ወንድወሰን ሽመልስ
መጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ማለዳ 12፡00 ላይ ነበር አስደንጋጩን ዜና የሰማሁት። ጉዳዩም የህወሓት ጁንታ በትግራይ ክልል ባለው የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን የሚገልጽ ነበር።
ይሄን በተመለከተም መግለጫ የሰጡት እና አገርን የመታደግ የህግ ማስከበር እርምጃ ትዕዛዝ ያስተላለፉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር አብይ አህመድ ከተናገሯቸው ሀሳቦች አንዱ “ኢትዮጵያ ያጎረሰ እጇ ተነክሷል፤” የሚል ነበር፡፡
ተግባሩ ኢትዮጵያ በዘመኗ ከገጠሟት አስከፊ ክስተቶች ሁሉ የከፋው ነው። አገር በልጆቿ የተወጋችበት፤ የእናት ጡት ነካሾችም እኩይ ተግባራቸውን እንደ ጀብድ በመቁጠር በአደባባይ “የሰሜን ዕዝን መብረቃዊ በሆነ ጥቃት በ45 ደቂቃ ውስጥ ደምስሰነዋል” ሲሉ በባዶ ትዕቢት ሲናገሩ የክህደታቸውን ልክ ለህዝብ ያሳዩበት፤ መንግስት እና ህዝብ ከምንም በላይ ስለ ኢትዮጵያ በአንድ ቆመው አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት የከፈሉበት፤ ከሃዲዎች እንዲያፍሩ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት በህብር ማማ ላይ ከፍ ብለው እንዲገለጹ ያደረገ ሆኖም አልፏል፡፡
ይሄን ያነሳሁት በወቅቱ ስለሆነውና ስለተፈጸመው ለማውራት አይደለም። ምክንያቱም ስለሱ ብዙ ተብሏል፤ በቀጣይም በታሪክ ድርሳናት ሰፍሮ ለትምህርት እንደሚውል ተስፋ አለኝ።ወደ ዋናው ጉዳዬ ስመለስ ኢትዮጵያ ያጎረሰ እጇ ዛሬም በዓለም አደባባይ ሲነከስ ታዘብኩ።
በሌላት አቅም ያስተማረችው ብቻ ሳይሆን ከሌላት ሃብት ቆርሳ፣ በህዝብ ፍቅርና ደግፋ፣ በገናና ታሪኳ አህጉራዊ ድጋፍ አስገኝታ ከፍ ባለ የዓለም ወንበር ላይ ባስቀመጠችው ሰው ዳግም ተከድታለች፡፡
ስለ እናት ጡት ነካሽነት ሳስብ አንድ ነገር አስታወስኩ፤ የጁንታውን ክህደት ተከትሎ በትግራይ ክልል የተወሰደውን የህግ ማስከበር እርምጃ አስመልክቶ የመከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹሙ መግለጫ ሲሰጡ ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች “በዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት የሚሰሩት ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለጁንታው በመወገን በኢትዮጵያ ላይ ዓለም አቀፍ ጫናን ለመፍጠር እየሰሩ ስለመሆኑ እና ለጁንታውም ድጋፍ እያሰባሰቡ ስለመሆኑ ይነገራል፤ በዚህ ላይ እርሶ ምን ይላሉ?” የሚል አንድ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡
እሳቸውም ጉዳዩን ቀድመው ተረድተውም ስለ ጁንታው አባላት እኩይ ተግባር አውቀውም ነበርና በምላሻቸው፤ “ይሄ ሰውዬ እኮ የጁንታው አባል ነው፤ እንደምታውቁትም የእነሱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነው፤ አጋጣሚ ደግሞ የዓለም ጤና ድርጅት ውስጥ ገባ፤ እናም አሁን የእሱ አባላት እና የእሱ አመለካከት አይነት ያላቸው ሰዎች ወደ ጦርነት በገቡ ጊዜ ከእሱ ምን ልትጠብቁ ነው?” ሲሉ ነበር የመገናኛ ብዙሃኑን መልሰው የጠየቁት፡፡
ጠይቀው ግን ዝም አላሉም፤ ይልቁንም “ይህ ሰው ከኢትዮጵያውያኖች ጋር ወግኖ እነዚህን ሰዎች ያወግዛል ብለን እኛ አንጠብቅም፤ እነሱን ለመርዳትም ያልቆፈረው ጉድጓድ የለም፤ ‘ጦርነቱን ተቃወሙ፣ አውግዙ’ በሚል ጎረቤት አገራትን ሁሉ ቀስቅሷል፤ የጁንታው አባላት ጦር መሳሪያ እንዲያገኙ ሰርቷል፤ የዓለም አቀፍ ተልዕኮ እድሉን ተጠቅሞም የህወሓት ጁንታ እንዲደገፍ ሰዎችን ለማሳመን ጥረት አድርጓል፤ እሱ በዚህ ልክ ጥረት እያደረገ ቢሆንም ይህ ግን የሚሳካለት አይሆንም፤” በማለት ስለ ግለሰቡ የስብዕና ደረጃ የሚያስረዳ ሀሳባቸውን ለሚዲያ ባለሙያዎች አጋሩ፡፡
ዛሬም ስለ ግለሰቡ እየታየም እየሆነው ያለው እውነት ይሄ ነው።ይህ ሰው፣ ዛሬም በኢትዮጵያ እየሆነ ስላለው የንጹሃን ሞትና መፈናቀል፤ ዓለምን እያስጨነቀ ስላለው እና ዓለም ስለሰጠው ኃላፊነት፤ ኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ስላለው አስከፊ ሁኔታ፣ ወይም ስለ ሌሎች ስለሚመለከተው ሰብዓዊ ጉዳዮች ሳይሆን፤ ስለ ገዳዮቹ የጁንታው ግብረ አበሮቹ መጥፋት እያሰበ እንቅልፍ ማጣቱን በአደባባይ አወጀ።ዓለም አቀፍ ህጎችን በመጣስ ጭምር በዓለም አደባባይ ጩኸቱን አሰማ።
ይልቁንም ወቅታዊውን የኮሮና ወረርሽኝ ስጋት በኢትዮጵያ ካለው የህግ ማስከበር እርምጃ ጋር በማነጻጸር ጉዳዩ እጅጉን እንዳሳሰበው ሲገልጽ ተደምጧል፡፡
በመሰረቱ ይህ መድረክ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በማስተላለፍ ውስጥ ስለ ስራውና ከስራው ጋር ተያያዥ ስለሆኑ ጤና ነክ ጉዳዮች ግንዛቤ የሚያስይዝበትና መልዕክት የሚያስተላልፍበት ነው።
ከዚህ በዘለለ የግል ፍላጎትና ጥቅም ማራመጃ፤ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እና የወንጀለኛ ቡድንን ህልውና ለማስጠበቅ ቅስቀሳ ማካሄጃ፤ እንዲሁም ለራስና ለቡድን እኩይ ፍላጎት መሳካት ሲባል አገርን ያውም ታፍራና ተከብራ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ ሺህ ዓመታትን የዘለቀችን ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ የማጠልሸት ተግባር ማከናወኛ አይደለም፡፡
የቦታው ሥነ-ምግባርም፤ ዓለም አቀፍ ሕጎችና ፕሮቶኮሎችም ይሄን አይፈቅዱም።ይህ ሰው ግን የጥፋት መልዕክተኛ ነውና ከፍ ብሎ እንዲታይ በሌላት ሃብት ያገዘችውን አገር ያበላ እጇን የነከሰበትን፤ ከጎኑ ሆኖ የደገፈውን ህዝብ መልሶ የወጋበትን፤ አህጉራዊ ጋሻ ሆኖ እንዲያገለግለው አጋር የሆነውን አፍሪካዊ የከዳበትን ተግባር ዳግም ፈጸመ።ዋናው ጉዳይ የሰውየው ወሬ ለፍሬ መብቃት አለመብቃቱ አይደለም።ምክንያቱም ጄኔራሉ እንዳሉት ይለፋል እንጂ አይሳካለትም። ዋናው ጉዳይ የሰውዬው የበሬ ወለደ የሀሰት ስብከት ነው፡፡
ምክንያቱም፣ ዛሬ ላይ ትግራይ ብቻ ሳትሆን መላው ኢትዮጵያዊ ከገዳዩ የጁንታ ቡድን ተገላግለዋል። ትግራዋይም ከጁንታው የፊውዳልና አምባገነን አገዛዝ ተላቅቀው የነጻነት አየር መተንፈስ ጀምረዋል።ጁንታው የነጠቃቸውን ሰላምና ዴሞክራሲም ለማጣጣም መንገድ ጀምረዋል።
የፖለቲካ ምህዳሩም ሰፍቶ የተለያየ የፖለቲካ አስተሳሰብም ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች በክልሉ በነጻነት ከመንቀሳቀስ አልፈው የጊዜያዊ መንግስቱ የካቢኔ አባል ሆነው የሚታገሉትን ህዝብ የሚያገለግሉበትን እድል አግኝተዋል።ከፖለቲካ ነጻ ሆነው ፓርቲን ሳይሆን ህዝብን ማገልገል እንፈልጋለን ያሉ ምሑራንም በመዋቅሩ ውስጥ ገብተው ከቢሮ አስተባባሪነት ጀምሮ ኃላፊነት ወስደው ለትግራዋይ የተሻለ መጻኢ እድል እየተጉ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል፣ ክልሉ በጁንታው አጥቶት የነበረውን ሰላም ለማጣጣም ህዝቡ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጎን ሆኖ እየሰራ ነው።በጉያው ተሸሽጎ ሲያደማው ኢትዮጵያዊነቱን ሊቀማው እየሰራ የነበረውን ጁንታ ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር ሆኖ ለአንዴና ለመጨረሻ ለማስወገድም በቁርጠኝነትና በፍጹም ኢትዮጵያዊነት ሲታገለው ቆይቷል።
በዚህም የህግ ማስከበር እርምጃው ተጠናቅቆ ወንጀለኞችን አሳድዶ(አድኖ) ለህግ የማቅረብ እና የመልሶ ግንባታ ምዕራፍ ላይ ተገብቷል።በዚህም እንደ ህግ ማስከበር እርምጃው ሁሉ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል፡፡
ጁንታው ከልማት ይልቅ ጥላቻን በተደራጀ መልኩ ሲሰራበት ከመቆየቱም በላይ፤ እኔ ካልኖርኩበት ለማንም አይሁን በሚል እሳቤ የህዝብ ጠላትነቱን ያረጋገጠበትን የመሰረተ ልማት የማውደም ተግባር መፈጸሙ ይታወቃል። ይሄን ተከትሎም አየር ማረፊያዎችን ጨምሮ የጤና፣ የትምህርት፣ የውሃ፣ የመብራት፣ የስልክና የመንገድ መሰረተ ልማቶች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው፤ አንዳንዶቹም ከጥቅም ውጪ መሆናቸው የሚታወስ ነው።
ሆኖም መንግስት ህዝቡ አስፈላጊውን አገልግሎት ማግኘት እንዲችል በሁሉም መስክ የመሰረተ ልማቶች ቶሎ ተጠግነው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ አድርጓል። የመብራት፣ የስልክና የባንክ አገልግሎቶች ጭምር ስራ ጀምረዋል፡፡
ይህ ሰው ግን በክልሉ ዛሬም ጦርነት እንዳለ፤ ዛሬም ስልክና መብራት፣ ሌሎችም አገልግሎቶች ወደ ስራ እንዳልገቡ፤ በአካባቢው ያለው ሁኔታም ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባልተናነሰ መልኩ እንደሚያስጨንቅ ሲናገር ተደምጧል።
ሰውየው፣ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት የቀሩትን የፈረንጆች 2020 አስመልክተው ባደረጉት ንግግር ላይ “ኮቪድ አልበቃ ብሎ እኔ ደግሞ የግል ህመም አለብኝ። ስለ አገሬ እጨነቃለሁ ሲል ተደምጧል።በዚህ ንግግሩ የጭንቀቱ ምንጭ ከኮቪድ-19 በተጨማሪ 2020 ከባድ የሆነበት ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ በመሆኗ፣ በተለይም በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ ያሳሰበው በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ለማስረዳት ይሞክራል፡፡
ለዚህ ደግሞ “አገሬ ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ ናት። በእናት አገሬ ኢትዮጵያ፣ በትውልድ ቀዬዬ ትግራይ እየተካሄደ ያለው አስከፊ ጦርነት ያስጨንቀኛል፤ የግንኙነት መስመሮች ስለተቋረጡ ታናሽ ወንድሜንና ዘመዶቼን አላገኘኋቸውም። ወንድሜና ዘመዶቼ የማኅበረሰቡ አካል ናቸው። ስለ ታናሽ ወንድሜና ስለ ዘመዶቼ ብቻ ልጨነቅ አልችልም። የምጨነቀው ስለመላው አገሪቱ ነው” ሲል ጉዳዩን ቅጥፈት በተላበሱ ቃላቶቹ ታግዞ ለማብራራት ይጥራል።
ሆኖም ይህ ሁሉ ሰውዬው የጁንታው በሞት አፋፍ ላይ መገኘት ውስጡን እረፍት እንደነሳው፤ ይልቁንም የተደበቀ ማንነቱን ለኢትዮጵያውያን ግልጽ ያወጣበት ሆኗል።ምክንያቱም ይህ ሰው እውነት የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ በኢትዮጵያውያን በተለይም በትግራዋይ ላይ የሚፈጥረው አደጋ ታስቦትና አስጨንቆት ቢሆን ኖሮ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ለህዝብ ህልውና ሲል ምርጫውን ባራዘመበት ወቅት ግብረ አብሮቹ የህወሓት ጁንታ አባላት ምርጫ እናካሂዳለን ባሉበት ወቅት ተው ባላቸው ነበር፡፡
ይህ ሰው እውነት የህዝብ ሞትና እልቂት አሳስቦት ቢሆን ኖሮ፤ ጁንታው ራሱን ለጦርነት ሲያዘጋጅ፣ ከ200 ሺህ በላይ ለጋ የትግራይ ወጣቶችን በልዩ ሃይል ስም መልምሎ ለጦርነት ሲያሰለጥን እረፉ ባላቸው ነበር። እውነት ይህ ሰው ለንጹሃን አዝኖ ቢሆን ኖሮ፤ በጁንታው ረጃጅም እጆች በሚደረግ የገንዘብና የስልጠና ድጋፍ በመላው ኢትዮጵያ ንጹሃን በግፍ ሲገደሉና ሲጨፈጨፉ የህዝቦች በህይወት መኖር አደጋ ላይ በመውደቁ በዓለም አደባባይ ስለ ንጹሃን ደም አቤት ባለ ነበር፡፡
እውነት ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ተጨንቆ ቢሆን ኖሮ፤ አገርና ህዝብን ለጥፋት ለማዳን እርምጃ የሚወስደውን መንግስት በዓለም አደባባይ የዲፕሎማሲ ጫና እንዲፈጠርበት ባልሰራ ነበር።
እውነት እንደሚለው ለወንድሙና ለቤተሰቦቹ አስቦ ቢሆን ኖሮ፤ ስለ ወንድምና ቤተሰቦቹ ሲል ለክልሉ ሰላምና ለቤተሰቡ ህልውና ተግቶ ሊሰራ እንጂ፤ ጁንታው በትግራይ ምድር እሳት እንዲነድድ ሲሰራ መቆየቱን እያወቀ ከጁንታው ጎን ቆሞ አገራት ለጁንታው ድጋፍ እንዲያደርጉ የማግባባት ስራ ላይ ባልተጠመደ ነበር፡፡
እውነቱ ግን፣ ጭንቀቱ ስለ ወንድምና ቤተሰቡ፣ ስለ ትግራዋይ እና ኢትዮጵያውያን አይደለም።እንቅልፍ ማጣቱ ስለ ንጹሃን በግፍ መጨፍጨፍ፤ ስለ ንጹሃን አስከሬን በየሜዳው መቅረት፤ የአገር አለኝታው የመከላከያ ሰራዊት መጠቃት አይደለም። አዕምሮው ሰላም ማጣቱ፣ በጁንታው ሴራ ማንነትን መሰረት አድርጎ በየቦታው ስለሚፈጸመው ጥቃት፤ መፈናቀልና ሞት፤ በግፍ ሲለሚፈስሰው የንጹሃን ደም አይደለም።የአዞ እንባውም ስለ ንጹሃን ሞት ሲል በርህራሄ የሚፈስስ አይደለም፡፡
ይልቁንም ጭንቀቱም፣ እንቅልፍ ማጣቱም፣ አዕምሮው ሰላም ማጣቱም በህዝቦች ላይ ግፍ ሲፈጽም ለኖረው፤ ህዝቦችን እርስ በእርስ ሲያፋጅ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ ለዘለቀው፤ ንጹሃን በየቦታው በግፍ እንዲገደሉ እና ደማቸው ያለ ዋጋ እንዲቀር ሲያደርግ ለኖረው፤ በትግራይ እናቶች ሃዘንን፣ በትግራይ ታዳጊ ወጣቶች ላይም ሞትን ለፈረደው፤ ለራሱ ህልውና ሲል የአገር አለኝታ በሆነው መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃትን ፈጽሞ አገርን ለአደጋ ላጋለጠው፤ ይሄን እኩይ ተግባሩንም በአደባባይ እንደ ጀብዱ ቆጥሮ ለሚያወራው፤ ዛሬ ላይ በለኮሰው እሳት ነድዶ እየተቃጠለ በመጥፋት ላይ ላለው የህወሓት ወንጀለኛ ቡድን ሲል ነው፡፡
ይህ እጅጉን የሚያሳዝን፤ እጅጉንም ልብ የሚሰብር፤ ኢትዮጵያውያን በአደባባይ በገዛ ዜጋቸው ቅጥፈት ያፈሩበት፤ አገር በገዛ ልጇ ያጎረሰ እጇ የተነከሰበት፤ ንጹሃን ጩኸታቸው ተነጥቆ ለገዳዮች የሆነበት ነው። ምክንያቱም ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ከ123ሺህ በላይ ወገኖች በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል፤ ከ1ሺህ 900 በላይ ደግሞ በቫይረሱ ህይወታቸውን አጥተዋል።ይህ ብቻም አይደል፤ በጁንታው እኩይ ስራ በማይካድራ ከ1ሺህ 100 በላይ ንጹሃን በግፍ ተጨፍጭፈዋል፤ በመተከል በአንድ ምሽት ከ200 በላይ ንጹሃን በግፍ ተገድለዋል።ይህ በጁንታው ከተፈጸሙ ግፎች መካከል “ውቅያኖስን በጭልፋ” እንዲሉት አይነት ነው፡፡
እናም ይህ ሰው ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ከፍ አድርገው ባኖሩት መድረክ ላይ ሆኖ ስለ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን በአደባባይ ካደ፤ ስለተበደሉ እና በግፍ ስለተጨፈጨፉ ንጹሃን ድምጽ መሆን ሲችል፣ የንጹሃንን ጩኸት ቀምቶ ስለ ገዳዮች ድምጽ ሆነ፤ ንጹሃን በግፍ ሲገደሉ የተደበቀ ማንነቱ በገዳዮች መቃብር ላይ ሆኖ ለገዳዮች ድምጽ በመሆን ተገለጠ፤ ተደብቆ የኖረም የጁንታነት ስሜት እንዲጠፋ ስለማይፈልገው ስለ ህዝብና አገር ሳይሆን ስለ ቡድን ፍላጎትና ዓላማ ሲል አደባባይ ወጣ፡፡
ይሁን እንጂ ማንም ምን ይበል ኢትዮጵያን የነካ እና የወጋ መጨረሻው ሽንፈት እንደመሆኑ፤ የዚህ ሰው ባዶ ቅዠትም እንዲሁ ከጩኸት የማያልፍ መሆኑ በእስካሁን ሂደት ማየትና ማረጋገጥ ተችሏል።
ዋና ነገር ግን ሴትዮዋ “ታዘብኩሽ..” አለች እንደሚባለው፤ ይህ ሰው ለሚያልፍ ጊዜ የማያልፍ እና ታሪክም ይቅር የማይለው የክህደት ተግባር መፈጸሙን መረዳትም፤ ማወቅም ይገባዋል። ከዚህም በላይ ለምን የንጹሃንን ጩኸት ማሰማት ሲገባው፤ ለገዳዮች ድምጽ መሆን ፈለገ? የሚለውን ሁሉም ህዝብ፣ በተለይም በስሙ ሊነግድበት የተጠጋው ትግራዋይ መጠየቅ ይኖርበታል፡፡
ሆኖም “ግመሉም ይሄዳል፤ ውሻውም ይጮኻል፤” እንዲሉ፤ ጁንታው እና በየቦታው ያሉ ግብራበሮቹ መሰል ውንጀላና ክስ ማቅረባቸውን ይቀጥላሉ፤ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያንም የልዕልና ማማቸውን ለመቆናጠጥ በህብር ተሳስረው ይጓዛሉ። ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ቸር ተመኘሁ፤ ቸር ሰንብቱ!!!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2013