አስናቀ ፀጋዬ
በአማራ ክልል በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ ጥናቶች በርካታ የከበሩ ማእድናት በተለያዩ አካባቢዎች ላይ እንደሚገኙ መረጋገጡን አስታውቋል። በጥናት ከተረጋገጡ የከበሩ ማእድናት ውስጥም ኦፓል በተወሰኑ ደረጃዎች ደግሞ ወርቅ እንደሚገኝ ከክልሉ የማዕድን ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።
የኮንስትራክሽን፣ ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚውሉና የኢነርጂ ማእድናት እንዳሉም በጥናት መረጋገጡን እነዚሁ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የአማራ ክልል የማእድን ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ይታየው ተስፋሁን እንደሚገልፁት የኢነርጂ ማእድናት በተለይ የከሰል ድንጋይ በክልሉ በስፋት የሚገኝ ሲሆን በዋናነት በማእከላዊ ጎንደር ጭልጋ ወረዳ በስፋት መኖሩ ተረጋግጧል። የክምችት መጠኑም 19 ነጥብ 9 ቢሊየን ቶን እንደሚሆን በጥናት ተመላክቷል።
በተመሳሳይ ሰሜን ሸዋ ሙሽ ሸለቆ በሚባል አካባቢ የክምችት መጠኑ 0 ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ የከሰል ድንጋይ ኢነርጂ ማእድን እንዳለ በጥናት የተረጋገጠ ሲሆን በደቡብ ወሎ ውጫሌ ለጌዳ ወረዳ በሚባል አካባቢም የክምችት መጠኑ ሶስት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ የከሰል ድንጋይ እንደሚገኝ ታውቋል።
በሰሜን ወሎ ጉባ ላፍቶ ወረዳም የከሰል ድንጋይ በጥቆማ ደረጃ እንደሚገኝ ተረጋግጧል።
እንደ ሃላፊው ገለፃ በአማራ ክልል የከሰል ድንጋይን ጨምሮ የኢነርጂ ማእድናት በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማስተዋወቅ ስራዎች በየጊዜው ቢሰሩም አልሚዎች በስፋት ገብተው እየሰሩበት አይደለም።
የማእድን ሃብቱን አውጥተው ጥቅም ላይ ለማዋል የተለያዩ አልሚዎች ወደ ኤጀንሲው ቢመጡም ፍቃዱን አውጥተው ወዲያው ወደስራ የመግባት ክፍተትም ይታይባቸዋል።
ባለሀብቶች የኢነርጂ ማእድናትን አውጥተው ጥቅም ላይ እንዲያውሉ በተለያዩ ግዚያት የተለያዩ ሙከራዎች ቢያደርጉም እስካሁን ድረስ ግን አንድም ወደ ስራ የገባ ባለሃብት የለም።
እስከአሁን ድረስ ባለሃብቶች በእነዚህ የኢነርጂ ማእድን ልማት ዘርፍ ደፍረው ያልገቡበት ምክንያት በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ ባጠቃላይ ለማዕድን ዘርፉ በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱ ነው።
ይሁንና ሃገራዊ ለውጡን ተከትሎ የሀገር ውስጥና የውጪ ባለሃብቶች በዚህ ዘርፍ ለመግባት ፍላጎት እያሳዩ መጥተዋል። በአንድ ሳምንት ብቻም ኤጀንሲው ለሃያ ባለሀብቶች ፍቃድ ሰጥቷል።
ቀስ በቀስም ባለሃብቶች ወደዚህ ማእድን እየተሳቡ መጥተዋል። ይሁንና የማእድን ዘርፉ አሁንም ያልተነካ በመሆኑ ዘርፉ በርካታ ባለሃብቶች እንዲያለሙ ይጋብዛል።
ሃላፊው እንደሚሉት በጥናት የተረጋገጡ የብረት ማእድንም በዋግምራ ዞን ሰቆጣ፣ ምስራቅ ጎጃም ዞን መርጦለማርያምና፣ ደቡብ ወሎ ዞን ለጌዳ ወረዳ አካባቢዎች ላይ የሚገኝ ሲሆን የክምችት መጠኑ ግን ገና በጥናት አልተረጋገጠም። ሆኖም የክምችት መጠኑን ለማረጋገጥ የተለያዩ ሙከራዎች እየተደረጉ ይገኛሉ።
ከዚህ በፊት በዋግምራ ዞን ሰቆጣ አካባቢ በብረት ማእድን ልማት የገባ አንድ የውጪ ድርጅት ነበር። ሆኖም ግን የምርመራ ፍቃድ ከወሰደ በኋላ ስራ ሳይጀምር ቀርቷል።
በዚህ የብረት ማእድን ማውጣት ስራ ባለሃብቶች ገብተው እንዲሰሩ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ የነበረ ቢሆንም ባለሃብቶች የመጀመሪያ ምርመራ ፍቃድ ወስደው ቦታውን ከማጠር በዘለለ የሰሩት ስራ አለመኖሩ አቶ ይታየው ይናገራሉ።
ይሁንና በአሁኑ ወቅት በዚሁ የማዕድን ልማት ባለሃብቶችን ለመሳብና የምርመራ ፍቃድ እንዲወስዱ ለማድረግ በኤጀንሲው በኩል የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ነው የገለጹት።
በዘርፉ ባለሀብቶች በደምብ ወደ ስራ አለመግባት ችግሮች ውጪም በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ባለሃብቶች በዚሁ የማዕድን ማውጣት ስራ ለመግባት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። የከፍተኛ ደረጃ ማእድን ማውጣት ፍቃድ በፌደራል ደረጃ የሚሰጥ ከመሆኑም አኳያ በርካታ ባለሃብቶች የማእድን ማውጣት ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የክልሉ የማኔጅመንት ኮሚቴም ተሰባስቦ አንድ ባለሀብት ፍቃድ ከወሰደ በኋላ በስንት ግዜ ወደ ስራ መግባት እንዳለበት የሚያመላክት መመሪያ በውሉ ላይና በአዋጁ ላይ በሰፈረው መሰረት አርባ አንድ የሚሆኑ ከሁለት ዓመት በላይ የሆናቸውና ወደስራ ያልገቡ ባለፍቃዶችን የግዜ ቆይታ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።
በዚሁ ማስጠንቀቂያ መሰረትም እርምጃ ለመውሰድ ተወስኗል። በተመሳሳይ አዲስ ፍቃድ ለወሰዱ ባለሃብቶችም በተሰጣቸው የቆይታ ግዜ ወደስራ ካልገቡ ፍቃዳቸው የሚሰረዝ እንደሆነ በደብዳቤ እንዲያውቁ ተደርጓል።
በዚሁ መነሻነትም ሁለት ባለፍቃዶች የቆይታ ጊዜያቸው እንዲራዘምላቸው ጠይቀዋል። የማኔጅመንት ኮሚቴውም ተወያይቶ ባለሃብቶቹ በተለይ ለማዕድን ምርመራ የሚጠቀሙበት መሳሪያ በውጪ ምንዛሬ እጥረትና በተለያዩ ምክንያቶች ገና ከውጪ ያልገባ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ፍቃዳቸው እንዲራዘም ውሳኔ አሳልፏል።
ለኮንስትራክሽን ግብአት የሚውሉ እምነበረድ፣ ላይም ስቶን፣ ኢግናማራይድ፣ግራናይትና ሳንድስቶንን የመሳሰሉ ማእድናትም በክልሉ በሁሉም ቦታዎች ላይ እንደሚገኙ ከክልሉ የማእድን ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የተገኙ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን ከኢነርጂ ማእድናት በተሻለ በስፋት ፍቃድ ተሰጥቶባቸው ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተደረገ ይገኛል። በስራ እድል ፈጠራም ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 26 2013