ውብሸት ሰንደቁ
አስመጪና ላኪ ነጋዴዎች ደጅ አስጠኝና አንከራታች ለቅሬታ የዳረጋቸውና ለሙስና ያጋለጣቸው አሠራር መሆኑን አቤት ሲሉ ዘመናት አስቆጥረዋል።ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ መንግሥት በዘየደው መላ ነጋዴዎች ተመችቷቸው እንዲሠሩ፤ የማንንም ቢሮ ለማንኳኳትና የየትኛውንም አገልጋይ ለማየት እንዳይገደዱ የሚያደርግ አሠራር ተዘርግቶ ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል።
አገልግሎቱ ኤሌክትሮኒክ አንድ መስኮት ይሰኛል። የኢትዮጵያ መንግሥት ኤሌክትሮኒክ አንድ መስኮት አገልግሎት እንዲጀምር ገፊ ሁኔታዎች በርካታ ናቸው።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሮኒክ አንድ መስኮት አገልግሎት ፕሮግራም ጽህፈት ቤት የፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ሮቤል ተስፋዬ ባንድ ወቅት ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ በገቢና በወጪ ንግድ ዙሪያ የተስተዋሉ ነባራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የዛሬ አምስት ዓመት አካባቢ የኤሌክትሮኒክ አንድ መስኮት አገልግሎት እንዲጀመር ፕሮጀክቱ መቀረፁን ተናግረው በዘርፉ ይታዩ ከነበሩ በርካታ ችግሮች የመጀመሪያው አስመጪዎች፣ ላኪዎች፣ አምራቾችና ኢንቨስተሮች በወጪ ንግድ ዙሪያ ላይ የተለያዩ ፈቃዶችን ለማግኘት በሚሞክሩበት ጊዜ ከመንግሥት ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቶች ለብዙ የገንዘብ፣ የጊዜ ብክነት እንዲሁም ለእንግልት ይዳረጉ እንደነበር አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሮኒክ አንድ መስኮት አገልግሎት ፕሮግራም ከመጀመሩ በፊት ነጋዴዎች አንድን ዕቃ ለማስመጣት ወይም ለመላክ ሲፈልጉ ከመንግሥት ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቶች ፈቃድ ለማግኘት በርካታ ቢሮዎችን ማንኳኳት ይጠበቅባቸው ነበር።
እያንዳንዱ ቢሮም በርካታ የወረቀት ሰነዶችን በአካል ይዘው መሄድ ይጠበቅባቸው ነበር። ይህ አሠራር በአጠቃላይ ደህንነቱ የተጠበቀ ካለመሆኑም ባሻገር ወጪ ቆጣቢም አልነበረም። አስመጪና ላኪዎች አንድን መሰል ጉዳይ ለማከናወን በአማካይ ከስድስት እስከ 14 ቀናት ይወስድባቸዋል።
ይህ ሂደት በአጠቃላይ የነበረው አሠራር በመንግሥትም ሆነ በነጋዴው በኩል ጊዜም ሆነ ወጪ ቆጣቢ አለመሆኑን የሚያሳይ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ መንግሥት የኤሌክትሮኒክ ሥርዓቱን እንዲጠቀም ከገፋፉት ምክንያቶች ሌላኛው ዘርፉ ለሌብነት የተጋለጠ መሆኑ ነው።የፈቃድ መስጠት ሥርዓቱ የገፅ ለገፅ ግንኙነት ያስፈልገው ስለነበረና ነጋዴዎች በእያንዳንዱ ቢሮ በአካል ስለሚገኙ ጉዳያቸውን ለማስፈፀም ላልተገባ ወጪና ለሙስና ይዳረጉ ነበር።
በመሆኑም በነበረው አሠራር ሙስና የሚከፍሉ ከሆነ ቶሎ ይሠራላቸዋል፤ ካልከፈሉ ደግሞ ለረጅም ጊዜ እንግልት የሚዳረጉበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር።
የነበረው የወጪና ገቢ ንግድ እንዲሁም የኢንቨስትመንት የፈቃድ አሰጣጥ ዘርፉ ከተገማችነትና ከግልፅነት አንፃር ችግሮች ይንፀባረቁበት ነበር።
ነጋዴው ማመልከቻ ካስገባ በኋላ የገባው ማስረጃ እየተፈተሸ ስለመሆኑ፤ ተቀባይነት ስለማግኘቱ እና በቢሮ ውስጥ የአሠራር ቅደም ተከተሎች ምን ላይ ደርሷል የሚለውን ነገር ግልፅ በሆነ መንገድ ማየት እና መከታተል የሚችልበት ሥርዓት አልነበረም።
በመንግሥት በኩል ሲታይ በፖሊሲ አውጪነት፣ በምርምር ሥራ ወይም በተለያየ ጉዳይ ላይ ያሉ ስለኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ንግድ ደረጃ መረጃ የሚፈልጉ አካላት በቀላሉ ማግኘት አይችሉም። ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች የኢትዮጵያ መንግሥት ወደኤሌክትሮኒክ አንድ መስኮት አገልግሎት አሠራር እንዲገባ ሆነ።
ኤሌክትሮኒክ አንድ መስኮት ማለት በነጋዴዎች በኩል አስመጪዎችን፣ ላኪዎችን፣ አምራቾችንና ኢንቨስተሮች ዕቃዎችን ገቢና ወጪ በሚያደርጉበት ጊዜ ለመንግሥት ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቶች የፈቃድ ጥያቄ የሚያቀርቡበት ኤሌክትሮኒክ ሥርዓት ነው። ይህ ኤሌክትሮኒክ ሥርዓት አንድ መስኮት ነው ያለው።
ማንኛውም ነጋዴ ሲስተሙ ላይ የሚጠቀምበት የመገልገያ ሥምና ይለፍ ቃል በመያዝ ገብቶ የንግድ ሰነዶቹንና ማመልከቻ በማስገባት የመንግሥት ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቶችም በዚሁ በአንድ መስኮት በኩል ነጋዴዎች የላኳቸውን ኤሌክትሮኒክ ሰነዶች የሚቀበሉበት ሥርዓት ነው።ይህ የኤሌክትሮኒክስ መስኮት የመንግሥት ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቶችንና ነጋዴዎችን አካላዊ ባልሆነ መንገድ የሚያገናኝ ነው።ነጋዴዎች የትም ሆነው ማመልከቻቸውን ማስገባት ይችላሉ።
የአንድ መስኮት የኤሌክትሮኒክ አገልግሎት ሥርዓት የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ ግብርና ሚኒስቴር፣ የማዕድን ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ፣ የመንግሥትም የግልም ኢንሹራንስ ድርጅቶችን፣ ሁሉም የክልል ኢንቨስትመንት ቢሮዎችና የመአድን ፈቃድ ሰጪ ተቋማት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አስተሳስሯል።
ሥርዓቱ የተዘረጋው የወጪና ገቢ ንግድ ጊዜን ለማሳጠርና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተወዳዳሪነት ከፍ ለማድረግ ነው።ዓለም አቀፉን ንግድ ወደሀገር ውስጥ መሳብ እና ለነጋዴውም ለመንግሥትም ቀላልና ተገማች የሆነ ሥርዓት መፍጠር መቻል የአገልግሎቱ ትልሞች ናቸው። የገንዘብ፣ የሎጅስቲክስ፣ የወረቀት፣ የህግ ተገዢነት እና የአስተዳደር ወጪዎችን በነጋዴውም ሆነ በመንግሥት በኩል በእጅጉ መቀነስ ስላለባቸው ሥርዓቱ ተግባራዊ እየተደረገ ነው። አገልግሎቱ ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘም ሌብነትና ሙስናን መቀነስና የደንበኛን እርካታ መጨመርን ያለመ ነው።
አገልግሎቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑ ኤሌክትሮኒክስ ፈቃዶች ተሰጥተዋል።ከ12 ሺህ በላይ ነጋዴዎችም ኤሌክትሮኒክ አገልግሎቱን መጠቀም ጀምረዋል። በተቋም ደረጃ ሲታይ ደግሞ 16 ተቋማት ሲስተሙን መጠቀም ያለባቸው ሲሆን 13ቱ መጠቀም ጀምረዋል።
በተለይ ከሐምሌ አንድ ጀምሮ ሁሉም ባንኮች ከዚህ በፊት ይሰጧቸው የነበሩ የወረቀት አገልግሎቶችን ሌሎች አስገዳጅ ሁኔታዎች ከሌሉ በስተቀር ሙሉ ለሙሉ ማስቀረት ተችሏል።ጉምሩክም በኤሌክትሮኒክ የሄደውን እንጂ በወረቀት የተሰጠውን መቀበል ካቆመ ቆይቷል።
አብዛኞቹ በእጅና በወረቀት ሲሰሩ የነበሩ ሥራዎች 90 በመቶው በኤሌክትሮኒክ ሥርዓቱ እየተሰጡ ይገኛሉ።ኤሌክትሮኒክ ሥርዓቱ በመኖሩ ለጥናት፣ ለፖሊሲና ሌሎች ጉዳዮች መረጃ የሚፈልጉ አካላትም በቀላሉ መረጃዎችን ማግኘት ያስችላል። የወጪና ገቢ ነጋዴዎችም ጊዜያቸውንና ሌሎች ወጪዎቻቸውን መቆጠብና ማዳን የሚችሉበት ሥርዓት ተገንብቷል።
ይህ ከላይ የተዘረዘረው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሮኒክ አንድ መስኮት አገልግሎት ፕሮግራም ያገኘነውን መረጃ መሰረት ያደረገ ነው።አገልግሎቱ ከተጀመረ የወራት ዕድሜ ያስቆጠረ መሆኑንና የአስመጪና ላኪ ነጋዴዎችም የተጠቃሚነት ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱ ከፕሮግራም ዳይሬክተሩ አቶ ሮቤል ሰምተናል።በዚህ ረገድ እየተነገረለት ያለው የኢትዮጵያ ኤሌክትሮኒክ አንድ መስኮት አገልግሎት ግልጋሎቱን እያገኙ ያሉ የወጪና ገቢ ነጋዴዎች ሃሳብና አስተያየት ምን ይመስላል የሚለውን ለመቃኘት ሙከራ አድርገናል።
ወይዘሮ አይዳ ደስታ ኦል ዊል ጠቅላላ ንግድ ኃ.የተ.የግ.ማህበር ሥራ አስኪያጅ ናቸው።ድርጅቱ ለበርካታ ዓመታት ለፋብሪካዎች፣ ለተለያዩ ማሽኖችና ለእርሻ መሣሪያዎች ኩሽኔቶችን ያስመጣል።ወይዘሮ አይዳ የኢትዮጵያ ኤሌክትሮኒክ አንድ መስኮት አገልግሎትን እንደጀመረ ከጀመሩት ቀዳሚ አስመጪና ላኪዎች ተርታ የሚጠቀሱ ናቸው።
ለመሆኑ አገልግሎቱን እንዴት አገኛችሁት? ስንል ጠይቀናቸው ነበር። የአንድ መስኮት አገልግሎት በጣም እንደተመቻቸው ገልፀው በእርግጥ መጀመሪያ አካባቢ ከባንኮች ጋር መናበብ ስላልነበራቸው አገልግሎቱን አልወደድነውም ነበር።ሲስተም ውስጥ ከገባን በኋላ ግን ጥሩ መሆኑን ተረድተናል ብለዋል።
ወይዘሮ አይዳ የኤሌክትሮኒክ አንድ መስኮት ትልቁ ጥቅሙ ያለደረሰኝ መሸጥን የሚያስቀር ሥርዓት መሆኑ ነው።ምክንያቱም ሥርዓቱ ኤሌክትሮኒክ በመሆኑ ወደ ድርጅቱ የገባውን ምርት ማጭበርበር አይቻልም። ሁሉም ነጋዴ በዚህ መልኩ ተጠቅሞ በደረሰኝ ከሸጠ በነጋዴዎች መካከል የሚኖረው ውድድር ትክክለኛ ውድድር ይሆናል ያሉ ሲሆን የኤሌክትሮኒክ አንድ መስኮት አገልግሎት ኮንትሮባንድን ለመከላከልም ጥሩ ሥርዓት ነው ብዬ አምናለሁ ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ አስመጪዎች ባነሰ ቀረጥ እንዲቀረጡ የሚያደርጉትን ማጭበርበር ያስቀራል ብለዋል።‹‹አሁን ላይ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪዎች ራሳቸው ሲስተሙን ስለለመዱትና ለእኛም ቅልጥፍና ስለጨመረልን ደስተኞች ነን።
ሂደቱን ያፈጥነዋል፤ ከሰዎች ጋር ሳትገናኝ የሠለጠነ አካሄድ ተጠቅመህ ጉዳይን ታስፈፅማለህ፤ ሙስናንም ይቀንሳል›› ሲሉ ጠቀሜታውን ይናገራሉ።አስፈላጊውን ማስረጃ ከፈለጉት ቦታ ሆነው እንደሚልኩ ሂደቶችን ለማስፈፀም የሚያባክኑት ጊዜ መቀነሱንና ድሮ ጉዳያቸውን ለማስፈፀም ከሚወስድባቸው ጊዜ በግማሽ መቀነስ የቻለ ሥርዓት መሆኑን ይናገራሉ።
ወይዘሮ አይዳ እንደሚሉት አገልግሎቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ የአጠቃቀም ለውጦች እየታዩ ነው። በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በኩልም መናበቡ ጥሩ ሆኗል።እንዲያውም በግል ባንኮች ጭምር ከመረጃ ቋቱ ላይ ይህን ጉዳይ የሚመለከት ሰው ማስቀመጣቸውን አይተዋል።
ይህ በጣም ጥሩና ሥራቸውን ያቀለለላቸው ተግባር ነው። የኤሌክትሮኒክ አንድ መስኮት አገልግሎት መንግሥት በትክክል ግብር እንዲሰበስብ ዕድል የሚፈጥር እና ነጋዴው በጥራት እንዲወዳደር ከማድረጉም በላይ ሕገወጥ ንግድ እንዲቀንስ አስተዋፅኦ ያበረክታል።
የላይምኮ ጠቅላላ አስመጪ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሪት አህላም ከሊፋ ኤሌክትሮኒክ አንድ መስኮት አገልግሎት ተጠቃሚ ናት። የምትመራው ድርጅት ለአራት ዓመታት በአስመጪና ላኪነት ስራ ላይ ተሰማርቶ ቆይቷል። የኢንዱስትሪ ዕቃዎችን፣ የቤት፣ የፅህፈት እና የተለያዩ ዕቃዎችን ከውጪ በማስመጣት ላይ ይሠራል። ኤሌክትሮኒክ አንድ መስኮት አገልግሎት ከተጀመረ ጀምሮ ሲገለገሉ ከነበሩ ቀዳሚ ድርጅቶች አንዱ ነው።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሪት አህላም ኤሌክትሮኒክ አገልግሎቱ ጥሩና ጊዜ ቆጣቢ እንደሆነ ትናገራለች። አገልግሎቱን ለመጠቀም በአካል መሄድ ሳይጠበቅባት አስፈላጊ ሰነዶችን ኦንላይን በመጫን አገልግሎቱን እያገኘች እንደሆነ ትናገራለች።የአንድ መስኮት አገልግሎት ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት አገልግሎቱን ለማግኘት ከሚወስድብን ጊዜ በግማሽ ቀንሶልኛል ትላለች።አጠቃቀም ላይ መጀመሪያ አካባቢ ክፍተቶች እንደነበሩ ታስታውሳለች።
የኢንተርኔት ደካማ መሆን በሥራው ላይ ትንሽ ተፅዕኖ ያሳድራል የምትለው ወይዘሪት አህላም ባንክ ላይ አልፎ አልፎ የክህሎት እጥረት ይታይ እንደነበርና ይህም ተስተካክሎ ሥራው በተሳለጠ መንገድ እንደሚሠራ ተስፋዋን ገልፃለች።እያንዳንዱ ፋይል ለሁሉም ተቋማት በሚታይ ሁኔታ የሚቀመጥ ኤሌክትሮኒክ ሲስተም በመሆኑ ሙስናን ለመከላከል አስተዋጽኦ ያደርጋል ብላ ታስባለች።
ሌላው በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው አቶ አብዱራዛቅ ሐሰን በስማቸው ለሚጠራው አብዱራዛቅ ሐሰን አስመጪ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው።ድርጅታቸው የጨርቃ ጨርቅና ቴክስታይል ምርቶችን በማስመጣት ሥራ ላይ ሁለት ዓመት ያህል ቆይቷል።
የኤሌክትሮኒክ አንድ መስኮት አገልግሎት መስጠት እንደጀመረ መጠቀም የጀመሩ ሲሆን ድሮ የነበረው በወረቀት ላይ የተመሠረተ አሠራር በጣም አስቸጋሪ መሆኑን አስታውሰው ‹‹በአካል መሄድ ይጠበቅብን ነበረ፤ በተጨማሪም የወረቀት ፋይሎችን ለመንግሥት አካላት ለማቅረብ ብዙ እንግልት ነበረብን›› ይላሉ።
እያንዳንዱን ነገር ለመሥራት በርካታ ቦታዎችን መርገጥ ነበረብን ያሉት አቶ አብዱራዛቅ ከሰዎች ጋር በአካል ስለማንገናኝ የባህርይ ግጭት ራሱ የለም በማለት ይገልፃሉ።አሁን ባለው ሥርዓት በፊት እስከ 15 ቀን ይወስድብኝ የነበረውን አገልግሎት አሁን በአራትና በሦስት ቀን ማስፈፀም ችያለሁ ሲሉም ይናገራሉ።
የአገልግሎቱ አሳላጮች እያስተካከልን ነው እያሉ ቢሆንም አሁን ያየሁት ችግር ከፊል የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት የአንድ መስኮት አገልግሎቱ መቀበል አለመቻሉ ነው። ከዚህ ውጪ አገልግሎቱ ለመንግሥትም ሆነ ለአስመጪና ላኪ ነጋዴዎች በጣም የተሻለ ሥርዓት ነው።በኤሌክትሮኒክ አንድ መስኮት አገልግሎት ሁሉም ነገር በቅደም ተከተልና በግልፅ ነው የሚከናወነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ማንም ደጅ ሳንጠና ሳይጠበቅብን ሥራችንን ማከናወን ችለናል በማለት አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 21/2013