አብርሃም ተወልደ
በኢትዮጵያ ስለጋዜጣ ስናነሳ በታሪክ ውስጥ ጎልተው የምናገኛቸው ዳግማዊ አጤ ሚኒልክን ነው። “… ሚኒልክ በሰላም ጊዜ የቤተ ክርስቲያን አባል በጦር ጊዜ ደግሞ፤… ተዋጊ ንጉስ ነበሩ። ስለዘመናዊው አለም ዜናም አእምሮው ክፍት ነው፡” ብሎ ጸሐፊው ማርገሪ ፐርሐም በአንድ ወቅት ጽፎ ነበር።
ሚኒልክ የጋዜጣን ታሪክ ቢያውቁም ለጋዜጣ ሰራተኛነት ሰው በማጣት ቆዩ። አቶ ገብረ እግዚያብሔር የተባሉ የሐማሴን ተወላጅ በ1888 ዓመተ ምህረት በሰኔ ወር ከኢጣሊያኖች ከድተው ሐረር ልዑል ራስ መኮንን ዘንድ ገቡ። ስለ ኢትዮጵያ ባላቸው ፍቅር ምክንያት ብዙ የስልጣኔ ነገሮችን እንደሚናገሩ ሚኒልክ ሰሙ።
ሚኒልክም በአቶ ገብረ እግዚያብሔር ንግግር እየተደሰቱ “መኮንን ባይቀየመኝ ይህን ሰውዬ ለኔ አደርገው ነበር”እያሉ ለየመኳንንቱ ይነግራሉ። በዚህ መሐል ልዑል ራስ መኮንን ሞቱ። የአቶ ገብረ እግዚያብሔር ደጋፊ ራስ መኮንን ሲሞቱ የሀረርጌ መኳንንት አቶ ገብረ እግዚያብሔርን ከሰሰ። የከሰሷቸውም ይሰድቧቸውም በነበረው ስድብ ሳይሆን “መሬት ትዞራለች እንጂ ጸሐይ አትዞርም ብለህ ተናግረሃል”ብለው ነበር።
አጤ ሚኒልክም ይህንን እንደሰሙ የሀረርጌ ግዛት ለተሰጣቸው ለራስ መኮንን ልጅ ለደጃች ይልማ ደብዳቤ ጽፈው ገብረ እግዚያብሔርን ወደ አዲስ አበባ አስመጧቸው፤ ከዚህ በኋላ ሀረር ሆነው ይናገሩት የነበረውን ሁሉ በወረቀት እየጻፉ ለየመኳንንቱ እንዲያድሉ አዘዟቸው። ይህም ልክ እንደ ጋዜጣ በእጅ እየተጻፈ በሳምንቱ በሚኒልክ ግብር ላይ ይታደል ጀመር። በስራው የተደሰቱት ሚኒልክ በብዛቱ ማነስ ይበሳጩ ጀመር።
ግሪካዊው ካባዲስ ደግሞ ለሚኒልክ ባቀረቡት ምክር ከጋዜጣው መልክ ያለው በእጅ እየተጻፈ በየሳምንቱ 24 ግልባጭ እየወጣ ለመኳንንቱ ይታደል ጀመር። የዚህን ስም ሚኒልክ ራሳቸው “አእምሮ” ብለው ሰየሙት። ኮፒ ማድረጊያ መሳሪያ በመገኘቱም በየሳምንቱ የአእምሮ ብዛት 200 ኮፒ ሆነ። ይህን የተመለከቱት አጤ ሚኒልክ በካባዲስ ስራ ተደስተው አዘጋጁ በስራው እንዲገፉበት እና የማተሚያ መኪና እንደሚያስመጡላቸው ተስፋ ሰጡአቸው።
የእጅ ጽሁፉን የማባዛት ስራ ግን በ1895 ዓ.ም ቆመ። የማተሚያው መኪና እስከ 1898 ዓ.ም ድረስ አልመጣም ነበር። ማተሚያው መኪና በኢድልቢ አስመጪነት ከመጣ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በህትመት “ጎህ” የተባለው ጋዜጣ ወጣ። ይህ ጎህ ተብሎ የተሰየመው ጋዜጣ በ1900 ዓ.ም ሐምሌ 17 ቀን ታትሞ ወጣ።
እንዲህ እያለ የቀጠለው የጋዜጣ ህትመት በኢትዮጵያ የጋዜጦች ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የነበረው ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕትመት የበቃው ደግሞ ከ96 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታኅሳሥ 23 ቀን 1917 ዓ.ም ነበር። ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ መታተም የጀመረው በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ መኖሪያ ግቢ ጨው ቤት በሚባለው ቤት ውስጥ መስከረም 3 ቀን 1914 ዓ.ም ማተሚያ ቤት ከተቋቋመ ከሶስት ዓመታት በኋላ ነው። ብዙም ሳይቆይ ማተሚያ ቤቱ የጋዜጣውን ስም ወረሰ። እስካሁንም ድረስ “ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት” እየተባለ ይጠራል።
ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ በየሳምንቱ ሐሙስ ዕለት በ500 ቅጂዎች እየታተመ በሁለት ፈረሰኞች አማካኝነት ይሰራጭ ነበር።
ጋዜጣው ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 1921 ዓ.ም ድረስ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ገብረ ክርስቶስ ተክለ ሃይማኖት ነበሩ። ቀጥሎም ዋና አዘጋጅነቱ በ1921 ዓ.ም አቶ ማኅተመ ወርቅ እሸቴ ተተኩ። አጼ ሀይለ ስላሴ ጋዜጣውን “ብርሃንና ሰላም” ብለው የሰየሙት መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ የብርሃንና የደስታ እንዲሆን በመመኘት እንደሆነ ይናገራል።
ሃሙስ ታህሳስ 23 ቀን 1917 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመው ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ አንደኛ ዓመት ቁጥር አንድ እትም ስለጋዜጣው ስያሜና ስለሚተላለፍበት መልዕክት ተከታዩን ሀተታ ይዞ ወጥቶ ነበር።
ብርሃን የጨለማ ተቃራኒ ነው፤ ሰላም ደግሞ የጠብ ተቃራኒ ነው። ብርሃን በሌለበት ጨለማ ይሰለጥናል፤ ሰላም በሌለበትም ጠብ፣ ሁከትና ጦርነት ይሰለጥናሉ። የፀሐይ ብርሃን ለሰውና ለእንስሳ ለተክል ሕይወት ሊሆን የሚያስፈልግ ነገር ነው። የሌሊቱ ጭለማ ማለዳ ፀሐይ ስትወጣ ይርቃል፤ ፀብና ሁከትም ሰላም ሲመጣ ይጠፋል።
በሌሊት ደግሞ ጨለማን ለማራቅ ብንፈልግ መብራት እናበራለን፤ ሥራ የሚሠራ ሁሉ በብርሃን ነው፤ በጨለማ የሚሠራ ግን የክፋት ሥራ ብቻ ነው፤ ሌባና ወንበዴ በቀን ይተኛል፤ በሌሊት ግን ወደ ሌብነቱና ቅምያው ይገሰግሣል፤ ክፉ የሚሠራ ሁሉ ክፉ ሥራው እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን ሊመጣ አይወድም።
እኛም የኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ ጤናማ የሆነ የፀሐይ ብርሃን በየጊዜው እናገኛለን፤ እንዲሁ ደግሞ ለነፍሳችን ብርሃን የሚሆን ፀሐያችን ክርስቶስ በልባችን ሊያበራ ያስፈልጋል፤ እኔ ብርሃን ሁኜ ወደ ዓለም መጣሁ፤ ያመነብኝ ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር ብሎ እርሱ ራሱ እንደ ተናገረው። ወደ ስልጣኔ የሚያደርስ ጥሩ የትምህርት ብርሃን ደግሞ ያስፈልጋል። በትምሕርት አእምሮ ይበራል፤ ካለ መማር ግን አእምሮ ይጨልማል፤ እንግዲህም የኢትዮጵያ ሕዝብ የስራ አእምሮ እንዲያገኝ ለትምህርት በሙሉ ኃይሉ ይጣጣር።
የኢትዮጵያ መንግስት አልጋ ወራሽና እንደ ራሴ ልዑል ተፈሪ መኰንን የትምህርት ብርሃን ላገራቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ በጣም የሚያስፈልግ መሆኑን አውቀው ሊያበሩለት እንደሚጣጣሩ፣ ለትምርት ቤትና ለመጻሕፍት አዕላፋት ገንዘባቸውን ማውጣታቸው ያስረዳል።
እንግዲህ የኢትዮጵያ መንግሥት መኳንንት ሆይ በሚቻላችሁ ነገር ተግታችሁ ለትምህርት በመጣጣርና ገንዘባችሁን በሙሉ ፈቃድ በመሠዋት ለምትገዙለት አገር የትምሕርት ብርሃን አውጡለት። እንዲህ ብታደርጉ ባገራችን ብርሃንና ሰላም ይሰለጥናል፤ የድንቁርና ጨለማና ሴራ ጠብ ወንበዴና ሌባም ይርቃል።
ይኸን ጋዜጣ የጻፍንበት ምክንያት እንደሚቻለን ያህል ለሕዝባችን ጥቅም የሚሆነውን ነገር በየሳምንቱ ለማመልከትና ምክር ለመስጠት ለማንቃትና አዕምሮውን ለማበርታት ነው እንጂ ሰውን ለማሳዘንና ለመንቀፍ አይደለም፤ ሰውን ከማሳዘንና ከመንቀፍ የሚጠቅም ፍሬ አይገኝም፤ በዚህስ የሚገኘው ቂምና ቁጣ ሁከትና ጠብ ነው።
ልብ አድርጋችሁ ብትመለከቱ ማናቸውንም ክፉ አድራጊ አንተ እንዲሀ ነህ ብለው በቁጣ ቃል ቢሰድቡት ይጣላል፤ ይሳደባል፤ ይማታል እንጂ ከክፉ መንገዱ ይመለሳልን ? እንዲያውም ከመናደዱ የተነሣ በክፋት ላይ ክፋትን ይጨምራል። ነገር ግን መሳደቡ ቀርቶ በለዘበ ምላስ ከክፉ ሥራ የተነሣ የሚመጣውን ጉዳት ቢያስታውቁት ዳግመኛም ዕውቀት የሚሆነውን ነገር ቢመለከቱ የሚገኘውን ጥቅምና መልካሙን ጤና ሲያስረዱት ምናልባት ይመለስ ይሆናል ማን ያውቃል ? ባይመለስም ለጊዜው ልቡ ሳይነካ አይቀርም፤ ሁሉም ቢቀር አይጣላም። ስለዚህ የጻፈውን ነገር በዚህ ጋዜጣችን ሊያሳትም የፈለገ ሰው ቢኖር ለሕዝባችን ምክርና ዕውቀት ትምሕርትም የሚሆን ነገር ጽፎ እንዲያመጣልን እንለምነዋለን።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2013