በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
ኢኮኖሚክሱ የሰው ልጅ ፍላጎት ገደብ የለሽ መሆኑን ነገር ግን ያለው ሃብት ውስን እንደሆነ ያስተምረናል፡ ውስን በሆነው ሃብት እና በፍላጎት መካከል ያለውን ለማጣጣም ምን መሆን እንዳለበትም በማመልከት፡፡
ውስን በሆነው ሃብት ዙሪያ የሰው ልጅ በማልማትም ሆነ በማጥፋት ተሰማርቷል።ከውስኑ ሃብት ውስጥ ዛሬ በእኛ እጅ ያለውን ስንቆጥር ምን እናገኛለን? ብለን በመጠየቅ ውስጥ ትምህርትን እንቀምራለን።አለን ብለን የቆጠርነውን ስናስብ የሚሰማን ባለጸጋ መሆናችንን ያሳይ ይሆን ወይንስ ምን? ሌላው ጥያቄ፡፡
የእኛ ብለን የቆጠርነው ሃብት በእጃችን ያለ፣ በባንክ ያለ፣ በሰዎች ዘንድ ያለ፣ በንብረት ያለ፣ ወዘተ አድርገን ቆጥረንም ይሆናል።የሃብት ቆጠራው በእዚህ መልክ የተቃኘ ስለሆነ ማለት ነው።ዛሬ ግን በሃብት ቆጠራነት የማይቆጠረው ነገር ግን የሚቆጠረው ሁሉ መነሻ የሆነውን በልብ ውስጥ ስላለ ወይንም ስለሚሆን ሃብት እናነሳ።በልብ የሞላውን እጅና እግር ሊፈጽመው ይተጋልና ኢኮኖሚክሱ ስርዓት ሊያበጅለት ስላልቻለው በልብ መዝገብ ላይ ስለሚሆነው እናያለን።
በልብ የሞላው …!
የልብ መዝገብ ውስጥ የሚብላላው አመለካከትን የሚቃኝ ሆኖ የሕይወታችንን አቅጣጫ ይመትራል።የአመለካከታችን ጥራት የእርምጃችንን ጥራት፤ የአመለካከታችንን ጥንካሬ የትጋታችን ምክንያት ሆኖ በዙሪያችን ያለውን የሚቆጠረውን ይወልደዋል።በመዳረሻችንም በልባችንና በእጃችን ያለውን ሃብት ለመመልከት አንባቢውን እንጋብዛለን።
አመለካከት ማለት ህይወትን የምትገጥምበት በሂደት ባህሪህን የመወሰን አቅም ያለው የአንተነትህ ማሳያ ነው።አመለካከት በመሰረታዊ ደረጃ ሦስት ነገሮችን የያዘ ነው።እነርሱም የአዕምሯዊ-እይታ ውቅር (mindset)፣ ምልከታዊ ነጥብ (view point) እና የእምነትህ ስርዓት (belief systems) ናቸው።የአመለካከት ጤናማነት ያለንን ማየት እንድንችል ሲያደርግ በተቃራኒው ደግሞ ያለንን አለማየት ሆኖ በሃብት ላይ መተኛት ይከተላል፡፡
የለንም ግን አለን!
በሀገራችን ኢትዮጵያ በቅርቡ በሆነው የመገበያያ ገንዘብ ቅያሬ ጋር በተገናኘ ከሰማናቸው ዜናዎች መካከል ብዙ ገንዘብ እንዳላቸው ከማይታሰቡ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ የሚወጣው ገንዘብ ነው፤ በተለይም በልመና ሥራ ከሚተዳደሩቱ።እንዴት ሰው በልመና ሥራ እየተዳደረ ይህን ያህል ገንዘብ ሊኖረው ቻለ? የሚል ጥያቄ የሚያጭር ክስተት ሊያጋጥም ሁሉ ይችላል።በእርግጥ ይህ መሰሉ ክስተት ሁልጊዜ የሚፈጠር ባለመሆኑ ሁሉም በልመና ላይ የተሰማሩት ዘንድ ተመሳሳይ ነው ሊባል አይችልም።
መሰል ገጠመኞች ግን “የለንም ግን አለን” እንድንል ያደርጉናል።የለኝም ብሎ በልመና ተግባር ላይ የተሰማራ ሰው ወደ ባንክ ለመለወጥ ይዞት የሚሄደው የገንዘብ መጠን የለውም የሚያስብል ሆኖ ሳይገኝ ሲቀር የለውም ግን አለው እንላለን።በልመና የሚተዳደረው ሰው ገንዘቡን ከሌላ አካል ይዞት የመጣ አይደለም የራሱ የሆነ የተጠራቀመ ገንዘብ ነው ብለን እናስብና ባለው ገንዘብ ምን ማድረግ እንደሚችል እይታው ስለሌለው የለውም ግን አለው እንላለን።
የአመለካከት ችግር ሰለባ የሆነ ሰውም የሚመስለው እንዲህ አይነቱን ሰው ነው።የሌለው ግን ያለው! ያለውን የማያውቅ ነገር ግን በየለኝም ውስጥ የሚኖር።ገጠመኙንም የአመለካከት ችግር ሰለባ ለሆነው ሰው እናውለው።የአመለካከት ችግር ውጤቱም የለንም ግን አለን አይነት ውስጥ የሚያኖር ስለሆነ።
በአጠቃላይ ምልከታ ህይወትን የምንገልጥበት ውስጣዊ መሳሪያችን ነው።አእምሮዊ ድምጸት እንዲሁም አስተሳሰብንና ስሜትን የምንገልጥበት መንገድ በአጭሩ ማን መሆናችንን የሚያመለክት የሂደት ውጤት ነው።በአንድ አዳር የማይገነባ በአንድ አዳርም የማይፈርስ የሂደት ውጤት።አመለካከት እስከ እለተ ሞት ድረስ ሁልጊዜ የሚገነባ።እራስህን የምታይበት መስታወት።የሞላ የጎደለውን ሁሉ መመልከት የሚያስችል፡፡
የጎደለውና ያለው ሲቆጠር
በመንገድ ላይ እየሄደ ያለን አንድን ሰው አቁመህ የጎደለውን ነገር ጠይቀው።ይጎድለኛል የሚለውን አንድ ብሎ ጀምሮ ይህን፣ ያንን እያለ የጎደለውን ነገር በሚገባ ይዘረዝርልህ ይሆናል።ያለውን ነገር እንዲቆጥር ብትጋብዘውስ? እውን እንደ ጎደለው ነገር ያለውን ነገር የመቁጠር አቅም ይኖረውስ ይሆን? ምላሹን ለራሳችን፡፡
ካለን ይልቅ የጎደለን ነገር ላይ የማተኮርና የጎደለንን ነገር ለማግኘት የመሮጥ ቅኝት ውስጥ እንድንገባ አድርጎናል።
የእይታ ለውጥ ሲመጣ እውነታውን የተገላቢጦሽ ሊያደርገውም ይችላል።ያለን ከጎደለው መብዛቱ፤ ነገር ግን ማየት ያለመቻላችን ችግር የእይታቻን ለውጥ ሊያስከትል ይችላል።ያለንን ማየት አለመቻላችንን ከጎደሉን ነገሮች ሁሉ ቀዳሚው አድርገን እንድንቆጥር የሚያደርገንም ሊሆን ይችላል፡፡
ጤንነት በጠፋ ጊዜ የጤንነት ዋጋው ፍንተው ብሎ እንደሚታየው።በአጠገባችን ሰውን ፈልገን ባጣን ጊዜ አጠገባችን ያሉት ሰዎች ዋጋ በልዩ ሁኔታ እንድናስብ እንደምንሆነው።ገንዘብን ፈልገን ባጣነው ጊዜ በእጃችን ያለው ገንዘብ ያለው ትርጉምን በተረዳን ጊዜ ወዘተ።ያለንን ተረድቶ ላለን ነገር ትርጉም ለመስጠት የግድ እስክናጣው መጠበቅ እንደሌለብን የእይታ ለውጥ ያስተምረናል፡፡
ያለንን ነገር በብዙ ጎተራዎች አስቀምጠን ማየት ብንችልም ለዛሬው በልብና በእጅ ብለን እንመልከት፡፡በልባችን ያለውን መመልከት።በእጃችን ያለውን መመልከት።የጎደለው ነገርን በአመለካከት ለውጥ ውስጥ ወደ እድል መቀየር እንድንችል የአመለካከት ለውጥ በልብና በእጃችን ያለውን እንድናይ ሊያደርገን ይገባል።
በልብ ያለው – ከትላንት እስከ ነገ!
በልባችን ውስጥ ያለው ነገር እርሱ ያለንን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ትልቅ መስታወት ነው።በእጅህ ያለው ነገር ያለበት ቅርጽም ሆነ ውበት የሚወሰነው በልብህ ውስጥ ባለው መኖር ውስጥ ነው።በልብህ ውስጥ ምን አለ? ለጥያቄው የምትሰጠው መልስ ያለህበት አተያይ በልብህ ያለውን እንዳፈራ ትረዳለህ፡፡
በልብህ ውስጥ እሴትህ አለ፤ በልብህ ውስጥ ትልምህ አለ፣ በልብህ ውስጥ ሚስጥርህ አለ፣ በልብህ ውስጥ ቁጭትህ አለ፣ በልብህ ውስጥ ህልምህ አለ፣ በልብህ ውስጥ እጅህን የሚያሰራው እግርህን የሚያራምደው ነዳጅ አለ።በልብህ ውስጥ ያለህ ነገርህን የምታይበት ትክክለኛም ሆነ የተንሸዋረረው አተያይ አለ።በልብህ ውስጥ ልብህ አለ፤ እርሱም አተያይህ!!!
መኪና የመኪናነት አገልግሎትን ለመስጠት ከሞተሩ ጀምሮ የድርሻቸውን የሚወጡ በርካታ አካላት አሉት። ሞተሩ ደግሞ ከሁሉም የተለየ።የሰው ልጅ ልቡ ውስጥ የሞላው መላ እንቅስቃሴውን የሚወስን ነው።በህይወታችን ጉዞ ውስጥ ከሰው ጋር በመልካም ለመኖር፣ ያቀድነውን ዳር ለማድረስ፣ ደስታንም ሆነ ሃዘንን በልኩ ለማስተናገድ በልባችን ውስጥ የሞላው ነገር ሁለንተናችንን ይወስነዋል።
በህዝብ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች ላይ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ በርካታ አሰራሮችን ለማቅረብ ጥረት ይደረጋል።ይህ ጥረት ግን ውጤታማ የሚሆነው ጥረቱን ህይወት በሚሰጠው ሰው ነው።ሰው ደግሞ በልቡ ውስጥ ያለው መነሳሳት ዋናው ማሳያው ነው።መነሳሳቱም ዘመንን በማትረፍ ትርፍ ውስጥ የሚመዘን፡፡
1. ግቡ – ዘመንን ማትረፍ
ዘመናችንን ስለማትረፍ በብዙ እናስብ ይሆናል።በህይወት ዘመኔ እንዲህ አድርጌ፣ እንዲያ አልፌ መዳረሻዬን እዚህ ጋር ቢሆን ወዘተ ብለን እንንቀሳቀሳለን።በእዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ልብ ትልቁን ቦታ ይይዛል።በተቃኘበት የእይታ ቅኝት ውስጥ ሆኖ።በልቡ የጠወለገ የሚያደርገው ነገር ሁሉ የጠወለገ ይሆናል።
በልቡ የከሳ ድርጊቱ ሁሉ የከሳ ይሆናል።በልቡ የለገመ በነገሩ ሁሉ የለገመ ይሆናል።በተቀራኒው በልቡ የበረታ ደግሞ ከፊቱ የሚገጥመውን ማንኛውንም ፈተና እያለፈ ወደ መዳረሻው ይደርሳል።ይህም ዘመንን ማትረፍ ነው።በጤናማ አመለካከት በተቃኘ ልብ የሆነ የዘመን መትረፍ፡፡
ስለሆነም በልባችን ያለውን በመመርመር በልባችን ውስጥ እግራችንን ወደ መዳረሻው ሊያደርሰው በሚያስችለው ነዳጅ መሙላት አስፈላጊ ነው።በልባችን ያለውን አላስፈላጊውን በማውጣት በልባችን ውስጥ ነገ ራሳችንን ልንገኝ በሚያስፈልገን ስፍራ ላይ እንድንገኝ የሚረዳንን ልንጨምር ይገባናል።
ለግብ መሳካት ትጋትን፣ ቂምን በይቅርታ መተውን፣ መሰጠትን፣ ሰላም ወዳድነትን፣ ፍቅርን፣ ትብብርን፣ ወዘተ፡፡የለውጥ መንገዱ ላይ ለመግባት መነሻው ደግሞ ልብን ማድመጥ።ቢቻል በዙሪያችን ካለው ጩኸት ለሰዓታትም ቢሆን ገለል ብሎ ልብን ማድመጥ።
2. መነሻው – ልብን ማድመጥ፣
በሰዎች መካከል በሃሳብ ጭልጥ ብለው የሄዱ ሁለት ሰዎችን በምናባችን እናስብ።ሁለቱም ሰዎች በራሳቸው ዓለም ውስጥ ጭልጥ ብለው ሄደው እያወጡ እያወረዱ ነው።የሚያወጡ የሚያወርዱትን ሲጨርሱ ነገራቸውን በልባቸው ውስጥ ይሰውሩታል።በልብ ውስጥ ሰፊ የመወያያ አዳራሽ አለ።ግለሰቡ አንስቶ ከሚጥላቸው ጉዳዮች ጋር በአዳራሹ ይሰየማል።በሁላችን ልብ ውስጥ ይህ አዳራሽ አለ።በአዳራሹ ውስጥ በጥሞና የሚቆየው ሰው የራሱን ሃሳብ ትቶ ከልቡ የሚወጣውን ድምጽ ለማድመጥ ከፈለገ እንዲሁ ድምጽ ከልቡ ይወጣል።ልብ ውስጥ ድምጽ አለ።
ድምጹን ለመስማት በጥሞና መሆንን ግን ይፈልጋል።ትላንትን በሚገባ አገናዝቦ ነገ ልንሄድ የሚገባን መንገድ በማሳየት ረገድ በልቦናችን ውስጥ የሚሰማ ድምጽ።ድምጹን ላለመስማት በዙሪያችን ጩኸት ማብዛት ተገቢ አይደለም።በልባችን ውስጥ ያለውን ድምጽ አዳምጦ መሆን ያለበትን አንድ ሁለት ብሎ አስቀምጦ ወደፊት ከመራመድ ውጪ መቆም አዋጭነት የለውም። አተያይ በእጅጉ የሚረዳን ልብን ማረቅ ደግሞ ልብን ከማድመጥ በልብ ያለውን ወደ መኖር ያመጣል፡፡
3. መንገዱ- ልብን ማረቅ፣
የሚመጠው የሚሄደው ሁሉ በልባችን ቀጠና ጎራ ማለትን ይፈልጋል።ሚዲያው የልቦናችንን ትኩረት ይፈልጋል።በማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች የምንከተላቸው ሆኑ የሚከተሉን ትኩረትን ፍለጋ በልባችን ኮሪደር በኩል ማለፍን ይፈልጉም ይሆናል።በማህበራዊ ህይወታችንም ይሁን ቅርብ የሆነው ቤተሰባዊ ህይወታችን ውስጥ ልባችንን መሻቱ በሰፊው አለ።
የልባችን ውስንነት በኢኮኖሚክሱ የሃብት ውስንነት አንጻር ሊታይም ይችላል።በፍጹም ለሁሉም ነገር ጊዜ ልንሰጥ አንችልም።በሁሉም ቦታ መገኘትም እንዲሁ።ሁሉንም ችግር ልንፈታው አንችልም።ሁሉንም መስራት የምንፈልገውን ሁሉ መስራትም አንችልም።ስለሆነም ልባችን ሊታረቅ ይገባዋል።የሚታረቀውም በጠንካራ እሴቶች የተቃኘ አንድ ሁለት ብለን ልናከናውን ያቀድነውን ለማሳካት በትኩረት በመዘርጋት ነው።
ልባችን በአግባቡ ሲታረቅ የእግራችን እርምጃም ሆነ የእጃችን እንቅስቃሴ ድምር ውጤቱ መድረስ የምንፈልገው ላይ ነገ ላይ ደርሰን መገኘት ይሆናል።በየቅጽበቱ ትኩረት ከሚሻ ነገር ሁሉ ተገድበን ልብን በማረቅ ከትላንት እስከ ነገ ቅኝቱ ፍሬያማነት የሆነን ጉዞን መጓዝ።
ያለንባት ዓለም ነገሮች አልጋ በአልጋ የሆኑባት ባለመሆኑ ልብ የሚያዝል ነገር ሲከሰት እንዴት ማለፍ እንደሚገባ እንዲሁ ማወቅ ያስፈልገናል።የልብ ዝለት ከሩጫችን መገታትን እንዳያመጣ ማለት ነው።
4. መጽናቱ – ልብ ሲዝል
እንጨት ለቅሞ ለማምጣት ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጦ በመሄድ ውስጥ ጉልበት ይዝላል።እቃ በመሸከም ሥራ ላይ የተሰማሩ ወገኖቻችንም የሚሰሩት ስራ እንዲሁ ለጉልበት መዛል ምሳሌ ሊሆን ይችላል።የጉልበት መዛል እንዳለ ሁሉ የልብ ዝለትም አለ።በምን ጉዳይ ልብህ ዝሎ ያውቃል? መፍትሄው የዝለቱን ምክንያት ማወቅ መቻል ላይ ነው።
የልብ ዝለት ምክንያት የሆነውን ነገር ለመፍታት ጥረት ማድረግም እንዲሁ።በዛለ ልብ ውስጥ ቀናትን ከማበላሸት የዝለትን ምክንያት በመፈተሽ ወደ መፍትሄ መሄድ ተገቢነት አለው፡፡
ልብ የሚያዝሉ ነገሮች በሚገጥሙን ጊዜ የሚኖረን ምላሽ የህይወታችንን አቅጣጫ ወደማይሆን መስመር እንዳይወስዱት የታነጽንበት አመለካከታችን ስራውን ይሰራል።አንዱ ሰው ወጀቡን ወደ አንድ ሌላ የእድል ምዕራፍ መቀየሪያ አድርጎ ማሰብ ሲችል ሌላው ሰው ደግሞ ወጀቡን እንደ መጠፊያ አድርጎ ይቆጥራል፤ ሁለቱም ከአመለካከታቸው ቅኝት ይነሳሉና።ምክንያቱም አመለካከት እራስህን፣ ሌሎችን፣ ሁነቶችን፣ ልምዶችን፣ ነገን እንዲሁም በዙሪያህ ያለውን መላውን ዓለም የምታይበት መስታወት ስለሆነ።
ሁሉም ሰው የራሱ የሆነን የአመለካከት መነጽርን ለብሶ ይዞራል፤ ለአንተ የእራስህ አመለካከት ልዩ ነው።አንተ እያየህ ያለኸው ብርሃናም፣ ጨለማ፣ ጽጌሬዳማ፣ ግልጽ፣ የተበላሸ ወይንም ሌላ ሊሆን ይችላል።አመለካከትህ ደግሞ ባህሪህ ላይ ተጽእኖን ያሳድራል።
ባህሪህን በተግባር የምትኖረው ከአመለካከትህ ጋር ባለው ወጥነትም ነው።የአመለካከት ዙር በሚዞርበት መዞር ውስጥ የምታየውን እየተረጎምክ በትርጉምህ ውስጥ እይታህን አድርገህ ከመንትዬ ወንድምህ በተለየ አቅጣጫ እንድትሄድ በሚያደርግ መንገድ ልትሄድ ትችላለህ።መጽናቱም ሆነ አለመጽናቱ ያለው በአመለካከትህ ውስጥ ስለሆነ።ልብህ ደግሞ ማብላያው ስፍራና የምትራመድበት ጉልበት ሃይል ማመንጪያ፡፡
ለእራስህ ፈጽሞ እንደማይሳካልህ ስትናገር ጽናትህን የሚፈትን ልብህን የሚያዝል በእራስህ ላይ ያለህ እምነት ማሳያ ነው።በእራስህ ላይ የሚኖርህ እምነትን የምትገልጥበት መንገድ እርሱ ወሳኝነት አለው።… እኔ ፈጽሞ አይሳካልኝም ማለት እርሱ… (የእራስ እምነት/self-belief)፤ በእራስህ ላይ ያለው እምነትህ አንተ ዋጋ ያለህ አድርገህ እራስህን እንዳትቆጥር ወደሚያደርግ እይታ ሲመጣ (perception)፤ ከእዚህ የተነሳ ተሸናፊ እንደሆንክ የሚሰማህ ስሜት ሲጎለብት (ስሜት feelings)፤ ይህ ሁኔታ አመለካከትህ ላይ ተጽእኖ ሲኖረው attitude፤ ስለእዚህ እንደ ተሸናፊ መመላለስ ስትጀምር በራስ ራስህን አፍነህ ስታጨናግፋው (ባህሪ behaviour)፤ የመጨረሻ ውጤቱ – ያልተሳካለት ሰው መሆን ሲሆን! (ውጤት outcome)፤ ይህ ሁኔታ አንተ ፍጹም የተሳካለት ሰው ልትሆን እንደማትችል እንድታምን ሲያደርግህ (self-belief) ከአስተሳሰብህ ቅኝት የተነሳ የዙረቱ ድምር ውጤት መክሰር ሲሆን ራስህን ታገኘዋለህ።
ልብ ሲዝል ሊሆን የተገባው መጽናት ከአመለካከት ውስጥ የሚወጣው በእዚህ መንገድ ነው።ይህ የባህሪ ዙረት ነው፤ ከቀን ወደ ቀን የሚደጋገም።በአሉታዊ አመለካከት የመቅረጽ ሂደቱ ድግግሞሹ በጨመረ ቁጥር የበጎ ነገር ንቃትህ እየቀነሰ እንድሄድ የሚያደርግ። በልብ ውስጥ የሚብላላው እግርን የሚያራምደው ሃይል ክብደት ማሳያ።ያለህበትን ሁኔታ ለመለወጥ ካልመረጥህ በስተቀር ተሸናፊነትህን እየጨመረው መሄዱ አይቀሬ ነው።
መፍትሄው በአንተው ዘንድ አለ።ምክንያቱም …!!! አመለካከት ምርጫህ ስለሆነ/Attitude is a choice. ለራስህ አሉታዊ አመለካከት ፈጥረህ እራስህን የማይረባ ወይንም ለውድቀት የሚኖር አድርገህ ስትኖር አእምሮህ ይህንን ወደ ባህሪ በመውሰድ እስረኛ ያደርግሃል።በታሰረ ልብ የሚኖር ኑሮ።ስለ እራስህ ያለህን አመለካከት እስካልቀየርክ ድረስ ዙረቱ/cycle እራሱን እየደገመ የሚቀጥል ይሆናል፡፡እስረኛው ልብ ሌላ እስረኛ ልብን እየፈጠረ።
ስለሆነም አመለካከትህን ለመቀየር የተግባር እርምጃን መውሰድ ከአንተው ይጠበቃል።ይህም ከልብህ ውስጥ ያለውን በማወቅ እና ሊኖር የሚገባውን በመወሰን ይሆናል።በልብህ ምን አለ? አስተሳሰብህ ከልብህ ያደረገውን በመመርመር ለመፍትሄ የመነሻው ጥያቄ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2013