መልካሙ ተክሌ
የሰሞኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች አርአያነት አጠያያቂ ነው ለኔ።በቴሌቪዥን የተመለከትኳቸው አብዛኞቹ ተማሪዎች የአፍ እና የአፍንጫ መከለያ ጭንብል አላደረጉም።ካደረጉትም አንዳንዶቹ ጺም መያዣ ይመስል አገጫቸው ላይ እንጂ አፍ እና አፍንጫቸው ላይ አላደረጉም።
በቴሌቪዥን መስኮት የሚመለከቷቸው እነሱን አርአያ ያደረጉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሙዋለ ሕጻናት፣ አንደኛ ደረጃ እና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ጭንብል እንዳያደርጉ መጥፎ ምሳሌ የመሆናቸው ዕድል የሰፋ ነው።ይህም ለኮረና ቫይረስ መዛመት የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ ይፈጥራል።
መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም የመጀመርያው የኮረና ቫይረስ ተጠቂ በኢትዮጵያ ተገኝቶ በማግስቱ ከአዲስ አበባ በሚኒባስ ወጥቼ ነበር።በወቅቱ የሚኒባሱ ተሳፋሪዎች ጥንቃቄ አጀብ የሚያሰኝ ነበር።አሁን የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር በመቶ ሺዎች እየተቆጠረ ግን ያለው መዘናጋት አስደንጋጭ ነው።
በዚያን ጊዜ መንግሥት ከወሰዳቸው እርምጃዎች አንዱ ትምህርት ቤቶችን መዝጋት እና ተማሪዎች ከቤት ሆነው በተለያዩ አማራጮች ከትምህርት ገበታ እንዳይርቁ (ትምህርት እንዲከታተሉ ማለት ይከብዳል) ማድረግ ነው።
የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ብዙ ሰው የሚሰበሰብባቸው ትምህርት ቤቶች ቢዘጉም ተማሪዎች ግን በየሰፈራቸው የትምህርት ቤቱን ያህል ባይሆን መሰብሰባቸው አልቀረም።
ከወራት በኋላ ትምህርት ቤቶች አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደርጎ ይከፈቱ ቢባልም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ተማሪዎች ግን ተገቢውን ጥንቃቄ ሲያደርጉ ማየት አልተዘወተረም።ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአንድ ትምህርት ቤት አጥር አቅራቢያ የተለጠፈ ማስታወቂያ እንዲህ ይላል።
ማስታወቂያ
ለትምህር ቤቱ ተማሪዎች የተሰጠ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ
ከመጋቢት 7/2012ዓ.ም ጀምሮ በኮረና ቫይረስ /በኮቪድ 19 በሽታ ምክንያት ት/ቤቶች መዘጋታቸው የሚታወቅ ነው።ይሁን እንጂ ከትምህርት ቢሮ CRC በስልክ በተላለፈልን መልዕክት መሠረት ከኅዳር 21/2013ዓ.ም ጀምሮ ተቋርጦ የነበረው ትምህርት እንደሚጀመር የተነገረን በመሆኑ፡-
1. እያንዳንዱ ተማሪ አፍንጫውን እና አፉን በማስክ መሸፈን እንዳለበት
2. ወደ መማርያ ክፍሎች ከመግባት በፊት በመግቢያ በር ላይ በተዘጋጀው የእጅ መታጠቢያ ቦታ ላይ እጅን በሳሙና መታጠብ
3. በአንድ ዴስክ ላይ አንድ ተማሪ ብቻ መቀመጥ እንዳለበት
4. በእረፍት ሰዓት ላይ ተራርቆ መናፈስ
5. ወደ መማርያ ክፍል እንዲሁም በመውጫ በር ላይ መገፋፋት እንዳይኖር
6. የህመም ምልክት ወይም ስሜት የሚሰማ ከሆነ ለት/ ቤቱ ቢሮ በፍጥነት ማመልከት
ተማሪዎች ይህንን ሁሉ እና ተያያዥ ነገሮችን አሟልተው ካለፈው ኅዳር ጀምሮ መማር መጀመራቸው ይታወቃል። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ በሳምንት ሁለት ወይ ሦስት ቀን ነው የሚማሩት። ይህ ት/ቤቶች ዝግ ሆነው ከሰነበቱበት ከመጋቢት እስከ ሰኔ እና ከመስከረም እስከ ኅዳር ከነበረው ጊዜ ይሻላል። ቢያንስ ለጥቂት ቀናት ት/ቤት ይሔዳሉና።
ይሁን እንጂ ትምህርት የሚሰጥባቸው ቀናት ብቻ ሳይሆኑ በአንድ የትምህርት ቀን ያሉ ክፍለ ጊዜያት (periods) ርዝመትም እንዲያጥር ሆኗል።አንድ ክፍለ ጊዜ በመደበኛው የትምህርት ጊዜ ከ40-45 ደቂቃ ይረዝም ነበር።አሁን ግን በብዙ ትምህርት ቤቶች 35 ደቂቃ እና ከዚያ በታች ሆኗል።
አንድ መምህር በዕለቱ ለማስተማር ሲገባ በመጀመርያ ያለፈውን ትምህርት ዋና ዋና ሐሳቦች ይከልሳል።ከዚያ የዕለቱን ትምህርት ያቀርባል።ቀጥሎ የዕለቱን ትምህርት አንኳር ነጥቦች ጨምቆ ያቀርባል።የትምህርቱን ማጠ ቃለያ ያቀርብና የዕለቱን ትምህርት አጠናቆ ለቀጣዩ ትምህርት ይዘጋጃል።
በዚህ መልኩ መቅረብ ላለበት ትምህርት የክፍለ ጊዜ ማጠር ካለ ተማሪዎቹን የሚያሳትፍ የክፍል ሥራ መስጠት አይታሰብም።የቤት ሥራ መስጠትም ሆነ ማረም አዳጋች ነው።
በርካታ የቤት ሥራ በመስጠት ግን ተማሪዎች ትምህርት ቤት በማይሔዱበት ቀናት በጥናትና ቤት ስራ እንዲያዙ በማድረግ እና አብዛኛውን ጊዜ ለትምህርት እንዲሰጡ ማድረግ ይቻላል።
ይህ ግን እየተደረገ አይመስልም።
ችግሩን ለማቃለል ጠዋት ትምህርት ቤት የመግቢያ ሰዓት ቀደም በማድረግ እና ክፍሎቹ ፀረ ተሃዋስያን የሚረጩበትን ጊዜ በማቀላጠፍ የማታ ትምህርትን ሳይጨምር ሦስት ፈረቃ ማድረግ ይቻላል።በርግጥ አንድ የትምህርት ቀን ስድስት ክፍለ ጊዜ መሆኑ ቀርቶ አምስት ወይ አራት መሆን ሊኖርበት ነው።ተጨማሪ መማርያ ከፍሎችንም አቅም በፈቀደ ማዘጋጀት ያስፈልጋል።የተማሪዎች መኖርያ ከትምህርት ቤቱ ያለው ርቀትም ከግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል።
በዚህ ለሚከሰተው የመምህራን እጥረት በጎ ፈቃደኞችን ማሰማራት ይቻላል።ይህ ግን ትምህርት ሚኒስትሩ አርአያ ሆነው ባስተማሩበት መጠን ቀጣይነት እንዲኖረው አልተደረገም።
የማስተማር ዘዴውን ተማሪ ተኮር ማድረግም (ይህ ከኮረና ወረርሽኝ ዓመታት ቀደም ብሎ ቢጀመርም) ማጠናከር ይቻላል።መምህር ተኮር ለዘመናችንም ሆነ ለወቅታዊ የኮረና ወረርሽን ይመጥናል አልልም።ባሁኑ ዘመን ተማሪ ተኮር የትምርት አሰጣጥ ነው ተመራጭ።
ከዚህም ሌላ ትምህርቱን በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ማድረግ ነው።ግን ስንት ትምህርት ቤቶች ናቸው ለኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ምቹ የሆነ መሠረተ ልማት ያላቸው? ለሚሊዮኖች ተማሪዎችስ ኮምፒዩተር ማዳረስ ይቻላል ወይ ብሎ መጠየቅ የግድ ነው።አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት ሁኔታ የሚቻል አይመስልም።በእርግጥ እንደ ደቡብ ኮርያ ያሉ ሀገራት ተማሪዎቻቸውን ደብተር የለሽ አድርገዋል-ወረቀት አልባ የኮምፒዩተር ደብተር እንደ ማለት።እኛ ግን ብዙ ይቀረናል።
በውሃ እና በሳሙና መታጠብ ኮረና ባይኖርም መሠረታዊ የጤና አጠባበቅ መርህ ነው።ነገር ግን በሀገራችን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ብዙ ት/ቤቶች እንኳን ለመታጠቢያ ለመጠጥ የሚሆን ንጹሕ ውሃ ማቅረብ አይችሉም።ስለዚህ ኮረናን ለመከላከል እጅን በአግባቡ በሳሙና እና በውሃ መታጠብ የሚለው ምክር ውሃ ማግኘት ለማይችሉት አይሠራም።
ተራርቆ መቀመጥ
ት/ቤቶች በአንድ መቀመጫ ሦስት እና ሁለት ተማሪዎች ያስቀምጡ ነበር።አሁን ግን በአንድ መቀመጫ አንድ ተማሪ ይሁን ተብሏል።ይህ ወረርሽኙን ለመከላከል አንድ አማራጭ ቢሆንም ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የመማርያ ክፍል እና የመምህራን እጥረት መግጠሙ አይቀሬ ነው።ችግሩን ለመቅረፍ የፈረቃ ትምህርት ማጠናከር፣ ተጨማሪ መማርያ ክፍሎች መገንባት እና የሥነትምህርት ዕውቀት ያላቸውን በጎ ፈቃደኞች በመምህርነት ማሰማራት አንድ መፍትሔ ነው።
እነዚህ አማራጮች በትኩረት ካልታዩ ግን ተማሪዎች እንዲማሩ ትምህርት ቤት ቢሔዱም የኮረና ስርጭትን ከመግታት ይልቅ ሊያስፋፉ ይችላሉና መጠንቀቅ የግድ ነው።
(melkamutekle@gmail.com)
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2013