ወርቅነሽ ደምሰው
አበው ‹‹ክፉ አውሬ አይግባ ከሀገሬ፤ ከገባም አይልመድ፤ ከለመደም አይውለድ›› ይላሉ። ውዶቼ ይህንን አባባል ልብ በሉ እስቲ! መቼም የአውሬ ደግ ባይኖርም ‹‹ክፉ አውሬ ›› ግን ከአውሬዎች የተለየ አደገኛ በመሆኑ ምን ያህል እንዲኖር የማይፈለግ መሆኑን የሚገልጽ ነው። ረቂቅ ትርጉሙ ደግሞ፤ ያልተለመደ የሰውን ልጅ ክፉ ድርጊት ያመላክታል።
የሰው ልጅ ክፉና ደጉን የሚለይበት አእምሮ የተሰጠው ለየት ያለ ፍጡር ነው። እርስ በእርሱ ተከባብሮና ተቻችሎ የመኖርን ባህል የዳበረ የመልካም እሴቶች ባለቤትም ነው። እነዚህ ከኛ አልፈው ለሌላው የሚተርፉ ባህልና እሴቶች ቀስ በቀስ የተሸረሸሩት ለምን ይሆን? በፊት ያልነበረ ልምድ ከየት መጣ? ክፉ አውሬ የተባለው ክፉ የሆነው ልማድ ከየት መጣ? ይህ ክፉ ልማድ ተለምዶ ውሎ ካደረ ደግሞ ተራብቶ ይዋለዳል። ይህንን አባባል አጽኖት ሊሰጠው የግድ የሚለው ለዚህ ነው።
ውዶቼ! ዘንድሮማ ጉድ ፈልቷል። ክፉ አውሬ ገብቶ አገር ማተራመሱን ቀጥሏል። ክፉው ልማዱ ውሎ አድሮ ተራብቷል። አሳቻ ሰዓት ጠብቆ ከተደበቀበት ብቅ እያለ የንጹህን ደም እያፈሰሰ ይገኛል። በዘግናኝና በአጽያፊ ድርጊታቸው ክፉውን አውሬ የመሰሉት ‹‹እነ እንቶኔ ›› ደብዛቸው ከጠፉ ከራረመ አይደል እንዴ? ታዲያ ሌላኛው የድርጊታቸው ተተኪ ማን ይሆን ? የጭካኔ ጥግ መገለጫ አውሬውን ፈትቶ የለቀቀበን?
በጭካኔ ተግባሩ ተገልጾ በይፋ ያየነው ‹‹ጁንታን›› ነበር። እየሞተ ያለው ጁንታ ዳግሞ አገገመ እንዴ? መቼም በዚህ ፍጥነት አገገመ ለማለት ይከብዳል፤ ወይስ የጁንታውን ካባ የደረቡ ትናንሽ ጁንታዎች ተፈጥረው ይሆን? ብለን ስንጠይቅ፤ ለሰሚው ግራ ነው። ተግባሩ ተገልጦ ለምን ማንነታቸው ይደበቃል? ብቻ ያው መሳሪያ ታጥቀው በክፋት ተነሳስተው ንፁሀንን የሚያጠቁ በመሆናቸው እነርሱንም ሌላዎቹ ጁንታዎች ለምን አንላቸውም ? እናላችሁ ስለ እነዚህን ተግባረ ጁንታ የሆኑ ርዝራዦች ብዙ አወጋችኋላሁ።
እኔ ግርም የሚለኝ! ጭካኔን እንደዚህ በገሃድ በወገን ላይ የመፈጸም ሞራል ከየት መጣ? ማስተዋላቸውን ምን ነጠቃቸው? እንደው የኢትዮጵያዊያን ባህላዊ መገለጫችን የሆነው ተከባብሮና ተቻችሎ መኖርን ማን ነጠቀን ? ዳሩ ተውት! ‹‹ከአህያ ጋ የዋለች ጊደር- — ›› ይባል የለ። እነዚህ የጭካኔ ድርጊት ባለቤቶች ዞሮ ዞሮ መነሻቸው ያው የቀዳሚው የጁንታው ጥንስሶች መሆናቸው የሚዘነጋ አይደለም። ግብራቸው ተመሳስሎ አንድነታቸው ይፋ ሆኗል።
እንደው እኮ! የሰው ነገር ይገርማል። የአንድ ነገር ተምሳሌትነት የሚጠቀሰው ለበጎ ተግባር ነበር። ‹‹ ያ ሁሉ ቀርቶ አዲስ ዘፈን መጥቶ›› እንዲሉ ሆኗል። ፋሺስቶች እንኳን በሌሎች ወገኖች ላይ ያደርጉታል የማይባል የጅምላ ጭፍጨፋን አካሂደው፤ ለጭካኔ ተግባር ተምሳሌት በመሆን ግንባር ቀደም ሆነው መገኘታቸው ሲወሳ፤ በዚች የመልካም ተምሳሌት በሆነች ሀገር የእነዚህ የክፋት ግንባር ቀደሞች መፈጠር ያስገርማል! ማስገረም ብቻ አይደለም ያስደንቃልም!።
‹‹ድንቄም ! ጁንታ›› አሉ እማማ። ከዚህ ሁሉ ከፍ የሚለው ግን በበጎ ተግባር የሚጠቀሱት ተምሳሌት የሆኑ ሰዎች በርካታ ተከታዮችን ያፈራሉ። ድርጊታቸው ክፋት ብቻ የሆነ ጨካኞች ደግሞ ብዙ እንኳን ባይሆኑ ጥቂት ለዓላማቸው ማስፈጸሚያ የሆኑ ተጋሪ ጀሌዎችን ማፍራታቸው አይቀሬ ነው።
ታዲያ የጁንታው ተከታይ ጀሌዎችን ቢያፈራ ይገርማል እንዴ? ኧረ አይገርምም። ረዘም ላለ ዓመታት አቅዶበትና አልሞ ሲሰራ የነበረ ተግባር ማሳያ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እንዳሉት ከለውጡም በኋላ በኢትዮጵያ ከተከሰቱት 113 ግጭቶች ውስጥ 15ቱ በቤኒሻንጉል የተከሰቱ ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ግጭቶች ጀርባም የቡድኑ እጅ እንደነበረበት በተለያየ መልኩ ይገለፃል።
እጁ ረጅም የነበረው ጁንታ፤ በስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜያት፤ ያላካለለው ክልል ያልደረሰበት የኢትዮጵያ ምድር ያለ አይመስለኝም። በመላው አገሪቱ በተለያየ መልኩ መረቡን ዘርግቶ እንደ ሸረሪት ድሩን አጠላልፎ እያሽከረከረ ያሻውን ሲያደርግና ሲፈጸም ኖሯል።
“ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ነሽ ይሏታል” እንዲሉ አበው ጁንታው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኢላማ በማድረግ አርቆ በቀበረው ድብቅ ሴራ የራሱን ድርጊት እያስደገመ ‹‹ እንደ መስታወት›› ያሳየን ይዞል።
ቆዩኝማ! ሰሞኑን የአገራችን የሰሜኑ ክፍል አንጻራዊ መረጋጋት ሰፍኗል። ጁንታው የገባበት ደብዛው ጠፍቶ አፋልጉኝ ተጧጡፎል። ይሁን እንጂ ዱሮም ብልጭ ድርግም ሲል የቆየው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ሰላም ርቆት ለይቶለት ከርሟል። ንጹሀን ዜጎችን ዒላማ ያደረገ አሳዛኝ የጭካኔ ተግባር ተፈጽሟል።
ውዶቼ! እንግዲህ ይህንን ድርጊት የፈጸሙት የጁንታው ርዝራዦች ስለመሆናቸው ምንም ጥርጥር የለውም። በከሀዲው የህወሐት ጁንታ ቡድን የክልሉ ሰፋፊ መሬቶች በስፋት ሲቀራመቱት እንደቆዩ ሁሉ፤ ለዚሁ ዓላማ ዒላማቸውን መምቻ ብለው ያደራጇቸው አካላት መኖራቸው እሙን ነው። በዓላማ ህዝብን ከህዝብ፤ ብሔርን ከብሔር፤ ጎሳን ከጎሳ፤ እርስ በእርሱ እያጋጩ ኖረዋል።
ለዚህም ምስክር ሳያሻው በክልሉ መረጋጋት እንዳይሰፍን በየጊዜው የሚፈጠሩ የንጽህ እልቂት ህያው ምስክር ነው። እነዚህ የጁንታው አለቅላቂዎች ክፉ ልምዱ ተጠናውቷቸዋልና። እነዚህ የክፋት ሀይሎች እንደህልማቸው ያልሰመረ ዕቅዳቸው ቢከሽፍ በቃንን አልመረጡም። ዘርን ከዘር፤ ወገን ከወገን በመለየት በወገኖቻቸው ላይ የመከራን በትር አሳርፈዋል።
መች ይሄ ብቻ! በኢትዮጵያ ምድር ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ወንድም በወንድም ላይ የጭካኔ በትር ሰንዝሯል። በማይካድራ ላይ የታየው የጭካኔ ድርጊት በመተከል ተደግሟል። የማይካድራው ድርጊት አስፈጻሚዎች ጀሌዎች ተመሳሳይ ድርጊት ፈጽመዋል።
የገደለው ባልሽ፥
የሞተው ወንድምሽ፣
ሐዘንሽ ቅጥ አጣ
ከቤትሽ አልወጣ። እንዲሉ ኢትዮጵያን እዚያም እዚህም በሚፈሰው የንጹህ ዜጎቿ ደም ክፉኛ አዝና፤ ልቧ ደምቷል። አይሞቱት አሟሟት ልጆቿን አጥታ፤ በጭካኔ በግፍ በተሞላው መልኩ በቄያቸው እንደቅጠል ረግፈዋል።
ህጻናት፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና አዛውንቶች በርካቶች በማንነታቸው ህይወታቸውን አጥተዋል፤ በተኙበት በግፍ ተገድለዋል።
ኢትዮጵያም የግፍ ጽዋ የተጋቱ ዜጎቿ መሬት ላይ ሲወድቁ ቆስላለች። ልጆቿ እርስ በእርሳቸው ሲጨካከኑ ከማየት በላይ ምን ያሳምማል። እናቶች ሀዘናቸው መቋቋም አቅቷቸው የማያቋርጥ እንባ አንብተዋል።
ውዶቼ! አይዞችሁ በርቱ! አለሁ ከጎናችሁ እያለ ሲመራና ሲያደራጅ፣ በብር ሲደገፍና ከኋላ ሆኖ በለው! በለው! ሲል የነበረው የለም። ለራሱ የቀለጠው መንደር ውስጥ ገብቶ አይሆኑት ሆኖ ብትንትኑ ወጥቶ ፈርሶ የለም እንዴ ! እንኳን ሌላውን ሊያጀግን ለራሱ መላው ጠፍቶቷል። መግቢያ ቀዳዳ አጥቶ፤ እንደ አይጥ ጥሻ ለጥሻ እየተሽለኮለከ ቀኑን እየገፋ እድሜውን ለማራዘም እየሞከረ አይደል እንዴ? መቼም ከህግ ማምለጥ ባይችልም፤ የጁንታው መጻኢ እድል በፍርድ አደባባይ መቆም እንጂ! ‹‹ መቼ ቢሆን የፈሰሰ ውሃ አይታፈስ›› ጁንታው ወደነበረበት ላይመለስ ተሰናብቷል።
እነዚህ ርዝራዦች የጁንታው ማለቂያ የለሽ ውሸት አምነው ይሆን እንዴ? ሞኝ ታላለ ሆነው መመለሻውን እየተጠባበቁ ባልሆነ! ወይስ ከህዝቡ ጎን ቆሞ ባልሰማና ባላየ የሚያልፋቸው ሌላ አጋር አገኙ? አዎን ! እውነትና ንጋት እያደር እየጠራ መሄዱ አይቀርምና የማይደብቁት እውነት በግልጽ ፍንትው ብሎ ይታያል።
ኡኡቴ ! አሉ እማማ ! ህዝቡን ሊያገለግሉ ለቃላቸው ሊታመኑ ቃል ገብተው ነበር። አንዳንዶች ቃላቸውን ሳይጠብቁ አጥፈው ህዝቡን ክደው አረፉት እንጂ! የህዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ የተሰጣቸው ‹‹ስልጣን ማገልገያ እንጂ መገልገያ አይደለም›› ሲሉ ከርመው ከህዝቡ የተቀበሉት ታላቅ አደራና እምነት ወደጎን ትተው ህዝብ በጭካኔ ሲጨፈጨፍ በዝምታ ሲያልፉም ተስተውለዋል። እነዚህም አካላት ዞሮ ዞሮ ከደሙ ንጹህ አለመሆናቸውን እያሳዩ ነው።
እናንተዬ! ለህዝብና ለወገን አለኝታ ነኝ ባዮችን ስልጣኑ ህዝቡ ቢሰጣቸውም ከህዝቡ ጎን መቆም አልቻሉም። ነገሮችን በእንጭጩ ከመቅጨት እያድበሰበሱ በዝምታ ሲያልፉ ኖረዋል። ‹‹ አለባብሰው ቢያርሱ፤ በአረም ይመለሱ ›› እንዲሉ ሆኗል። በእነርሱ በቸልተኝነት ይሁን ሆን ብለው ያለፉት ነገር ህዝቡን ዋጋ ሊያስከፍል ችሏል።
በህዝብ ላይ በደረሰ ጉዳት በህግ መጠየቅ የማይቀር ቢሆንም፤ በንፁሃን ላይ የሚፈጸምን ጭካኔ ጥግ እያዩ ዝምታን መምረጥ በራሱ የጤንነት አለመሆኑን ያሳያል። ስልጣናቸው ህዝብን ከእነዚህ ክፉ አውሬዎች መታደግ የማይችል ከሆነ፤ ‹‹ ስልጣን በአፍንጫቸው ቢወጣ›› ይሻላቸው ነበር።
‹‹ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል›› እንዲሉ የተማመኑበት በኢትዮጵያ ታሪክ ሆኖ የማያውቀውን አጸያፊ ድርጊት የፈጸመው ጁንታ እንኳን፤ ያሰባትን ሳይፈፅም ያልጠበቀው ዱብ እዳ ገጥሞታል።
አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ነፍስ ውጪ ግቢ ላይ ነው። ምነው ታዲያ መጥፊያችሁ መድረሱን ከእሱ አልተማራችሁ! መንፈራገጥ አይበጅምና! ‹‹ከጁንታ በላይ የተንፈራገጠ ለአሳር››!
እንደው በጁንታው የተማመናችሁ እየፈራረሰ እያያችሁ እንኳን ‹‹ነግ በኔ›› የሚለውን እንዴት ማሰብ ተሳናችሁ? በየቦታ በማሳው ጉድጓድ እየተቀበረ ምን ሆናችሁ አሁንም እርዝራዦቹ አብራችሁ በጥልቀት ቆፍራችሁ መቀበር ለምን አማራችሁ? ህዝቡ ጎን ሆናችሁ ጎኑን ለመውጋት ደፈራችሁ።
ሌሎችስ ብትሆኑ በድርጊቱ ውስጥ የነበራችሁ፤ በሥራችሁ አፍራችሁ እጃችሁን መስጠት ሲገባችሁ መደበቁ እስከመቼ ነው? በከንቱ የፈሰሰው የንጹህ ወገኖቻችሁ ደም ለፍርድ ይጣራልና ተሸሽጎ ከህዝብ መደበቅ አይቻልም። ድርጊታችሁ ተመሳሳይ ስለሆነ፤ እጣ ክፍላችሁ አንድ ነውና የጊዜ ጉዳይ እንጂ በቅርብ በፍርድ አደባባይ መቆማችሁ አይቀርም።
እናንተዬ! ምግባራችሁ የጎደፈ ሆኖ ወገንነታችሁን አሳጥቷችኋል።
ትናንት የተጓዙበት መንገድ ምቹ ቢመስላችሁም ዛሬ የራሱ ቀን ሆኖ የእፍረት ሸማ ሊያከናንባችሁ ነው። የህሊና ፀፀት ሊሰማችሁና ‹እኔን ያየ ይቀጣ ›ብላችሁ ለሌላው ትምህርት ለመሆን በቅታችሁ ሸማችሁን ገፋችሁ ለፍርድ ቀረቡ። የወገን ደምና ለቅሶ ከምንም አይታደጋችሁም።
የጁንታው ጀሌዎች! መቼም ከህዝብ አይን ሥር ተሸሽገው የሚያመልጥ የለም። መጨረሻቸው እንደ መሰሎቻቸው ነውና እጃቸው በካቴና ታስሮ ለፍርድ ይቀርባሉ። አሁን ሀገራችን በለውጥ ጉዞ ላይ ናት። እናንተ ያጠፋችሁትን ለማልማት በተባበረ ክንድ ወደ ከፍታ ለመውጣት ክንፏን ዘርግታ በመብረር ላይ ትገኛለች። መፈንጠቅ የጀመረውን የሰላም ብርሃን እጅ ለእጅ ተያይዘን እናሰፋዋለን። በለውጥ ጎዳና ወደፊ በመልካም መንገድ እንጓዛለን። መልካም ጉዞ!
አዲስ ዘመን ታሕሣሥ 22/2013