆን በቅታለች። እ.ኤ.አ ጁላይ 24/2020 በተደረገ ጨረታ አንድ ኪሎ ግራም ቡና በ407 የአሜሪካ ዶላር በወቅቱ በነበረ ምንዛሪ በኢትዮጵያ ብር ሲለወጥ ደግሞ በ14 ሺህ ብር ነበር።
በዚህ ረገድ ተጠቃሚ ለመሆን ችላለች። በሀገር ውስጥ ገበያ ግን ሽያጩ ከ200 ብር በላይ አልነበረም። ወደዚህ ሥራ ቀድሞ ቢገባና በውድድሩ ላይ መሳተፉም ጎልብቶ ቢሆን ከፍተኛ ጥቅም ይገኝ እንደነበር ከቅርቡ ተሞክሮ መገንዘብ ይቻላል።
ቡና አምራቹም ለተሻለ ጥራት በመሥራት ይነቃቃ ነበር። የተሻለ ገቢ ሲያገኝ ኑሮውም በዚያው ልክ ይለወጣል። እንደሀገርም ጥሩ ገጽታ ይገነባል።
ለሀገራችን ሁለተኛው የምርጥ ቡና ቅምሻ ውድድርም ሰሞኑን በሂልተን ሆቴል ይፋ ሆኗል። ቀደም ብለው መገኘት ሲገባቸው ያልተገኙ ዕድሎች የረፈዱ ቢሆኑም አሁን ላይ መጀመራቸውም በመልካም ጎን መታየት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ ጃና ነግረውናል። በዚህ እየቀጠለ ከሄደ ሰፊ ቁጥር ያለው ቡና አምራች አርሶአደር ተጠቃሚነቱ እየጎለበተ እንደሚሄድም አመልክተዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም በዓይነቱ በጣም የተለየና ተመራጭ ነው።
ይሄ ቡና ተገቢውን ዋጋ ማግኘት ከቻለ በራሱ ልማቱን ለማስፋት እና ጥራቱን በተሻለ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚያስችል አቅም ይፈጥራል። ሀገራችን በአፍሪካ ከፍተኛ መጠን ያለው የቡና ምርት ከሚያቀርቡ ሀገሮች አንዷ መሆን የቻለችውም ለዚህ ነው። ይሁንና ኢትዮጵያ በደረጃውና በጥራቱ መጠን ተገቢውን ዋጋ አላገኘችም።
የቡና አምራቹ አርሶ አደርም የምርቱን ያህል በገበያ ተጠቃሚ አልሆነም። በመሆኑም እየተካሄደ ያለው የሁለተኛው የምርጥ ቡና ቅምሻ ውድድር ሀገሪቱ ተገቢውን ዋጋ እንድታገኝ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል።
ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ አርሶ አደሩ ምርቱን በቀጥታ ለውጪ ገበያ አቅርቦ በመሸጥ የተሻለ ጥቅም እንዲያገኝ ማስቻል፣ ፍትሃዊ የሆነ የውድድር መንፈስ በመፍጠር አርሶ አደሩ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ስርዓት ይፈጥራል።
ለሀገሪቱ የመጀመሪያው የሆነው የቡና ቅምሻ ውድድር ብዙ ፋይዳዎች አስገኝቷል። ባለፉት ጊዜያቶች የቡና ዋጋ በመውረዱና የሚገኘው ጥቅም እያነሰ በመምጣቱ የቡና ተክል በመንቀል እንደጫት ባሉ የተክል አይነቶች የመቀየሩ እንቅስቃሴ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።
ውድድሩ የፈጠረው መነቃቃት ብዙዎችን ወደ ቀድሞ ቡና አምራችነታቸው እንዲመለሱ እያደረጋቸው እንደሆነ ከውድድሩ ለመረዳት ተችሏል። በገበያ በላይ የሚፈጠረውን ማጭበርበር ለመቀነሥም ዕድል ሰጥቷል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት ኢትዮጵያ እስከአሁን በነበራት የቡና ገበያ በብሄራዊ ደረጃ ብራንድ አልነበራትም።
ቡናው ውጪ ሀገር ሲሄድ የራሷን መብት ማስከበር የምትችልበት አሰራርም አልፈጠረችም። ይህ ደግሞ ተጎጂ ሲያደርጋት ቆይቷል።
ከውድድር በኋላ ግን ብሄራዊ ብራንድ ማዘጋጀት ተችሏል። እንዲሁም የሀብት መብት ማስመዝገብ ሥራዎች የተጀመረ ሲሆን፣ ቡና ለገበያ በምታቀርብባቸው ሀገሮች ማስመዝገቡ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። የራስ መለያ (ብራንድ) መኖሩ በራሱ ዋጋ አለው። ገበያ ይፈጥራል፤ እውቅናን ያስገኛል።
በቴክኖሎጂ የታገዘ ግብይት በማካሄድም አርሶ አደሩና ገዥው በቀጥታ እንዲገበያዩም ሥራዎች መጀመሩን፣ ባለስልጣኑ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ስትራቴጂ በመንደፍና ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን፣ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ ሁለተኛው የምርጥ ቡና ቅምሻ ውድድር የስትራቴጂው ዋና ተልዕኮ መሆኑን ይናገራሉ።
‹‹ኢትዮጵያ መጥፎ የሚባል ወይንም የሚጣል ቡና የላትም።›› ያሉን የኢትዮጵ ቡና ላኪዎች ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅና የዘንድሮው ውድድር አስተባባሪ አቶ ግዛት ወርቁ በአምናው ውድድር በዓለም አቀፍ ገበያ ከመላው ዓለም 168 ሀገሮች የኢትዮጵያን ቡና ለመግዛት ፍላጎት ማሳየታቸውንና መመዝገባቸውን ነግረውናል።
እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ማብራሪያ ከባለፈው ውድድር አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ዶላር የውጪ ምንዛሪ ገቢ ተገኝቷል። በዘንድሮ የሁለተኛው ውድድር የበለጠ ይጠበቃል። በአምናው ውድድር ላይ 1ሺ400 አርሶ አደሮች የተሳተፉ ሲሆን፣ ዘንድሮ የተወዳዳሪዎቹ ቁጥር ወደ 2ሺ ከፍ ብሏል። የተሳታፊዎችን ቁጥር ለመጨመር ቡና አምራች በሆኑ አካባቢዎች ግንዛቤ የመፍጠርና የቅስቀሳ ሥራ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 26 2013