ጽጌረዳ ጫንያለው
ቢሻው በለጠ ይባላሉ። የቀድሞ ማዕከላዊ ማርሽ ባንድ ቴነር ሳክስፎን መሳሪያ ተጨዋች ናቸው። አገራቸውን በደርግ ጊዜ በውትድርናው ዘርፍ እግረኛ እንዲሁም የሙዚቃ መሳሪያ ተጨዋች ሆነው አገልግለዋል። ኢህአዴግ በመግባቱ የተነሳ ስለተበተኑ ራሳቸውን ለማሸነፍ ደፋ ቀና ሲሉ ቆይተዋል። ያልሞከሩት የቀን ሥራም አልነበረም። መጨረሻ ላይ ግን ታታሪና ተወዳጅ ሰራተኛ በመሆናቸው በቋሚነት የተቀጠሩበትን ግብርና ሚኒስቴርን በጥበቃ ሰራተኝነት ተቀላቅለዋል።
አገርን በየትኛውም መስክ ላይ ሆኖ ማገዝ መቻል ታላቅ ደስታን ይፈጥራል ብለው የሚያምኑት ባለታሪኩ፤ ብዙዎች እንዴት ሳክስፎኒስት ወይም ሙዚቀኛ ሆነህ ወደ ጥበቃ ወርደህ ትሰራለህ ይሏቸዋል። ነገር ግን ለእርሳቸው ይህ ወሬ እርባናቢስ ነው። እንደውም መከበር በሙያ እንጂ በልመና እንዳልሆነ እንዲረዱ የሚያደርጉት ብዙ ጊዜ መሆኑን ይናገራሉ። አሁንም ቢሆን ጥበቃነት ትንሽነት አይደለም የሚል አቋም አላቸው።
ለሰዎችም ምላሽ ሲሰጡ ‹‹ጥበቃነት መታመንና ሙያን አክብሮ መስራትን የሚጠይቅ ነው። ለዚህ በመታጨቴ ደግሞ አምላኬን አመሰግነዋለሁ። እኔም ለመኖር አገሬንም ለመጥቀም የሥራ ትንሽ የለውምና አገለግልበታለሁ›› የሁልጊዜ መፈክራቸውም ነው። ለመሆኑ ይህ ጥንካሬያቸው እንዴት መጣ፣ ፈተናዎቻቸው ምን ይመስላሉ እንዴትስ በድል አለፏቸው የሚሉትና መሰል ተሞክሯቸው ለእናንተ ብዙ ልምዶችን የሚያቋድስ በመሆኑ ለዛሬ ‹‹የህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን አድርገናቸዋልና እንድትማሩባቸው ጋበዝን።
ያሻው ይሁንለት ትውልዳቸው እዚሁ አዲስ አበባ ወታደሮችን በምታመርተውና የብዙ አርቲስቶች መፍለቂያ ከሆነችው ፈረንሳይ ለጋሲዮን ነው። ልዩ ስፍራው በተለምዶ ኢየሱስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢም ነው።
በጎረቤት ውስጥ መረዳዳትና መተጋገዝ በበረታበት በ1963 ዓ.ም የተወለዱት ባለታሪካችን፤ ቆንጥጦ ያሳደጋቸው ቤተሰቡ ብቻ ሳይሆን ጎረቤቱም ጭምር ነበር። እርሳቸውም ቢሆኑ ለጎረቤት ሟች እንደነበሩ አይረሱትም። ምክንያቱም ጎረቤት ሲልካቸው የት ወዴት ብለው ነው። የታዘዙትን እንቢ የማይሉ፤ አዛውንቶችን ከሸክማቸው የሚያሳርፉም ልጅ ነበሩ።
እንግዳችን ምንም እንኳን ለቤተሰቡ ሦስተኛ ልጅ ቢሆኑም እንደ መጨረሻም መጀመሪያም ልጅ ነበር ልዩ እንክብካቤ የሚደረግላቸው። በተለይም እናታቸው በጣም ከመውደዳቸው የተነሳ ታናናሾቻቸው እያሉ እርሳቸውን አዝለው የማይሄዱበት ቦታ አልነበረም። የፈለጉት ቦታ ይወስዷቸዋል፤ የፈለጉትንም ነገር ያደርጉላቸዋል። እንደውም ስማቸው እንኳን የወጣው ከዚህ ጋር ተያይዞ ነው። የፈለገውን፣ ያሻውን ያድርግ ሲሉም ቢሻው እንዳሏቸው አጫውተውናል።
የልጅነት ህልማቸው ሙዚቀኛ መሆን የነበረው አቶ ቢሻው፤ ገና አስሮቹ እድሜ ላይ ሆነው ነበር በኪነት ውስጥ መሳተፍ የጀመሩት። መዝፈንንም የተለማመዱት። ለዚህ ደግሞ መነሻቸው የሚያዳምጧቸው ሙዚቃዎች እንደነበሩ ያስታውሳሉ።
በእርሳቸው የልጅነት ጊዜ ሬዲዮ እንኳን ለማግኘት የባላባትና የባለስልጣናት ልጅ መሆን ግድ ነው። አለዚያ እሰው ቤት እየተኮረኮሙ ነው ይህንን ማድረግ የሚቻለው። እነ ቢሻው ግን ከዚህ የተለየ አኗኗር ገጥሟቸዋል።
ምክንያቱም አባት መሀንዲስ በመሆናቸው የተነሳ በቤት ውስጥ የሚጎል ነገር የለም። በዚህም ባለታሪካችን ሰው ቤት ሄደው ሳይሆን ራሳቸው ቤት ሆነው አዲስ የወጡ ካሴቶችን ይሰማሉ። ሬዲዮም ቢሆን ቤት ውስጥ ሆነው ያደምጣሉ።
በባህሪያቸው ተጨዋች፣ አትንኩኝ ባይና ከነኳቸው ለምን በእድሜና በጉልበት አይበልጣቸውም አጋጣሚ ጠብቀው ምላሽ የሚሰጡ አይነት ልጅ እንደሆኑ ያጫወቱን አቶ ቢሻው፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ ‹‹ታገለ›› የሚል ቅጽል ስም እንደወጣላቸው አይረሱትም።
ሌላው ባህሪያቸው ያዩትንና የሰሙትን እንዲሁም የተማሩትን በፍጥነት የሚይዙና ወደ ተግባር የሚቀይሩ መሆናቸው ደግሞ በማስታወስ ባህሪያቸው ቤተሰቦቻቸው ብቻ ሳይሆን ጓደኞቻቸው ጭምር ይቀኑባቸው እንደነበርም ያስታውሳሉ።
ለሰዎች ቀና እና ያላቸውን ማካፈልም የሚወዱ ሲሆኑ፤ ከዚህ ባህሪያቸው አንጻር ከራሳቸው ይልቅ ዛሬ ድረስ ለሰዎች የሚያስቡ ሆነዋል። እንደውም በሰፈር ሰው ሳይቀር ያ ደግና ተጨዋቹ ሰው ነው የሚባሉት።
ትምህርትን እስከ ዘጠኝ
የትምህርት “ሀ–ሁ–”ን የጀመሩት ከቤት ውስጥ ከአባታቸው እግር ስር ነው። አባታቸው የተማሩ በመሆናቸው ፊደላትን አስቆጥረዋቸዋል። ከዚያም ዘመናዊ ትምህርታቸውን እንዲጀመሩ በኮልፌ አካባቢ በሚገኘው ‹‹ብርሀን በር›› የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አስመዘገቧቸው። እስከ ስድስተኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ ደግሞ ጉዟቸው ወደ መሳለሚያ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተሸጋገረ። በዚህም ሰባተኛ ክፍልን በሚገባ ተማሩ።
በትምህርታቸው በጣም ጎበዝና የደረጃ ተማሪ የሆኑት አቶ ቢሻው፤ ስምንተኛ ክፍልን የተማሩት ለቤተሰቡ ቅርብ እንዲሆኑ በማሰብ ምኒልክ ትምህርት ቤት በመግባት ነው። አሁንም ከቤት መመላለሱ የተሻለ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ቤተሰብ ስላመነበት ወደዚያው ወደ ትውልድ ሰፈራቸው ወሰዷቸው።
በዚህም በፈረንሳይ ለጋሲዮን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም ዘጠነኛ ክፍልን እንዲማሩ ሆኑ። በእርግጥ ይህንን የክፍል ደረጃ ማጠናቀቅ አልቻሉም። ምክንያቱ ደግሞ የውትድርናው ሥራ አንድ ቦታ ላይ ሆነው የሚተገበር ስላልሆነ በተለያዩ ክልሎች ላይ ስለሚዘዋወሩ መማር ባለመቻላቸው ነው።
‹‹የውትድርና ፍቅር አይሎብኝ ከዘጠነኛ ክፍል ትምህርቴን እንዳቋርጥ ሆኛለሁ። ነገር ግን ውትድርናውም ብዙ ትምህርቶችን እንደሰጠኝ አምናለሁ›› የሚሉት ባለታሪካችን፤ ወታደር ለመሆን በመመልመላቸው ለውትድርና ስልጠና ወደ ደብረብርሀን ከተማ ማቅናታቸውን ይናገራሉ።
በውትድርናው ሳይንስ የተለያዩ ስልጠናዎችንም እንደወሰዱ አጫውተውናል። በተለይም በእግረኛነትና በሙዚቃው ዘርፍ ብዙ ሥልጠናዎችን መውሰዳቸውንም አጋርተውናል። በተለይ ግን ለረጅም ዓመታት በሙዚቃ መሳሪያ ዙሪያ የወሰዱት ትምህርት መቼም እንደማይረሳቸውና ሳክስፎኒስት እንዳደረጋቸው ይናገራሉ።
በቀጥታ ትምህርት ቤት ገብተው በክፍል ደረጃ እስከ ዘጠነኛ ክፍል ብቻ የተማሩ ሲሆን፤ ከዚያ በኋላ ሌሎች ክፍሎችን አልቀጠሉም። ግን ከሙዚቃው ጋር በተያያዘ በማዕከላዊ ዕዝ የሚሰጡ ማንኛውንም ስልጠና በሚገባ ተከታትለዋል፤ ወስደዋልም። ይህ ደግሞ ሙሉ ሙዚቀኛ እንዳደረጋቸውና ዛሬም ቢሆን መሳሪያውን ቢያገኙት በሚገባ መጫወት እንደሚችሉ አጫውተውናል።
ከሳክስፎኒስት ወደ ጥበቃ
ከውትድርና ሥልጠናው በኋላ እግረኛ ሆነው ለጥቂት ጊዜ ካገለገሉ በኋላ ነበር የተለያዩ ክፍሎች ስለነበሩ ሁሉንም ባላቸው ክህሎት ሲመድቧቸው እርሳቸውና ጥቂት ጓደኞቻቸው በስልጠናው ቦታ አካባቢ የነበሩ ኪነቶች ውስጥ ያገለግሉ ስለነበር ያ ታይቶ የሙዚቃው ክፍልን እንዲቀላቀሉ የሆኑት። በዚህም ጀማሪው የማዕከላዊ ዕዝ የሙዚቃ መሳሪያ ተጨዋች ወይም ሳክስፎኒስት ሆኑ። በእርግጥ ይህም ቢሆን በአንድ ጊዜ አልመጣም። ብዙ ትምህርት እንዲወስዱ ከሆነና ብቃታቸው ታይቶ ተፈትሾ ነው።
መጀመሪያ አካባቢ በሰፈር ውስጥ ኪነት ቡድን ገብተው ያገለግሉ ነበር። ይህ ደግሞ ምርጥ ድምጻዊ አድርጓቸው ቆይቷል። እናም ማዕከላዊን ሲቀላቀሉ ከቴነር ሳክስፎን መሳሪያ ተጨዋችነት ባለፈ በድምጻዊነትም የማገልገሉ እድል ገጥሟቸዋል። በመሆኑም በቀድሞ የማዕከላዊ ማርሽ ባንድ ውስጥ ከ1973 እስከ 83 ዓ.ም እንዲያገለግሉ ሆነዋል። የመጀመሪያ በደመወዝ የሰሩበት ጊዜም ይህ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር የማዕከላዊ ዕዝ ሙዚቀኛ በመበተኑ የተነሳ ማንም ላይ ጥገኛ ላለመሆን የተለያዩ ሥራዎችን የሞከሩት እንግዳችን፤ በቋሚነት በጓደኛቸው በተከፈተ ምግብ ቤት ውስጥ የምግብ ቤቱ ተቆጣጣሪ ሆነው ለአራት ዓመት ያህል ሰርተዋል።
ከዚያም ወጥተው የሞካከሯቸው የቀን ስራዎች ነበሩ። ግን ሁሉም ቢሆን ለቤተሰብ ማኖሪያ የሚበቃ አልነበረም። እናም ቤተሰቤም ሆነ ራሴን ከፍ ማድረግ አለብኝ በማለት ለጥበቃ ሥራ በተሻለ ደመወዝ ግብርና ሚኒስቴር ተመዘገቡ። ከ20 ዓመት በላይም አገልግለውበታል። አሁንም ቢሆን በዚሁ መስሪያ ቤት እየሰሩ ይገኛሉ።
‹‹ይህ መስሪያ ቤት ቤተሰቤንም ሆነ እኔን ከችግር ያወጣኝ ነው። ተጨማሪ እድሎችንም ያመቻቸልኝ አባቴ በይው። ምክንያቱም በጥበቃ ብቻ ሳይሆን በዶሮ ማርባት ሥራም እንድሰማራ አግዞኛል›› የሚሉት ባለታሪኩ፤ ከጥበቃ ሥራው ጎን ለጎን የዶሮ ማርባት ሥራ ይሰሩ እንደነበር ይናገራሉ። በዚህ ደግሞ ብዙ ነገሮችን መለወጥ እንደቻሉም ያብራራሉ። ለዚህ ያበቃቸው ግን የመስሪያ ቤቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ብቻ ሳይሆን የራሳቸውም ጥንካሬ እንደሆነ ያምናሉ።
ሰዎች ዝቅ ብሎ መስራት ለትልቅ ነገር ያበቃል ብለው ካመኑ የተሻለ ኑሮን መኖር ይችላሉ። በዚያው ልክ ክብሬ ይዋረዳል ብለው ካሰቡ ከችግራቸው ጋር ይከርማሉ። ለዚህ ማሳያው ደግሞ አብረዋቸው የተበተኑት የማዕከላዊ ዕዝ አባላት ሲሆኑ አንዳንዶች እንደርሳቸው ዝቅ ብለው ሰርተው ተለውጠው የተሻለ ነገር ይዘዋል። አንዳንዶች ደግሞ የሰው እጅ እየጠበቁ እንደሚኖሩ ነግረውናል።
ሰው ከሰራ የፈለገው ላይ መድረስ ይችላል። ሥራ ከናቀ ግን መቼም ቢሆን አይለወጥም የሚል እምነት ያላቸው አቶ ቢሻው፤ ለትልቁ ስራ ትንሹ መሰረት መሆኑን ማንም መካድ የለበትም። ተራራን እያሰቡ ለመኖር መፍቀድም ተገቢነት የለውም። በተለይም ራስን እንጂ ሰውን ማየት አይገባም። ምክንያቱም ሰው እንደራሱ እንጂ እንደጎረቤቱ መኖር አይችልምና። እናም ሰዎች ራሳቸውን ሆነው ያቀዱት ላይ ለመድረስ መታተር ይኖርባቸዋል ይላሉ።
የውትድርና ፍቅር ከሰፈር እስከ አገር ወታደር አገር ማለት ነው፤ የአገር ሉዓላዊነት ማለት ነው። ወታደር ከማንም በላይ ትዕዛዝ አክባሪ ነው። በስነ ምግባር የታነጸም ነው። የስነ ምግባር ልዕልናቸው እንድናከብራቸው ብቻ ሳይሆን ሙያውንም እንድንወደው የሚያደርግ ነው። የወታደር የአገር ፍቅር ከማንም በላይ ነው፤ የታማኝነት ጥግ ያለው ወታደር ዘንድ እንደሆነ ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። ለአብነት አንድ ወታደር ወደ ጦር ሜዳ ሲሄድ ሞቱን ጨርሶ መሆኑ አንዱ መገለጫ ነው። ሞት ለእርሱ ምንም አይደለም። ትልቁ ነገር ለእርሱ የአገሩ ማሸነፍና መከበር ብቻ ነው። ስለዚህ ለወታደር አገር ከህይወት በላይ ነው። ይህ ሁሉ ባህሪያቱም ነው እኔን ወደ ውትድርናው እንድገባ የገፋኝ ይላሉ አቶ ቢሻው።
መጀመሪያ ወታደር ለመሆን ያደረገኝ ሰፈር ውስጥ ያለ የሙያው ክብር ነው። ከአለባበሳቸው እስከ አረማመዳቸው ያላቸው ግርማ ሞገሳቸው እጅጉን የሚመስጥ ነበር። ጥንካሬያቸውም ቢሆን በዚያው ልክ ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ በማንም አለመበገርና ሁሉንም ማሸነፍ መቻል ፊት ለፊት ለሚያየው ሰው በቀጥታ የሚመረጥ ሙያ ነበር። እናም ወደዚህ ሙያ እንድገባ ያደረጉኝ እነዚህ ምክንያቶች ናቸው ይላሉ። በዙሪያቸው ያሉ ሁሉ የወታደር ልጆች መሆናቸውም ሌላው ምክንያት እንደነበር ያነሳሉ።
መጀመሪያ የእድሜ ጓደኞቻቸው ጉትጎታና ስለሙያው የሚነግሯቸው ነገር በእጅጉ ይስባቸው ነበር። ሆኖም አንድም ቀን ወታደር እሆናለሁ ብለው አያስቡም። ከዚያ ይልቅ ሙዚቀኛ መሆን ስለሚወዱ ወታደር ሆነው ሙዚቀኞችን ሲያዩ ግን ከላይ የጠቀሷቸውን ሁሉ የሚያሟሉም ስለነበሩ ሁሉንም ለማግኘት ሲሉ እንደገቡ አጫውተውናል። ሙሉ መስፈርቱን እንዳሟሉ ሲነገራቸው ጮቤ እንደረገጡ የሚያስታውሱት ባለታሪካችን፤ ተመልምለው ለስልጠና ወደ ደብረብርሀን ሲጓዙም መደሰታቸውን ይናገራሉ። ጠባሴ እየተባለ በሚጠራው ማሰልጠኛ ውስጥም የውትድርና ስልጠናቸውን ሲወስዱ ልዩ ስሜት እንደነበራቸው አይረሱትም።
ውትድርና የወደፊትን ሁሉ የሚያስተምርና ጥንካሬን አላብሶ ህይወትን በተግባር ለመኖር የሚያስችል ትምህርት ቤት እንደሆነ በስልጠናው አይቻለሁ። ውትድርና ቤተሰብን ጭምር በስነምግባር ለመምራት ትልቅ እድል የሚሰጥ እንደሆነም ተመልክቻለሁ። ከዚያም አልፎ ለህዝብ ጠበቃ የሚኮንበትም ሙያ እንደሆነ አውቄበታለሁ፤ ኖሬበታለሁም። ግን ዛሬ የተለየ ነገር ሲገጥመኝና ስለ ውትድርና የሚሰጠው ክብርን ሳይ ውስጤ ይታመማል። ምክንያቱም የፖለቲካው ጣጣ ሁሉን ነገር ቀይሮታል። ሥርዓት በተቀያየረ ቁጥር ለወታደሮች የሚሰጠው ክብርም እንዲሁ ሥርዓት ያጣና ህይወቱን የለገሰ አላስመሰለውም ይላሉ።
የአገሩን ዳር ድንበር ሲያስከብር እግሩን ያጣ ጀግና ጎዳና ላይ ሲለምን መመልከትና የሚያግዘው ሰው ሲጠፋ ማየት እጅጉን ልብን የሚሰብር ነው። የአገር ፍቅር ዋጋ ይህ ነው እንዴ የሚያስብለኝም ጊዜ ብዙ ነው። በተለይም የወደቀውስ እሺ አለፈበት እንበለው ነገ አገርን ለመጠበቅ የሚተካው ትውልድስ ከዚህ ምን ይማራል።
የተስፋ መቁረጥ ጠባሳንስ አያሳርፍም? በእርግጥ የወታደር መገለጫ ሀብትና የተንደላቀቀ ኑሮ አይደለም፤ ግድ ተራራና ቁልቁለቱን መውረድና ህዝብን መጠበቅ፤ አገርን ማስከበር ነው ዋነኛ አላማው። ግን ሲወድቅ ለከፈለው ዋጋ ምላሽ ማግኘት አለበት። ለዚህ ደግሞ መንግስት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ህዝብ ጠብቆታልና የድርሻውን ማበርከት ይኖርበታል። አገር ወዳድ ነኝ የሚል ወጣትም ቢሆን ይህንን ሲያይ ዝም ማለት ተገቢነት የለውም። ይልቁንም ሙያውን የሚወድበትን ሁኔታ መፍጠር ላይ መስራት አለበት ባይ ናቸው።
በውትድርና ህይወት አንዳንድ ገጠመኞች ለማመን የሚከብዱ ናቸው። በፊልም የሚታዩ አስማታዊ ክስተቶችም ይመስላሉ። ግን እውነትነት ያለውና ለአገሩ ሲል የሚያደርገው መሆኑን ዳር ቆሞ የሚያየው ህዝብ ሳይቀር ያውቀዋል። ምክንያቱም ከሚነድ እሳት ውስጥ ብዙዎችን መንትፎ ሲያወጣ ይመለከታል።
በጨለማ ገደል ከገባ መኪና ውስጥ መትረፍ፣ ከአውሬ መንጋጋ ማምለጥ፣ ከጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ መትረፍ፣ ከጥይት ሀሩር መዳን ወዘተም ሲገጥመው አይቶ አጀብ ይላል። ለዚህ ሁሉ ድሉ መንስኤው የህግ ተገዥነቱ ነው። ከእኔ በላይ ሌላ ይዳን የሚል ሙያ ያለው የትም ሳይሆን ውትድርና ውስጥ ነው። እናም ክብር ለወታደር ከህጻን እስከ አዋቂ ሊሆን እንደሚገባም አበክረው ያስረዳሉ።
ውትድርናና ሙዚቃ
የሳክስፎን መሳሪያ በርከት ያሉ ባህሪያት ያሉበት ሙያ ነው። ከእንቅስቃሴው እስከ ድምጽ አወጣጡ ብዙ ክህሎት ያለበት ነው። ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ ልዩ የአገር ፍቅር የሞላበት ነው። ስለዚህም በፍቅር ውስጥ መዝፈንና የሙዚቃ መሳሪያ መጫወት ማለት ደግሞ ምን ማለት እንደሆነ የወደደ ይናገረው የሚሉት እንግዳችን፤ በውትድርና ስነምግባር መድረክ ላይ ገና ሲወጣ ሰላምታው ሁሉ ልብን ይሰልባል።
ማንጎራጎሩ ሲጀምር ደግሞ የበለጠ ያሉበት እስኪጠፋ ድረስ የሚመስጥ ነው። ከዚያ አለፍ ሲባል ደግሞ የህዝቡ ምላሽ ሲጨመርበት ራስን መቆጣጠር ያዳግታል። እናም በእነዚህ መካከል ሆኖ ነው ሙዚቃን በውትድርና የሚከወነውም ብለውናል።
የአገር ዘፈን ሲዘፈን ከእንባ ጋር ተቀላቅሎ ነው። ከግጥሙ እኩል ስሜቱም ይወጣል። በዚያ ላይ መሳሪያ ተጨዋቹም ቢሆን ከዘፋኙ እኩል ነው የሚመሰጠው። ዘፋኙም፣ የሙዚቃ መሳሪያ ተጨዋቹ ሆነ የሚያዳምጠው ሰው ከልብ ሆኖ ነው። ይህ ደግሞ ለአገረ መንግስት ግንባታው ጭምር ትልቅ ውለታ ውሏል።
የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን፣ የባህልና ታሪክ ቁርኝቱንም ቢሆን በእጅጉ አጠናክሯል። በተለይ ዛሬ ብዥታ የተፈጠረበት የባንዲራ ጉዳይ የእኛ ጊዜ ልዩ ክብር ያገኘ ነበር። ሲነሳም ሲቀመጥም የተለየ ክብር ይሰጠዋል። መዝሙሩ ሲዘመርም ማንም ሰው መንቀሳቀስ አይችልም። ስለዚህም ሙዚቃ የእኔ ሳይሆን የእኛ የሚለውን ስሜት በመፍጠር ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረገ እንደነበር በውትድርናው ውስጥ በነበሩበት ወቅት እንዳዩ ያስታውሳሉ።
የቀድሞ ዘፈኖች መስራትን፣ ለሌሎች ማካፈልን ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል አይነት ስሜት የሚያበረታቱ ናቸው። የዛሬዎቹን ስንመለከት ሁሉም ባይሆኑም አትጨናነቅ እያሉ አለመስራትን፤ ተነስ እያሉ እርስ በእርስ መጠላላትን የሚሰብኩ ናቸው። በተለይ ማን ይነከሀል የሚሉ ስሜት ቀስቃሽ መልዕክቶች መኖራቸው ባህላችንን ሙሉ ለሙሉ እንዲሸረሸሩ አድርገዋል። እናም ሙዚቃ ለአገር እንጂ ለግል ሀብት ማግበስበስ አይሆንምና ይህ ይታሰብበት ይላሉ።
ቤተሰብ
አቶ ቢሻው በለጠ የሁለት ልጆች አባት ናቸው። እርሳቸው ያለፉበትን ህይወት ልጆቻቸው እንዳይደግሙት ያልሞከሩት ሥራ አልነበረም። ከጎረቤት ልጅ ዝቅ ብለው እንዳይታዩባቸውም በክፍያ ጭምር አስተምረዋቸዋል። ብዙ እንደለፉባቸው በተለይ የአዲስ አበባን የትምህርት ቤት ክፍያ የሚያውቁት የአዲስ አበባ ነዋሪ እናቶችና አባቶች ይመሰክሩላቸዋል።
ምክንያቱም እርሳቸው ከሚያገኙዋት የጥበቃ ገንዘብ በተጨማሪ ሌሎች የቀን ስራዎችን እየሰሩም ነው ለዛሬው የክፍል ደረጃ ያበቋቸው። በዚህ ደግሞ አምላክ ክሷቸዋል። ሁለቱም ጎበዝና ተሸላሚ ናቸው። አንደኛው ልጃቸው አስራ ሁለተኛ ክፍል የደረሰላቸው ሲሆን፤ ሴቷ ደግሞ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ገብታ እየተማረች ትገኛለች።
ልጆቻቸው የአባታቸውን ቀና ልብ የያዙ ሲሆኑ፤ አባታቸውን ደስተኛ ለማድረግ ይታትራሉ። በተለይ ሴቷ ልጃቸው ገና ከስራ ሲገቡ ጀምሮ ፊታቸውን እንደምታነበውና ምን እንደሚፈልጉ እንደምታውቅባቸው ይናገራሉ። በትምህርታቸው የደረጃ ተማሪዎች በመሆናቸው ሁልጊዜ ያስመሰግኗቸዋልና አይደለም ጥበቃና የቀን ሰራተኛ ሌላም ብሆንላቸው ለልጆቼ አይቆጨኝም ይላሉ።
እንግዳችን ለልጆቻቸው ብቻ ሳይሆን ለእህቶቻቸው ጭምር አባት ናቸው። ምክንያቱም እነርሱን ለዛሬ ያደረሱት ለፍተው ጥረው ግረው ነው። እንደውም ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ቀን የሆነውን እንዲህ ያስታውሳሉ። ፍቅር ይዟቸው ልጅቷን ተከትለው ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ ተዘጋጁና ለእህቶቻቸው ነገሯቸው። እህቶቻቸውም ‹‹እኛ አሁን እናትም አባትም የለንም።
አባታችንም እናታችንም አንተ እንደሆንክ ታውቃለህ። ማን ዳቦ ሊገዛልን፣ ማን ደብተር መግዢያ ሊሰጠን ነው ትተኸን የምትሄደው? ያለ ተንከባካቢ ማስቀረት ከፈለግህ ትችላለህ። ሰርተን ዳቦ የምንቆርስበት አጋጣሚ እንኳን በሌለን ጊዜ ይህንን ካደረክም እናዝንብሃለን። ስለዚህ ለእኛ ዳቦና ደብተር መግዛት ከሰለቸህም አድርገው›› አሏቸው።
በዚህ ጊዜ ፍቅራቸውን ትተው እህቶቻቸውን ለመንከባከብ ቆረጡ። እንዳሰቡትም ተምረው ወልደው ከብደው እንዲኖሩ አስቻሏቸው። አሁን አባቴ እያሉም በተራቸው እየተንከባከቧቸው እንደሚገኙ አጫውተውናል።
አቶ ቢሻው ከዛሬዋ የልጆቻቸው እናት ጋር የተገናኙት በጓደኛቸው እህት አማካኝነት ሲሆን፤ መጀመሪያ ከጓደኛቸው ጋር ባላቸው ቤተሰባዊነት የተነሳ እህቱን እንዲያገቡ ይፈልግ ነበር። የእርሱ ቤተሰቦችም ቢሆኑ እንግዳችንን ይወዷቸዋል፣ ይመርጧቸዋልም። ሆኖም ባለታሪካችን ግን ይህ የሚሆንበት አጋጣሚ እንደማይኖር ያምናሉ። ምክንያቱም ልጅቷ ምንም እንኳን የጓደኛቸው እህት ብትሆንም እርሳቸው ከእህታቸው አይለዩዋትም። እናም እህትን ማግባት ደግሞ ፍጹም የተሳሳተ እንደሆነ ያስባሉ። ስለዚህም ጓደኛቸው አፉን አውጥቶ ጠይቋቸው የመለሱለት መልስ ይህንን አስተሳሰባቸውን የሚያንጸባርቅ ነበር። በእርግጥ ጓደኛቸው በወቅቱ አልጠላቸውም ነበር። የባሰ አከበራቸው እንጂ። እህቱን እንደእህታቸው የሚያስብ ጓደኛ በማግኘቱም እጅጉን ተደስቶ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ከጓደኛቸው እህት ጋር የምትዘዋወረዋ የዛሬዋ ባለቤታቸው ግን አይናቸውም ልባቸውም ተማርኮባታል። ሚስታቸው ቢያደርጓት እንደሚደሰቱም አምነዋል። እናም ጓደኛቸውን ነበር መጀመሪያ ልጅቷን ልባቸው እንዳሰባት ያስፈቀዱት። እርሱም ደስ ብሎት ‹‹ጠይቃት›› አላቸው። እንደተባሉትም አደረጉ። ግን ፈቃዷን በአንድ ጊዜ ማግኘት አልቻሉም ነበር። 10 ዓመታትን በፍቅር እንዲቆዩ አስገድዷቸው እንደነበር አይረሱትም። ነገር ግን ተስፋ መቁረጥ ማጣትን ትዕግስት ደግሞ ገጸ በረከትን ይሰጣልና በስተመጨረሻ የቤታቸው ንግስት አደረጓት።
መልዕክት
በሥራ እና በሙያ ላይ ድሮን ማሰብ ወደኋላ እንጂ ወደፊት አያሻግርም የሚሉት አቶ ቢሻው፤ የሰው ልጅ ከሰራና ጤናማ ከሆነ የማይለወጥበት ነገር አለ ብሎ ማሰብ ትክክል እንዳልሆነ ይናገራሉ። ራስን ማሳመን የመጀመሪያውና ዋናው ጉዳይ መሆን እንዳለበትም ይገልጻሉ። ይዞ ለመገኘትም መፍትሄው ይህ እንደሆነ ያስረዳሉ። አለዚያ ግን ወሬ ብቻ ይሆንና ተመጽዋችነትን ያላብሳል። ሁሉም ሰው እንዲሸሽ ያደርግሻልም ይላሉ። በትልቅ ደረጃ ላይ ሆነሽ የሚያውቅሽ ሰው ስለሚያዝንልሽ እስከ ሦስት ቀን ለያውም በጣም ከወደደሽ ሊሰጥሽ ይችላል። ሆኖም በቋሚነት አይደጉምሽም። እናም ሳይወድ በግድ አንቺን ላለማየት የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። ከዚህ ሁሉ መስራትና አለመለመን ዋጋው ቀላል አይደለም። ስለሆነም ዝቅ ላለማለት ተብሎ የሚከፈል ዋጋ አሁን ማክተም አለበት የመጀመሪያው መልዕክታቸው ነው።
ሌላው ያነሱት ነገር የራስ ላብ የውስጥ እርካታን ይሰጣል የሚለውን ነው። ሥራ ከፍና ዝቅ ተደርጎ የሚታየው በአገራችን ነው። በውጪው ዓለም ግን ይህ እንዳልሆነ ማሳያው ብዙ ሰዎች ከአገር ሄደው ጽዳትና መሰል ተግባራትን ሰርተው ዛሬ አገራችን ውስጥ እልል የተባለላቸው ሀብታሞች ሆነዋል። በላባቸው ያገኙትም ስለሆነ ይደሰቱበታል። እናም ሰዎችም ላባቸው ደስታቸው መሆኑን አምነው መስራት መቻል አለባቸው ሲሉ ይመክራሉ።
ማንም ሰው ለራሱ እንደሚኖር ማመን አለበት። እከሌ ይህንን ይለኛል እያልን የውስጥ ፍላጎታችንን የምንገታ ከሆነ መቼም ከችግር አረንቋ ውስጥ ልንወጣ አንችልም የሚሉት ባለታሪካችን፤ በላብ አንድ ብር እንዴት እንደሚገኝ ማሳየት እንጂ ተቀምጦ መብላትን ወላጆች ለልጆች እንዳያስተምሩ ይመክራሉ። እናት አባት ብቻ እንዲለፉ መፍቀድም ትክክል አይደለም። ሥራን በሚችሉት ልክ ትምህርታቸውን ሳይነካ ማስተማር ይገባል። ከዚያም ባሻገር ሰውን ማክበር ምን ጥቅም እንዳለው ማስረዳት የዛሬ ወላጆች ትልቅ ሀላፊነት ነውም ይላሉ።
የሌላውን ልጅ የራስ አድርጎ መቅጣት የሚያስችለውን ባህላችንን እንመልሰው። ዛሬ ጎረቤት መቅጣቱንና እንደ ልጅ ማሰቡን ትቶ ይህ የአንተ አይደለም ማለቱ የኢትዮጵያዊያን ባህል አይደለም። ስለዚህም ወላጆች አሁን የተቀረጹበትን ጠማማ ባህሪ በመልካም ስነምግባር መቀየር ላይ መስራት ይገባናል የሚለውም ሌላው መልዕክታቸው ነው።
በመጨረሻ መልዕክታቸውን ያደረጉት እናትና አባት የልጆችን ታሪክ ቀይረው የአገርን ታሪክ ያድሳሉ። ለዚህ ደግሞ ራሳቸው ሆነው ማሳየት ግዴታቸው ነው። ሳይሆኑ ማስተማር በምንም መልኩ አይቻልም። ስለዚህም እየሰጡ መስጠትን፣ እየሰሩ ማሰራትን፣ እያነበቡ ማስነበብን፣ ታሪክን ጠንቅቆ በማወቅ ማሳወቅን ማስተማርም አለባቸው። በተለይም ልጆች የተሳሳቱ ትርክቶችን ለማስተማሪያ እንጂ ለጥላቻ እንዳያውሉ ወላጆች ማስተማር አለባቸው ይላሉ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2013