ፍሬህይወት አወቀ
የመኖሪያ ቤት አቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም እንደየአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ቢለያይም ችግሩ ሀገራዊ እየሆነ ከመጣ ውሎ አድሯል።እንደሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ችግሩ ጎልቶ የሚታይበትን የአማራ ክልልን ለመዳሰስ ወደናል።ከክልሉ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ለመኖሪያ ቤት እጥረት በከተሞች ውስጥ የመኖር ፍላጎት መጨመርና ዕድሜ ያስቆጠሩ ለመኖሪያ ምቹ ያልሆኑ ቤቶች በብዛት መኖርና በአዳዲስ ግንባታዎች አለመተካት በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡
በክልሉ ያለው የመኖሪያ ቤት እጥረት በነዋሪው ላይ እያሳደረ ስላለው ተጽዕኖና ክልሉም ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራ ስላለው ሥራ በክልሉ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ዳይሬክተር ለሆኑት ወይዘሮ ዝናሽወርቅ አስፋው ጥያቄ አቅርበን በሰጡን ምላሽ በመኖሪያ ቤት አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት የክልሉ መንግስት የተለያዩ አማራጮችን ወስዶ በሰራው ስራ የተወሰኑ ነዋሪዎችን በቤት ልማቱ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል።
የተከናወነው ሥራ አበረታች ቢሆንም በማህበር ተደራጅቶ ለቤት መሥሪያ ቦታ ለማግኘት ተመዝግቦ የሚጠባበቀውን ነዋሪ ፍላጎት በሚፈለገው ልክ ማሟላት አልተቻለም።በእያንዳንዱ ማህበር ውስጥ የተደራጀው ከፍተኛ ቁጥር ያለው በመሆኑ ጥያቄውን መመለስ አልተቻለም።
በተለያዩ አካባቢዎች በተበጣጠሰ ሁኔታ የተገነቡ፣ ያረጁ ቤቶች መኖራቸውና ህገወጥ የሆነ ግንባታ መስፋፋት ለቤት ፍላጎት አለመሟላት ማሳያዎች ናቸው።በከተሞች ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ ከገጠር ወደ ከተማ በየጊዜው የሚደረግ ፍልሰት በከተሞች ያለውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር አድርጎታል።በመሆኑም በአሁኑ ወቅት በክልሉ የሚገኙ ከተሞች የቤት ፍላጎት መሸከም ከሚችሉት አቅም በላይ ሆኖባቸዋል፡፡
አቅርቦትና ፍላጎትን ለማጣጣም የክልሉ መንግስት አቅሙ በፈቀደው መጠን በተለያዩ አማራጮች የመኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ለነዋሪዎች ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።በዚሁ መሠረትም ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ የቤት ልማት አማራጮችን በመጠቀም ቤቶችን ገንብቶ ለነዋሪዎች ተደራሽ አድርጓል። በዚህ የቤት ልማት መርሃግብር የቤት ግንባታ ለማከናወን የተደራጁ የህብረት ስራ ማህበራት ከፍተኛ ድርሻ ይዘዋል።ማህበራቱ በ2006 ዓ.ም በተሰጣቸው ቦታ ላይ 178 ሺ 623 ቤቶችን በመገንባት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡
ከማህበራቱ በተጨማሪ ግለሰቦች በተናጠል ባደረጉት እንቅስቃሴ 12ሺ752 መኖሪያ ቤቶች ገንብተዋል። በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ለሚገኙ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላሉ ነዋሪዎች ደግሞ በክልሉ አቅም ሰባት ሺ 618 ቤቶች፣ በቤት ግንባታ ላይ የተሰማሩ ቤት አልሚዎች (ሪልስቴት) በተዘጋጁ የመኖሪያቤቶች መንደር 921፣ በቤቶች ልማት ድርጅትም እንዲሁ ሰባት መቶ 38 ቤቶች ተገንብተው ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል።
እነዚህ የቤት ልማት አማራጮች በተወሰነ ደረጃ የቤት ፍላጎት ጥያቄውን የመለሰ ቢሆንም አሁንም ፍላጎትና አቅርቦት አልተጣጣመም። በአሁኑ ወቅት ችግሩን ለመቅረፍ በአገር አቀፍ ደረጃ የተነደፈውን የቤት ልማት ስትራቴጂ መሠረት ያደረገ ሥራ ተጀምሯል።
ቀደም ሲል የነበረውን የቤት ልማት አማራጮችን በተሻለ ሁኔታ ማስቀጠል የሚሉት ይጠቀሳል።በክልሉ ከዚህ ቀደም ተግባራዊ ያልሆኑ ሌሎች የቤት ልማት ፕሮግራሞች እንደ 40/60፣ 10/90 እንዲሁም በመንግስት እና በግል ባለሀብት አጋርነት የቤት ልማትን ለማሳለጥ ጥረት ይደረጋል፡፡
ባለሀብቱ ለመሬትና ተያያዥ ለሆኑ ጉዳዮች የሚያወጣውን ወጪ በቤት ግንባታው ላይ ማዋል እንዲችል የመሬት አቅርቦቱን በመንግስት እንዲሸፈን ማድረግ አማራጭ የሌለው ነው። ይህ አማራጭም የቤት ግንባታውን በአነስተኛ ዋጋ መገንባት ያስችላል። የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር አመቺ ይሆናል። እንዲሁም በአነስተኛ ዋጋና በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ቤቶችን መገንባት የሚያስችል መሆኑም ይታመናል።
ለግንባታ የሚውል የገንዘብ አቅም አለመኖርም ሌላው ማነቆ ሲሆን፣ይህንን ችግር ለመፍታትም በእስትራቴጂው ላይ በተቀመጠው አቅጣጫ የመንግስትና የግል ባንኮች፤ የተለያዩ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የብድር አገልግሎት በማቅረብ በቤት ልማት ፕሮግራም ተሳትፎ እንዲኖራቸው ይበረታታሉ።
ከህግ ማዕቀፍ ጋር የተያያዙ ጎታች የሆኑ አሰራሮችም ለቤት ልማቱ እንቅፋት መሆናቸውን ዳይሬክተሯ አመልክተዋል። በአጠቃላይ አላስፈላጊ አሰራሮችን ለማስተካከል የሚያስችሉ ህጎችና መመሪዎች ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ያመለከቱት ዳይሬክተሯ፤ የሪልስቴት የቤት ልማትና ግብይት እንደ ሀገርም እንደ ክልልም የአሰራር መመሪያ የሌለው በመሆኑ በአግባቡ መምራትና ማስተዳደር እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክተሯ እንዳሉት ችግሩን መቅረፍ የሚያስችል በአገር አቀፍ ደረጃ አዋጅ የተዘጋጀ ሲሆን፣ አዋጁን መሰረት በማድረግ የሪልስቴት የቤት ልማትና ግብይቱን በተሻለ ሁኔታ ለመምራት ታሳቢ ያደረገ ሥራ በመከናወን ላይ ይገኛል። በህግ ማዕቀፍ የሚመራ የቤት ልማት አቅርቦትና የተቀናጀ የመሠረተ ልማት ሥራ በማከናወን በቀጣይ የቤት ልማት ፕሮግራሙን ከፍላጎት ጋር ለማጣጣም የሚሰራ ይሆናል፡፡
ሪልስቴት አንዱ የቤት ልማት አማራጭ ቢሆንም ተደራሽ የሚያደርገው ከፍተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ብቻ ነው። ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቤት ፈላጊ ደግሞ በመካከለኛና አነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኝ ህብረተሰብ በመሆኑ በቤት አቅርቦቱ ላይ ያለው ድርሻ አጥጋቢ እንዳይሆን አድርጎታል።
አስገዳጅ የሆነ ህግም ሆነ መመሪያ ባለመኖሩ የሁሉንም ቤት ፈላጊ አቅም ያገናዘበ የቤት ልማት ግንባታ እንዲያከናውን ማድረግ አልተቻለም።ክልሉ በራሱ አቅም እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ዘላቂ መፍትሄ ስለማይሆኑ የቤት ልማት አማራጮችን ከፌዴራል መንግስት ጋር በጋራ በመሆን በማጠናከር ኃላፊነቱን ይወጣል፡፡
በክልሉ ካለው የመኖሪያ ቤት እጥረት በተጨማሪ በማህበር ተደራጅተው የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ለማግኘት ገንዘብ ከፍለው ረጅም ጊዜ የቆዩ የክልሉ ነዋሪዎች መኖራቸውን እና መፍትሔው ምንድን ነው ብዬ ላነሳሁት ጥያቄም ጥቂት የማይባሉ ነዋሪዎች ለረጅም ጊዜ ቦታ ሳያገኙ መቅረታቸው እውነት መሆኑን ነው የገለጹት።
ይህም ነዋሪዎችን እያስቆጣና እያማረረ በመሆኑ ክልሉ ምላሽ ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆኑን አመልክተዋል። አያይዘውም እንዲህ አይነት ችግሮች ካለፉት ዓመታት ጀምሮ ሲንከባለሉ የመጡ ቢሆኑም በአሁኑ ወቅት ለረጅም ዓመታት ገንዘብ ከፍለው ቦታ ለማግኘት ሲጠባበቁ ለነበሩ ማህበራት ቅድሚያ በመስጠት ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ማህበራት እንደየቅደም ተከተላቸው የቤት መስሪያ ቦታ እንዲያገኙ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
ዳይሬክተሯ ሌላው እንደማነቆ ያነሱት መሬት የሚገኘው ከአርሶ አደር በመሆኑ፤ ለአርሶ አደሩ በወቅቱ ተገቢውን የካሳ ክፍያ ከፍሎ ማስነሳት ፈታኝ ነው። ለአርሶ አደሩ የካሳ ክፍያውን ለመክፈል ትልቁን ድርሻ የሚወስደው መንግስት ነው።የመንግስት አቅም በተዳከመ ጊዜ የአርሶ አደሩን መሬት በተፈለገው ጊዜ ማግኘት አይቻልም።ከመንግስት በተጨማሪም ግለሰቦች የሚጋሩት ወጪ ቢኖርም የመንግስት ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ የካሳ ክፍያ በወቅቱ አለመጠናቀቅ ለቤት ልማት ማነቆ ሆኗል፡፡
እንደ አማራ ክልል በቤት ልማት ፕሮግራሙ መምህራን እና ፖሊሶች በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ለመምህራን 30 በመቶ፣ ለፖሊሶች 25 በመቶ ቅድሚያ የሚሰጥበት ሁኔታ በመኖሩ ከሚገኘው መሬት ላይ መምህራን እና ፖሊሶች ቅድሚያ ተጠቃሚ ይሆናሉ።የመምህራን በጊዜ ገደብ የተገደበ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በክልሉ የሚገኙ መምህራን የቤት ልማቱ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
በመሆኑም በዘንድሮ ዓመት በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚሆኑ መምህራን የሉም።ነገር ግን የፖሊሶች ቀጣይነት ያለው በመሆኑ በየጊዜው ከሚዘጋጀው መሬት ቅድሚያ ይሰጣቸዋል።ሌሎች በክልሉ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞችን በተመለከተ ግን እንደማንኛውም የከተማው ነዋሪ ተራቸውን ጠብቀው የሚስተናገዱበት የአሰራር ሥርአት ተዘርግቷል።
በክልሉ ያለው የመኖሪያ ቤት የኪራይ ዋጋን በተመለከተ እንደ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ሁሉ ዕለት ከዕለት እየናረ የመጣበት ሁኔታ መኖሩን አንስተዋል።በመሆኑም ህብረተሰቡ ከሚያገኘው ገቢ የበለጠ ድርሻ ያለውን ወጪ የሚያወጣው ለመኖሪያ ቤት ኪራይ ነው።ወጪው ሌሎች መሰረታዊ የሆኑ ፍላጎቶቹን ለማሟላት እያስቻለው ባለመሆኑ ተቸግሯል ሲሉ ይገልጻሉ።
ይሁንና በአሁኑ ወቅት የቤት ልማት ስትራቴጂው ተሻሽሎ የተቀረጸ በመሆኑ በቀጣይ ችግሩን ለማቃለል ያስችላል የሚል እምነት እንዳላቸው የገለጹት ዳሬክተሯ፤ በተለይም በፋይናንስ አቅርቦት መንግስት ካለፈው ጊዜ በተሻለ ሁኔታ አሁን ላይ የተለያዩ አማራጮችን ማየት እየቻለ መሆኑንም አንስተዋል።
በመሆኑም ከዚህ ቀደም በክልሉ ያልነበሩ የቤት ልማት አማራጮችን በማምጣት ከዚህ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ያለበትና የፌዴራል መንግስትም እያገዛቸው እና አማራጮቹን ተግባራዊ ለማድረግም የክልል ከተሞችን የለዩበት ሁኔታ መኖሩን ይናገራሉ።
እለት ተእለት እየተስፋፋ የመጣውን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ለመመለስ አሁን የተጀማመሩና ከዚህ ቀደም ያልነበሩ አማራጮችን ተግባራዊ ማድረግ ተገቢ ነው።ምናልባትም የቤት ፍላጎቱ ከዚህ በበለጠ እየጨመረ ከመጣ በቀጣይም ሌሎች አማራጮችን መመልከት የግድ ይሆናል።
ለአሁኑ ግን የክልሉ መንግስት ከፌዴራል መንግስት ጋር በጋራ በመሆን እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ መቶ በመቶ ባይሆንም እስካሁን ከነበረው በተሻለ ሁኔታ ችግሩን ለማቃለል የሚሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2013