ታምራት ተስፋዬ
ኢትዮጵያ ግብርናዋን ከኢንዱስትሪ ጋር በማስተሳሰር ከጥምረቱ ፍሬ ተጠቃሚ ለመሆን በ2009 ዓ.ም በአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በይፋ ጀምራለች። ለፓርኮች ግንባታም 17 ቀጣናዎች ተለይተዋል።
በፓይለት ፕሮጀክት ደረጃ የጥሬ ዕቃዎች ምርት መገኛ መሆናቸውን መሰረት በማድረግ የመጀመሪያዎቹ አራት ፓርኮች ግንባታ በአማራ ክልል ቡሬ፣ በምዕራብ ትግራይ ባከር፣ በኦሮሚያ ቡልቡላ፣ በደቡብ ክልል ይርጋለም ከተማ ተጀምሯል።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱትም የአግሮ ኢንዱ ስትሪ ፓርኮች ግንባታ ሂደት በአጠቃላይ አራት ምዕራፍ አለው። ቀዳሚው የአዋጭነት ጥናት ጊዜ ነው። በዚሕ ረገድ ሶስት አመታትን የወሰደ ጥናት ተካሂዷል።
ምርጥ ቦታዎችን ለመለየት፣ በአካባቢው ምን አይነት ምርት አለ? ምን አይነት ፋብሪካ ቢቋቋም አዋጭ ይሆናል የሚለው ተቃኝቷል። ሁለተኛው ኮንስትራክሽን ምእራፍ ነው። የግንባታ ምእራፍ ከተጀመረ አመታት ተቆጥረዋል። አፈፃፀሙ ሲቃኝ ግን በታለመው ውጥንና በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እየሄደ ነው ለማለት እጅጉን አስቸጋሪ ነው። ይሕም በርካቶችን ሲያነጋግር ቆይቷል።
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም ከአንድ አመት ቀድሞ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የግንባታ ሂደት በሚመለከት በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪው ፓርኮች ልማት ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ለሆኑት አቶ አያልነህ አባዋ ጥያቄዎችን አቅርቦ ነበር።
በወቅቱም ዳይሬክተሩ አጠቃላይ የግንባታ ምእራፉ መዘግየቱን አረጋግጠዋል። ለዚህም ኢንዱስትሪዎቹ በተለይ ከአካባቢ ብክለት ተፅእኖ ላይ ስለሚያሳድሩት ጫና በሚመለከት የተደረገው ጥናት ጊዜ መውሰድና የዲዛይን ለውጦችን ጨምሮ ምክንያት የሚላቸውን መሰናክሎች ዘርዝረዋል።
ከሁሉም በላይ አራቱን የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ስራ ለማስጀመር የሚያስችሉ መሰረታዊ የግንባታ ስራዎች በታህሳስ 2012 ዓ.ም መጨረሻ እንደሚጠናቀቁና በተጠቀሰው ጊዜም ሁሉም ፓርኮች ተመቻችተው ለባለሀብቶች እንደሚተላለፉ ገልፀው ነበር።
ይሁንና መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለመረዳት እንደሚቻለው ከአንድ አመት በኋላም አራቱን የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በሙሉ አቅም ስራ ማስጀመር አልተቻለም። አጠቃላይ የፓርኮቹ ግንባታ ሂደቱ በእጅጉ ተንቀራፏል። በእርግጥ በአሁኑ ወቅት በፓርኮቹ መሬት አግኝተው ኢንቨስት ማድረግ የጀመሩ አሉ። በአንዳንድ አካባቢዎችም በተለይ በደቡብ በአማራ ክልል ቀድመው ወደ ስራ የገቡ ባለሀብቶች መኖራቸው እርግጥ ነው።
ይህ የማይናቅና መልካም የሚባል ጅምር ቢሆንም የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ግንባታ በታቀደለት የጊዜ ቀመር መፈፀም ቢችል እንደ አገር ከሚያበረክተው ትሩፋትና ካለው አቅም አንፃር በስኬት የሚጠቀስ አይደለም። ይህንኑ አስመልክቶም ለአቶ አያልነህ አባዋ ዳግም ጥያቄ አቅርበንላቸዋል።
እርሳቸውም የፓርኮቹ ግንባታ መዘግየቱን፣ አሁንም ቢሆን ከባድ የሚባሉ ፈተናዎችን መሻገር እንዳልተቻለና በክልሎች መካከል የአፈፃፀም ልዩነት ስለመኖሩ አምነው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እጅግ ከፍተኛ ወጪና አያሌ ጥናቶችን እንደሚጠይቅና በርካቶች እንደሚገነዘቡት ሕንፃ መገንባት እንዳልሆነ አፅንኦት የሚሰጡት አቶ አያልነህ፣ በአሁን ወቅትም በአጠቃላይ የፓርኮቹ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሂደት ድክመቶች እንዳሉ ሁሉ ጥንካሬና ስኬቶችም እየታዩ ስለመምጣታቸው ይገልፃሉ።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፣ በአሁን ወቅት በተገነቡት ፓርኮች ውስጥም በርካታ ባለሀብቶች ገብተዋል። በአንዳንድ አካባቢዎችም በተለይ በደቡብ በአማራ ክልል ቀድመው ወደ ስራ የገቡ ባለሀብቶች አሉ። ለአብነትም በቡሬ የአስራ አንድ ፋብሪካዎች ግንባታ ተጠናቋል። ሁለቱ ማምረት ጀምረዋል። በይርጋለምም አስራ አንድ ፋብሪካዎች ተሰርተዋል። አራቱ ማምረት ጀምረዋል። በዚህም ከፍተኛ የሚባል የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ተችላል።
ፓርኮቹን በሙሉ አቅም ስራ ለማስጀመር የሚያስችሉ መሰረታዊ የግንባታ ስራዎችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ለባለሀብቶች ለማስተላለፍም የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ናቸው። ሁለት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥም የቡሬና የይርጋለም ፓርኮች ለማስመረቅ ታቅዷል።
ከፕሮጀክቱ ግንባታ ፍፃሜ በተጓዳኝ ብቃትና አቅሙ ያላቸው ባለሀብቶች መመልመል ግድ ይላል። ታላላቅ ባለሀብቶችን ለመሳብና ለማምጣትም ከፍተኛ ቅስቀሳና መረጃን ተደራሽ ማድረግ ይጠይቃል። አቶ አያልነህም በዚህ ረገድ የሚፈፀሙ ስህተቶች አደጋቸው የከፋ ስለመሆኑ አፅንኦት ሰጥተው ነው የተናገሩት። ባለሀብቶች በመመልመል ረገድ ጥናት ላይ ከመመስረት ባሻገር የሌሎች አገራትን ተሞክሮ የመቃኘት ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም ያስረዳሉ።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት የፓርኮች ግንባታ አፈፃጸም ከክልል ክልል ይለያያል። አቶ አያልነህም በዚህ ይስማማሉ። ለአብነት የትግራይ ክልል ፕሮጀክት ወደ ኋላ መቅረቱን ይጠቁማሉ። እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፣ ቀደም ሲል የተለያዩ ባለሀብቶች በክልሉ በሚገነቡ ፓርኮች ውስጥ ለመግባት ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርገው ነበር። ይሁንና በህወሓት ጁንታ አባላት እኮይ ተግባርና በአገር ላይ በፈፀሙት ጥቃት ምክንያት ሂደቱ ተደናቅፏል።
በዚህ እኩይ ተግባር ምክንያትም ከፍተኛ አቅምና ፍላጎት ያላቸው የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችን ማጣት ግድ ብሏል። ከሁሉ በላይ ፕሮጀክቶቹ ይበልጥ አደጋ ውስጥ ገብተዋል። ሌላው ቀርቶ ኮንስትራክሽኑን የወሰደው ሱር ካምፓኒ እግድ ተላልፎበታል። ይህ በመሆኑም ሌላ ኮንትራክተር ከመፈለግ ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት ማከናወን ግድ ይላል።
በክልሉ የፓርኮቹ ፕሮጀክት ሃላፊ ከጁንታው አባላት ጋር አብሮ ጠፍቷል። ይህም ተገናኝቶ መነጋገርን አስቸጋሪ አድርጎታል። በአሁን ወቅትም ከሌሎች አመራሮቹ ጋር ብቻ ግንኙነት እየተፈፀመ ነው። ይህን የማስተካከል ስራ መሰራቱ አይቀሬ ነው። ይሁንና ቀውሱ በቀጣይ አጠቃላይ የግንባታ ምእራፍ ላይ መዘግየትን ማስከተሉ አይቀሬ ነው።
ከመሰል ቀውሶችና ግዙፍ ተግዳሮቶቹ ባሻገር በአጠቃላይ የፓርኮቹ የግንባታ ሂደት የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦትን ተደራሽ ማድረግ ሌላው ከባድ ፈተና ስለመሆኑ ይነሳል። አቶ አያልነህ እንደሚገልፁት፣ በአሁን ወቅት በፓርኮቹ ከሚፈለገው አንፃር የኤሌክትሪክ አቅርቦት ተደራሽ እየሆነ ነው ለማለት አያስደፍርም። ችግሩም በርካታ ባለሀብቶች ወደ ፓርኮቹ እንዳይገቡ ስጋትና መሰናክል ሆኗል።
ለችግሩ ፈጣን እልባት ለመስጠት ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል። ይሑንና ሃይል አቅራቢው ተቋም ለግንባታው የሚያስፈልገው ገንዘብ ማግኘት አልሆነለትም። በአሁን ወቅትም ችግሩን ፈር እየያዘ፣ ፈተናዎችም ምላሽ እያገኙ መጥተዋል። መንግስት ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ስምምነትም አድርጓል።
በአሁን ወቅትም አለምአቀፍ ጨረታ ወጥቷል። በሚቀጥለው ጥር ወር ላይ አሸናፊው ይታወቃል። ፕሮጀክቶቹ በአጠቃላይ 50 ሜጋ ዋት የሚፈልጉ ሲሆን አሸናፊውም ይሕን ተደራሽ ለማድረግ የሰብ እስቴሽን ግንባታ የሚጀምር ይሆናል። አጠቃላይ የሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታው ወጪም 136 ሚሊየን ዶላር ይሆናል።
እንደ አጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርክ ፕሮጀክቶቹ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል። ሂደቱንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበላይነት እየመሩት ይገኛል። የተለያዩ ባለድርሻ አካላትም የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ጀምረዋል። ይሕ በመሆኑም በአጠቃላይ ግንባታ ሂደት ለውጦች እያታዩ መጥተዋል።
30 ቢሊየን ብር የተመደበላቸውና በፓይለት ደረጃ በአራቱ ክልሎች የሚገነቡት የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታቸው በመዘግየቱ ብቻ አገሪቱን ለተጨማሪ ወጪ ዳርገዋል። ፕሮጀክቶቹም የኦፕሬሽን ወጪን ጨምሮ አስር ቢሊየን ብር ተጨማሪ ወጪን ጠይቋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2013