አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ በተለያየ ጊዜ ለልማት መሬት ወስደው ወደ ስራ ያልገቡ122ኢንተርፕራይዞች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ፡፡ በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ለ72ሺ ወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅዶ ለ44ሺ ዜጎች ብቻ የስራእድል መፈጠሩን አመለከተ፡፡
የቢሮው ኃላፊ አቶ ጀማሉ ጀምር ቢሮው በስሩ ከሚገኙ ኤጀንሲዎች፣ የክፍለከተማና የወረዳ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ጋር የበጀት አመቱን ስድስት ወር አፈጻጸም ትናንት ገምግሟል፡፡ በወቅቱ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ሲመልሱ እንዳሉት በአንደኛና በሁለተኛ ዙሮች በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመሰማራት መሬት ወስደው ወደ ሥራ ያልገቡ 168 ኢንተርፕራይዞች በጥናት የተለዩ ሲሆን በ122ቱ ላይ እርምጃ መውሰድ ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ ባለፈው በጀት ዓመት በሶስተኛ ዙር መሬት የወሰዱትም የማልሚያ ጊዜ ቢሰጣቸውም ባለመስራታቸው በሶስት ወር ጊዜ እንዲለቁ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው መሆኑን አቶ ጀማሉ ጠቁመዋል፡፡ እንዲሁም በህገወጥ መንገድ የተያዙ መስሪያና መሸጫ ቦታዎችን የመለየትና እርምጃ የመውሰድ ስራ ለማከናወን ዝርዝር ጥናት እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የማልሚያ መሬት የሚሰጣቸው የዕድገት ደረጃቸውን ላጠናቀቁ ኢንተርፕራይዞች እንደሆነና የወሰዱት መሬትም እንደስራቸው ስፋት እንደሚለያይ የጠቆሙት የቢሮ ኃላፊው፣ ዓላማውም ምርትና ምርታማነታቸውን ጨምረው በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ በዚያ መሰረትም አልምተው ወደ ስራ የገቡና በሂደት ላይ የሚገኙ መኖራቸውንም አመልክተዋል፡፡ በተሰጣቸው ጊዜ መጠቀም ካልቻሉት የተወሰደው መሬት በቀጣይ ለሚሸጋገሩ ኢንተርፕረይዞች እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ጀማሉ ገለፃ፤ የከተማ አስተዳደሩ ቆሻሻ መጣያና ለልማት ሳይውሉ የቀሩ 23ሺ ካሬ ሜትር የሚሆን ክፍት ቦታዎችን በጥቃቅንና አነስተኛ ለሚሰማሩ ዜጎች የመስሪያ ቦታ ሰጥቷል፡፡ ይህም ዜጎች ጥሪት አፍርተው ወደሌላ እንዲሸጋገሩ እንጂ በቋሚነት ግንባታ እንዲያከናውኑበት አይደለም፡፡ ለልማት በተፈለገ ጊዜም እንዲለቁ ይደረጋል፡፡ የማልማቱ ስራም የከተማዋን ገጽታ በጠበቀ መልኩ መከናወን ይገባዋል፡፡
ቢሮው ባለፉት ስድሰት ወራት ለ72ሺ ወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ቢያቅድም እድሉ የተፈጠረው ለ44ሺ ብቻ እንደሆነ የጠቆሙት ኃላፊው፤ ቢሮው በመልሶ ማደራጀት ላይ በመቆየቱና ዘግይቶ ስራ መጀመሩ ለአፈጻጸሙ ወደ ኋላ መቅረት ምክንያት መሆኑንና ብዙ መስራት እንዳለባቸው አስታውቀዋል፡፡ጅምሩ ግን አበረታች መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ቢሮው በሥራው ካጋጠሙት ተግዳሮቶች አብዛኞቹ በዘላቂነት ኑሯቸውን በሚለውጡበትና በጉልበት ሥራ ላይ ከመሰማራት ይልቅ ፈጥኖ ገቢ በሚያስገኝ ላይ የመደራጀት ፍላጎት እንዳላቸውም አቶ ጀማሉ ጠቁመው፤ ይህንን ተግዳሮት ለመፍታት ሰፊ ግንዛቤ የመፍጠር ተግባር እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል፡፡
ጥር 24/2011
ለምለም መንግሥቱ