የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተቋቋመው ከ74 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታህሳስ 21 ቀን 1938 ዓ.ም ነበር። የአፄ ሃይለ ስላሴ መንግስት የኢትዮጵያ አየር መንገድን ከትራንስ ወርልድ ኤይር ዌይስ ጋር በመተባበር ታኅሣሥ 21 ቀን 1938 ዓ.ም አቋቋመ። በወቅቱ አየር መንገዱን የሚያስተዳድሩት አሜሪካኖች ነበሩ። አየር መንገዱ የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ በረራውን ያደረገውም መጋቢት 30 ቀን 1938 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ካይሮ ነው።
አየር መንገዱ ስራ ሲጀምር ከአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል የተገዙና በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ያገለገሉ አምስት DC 3-C47 አውሮፕላኖች ነበሩት። አሁን የአንድ መቶ አስራ አንድ አውሮፕላኖች ባለቤት ነው። የቦይንግ 787 ድሪም ላይነርና 757 ትልልቅ ዕቃ ጫኝ አውሮፕላኖችን በመጠቀም በአፍሪካ የመጀመሪያው በመሆን የአዳዲስ አውሮፕላኖች ተጠቃሚ ለመባል በቅቷል።
ቢቢሲ በቅርቡ ያቀረበው ዘገባ እንደሚያመለክተው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኖች አማካይ እድሜ 5 ነጥብ 4 ዓመት ሲሆን፣ በብሪቲሽ አየር መንገድ የአንድ አውሮፕላን አማካይ እድሜ 13 ነጥብ 5 ዓመት፣ በዩናይትድ አየር መንገድ 15 ዓመት እንዲሁም በአሜሪካ አየር መንገድ 10 ነጥብ 7 ዓመት ነው።
አየር መንገዱ የአብራሪዎችና ቴክኒሻኖች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ባለቤት ነው። ከኢትዮጵያውያን ባለፈ ለበርካታ የተለያዩ አገራት ዜጎችን አሰልጥኖ በማስመረቅ በዘርፉ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል። ለአፍሪካ ሀገራት ብሔራዊ አየር መንገዶችና የግል አውሮፕላኖች የጥገና አገልግሎት ይሰጣል።
ኢትዮጵያ አየር መንገድ ለደህንነት አስተማማኙ የአፍሪካ አየር መንገድም ነው። እስከ አሁን አራት ከባድ አደጋዎች ብቻ ናቸው የደረሱበት። እንደ አውሮፓውያኑ በ2010 ET 409 ከቤሩት አውሮፕላን ማረፊያ ከተነሳ ከአምስት ደቂቃ በኋላ ነድዶ ሜዲትራኒያን ላይ በመውደቁ ነበር። በአደጋው 89 መንገደኞችና የአውሮፕላኑ ሰራተኞች ሞተዋል።
የሊባኖስ የምርመራ ቡድን የበረራ ስህተት ለአደጋው ምክንያት ነው ቢልም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን አውሮፕላኑን ያጋጠመው ፍንዳታ ነው በማለት የቡድኑን ሪፖርት ውድቅ አድርጎታል። አውሮፕላኑ አደጋው እንዲያጋጥመው የተሰራ ሴራ አለ፤ መብረቅ አጋጥሞታል ወይም እንዲወድቅ ተመትቷል የሚሉ ግምቶችም በኤክስፐርቶች ተቀምጠዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ1988 በባህር ዳር የአየር መንገዱ አውሮፕላን በማረፍ ላይ ሳለ ሞተሩ ውስጥ እርግቦች መግባታቸውን ተከትሎ በተነሳ እሳት 35 ሰዎች ሞተዋል። በ1996 ደግሞ ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ይበር በነበረው ቦይንግ 767 ላይ ጠለፋ በመደረጉ አውሮፕላኑ በኮሞሮስ ደሴት አቅራቢያ ህንድ ውቅያኖስ ላይ መውደቁ ይታወሳል። በዚህ አደጋ ከ 175 መንገደኞች 125ቱ ሞተዋል። በቅርቡ ባጋጠመው የቦይንግ 737-8 ማክስ ET302 አደጋ ከ100 በላይ ሰዎች ሞተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ከሚገኙ አየር መንገዶች ትልቁ ነው። በአፍሪካ አገራት ተጽእኖውን ይበልጥ ለማስፋት በማላዊ አየር መንገድ 49 በመቶ፣ በዛምቢያ 45 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ የገዛ ሲሆን፣ በሞዛምቢክም በአዲስ መልክ አየር መንገድ ስራ እንዲጀመር እየሰራ ይገኛል። በተመሳሳይ በጅቡቲ፣ ቻድና ኢኳቶሪያል ጊኒ ትንንሽ አካባቢያዊ ጣቢያዎችን ለመክፈት እንቅስቃሴ እያደረገ ሲሆን ማላዊንና ቶጎን በመሳሰሉ አገራት አሁንም ማእከላት አሉት።
በ2017/2018 በጀት ዓመት አየር መንገዱ 10 ነጥብ 6 ሚሊዮን መንገደኞችን በማመላለስ 245 ሚሊዮን ዶላር የተጣራ ትርፍ አግኝቷል። በቅርቡ የተጠናቀቀው የቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ የአየር መንገዱን ዓመታዊ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ ከፍያ ደርግለታል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ከእውቁ ሚዲያ ሂውስተን ክሮኒክል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩ፤ አየር መንገዱ በራእዩ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2025 የእድገት እቅዱ 90 ዓለም አቀፍ የበረራ መዳረሻዎችና 120 አውሮፕላኖች እንዲኖሩት አቅዶ የነበረ ሲሆን፣ ከእቅዱ 7 ዓመት ቀድሞ በ2018 ያሉት የዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ብዛት ከ 120 አልፏል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2013