ውብሸት ሰንደቁ
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የመጪዎቹን አሥር ዓመት ጉዞውን አቅዷል፡፡ ለአፈፃፀም ያመች ዘንድም ትልሙን በሁለት ምዕራፎች ከፋፍሏል፡፡ ከተቋሙ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ፤ የመጀመሪያው አምሥት ዓመት ከተያዝው በጀት ዓመት እስከ 2017 ዓ.ም የሚፈፀም ሲሆን ሁለተኛው አምሥት ዓመት ደግሞ ከ2018 እስከ 2022 ዓ.ም የሚዘልቅ ነው፡፡
የመጀመሪያው ምዕራፍ ከ2013 እስከ 2017 ዓ.ም ባሉት አምሥት ዓመታት ዘርፎችን ለመለየት የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ የሚያስገቡ ጉዳዮች በቀዳሚነት ተዘርዝረዋል፡፡
በዚህም መሰረት በዓለም ላይ እና በሀገር ውስጥ ያለውን የገበያ ተፈላጊነት ፣ ምርቶችን ለማምረት የሚያስፈልግ ቴክኖሎጂ፣ የሚፈጥሩት የሥራ ዕድል፣ በዘርፎች መካከል ሊኖር የሚችል ትስስር እንዲሁም የወጪ ንግድ ምርቶች ስብጥር ማስፋትን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተለያዩ ዘርፎች እንዲለዩ ተደርጓል፡፡
በመጀመሪያው አምሥት ዓመታት በአግሮ ፕሮሰሲንግ ምግብ፣ መጠጥ፣ ስኳር፣ ስጋና ወተት፣ ማርና ሰም፤ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ፤ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፤ የግንባታ ግብአቶች (ሲሚንቶ እና ብረታ ብረት፤ መሰረታዊ ኬሚካልና የኬሚካል ውጤቶች፤ ፋርማሲዩቲካል እና የሜዲካል ዕቃዎች)፤ ለወረቀት ምርት ግብዓት የሚሆን ፐልፕ ማምረት እና ህትመት፤ የእንጨት ውጤቶች፤ የግብርና ግብዓቶች (ማዳበሪያና ፔስታሳይድ፤ ፕላስቲክ/ፒቪሲ)፣ ኤሌክትሮኒክስ የመገጣጠም ሥራ ያሉት ዘርፎች ተለይተዋል፡፡
በሁለተኛው ምዕራፍ ከ2018 እስከ 2022 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ደግሞ ከፍተኛ ሙያዊ ክህሎት፣ ሀብትና መሰረተ ልማቶች የሚጠይቁ ምርቶችን የላዕላይ ትስስርን ታሳቢ በማድረግ ኬሚካልና የኬሚካል ውጤቶች፤ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ውጤቶች የትራንስፖርት መሣሪያዎች (አውቶሞቲቭ)፣የጨርቃ ጨርቅ፣ የቆዳና የወረቀት፣ ፕላስቲክ (ፖሊመር)፣ የሜዲካል እቃዎች፣ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ እና የኤሌክትሮኒክስ የተለያዩ ክፍሎችን ማምረት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል፡፡
እነዚህን ዕቅዶች ለማሳካት የንግድና የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ መሪ የልማት ዕቅድ በዋናነት ወደፊት የሚገነቡ አምራች ዘርፎች በተቻለ አቅም ጠንካራ የምርት ሰንሰለት እንዲኖራቸው ለማስቻል ይሠራል። ይህም በሀገር ውስጥ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ለጥሬ ዕቃነት የሚጠቀሙባቸውን ግብዓቶች በሀገር ውስጥ ምርቶች በመተካት የኢንዱስትሪዎች ትስስር እንዲፈጥሩ ምክንያት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ በመሄዱም ከአሥርት ዓመታት በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት አስቻይ ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል። ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን የትኩረት መስኮች በተለዩበት ወቅት በዘርፎቹ መካከል ያለው የኋልዮሽ እና የፊትዮሽ ትስስር ታሳቢ ተደርጓል።
ለዚህም የተለያዩ አገራት ተሞክሮ የታየ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት የዓለምን አጠቃላይ ኢኮኖሚ ከ28 በመቶ በላይ መቆጣጠር የቻሉትን የሩቅ ምሥራቅ ሀገራት በተለይም የኮሪያ ተሞክሮ ተወስዷል።
በመሆኑም በመጀመሪያ የአምሥት ዓመታት በተመረጡት ንዑስ ዘርፎች ዙሪያ የሚሠሩ አነስተኛ፣ መካከለኛ እና ትልቅ ኢንዱስትሪዎች ላይ በትኩረት በመሥራት አሁን ያሉትን የተፈጥሮና የሰው ሀብት እንዲሁም መሰረተ ልማቶች በመጠቀም ዕድገት እንደሚመዘገብ ይጠበቃል።
የኬሚካል የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪና ሌሎች እንደ ግብርና፣ ፋርማሲዩቲካል፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ ጨርቃጨርቅ እና ቆዳ ኢንዱስትሪዎች የሚፈልጓቸውን ግብዓቶች በጥናትና ምርምር ለይቶ ምርቶችንም በማልማት አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን እና ስትራቴጂዎችን በመቅረፅ እንዲሁም በጀት በመመደብ እና የተለያዩ ምንጮችን በማስተባበር የሚሠራ ይሆናል።
ከዚህም በተጨማሪ አንዱ ኢንዱስትሪ ከሌላኛው ኢንዱስትሪ የሚፈልገውን በመለየት የምርቶች የጎንዮሽ ትስስር በማረጋገጥ፤ ምርቶች ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በሀገር ውስጥ ብቻ ሊመረቱ የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር የሚያስችሉ አመቺ ሁኔታዎችን እና ትስስር መፍጠር የዘርፉ የውስጣዊ ትስስር ዕቅድ ነው።
ዕቅዱን ለማሳካት የሚደረጉ ውጪያዊ ትስስሮች በርካታ ሥራዎችን የሚጠይቁ ናቸው፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከሌሎች ዘርፎች ጋር ከፍተኛ ትስስር ያለው ሲሆን ከሌሎች ዘርፎች ምርቶችን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ እሴት በመጨመር ለሀገር ውስጥና ለውጪ ንግድ የሚያቀርብ ነው።
በመሆኑን ከሌሎች ጋር ለቀጣይ አሥር ዓመታት የቅንጅት ሥራ ለመስራት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ የክልል ቢሮዎች እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ተለይተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የንግድ ሥራ አመቺነት ደረጃን ለማሻሻል የንግድ ሥራ ለመጀመር ያለ አመቺነት ውጤቷን በማሻሻል በ2022 ዓ.ም ከምርጥ 50 አገሮች ተርታ ለማሰለፍ ይሠራል፡፡ ይህን ለማድረግ እንዲቻል በርካታ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ የምርቶችን ጥራትና የመለኪያ መሣሪያዎችን ትክክለኛነት በማረጋገጥ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እና የገበያ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ እንዲሁም ሀገር ውስጥ የሚመረቱ አስገዳጅ የሆኑ ምርቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን ኢንስፔክት በማድረግ ጥራታቸው፣ ደህንነታቸውና ትክክለኛነታቸውን የማረጋገጥ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡
በሀገር ውስጥ ተመርተው እንዲሁም ከውጭ ሀገር ተገዝተው የሚገቡ አስገዳጅ የሆኑ ምርቶች ላይ የሚደረግ የኢንስፔክሽን ሥራ አሁን ካለበት 28 የምርት ዓይነት በ2022 ወደ 68 ማሳደግ ብሎም የገቢ ምርቶች ላይ የሚደረግ የምርቶች ጥራት ፍተሻ አሁን ካለበት 1 ሚሊዮን 950 ሺህ ሜትሪክ ቶን በ2022 ወደ 3 ሚሊዮን 485 ሺህ 630 ሜትሪክ ቶን ለማሳደግ እንደሚሠራ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
የወጪ ምርቶች ላይ የሚደረግ የምርት ጥራት ፍተሻ አሁን ካለበት 650 ሺህ ሜትሪክ ቶን በ2022 ወደ 1 ሚሊዮን58 ሺህ 781 ማድረስ እንዲሁም የመለኪያ መሣሪያዎችን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ላይ በትኩረት ይሠራል፡፡
የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አሁን ካለው 6 ነጥብ 8 በመቶ የኢኮኖሚ ድርሻ በ2022 ወደ 17 በመቶ ማሳደግ፤ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ከነበረበት አማካይ 16 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 20 ነጥብ 6 በመቶ ማሳደግ እንዲሁም አሁን ያለውን 50 በመቶ አማካይ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም በ2022 ወደ 85 በመቶ ለማድረስ ይሠራል፡፡
በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ስትራቴጂክ ገቢ ምርት የሚተኩ አምራች ኢንዱስትሪዎች በማስፋት አሁን ያለው 30 በመቶ የሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻ በ2022 ወደ 60 በመቶ ማድረስ፤ በአጠቃላይም በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚፈጠረው አዲስ የሥራ ዕድል አምስት ሚሊዮን ለማድረስ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል፡፡
ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በተገኘው መረጃ መሰረት የዕቅዱ ማስፈፀሚያ ዋና ዋና ስልቶች ተዘርዝረዋል፡፡ ከማስፈፀሚያ ስልቶች ውስጥ አንዱ የአሠራር ማሻሻያ ማድረግ ሆኖ ተቀምጧል፡፡ በዚህ ውስጥ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ለማበረታታት የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀትና መተግበር፤ በጥናት ላይ የተመሠረተ ዘመናዊ የግብይት ሰንሰለት መዘርጋት፤ የጥራት ኢስፔክሽንና ሬጉላቶሪ ሥራዎችን ሪፎርም ማድረግ፤ የዘርፉን ተልዕኮዎች እና የትኩረት መስኮችን መሰረት ያደረገ አደረጃጀት መዘርጋት እና የሰው ኃይል ልማት ማካሄድ፤ የተቋማት ቁርኝት ትግበራ ማጠናከርና ማስፋፋት፤ የምርት ሰንሰለቱን ማሻሻል እና ለገበያ ተደራሽ ማድረግ ነው።
እንዲሁም የቁጥጥር ሥርዓትን በማጠናከር ህገወጥ ንግድን መቆጣጠር እና የጥራትና መሰረተ ልማት ፖሊሲና የደረጃዎች ስትራቴጂ ተግባራዊ ማድረግ የህግ ማእቀፎችን ማሻሻል የሚሉ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ምርቶች ሊያሟሏቸው የሚገቡ ደረጃዎችን ማውጣት እና መቆጣጠር፤ ንግድ ለመጀመር የሚያስፈልጉ ከባቢ ሁኔታዎችን ማሻሻል እና ዘመናዊ ማድረግ ብሎም የካይዘን ሥራ አመራር ፍልስፍና፣ የጥራት ሥራ አመራር፣ የቤንች ማርኪንግ ሥራዎች መተግበር ተቀምጠዋል፡፡
የቴክኖሎጂ ማሻሻያ ማድረግ የዕቅዱ ማስፈፀሚያ ሌላው ስልት ሆኖ ተቀምጧል፡፡ በዚህ ሥር በዓለም አቀፍ ደረጃ ምርትና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ምርጥ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ማምጣት፣ ማላመድና ማሸጋገር፤ ዲጂታል መር የሆነ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓትን ማስፈን፤ የገበያ መረጃ ክፍተቶችን በሥርዓት እና በቴክኖሎጂ በመታገዝ ማስወገድ፤ የፋይናንስና መሠረተ ልማት አቅርቦት የማበረታቻ ሥርዓቶችን ማጠናከርና የኢንዱስትሪ ግብዓትን አቅርቦት ማመቻቸት፤ ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን መሳብና ሌሎች ስልቶች ተቀምጠዋል።
በአጠቃላይ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት የቀጣይ አሥር ዓመታት የማኑፋክቸሪንግ ልማት የትኩረት አቅጣጫዎች በየደረጃው የመፈፀምና እና የማስፈፀም አቅምን ማሳደግ፤ ቅንጅታዊ አሠራሮችን ማጠናከር፤ የነባር ኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ፤ የምግብ፣ የልብስ፣ የመጠለያና የመድኃኒት ምርቶችን ተወዳዳሪ በሆነ መልኩ በማምረት የሀገር ውስጥ ፍላጎቶችን ማሟላትና ለውጭ ገበያ ማቅረብ፤ የሀገር ውስጥ ግብዓቶችን ለሚጠቀሙ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አምራቾች ቅድሚያ ትኩረት መስጠት ናቸው፡፡
የወጪ ንግድ ምርቶችን በዓይነት፣ በመጠንና በጥራት ማሳደግ እና የማኑፋክቸሪንግ የእሴት ሰንሰለት፣ ትስስርና ተመጋጋቢነትን ማጠናከር በጥናት ላይ የተመሠረቱ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችና የአሰራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት በማኑፋክቸሪንግ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ማብዛት ሌሎቹ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው፡፡
የግሉን ዘርፍ ሚናና አጋርነት ማሳደግ፤ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ውስጣዊ ትስስር ለማሳለጥ በቀጣይ ከባድ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ፣ የኬሚካልና የፋርማሲዩቲካል እንዲሁም ከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎችን ልማት ከሌሎች ኢንዱስትሪዎች ጋር ማስተሳሰር፤ የክላስተር አደረጃጀትን ማጠናከር፤ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት እና በሂደት ወደ ቀጣዩ ደረጃ የሚሸጋገሩበትን ምቹ መደላድል መፍጠርና የሥራ ዕድል ፈጠራን ማሳደግ የዘርፉ የትኩረት ተግባራት ናቸው።
የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ዓላማዎች የነባር አምራቾችን ምርትና ምርታማነት በማሻሻል ጥራት ያላቸው አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ ለሥራ ዕድል ፈጠራ አስተዋጽዖ እንዲያበረክት ማስቻል፤ የወጪ ንግድ ምርቶችን በብዛት፣ በጥራትና በዓይነት ማምረት እና የሀገር ውስጥ ባለሀብቱ በማኑፋክቸሪንግ በስፋት እንዲሰማራ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ለጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት የሚያደርገውን አስተዋጽዖ ማሳደግ እና የኢንዱስትሪው ልማት ከዘላቂና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ማድረግ በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት በትኩረት ይሠራባቸዋል።
የቀጣይ አሥር ዓመታት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ዓላማዎች ሥር የሚከተሉት ዋና ዋና ግቦች ተለይተዋል። የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን አማካይ የማምረት አቅም አጠቃቀም ከ50 ወደ 85 በመቶ ማሳደግ እና ስትራቴጂክ የሆኑ የገቢ ምርቶችን የሚተኩ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት የሀገር ውስጥ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ምርቶችን የሀገር ውስጥ የገበያ ድርሻ ከ30 ወደ 60 በመቶ ማሳደግ የዘርፉ አንዱ ግብ ነው፡፡
በተጨማሪም የምርት ጥራትን በማሻሻል የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነት ማሳደግ፣ ጥራት ያለው ኢንቨስትመንት በመሳብና ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ውጤት የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች ላይ በማተኮር የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችን ብዛት ከ2 ሺህ ወደ 11 ሺህ ማሳደግ፣ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በየዓመቱ የሚፈጠረውን አዳዲስ የሥራ ዕድል ከ172 ሺህ ወደ 850 ሺህ በማሳደግ በአጠቃላይ በዕቅዱ ዘመን በኢንዱስትሪው በድምሩ 5 ሚሊዮን አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ዘርፉ ያስቀመጣቸው ግቦች ናቸው፡፡
ይህ ግብ እንዲሳካ የሚደረጉ ርብርቦች እንዳሉ ሆነው ለዘርፉ አስቀድመው ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ ጉዳዮችም አሉ። ከእነዚህ ውስጥ በመካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ መሆኑ፤ አሜሪካ ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪካ አገራት የሰጠችው የነፃ የንግድ ዕድል ለቀጣይ አምስት ዓመታት መኖሩ፤ የአውሮፓ ህብረት በዕድገት ኋላ ቀር ለሆኑ አገራት የሰጠው የቀረጥና ኮታ ነፃ የገበያ ዕድሎች እንዲሁም ከጃፓን፣ ከቻይና፣ ከህንድ፣ ከቱርክ ጨምሮ ከ15 በላይ ሀገራት የተሰጠ የአንድ ወገን የገበያ ዕድል መኖሩ እና የቻይና ቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሼቲቭ ወደ ሥራ መግባቱ ዘርፉ ያስቀመጣቸውን ግቦች እንዲመታ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡
በተጨማሪም በአፍሪካ አህጉራዊ የነፃ ንግድ ስምምነት መሰረት 90 በመቶ የሚሆኑ የሀገሪቱ ምርቶች በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ከታሪፍና ኮታ ነፃ በሆነ መልኩ ወደሁሉም ስምምነቱን ወደፈረሙ የአፍሪካ ሀገሮች መግባት መቻላቸው፤ አገሪቱ ያላት ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር እንደ ከፍተኛ የገበያ አቅም ስለሚወሰድ እንዲሁም በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ ለበርካታ የዓለም ሀገራት የኢንቨስትመንትና የገበያ መዳረሻ አገር ልትሆን መቻሏ፤ እየተመዘገበ የመጣውን የልማት ውጤት ቀጣይነት ለማረጋገጥና በኢኮኖሚው ውስጥ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ነው። በዘርፉ ያለውን የኃይል አቅርቦት ማነቆ ሊፈታ የሚችለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ለቀጣዮቹ አሥር ዓመታት የተቀመጠውን ግብ ለመምታት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች ተብሎ ከተዘረዘሩት መካከል ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 23/2013