አዶኒስ ( ከሲኤምሲ)
‹‹የጆሮ ደግነቱ አለመስማቱ›› የምትል አባባል ስሰማ ደግሜ ደጋግሜ አባባሉን ወደ ቀልቤ ወሰድኩት። እውነት እኮ ነው ይሄ ጆሮ የሚባል አካል ሞላሁ፣ ጠገብኩ ቢለን ኖሮ ምን ይውጠን ነበር፤ የቱን ሰምተን የቱን በቃኝ እንል ነበር? ማንስ ይሄ ይሻላል የሚለውን መርጦ ያቀርበው ነበር ፤ ማለቴ ለእኛ የሚሆነው የሚያስማማንን፣ የሚያፋቅረውን እንጃ ብቻ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ወሬ መራጭ በላያችን ላይ ቢሾም ምን ሊያስደምጠን እንደሚችል ሳስበው ሳስበው ይደክመኛል።
ሁሉንም ነገር መስማት መቻላችን ደግሞ እድለኞች እንዳደረገን ይሰማኛል። ደግነቱ የጆሮ አለመሙላቱ እያልኩ አሁንም የምሰማቸውን ነገሮች ከወደ ጆሮዬ ወደ ልቡናዬ አሳለፍኩ። የእውነታ ማጣሪያ ወንፊቱ ግን ስራ እንደበዛበት አትርሱት።
በየዕለቱ በየሰዓቱ በየደቂቃውና ሰኮንዱ የሚሰሙ ነገሮች አቤት መጣፈጣቸው! መብዛታቸው ደግሞ እያልኩ አደንቃለሁ። የዓለሙ፣ የሀገሩ፣ የቤተሰቡ፣ የግል ጉዳዩ ኧረ ስንቱ ይዘረዘራል፤ ብቻ ጆሮ አይደል ሁሉንም ይሰበስባል፤ ያደምጣል ደግነቱ አለመሙላቱ። የእኛን ሀገር የፖለቲካ ጉዳይ ለሚከታተል እንኳንስ ጆሮ አልሞላ ያሰኛል። ስንት አስጨናቂ፣ የጭካኔ ዘግናኝ ወሬ ሰማን።
ስንቱን አስደናቂ ጀግንነት አደመጥን። ይሄ ሁሉ በእኛ ሀገር የሆነ ነው፤ ይሄ ሁሉ በእኛው ወገኖች የተፈጸመ ነው፤ ይሄ ሁሉ በእኛው ልጆች ነው… እያልኩ አሁን ድረስ ማውጣት ማወረዱን አላቆምኩም። እኔም ይሄንኑ ወሬ ሳነፈንፍ አደል ውሎዬ ብቻ እውነቱን ከሀሰት ለመለየትም ብዙ የምሰማውን ከማመን ይልቅ እውነታውን ለማወቅ ለማጣራት ሞክሬያለሁ።
ያም ሆኖ የሰማሁት ካልሰማሁት ሊበልጥ ብችልም የሰማሁት የሰሜኑ፣ የምዕራቡ አካባቢ የነበረውን ግፍና በደል ግን እስካሁን ከሰማሁት በጨካኞች፣ በአሰቃዮች በወራሪዎች ሁሉ ከተደረገው አሰቃቂ ግድያ ጋር የሚነፀፃር አለመሆኑን ተረድቻለሁ። ኧረ! በምንም መልኩ አይገናኝም፤ ያ የጨፍጫፊዎች ክፉ ዘመን የተባለው በስንት ጣዕሙ።
ያው እንዳልኩት የጆሮ ደግነቱ አለመስማቱ አይደል? የሰማሁትን ሰምቼ ያልሰማሁትን ለመስማት ደግሞም የሰማሁትን ከተለያዩ መገናኛ ብዙሀንና ከማውቃቸውም ሆነ ከማላውቃቸው እንዳው ሳጣራ ሁሉንም ብሰማ ብሰማ ግን ያተረፍኩት ነገር ቢኖር ጥላቻ ብቻ ነው። እንቶኔ እንዲህ አድርጎ እንዲህ ሰርቶ እንዲህ ያለውን ደብቆ፣ ሰርቆ፣ ከሀገር አሽሾ፣ ገሎ፤ ሰቅሎ፣ አስሮ፣ ገርፎ፣ ጥፍር ነቅሎ …ብቻ በዓለም ላይ አለየተባለ ግፍ ሁሉ አጠገባችን ሆኗል። እዚሁ ሀገራችን።
ኧረ! ይሄ በየትኛውም ዓለም ያልተደረገ የከፋ ከጭካኔ በላይ ነው የሚያስብል ጭካኔዎችም ተፈጽሟል። በተለይ በአንድ ብሄር ላይ ያነጣጠረው ጭፍጨፋ ደግሞ ከሞት ሁሉ በላይ የከፋ ሞት ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ከአንድ ቤተሰብ ለወሬ ነጋሪ እንኳን ሳይተርፍ የተሰዋው አራትና አምስት ቤተሰቦች፤ ባል በሚስቱና በልጆቹ ፊት ሲቀላ፣ ሰው ሲታረድ፣ በቀስት ሲወጋ፣ አስከሬን በእሳት ሲጋይ፣ የጅምላ ቀብር … ከመስማትና ከማየት በላይ የሚከብድ በዚህ ምድር ምን ዘግናኝ ነገር አለ? የመጨረሻው የጭካኔ ጥግ አይደል? አሁን ታዲያ ከዚህ የከፋ ምን ልንሰራ እንችላለን ብሎ ማሰብ ደግ ነገር ነው። ኧረ ደግ ደጉን ያሳስበን።
አንዳንድ የክፉ ቀን ደግ ሰዎች ይሄን ቁጭ ብለው ሲያስቡ ሰብሰብ ብለው ሲመካከሩ ደግሞ በቀራቸው ባልተሰማና ባልተሰራ ነገር ላይ አቋም ለመያዝ ተስማሙ፤ ጠላታቸውን ደበኛቸውን ሁሉ ለመበቀል አስበው ተመካከሩ። ሊሰሩት የሚፈልጉትን ያልተሰማ የበቀል አይነት ሁሉም በየራሳቸው አዘጋጅተው እንዲመጡ የቤት ስራ ተከፋፈሉ።
እንግዲህ ይዘው እንዲመጡ የተፈለገው የበቀል እርምጃ እስካሁን በሀገራችን፣ በየክልሎቹ፣ በየሀይማኖቱ በዘሩ ከተቀላው፣ እንደፈንድሻ በቆሎ በእሳት ካረረው፣ እንደ ድንጋይ በመዶሻ ከተፈለጠው፣ ከተቆራረጠው፣ ከተሰነጣጠቀው … የከፋ እርምጃ ነው። ሁሉም በትዕዛዙ ደስ ተሰኙ። እስካሁን ከተደረገውና ከተሰራው በላይ ቅጣት ቀጥተው፤ እርምጃ ወሰደው ጠላታችን ያሉዋቸውን ለመቅጣት በቀላቸውን በመወጣት አንጀታቸውን ቅቤ ሊያጠጡ ነው ውሉ።
እናም በሀሳቡ ተስማሙ ሌሊት በአልጋ ላይ ቀን በየመንገዱ በየሄዱበት ሁሉ የክፋትን፣ የተንኮልንና የብቀላን ጥግ ሲፈልጉ ከረሙ። በውላቸው መሰረት ይሄን ያገኘ ሰው ተሰብሳቢውን ጠርቶ ስራውን ለሁሉም ማከፋፈል ነው። በዚሁ መሰረት ሲያወጡ ሲያወርዱ እንቅልፍ አጥተው ቀን ከሌሊት በሀሳብ ሲዳክሩ ማግኘት ሳይችሉ ቀናቶች ሄዱ። እነሱ ውስጥ የነበረው የበቀል ስሜት፣ ጥላቻና ዛቻ እየቀነሰና እየበረዳ ሄደ። ሆኖም ግን ይሄ ጉዳይ እንዳይረሳ… እንዳይረሳ… እያሉ የሚወተውቱ ነበሩ።
በዚህ መሀል አንድ ሰው ከመሀከላቸው ለሁሉም መልዕክት አስተላለፉ ‹‹ ወገኖቼ ሁላችሁም ነገሩን ቸል ብላችሁ ይሆናል እንጂ ለዚህ ለተፈጸመው አረመናዊ ጭፍጨፋ መበቀያ ምላሽ ጠፍቷችሁ አልመሰለኝም። እኔ ግን ሁላችሁም ያልደረሳችሁበትን የቁጭት መመለሻ ጥይት አግኝቻለሁ›› እያሉ አስታወቁ። ሁሉም ተደሰቱ። የመሰባሰቢያውም ቀን ተቆረጠና እሳቸውም ሀሳባቸውን እንዲያቀርቡ ተጠየቁ።
እሳቸው ግን እስኪ ከእናንተ እንጀምር የእናንተን ግኝት እንስማ በማለት ቅድሚያ ለሌሎች እድሉን ሰጡ። አንዱ ይነሳና ‹‹የእነዚህን ሰዎች አካል እንደ ዶሮ አስራ ሁለት ቦታ መበጣጠስ ነው›› ሲል ተናገረ። ሌላውም ቀጠለ ‹‹ቤንዚን አርከፍክፎ እሳት መልቀቀ ነው››፤ ባለተረውም እጁን አውጥቶ እድል አገኘ ‹‹ ህዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ መስቀል ነው፤ መግረፍ መውገር›› እያለ የአለንጋውን አይነት የቅጣቱን መጠንና ቦታ ሁሉ ተነፈሰ።
ይሄን ጊዜ እሳቸው ፈገግ ደግሞ ግንባራቸውን ኮስተር እያደረጉ ‹‹ሁላችሁንም አዳመጥን ይሄ ያልተደረገው የት ነው? ›› ሲሉ መልሰው ጥያቄ አቀረቡ፤ ይሄን አልሰማንም ካላችሁ መገናኛ ብዙሃኑ ደብቀዋችኋል ማለት ነው። እኔ ግን ሁሉንም አይነት የክፋት የጭካኔ ጥግ በማህበራዊ ሚዲያው ስከታተል ከርሜያለሁ።
አሉ እናንተስ ሲሉ ጥያቄውን ደገሙ ሁሉም ጭጭ አሉ። እሳቸውም ቀጠሉ ‹‹ ይሄ በዚህ ቦታ … ይሄ በእዚያ ቦታ፣ ይሄ በዚህ ክልል፣ ያ ደግሞ በእንቶኔ ክልል፣ እንዲህ ያለው በሀይማኖት ግጭት … የተፈጸመ አይደል! እኛ ያልነው አዲስ ያልተደረገ ነው›› ሲሉ መልሰው እንዲያስቡ እድል ሰጡ። ያልተደረገ፣ ያልተሰማ ጭካኔና ሴራ የለም።
የክፋት ጥግ የሚባሉት ሁሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጽመዋል። የክፋትን ጥግ ከፈጸምን የቀረንን ስራ ሰርተን እንለፍ ብለው የመፍትሄ ሀሳብ አመጡ። እናም ‹‹አሁን የቀረን በጎ ስራ መስራት ብቻ ነው›› አሉ። ሁሉም ሰዎች በሰሙት ተደነቁ ጭንቅላታቸውን እየነቀነቁም መስማማታቸውን አረጋገጡ።
ከዛሬ እስኪ መልካም ስራ መስራት እንጀምር ብለው ተለያዩ። እኛም የክፋት መጨረሻውን ጨብጠናል፤ አሁን የቀረን መልካም መሆን ነውና ፊታችንን ወደ መልካምነት እናዙር። በቀል በቀልን እንጂ ሰላምን አላመጣም፤ አያመጣም።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21/2013