ፍሬሕይወት አወቀ
ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ በሁሉም ዘርፍ ሀገሪቱን ወደ ብልጽግና የምታደርገውን ጉዞ የሚያሳልጥ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይህ የልማት ዕቅድ ባለፈው ጊዜ ከነበረው ሀገራዊ ዕቅድ የሚለይበትና በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ የሚኖረው ተስፋ ምን ይሆን ስንል ላነሳነው ጥያቄ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የፕላንና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር ነመራ ገበየሁ እንዳሉት፤ የ10 ዓመት የልማት ዕቅዱ በሂደቱ፣ በትግበራ ጊዜ ርዝመቱና በይዘቱ ከዚህ ቀደም ከነበረው ዕቅድ እጅግ የተለየ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የዕቅዱ ዓላማ ኢትዮጵያ በልማት ስኬት እንዲሁም በብልጽግና ለአፍሪካ ተምሳሌት የሆነች ሀገር መገንባት ነው፡፡ ብልጽግናውም በኢኮኖሚያዊና በቁሳዊ ነገሮች ብቻ የሚለካ እንዳልሆነና በማህበራዊ ልማትም ሀገር ውስጥ በምንገነባቸው ስርዓቶች ተምሳሌት ሆና እንድትታይ ያስችላታል፡፡
እስካሁን ባለው ልምድ በረጅም ዕይታ ውስጥ ሆኖ ማቀድ ባለመቻሉ በሀገሪቱ ትላልቅ የልማት ማነቆዎች አጋጥመዋል፡፡ እነዚህን ማነቆዎች ለመፍታት ሀገራዊ ተቋማትን ለመገንባት የተዘጋጀ ዕቅድ ነው፡፡ ሌላው ከዚህ በፊት በአምስት ዓመት የሚወሰንና የፓርላማ እድሜ የነበረው ሀገራዊ የልማት ዕቅድ በአሁን ወቅት ከፖለቲካ አስተዳደር ስርዓት የወጣ በመሆኑ ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ማሳተፍ ተችሏል።
ዋናውና ትልቁ ነገር በእድገቱ በኩል የሚታይ ውጤት እንደመሆኑ ኢኮኖሚያዊ እድገቱ ቀዳሚ ነው፡፡ እርግጥ ነው ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ጥሩ የሚባል የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግባለች፡፡ ነገር ግን እድገቱ መሰረተ ልማቶችን ከማስፋፋት የመጣው ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞም የጥራት ጉድለቶች አጋጥሟል፡፡
የሚፈለገውን ያህል የስራ እድል መፍጠር አልተቻለም፡፡ ኢኮኖሚያዊ እድገት ቢመጣም የኑሮ ውድነቱም በዛው ልክ ጣራ ነክቷል፡፡ በተለይም በዋጋ ግሽበቱ በኩል የማክሮ ኢኮኖሚው እጅግ በጣም ችግር ውስጥ የገባበት እንደነበር ዶክተር ነመራ ይናገራሉ፡፡
አሁንም እድገቱ ሲቀጥል ከመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ባሻገር በሁሉም ዘርፎች ምርትና ምርታማነትን ማምጣት ካልተቻለ የሚፈለገውን የስራ እድል መፍጠር አይቻልም፡፡ ትልቁ የሀገሪቱ የዋጋ ግሽበት ችግር ከምግብ አቅርቦት በኩል የሚመነጭ ነው፡፡ በፋይናንስ በኩልም እንዲሁ ሀገሪቱ ወዳልተፈለገ የዕዳ ጫና ውስጥ እንዳትገባ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል፡፡
ዕቅዱ እድገትን ብቻ በቁጥር መለካት ሳይሆን በማህበራዊ አገልግሎት ሊሻሻሉ የሚገባቸውን ዘርፎች መሰረት በማድረግ ነው፡፡ የተለያዩ የህዝብ አገልግሎቶች ከፍትህ ተደራሽነትና ፍትሀዊነት የጤና፣ የትምህርት፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ በከተማም በገጠርም ተደራሽ በማድረግ የሰው ልጅ ትርጉም ያለው ህይወት መኖር የሚያስችላቸውን ተግባራት ይጨምራል፡፡
አሁን ያለውን 180 ዶላር የነፍስ ወከፍ ገቢ ከእጥፍ በላይ በማሳደግ ኢትዮጵያን ከዝቅተኛ ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ማሰለፍ ነው፡፡ እርግጥ ነው ኢትዮጵያ ዘንድሮ ባስመዘገበችው እድገት ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ገብታለች፡፡ ነገር ግን የመካከለኛ ገቢ ክፍል በገቢ እድገት ብቻ የሚለካ አይደለም፡፡
በማህበራዊ አገልግሎት ዘርፎች በሚገነቡ ስርዓቶችም መመዘን መቻል አለበት፡፡ እንደ ሰብአዊ መብት ባሉ ስርዓቶች መታየት ያለበትን የመካከለኛ ገቢ ክፍል ምሉዕ ማድረግ እንዲቻል አስር ዓመቱ ውስጥ አጠቃላይ ተቋም የመገንባት ስራ ይሰራል፡፡
ትልቁ ጉዳይ የዜጎችን ገቢ ማሳደግ ቢሆንም የሰው ልጅን ሕይወት ስኬት በገቢ ብቻ መለካት አይቻልምና የተለያዩ የማህበራዊ አገልግሎቶች እኩል ተደራሽ መሆን አለባቸው፡፡ ለዚህም መንግስት ትክክለኛውን የማስፈጸሚያ መንገድ መከተል ይኖርበታል፡፡
የልማት እቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግ ስንነሳ ከጅማሮ እስከ ፍጻሜው ድረስ ያለውን እንቅስቃሴ መከታተል የሚችል ጠንካራ ስርዓት መገንባት ትልቁ የቤት ስራ ነው፡፡ ይህን መሸከም የሚችል ስርዓት ከመገንባት ጎን ለጎን የሲቪክ ማህበራትን ሚና ማጉላትና በየጊዜው የሚኖራቸውን ተሳትፎ ማስፋት ያስፈልጋል፡፡
ከዚህም ባለፈም እቅዱን ማቀድ ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡን ቀጥታ ተሳታፊ በማድረግ እቅዱ በየጊዜው እየተገመገመ ማለፍ የሚችልበትን ስርዓት ማጠናከር ይገባል፡፡ እቅድ አውጥቶ ከ10 ዓመት በኋላ በመገምገም ዓላማውን ማሳካት አይቻልም፡፡ ስለዚህ በአንድ፣ በሁለትና በሶስት ዓመት እቅዱ እየተዘረዘረ ተፈጻሚነቱን የማረጋገጥ ስራ ይሰራል፡፡ ለተግባራዊነቱም የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ሀገራዊ የልማት እቅዱ ህዝቡ በሚያውቀውና በሚረዳው ቋንቋ መቀረጽና መገምገም እንዳለበት አመላክተዋል፡፡
ሌላኛው የምጣኔ ሀብት ምሁር ዶክተር ተሾመ አዱኛ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ የ10 ዓመት እቅድ ካለፈው ጊዜ የተለየና ራዕዩም የአፍሪካ ተምሳሌት መሆን እንችላለን በሚል መዘጋጀቱን አንስተዋል፡፡ የአፍሪካ ተምሳሌትነታችንም ድህነት ቅነሳ ላይ ብቻ ሳይሆን ከዛ ባለፈ ወደ ብልጽግና ጉዞ በሚል የተዘጋጀ ነው፡፡ ለዚህም ዋና ዋና የሚባሉ ሴክተሮች እንደ ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ማዕድን፣ የቱሪዝም ወዘተ ተለይተዋል፡፡
ከዚህ በፊት የገበያ ችግር አለ ተብሎ የሚታመን እንደነበር አስታውሰው ነገር ግን የ10 ዓመት የልማት ዕቅዱ በመንግስትም ሆነ በገበያው በኩል ያለውን የስርዓት ችግር ለመቅረፍ አልሟል፡፡ ያደገው ኢኮኖሚ እስካሁን ባለው ሂደት ፍትሀዊ መሆን አልቻለም። ስለዚህ አሁን የሚካሄደው የኢኮኖሚ ዕድገት ፍትሀዊ ይሁን የሚል ነው፡፡
ኢኮኖሚው አድጎ መንግስት በፈለገበት መንገድ የሚጠቀምበት እንዲሆንና መንግስት የራሱ ድርሻ እንዳለው ሁሉ የግሉ ባለሀብትም በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረውን ሚና አጠናክሮ መቀጠል የሚያስችል በመሆኑ እቅዱ ሲጠናቀቅ የሀገሪቷ የነፍስ ወከፍ ገቢ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ መሰለፍ የሚችል ነው። እንዲሁም የድህነት መጠኑን የሚቀንስ ይሆናል፡፡
እቅዱ በከተማ ደረጃ 18 በመቶ የደረሰውን ስራ አጥነት ወደ ዘጠኝ በመቶ ማውረድ፤ የኢኮኖሚውን ዕድገት በአማካይ በ10 ነጥብ ሁለት ማሳደግ፤ የነፍስ ወከፍ ገቢውን በየዓመቱ ስምንት ነጥብ ሁለት ማሳደግ፤ የግብርናን እድገት በማፋጠን አሁን ካለበት የ32 በመቶ ድርሻ ወደ 22 በመቶ ማውረድ፤ እንዲሁም የኢንዱስትሪን ድርሻ ከ27 በመቶ 35 በመቶ ከፍ ማድረግ፤ በእቅዱ የተካተቱ ናቸው፡፡
የኢኮኖሚውን መዋቅር ዘመናዊ ማድረግ ዋናው ግብ በመሆኑ ግብርና ያድጋል፤ ነገር ግን ባለድርሻው ይቀንሳል፡፡ ኢንዱስትሪ በፈጣን ሁኔታ ያድጋል ይህም ኢኮኖሚው ላይ ያለው ሚና ይጨምራል። ስለዚህ የመዋቅር ለውጥ ይመጣል፤ የግሉ ዘርፍ ሚናም ከፍተኛ ይሆናል፡፡
ከዚህ በፊት የኢኮኖሚው ለውጥ የሚለካው በኢኮኖሚው እድገት ብቻ በመሆኑ ኢኮኖሚው አደገ ብቻ ይባላል፡፡ ነገር ግን ይህ የ10 ዓመት የልማት እቅድ እድገቱ በዜጎች ሕይወት ላይ በተጨባጭ ምን ለውጥ ይዞ መጣ የሚለውን ለመመለስ በተለየ ሁኔታ ተካቷል፡፡ እስካሁን በሀገሪቱ የታየው ለውጥ እንደ ኢኮኖሚ ለውጥነቱ ብንቀበለውም የማህበረሰቡን ሕይወት በመለወጥ ሂደት ውስጥ ብዙ ችግሮች ያሉበት ነበር፡፡ በመሆኑም መሰረታዊና ዘመናዊ ለውጥ ማምጣት አልቻለም፡፡
ስለዚህ የ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ ኢኮኖሚው አደገ ከማለት በዘለለ በህብረተሰቡ ሕይወት ላይ በተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ያለመ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ስለሆነም እያንዳንዱ ዜጋ ለተግባራዊነቱ የራሱን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ ዶክተር ተሾመ ያሳስባሉ ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 23/2013