አስቴር ኤልያስ
በብዙ ኢትዮጵያን ዘንድ አሁን አሁን ጎጆ ሰርቶ የቤት ባለቤት የመሆን ህልም ጨርሶ የሚታሰብ አይደለም። ቀደም ሲል እኔ ነኝ ያለ ቪላ ሊሰራ የሚችል ገንዘብ ዛሬ ቦታ መግዣ እንኳ መሆን አይችልም። ቤት የመስራት ፍላጎቱ አለኝ የሚል አካል ካለ ደግሞ ገና ከቦታው ግዥ ጀምሮ ጨዋታው ሁሉ በሚሊዮን ቤት መሆኑ እሙን ነውና ኪሱን የተማመነ ሊሆን የግድ ነው።
ለዚህም ይመስላል መካከለኛ ገቢ ያለው ዜጋ ቦታ የመግዛትም ሆነ ቤት የመስራት ሐሳቡን ወደጎን ተወት አድርጎ መንግስት በጀመረው የቤቶች ልማት መርሃግብር በጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝግቦ ሳይታክትም በየወሩ ካለው በመቆጠብ እየተጠባበቀ የሚገኘው።
ምንም እንኳ የጋራ መኖሪያ ቤት በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተጠናቆ እንደመንግስትም ሆነ እንደዜጋው ፍላጎት ፈጣን ባይሆንም ጥቂት የማይባሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች የእድሉ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸው አይካድም፤ እንዲያም ሆኖ ቤት ፈላጊው የትየለሌ ሆኖ እድለኛው ጥቂት፣ ግንባታው ደግሞ ጉትት የማለቱን ሁኔታ በየጊዜው የምናስተውለው ጉዳይ ሆኗል።
ቤቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ያለመጠናቀቃቸው ምክንያት፣ የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለማስወገድ በአማራጭ ስለተያዘው መርሃግብር ብሎም የቤት ግንባታው ጥራትና የመሰረተ ልማቱንም ችግር አስመልክቶ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ከሆኑት ከአቶ ታደሰ ከበበው ጋር ቃለ ምልልስ አድርጎ እንደሚከተለው አሰናድቷል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡– የከተማ ነዋሪውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት የተያዙ መርሃግብሮች ምን ምን ናቸው? አፈጻጸማቸውስ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ታደሰ፡- በአገራችን ያሉ ከተሞች እየተስፋፉ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የሕዝብም ቁጥር እያሻቀበ ይገኛልና ይህንን ተከትሎ በዋናነት የሚነሳው ችግር የመኖሪያ ቤት እጥረት ነው። የመኖሪያ ቤት ደግሞ ለሰው ልጅ መሰረታዊ የሆነ ፍላጎት ነውና ይህን በአግባቡ ለማሟላት ከባለድርሻ አካላት የተለያየ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቃል።
እነዚህ ባለድርሻ የሚባሉ አካላት አንዱ መንግስት ሲሆን፣ ግለሰቦችና የተለያዩ ድርጅቶችም ተጠቃሾች ናቸው። እነዚህ አካላት በተቻላቸው አግባብ የመኖሪያ ቤቶችን ችግር የመቅረፍ ኃላፊነት ያላባቸው ናቸው።
በተለይ ከመንግስት አንጻር የቤት ችግርን ለመቅረፍ ከመጀመሪያም ጀምሮ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ነበር። የቅርቡን ለመጥቀስ ያህል አንኳ የተቀናጀ የቤት ልማት መርሃግብር ከመጀመሩ አስቀድሞም ቤቶችን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለማከፋፈል ሲደረጉ የነበሩ ጥረቶች አሉ።
ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በስፋት የቤት ልማት መርሃግብሩን ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህ የቤት ልማት መርሃግብርም በጥቅሉ ወደ 402 ሺህ ቤቶች ተገንብተዋል። በአሁኑ ወቅት ግንባታው ክልሎች ላይ የቆመ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ላይ ግን ተጠናክሮ መቀጠሉ ይታወቃል።
ይሁንና ይህ ማለት የዜጎች የቤት ችግር ተቀርፏል ማለት አይደለም። የቤት ፍላጎቱና የአቅርቦት መጠን መካከል በጣም ሰፊ ልዩነት አለ። ባለን መረጃ መሰረት በአገር አቀፍ ደረጃ ወደ ሁለት ሚሊዮን አካባቢ የቤት ችግር አለ።
እስካሁን የተደረገው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ የእኛ የቤት አቅርቦትና የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር መጨመር የሚመጣጠን አይደለም። ምንም እንኳን ከመንግስት በተጨማሪ በግልም ሆነ በማህበር ደረጃ ቤት እየተገነባ ቢሆንም አሁንም የቤት ችግር እንደቀጠለ ነው።
አዲስ ዘመን፡– እንደአገር የተያዘው ከጋራ መኖሪያ ቤት ውጭ በአማራጭ የተቀመጠው የመኖሪያ ቤት አማራጭ መርሃግብር ሂደቱ ምን ይመስላል? እሱስ መፍትሄስ ሊሆን አይችልምን?
አቶ ታደሰ፡– በዋናነት መታሰብ ያለበት የቤት ችግርን መንግስት ብቻ ሊቀርፍ አለመቻሉን ነው። ሌሎች ተጨማሪ ቤቶችን ለማቅረብ የሚያስችሉ አማራጮች አሉ። ለምሳሌ ዜጎች በማህበር ተደራጅተው የቤት ልማትን የሚቀላቀሉበት አንድ መንገድ ነው።
ይህ መሬትን በቁጠባ ለመጠቀምና አቅምንም በጋራ አሰባስቦ ለመጠቀም የሚያግዝ ነው። ዜጎች መሬቱ በሊዝ አዋጅ መሰረት ከጨረታ ነጻ እንዲሰጣቸውና ቤት እንዲገነቡ ነው የሚደረገው። ይህ ከሌሎቹ ሁሉ የተሻለ ነው ተብሎ ይታሰባል።
በአሁኑ ወቅት አማራጭ ተብለው ከሚታሰቡት ወደስራ ያልገቡ እንዳሉ ሆነው በአሁኑ ወቅት ግን ወደተግባር የገቡት ሶስት አማራጮች ናቸው። የመጀመሪያ ራሱ በመንግስት እየተገነቡ ያሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ አንዱ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ በማህበር ተደራጅቶ መገንባት ነው። ሶስተኛው ደግሞ ግለሰቦች ራሳቸው በራሳቸው ይዞታ ላይ ቤቶችን በሽያጭም ለራሳቸውም እየገነቡ ያለው ሁኔታ ነው።
እንደ አራተኛ የሚወሰደው ግን ሪልስቴት ግንባታ ነው። እሱም ቢሆን በሚፈለገው አይነት ሁኔታ እየተካሄደ ነው ማለት አያስደፍርም። በተለይ የድሃውን ህብረተሰብ የመግዛት አቅም የሚፈታተን ነው። ሪልስቴት ገንቢዎቹ ትናንሽ መሬቶችን ከግለሰብ በመውሰድ የሚገነቡ ናቸው።
መንግስትም መሬት እያቀረበላቸው የሚገነቡ አሉ። ይሁንና የድሃውን ህብረተሰብ አቅም የሚመጥን ባለመሆኑ ተደራሽነቱ ላይ ጥያቄዎች አሉ። እነዚህ የተጠቀሱት ላይ ጥረቶች እየተደረገ ያለ ሲሆን፣ ተግባራዊ ያልተደረገው ደግሞ የመንግስትና የግል አጋርነት በሚለው ላይ ነውና እሱም ቀጣይ ይሆናል ብለን እናስባለን።
አዲስ ዘመን፡– በአገር አቀፍ ደረጃ እየተሰሩ ያሉ የጋራ መኖሪያ ቤት የጥራት ጉዳይ ላይ ቢሮው እንዴት ይመለከተዋል? አንዳንድ ቦታ የዘመመ ቤትም እንዳለ ይነገራልና የተወሰደስ ርምጃ አለ?
አቶ ታደሰ፡- የቤት ግንባታ ጥራት አንዱ የኮንስትራ ክሽን ኢንዱስትሪውን ትኩረት ከሚያደርግባቸው ጉዳዮች ውስጥ ተጠቃሽ ነው። የግንባታ ሂደቶች ሁሉ ዋና ትኩረታቸው ጥራቱ ላይ ነው። ጥራት የሚጀምረው ከዲዛይን ነው።
የቤቱ ዲዛይን ሲዘጋጅ ብዙ ዓመት ሊያቆይ የሚያስችል ስለመሆኑና ወጪ ቆጣቢ ስለመሆኑ ታሳቢ ተደርገው ነው። ከዛ በተጨማሪ ደግሞ የተለያዩ እቃዎች ያሉ ሲሆን፣ እነዚህም ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ነው የሚደረገው።
ይህ ሲደረግ ግን ሁለት ነገር ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። አንደኛው ዋጋ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ጥራት ነው። ምክንያቱም የጥራት ደረጃው ከፍተኛ የሚደረግ ከሆኑ ቤቱን ለዜጎች በተመጣኝ ዋጋ የማቅረቡን ሂደት ይፈታተነዋል። ስለሆነም ሁለቱንም ታሳቢ ያደረገ ዲዛይን ነው የሚዘጋጀው።
ከዚህ ውጭ ግን መሬት ላይ ያለውን ነገር ስናይ ለምሳሌ ብሎኬት በሚመረትበት ወቅት ሲሚንቶና ውሃ እንዲሁም አሸዋ በሚደባለቅበት ጊዜ የአሰራር ችግር ሊፈጠር ይችላል። በእነዚህ ሂደቶች ላይ የሚቆጣጠረው አካል በአግባቡ ሳይቆጣጠር ሲቀር የጥራት ችግር ሊከሰት ይችላል።
አንዳንዴ ደግሞ ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ አጨራረስ ላይ የመብራት፣ ውሃና ሌሎችም የፍሳሽ ቱቦዎችን ከመስራት አኳያ የሚደረገው ሂደት ህንጻዎቹን ወደመቆርቆር ያመጣቸዋል።
ይህን ችግር ለመፍታት ግን አንድ ርምጃ ወስደናል፤ ለምሳሌ እነዚህ የመስመር ስራዎች ህንጻን ቆርቁሮ ማስገባት ሳይሆን መጀመሪያውኑ ህንጻው ሲገነባ አብሮ ውስጥ ለውስጥ መቀመጥ አለበት የሚል አቅጣጫ ተቀምጦ በዛ እንዲሰራ ተደርጓል። ግለሰቦች ከገቡ በኋላ ለራሳቸው እንዲስማማ አድርገው የሚያደርጉት መቆርቆር ካልሆነ በስተቀር ይህ እንዲቀር ተደርጓል።
አዲስ ዘመን፡– በቅርቡ እንደ አገር አቀፍ ሲካሄድ የነበረ የቤት ምዝገባ ነበርና ሂደቱና ውጤቱ እንዴት ይገለጻሉ? የመመዘገቡ ዓላማስ ግቡን መቷል ማለት ይቻላል?
አቶ ታደሰ፡– በዚህ ጉዳይ ዝርዝር መረጃ የለኝም። ምናልባት ይህ ጥያቄ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ የሰሩት ጥናት ይመስለኛል፤ ስራም ገና የተጠናቀቀ ባለመሆኑ የተጠናቀረ ሪፖርት አልደረሰኝም። ነገር ግን እንደ አገር አቀፍ ገና የቤቶች ቆጠራ አልተደረገም።
አዲስ ዘመን፡– ቢሮው ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር ተቀናጅቶ የመስራት ሂደቱ ምን ይመስላል?
አቶ ታደሰ፡– እንደሚታወቀው ቤቶችን የሚገነቡ የተለያዩ አካላት አሉ። ቤቶች የሚገነቡት ደግሞ በሁሉም ክልሎች እና በሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች አማካይነት ሲሆን፣ ቤቶች ኮርፖሬሽን አንዱ ተጠቃሽ ነው። እንደ ፌዴራል ተቋም እንደ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከሁሉም ጋር በጋራ ይሰራል።
አጠቃላይ አገር አቀፍ የሆነ ቤቶች ልማት የሚመሩበት ሁሉም የሚተገብሩትን ስትራቴጂ ማዘጋጀት፣ አቅማቸውን የሚያሳድግ ስልጠናዎችን እንሰጣለን።
በተመሳሳይ ሁኔታ ለቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር ያለን ግንኙነት እንዲሁ ነው። እንደማንኛውም ከተማ አስተዳደር ጋር ወይም ክልል ጋር ያለን ግንኙነት ማለት ነው። ነገር ግን ይህኛው የፌዴራል ተቋም ነው። ይሁንና እሱም ቢሆን የልማት ድርጅት ነው። በቦርድ የሚተዳደር ቢሆንም ተጠሪነቱ ለሚኒስቴሩ ነው።
ስራዎቹን ሁሉ የሚያስኬደው በራሱ ነው እንጂ የኛ ቢሮ የሚሰራውን የየዕለት ስራውን የሚቆጣጠር አይደለም። መንግስት ባስቀመጠው ስትራቴጂ መሰረት ቤቶችን ለዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ በኪራይ የማቅረብ ኃላፊነት ተሰጥቶት እየሰራ ያለ ተቋም ነው።
አዲስ ዘመን፡– በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ያለውን የመሰረተ ልማት ችግር ለመቅረፍ በሚደረገው ሂደት የቢሮው ድርሻ ምን ይመስላል?
አቶ ታደሰ፡– አንድ ቤት ቤት ሊባል የሚችለው መሰረተ ልማት ሲኖረው ነው። ከእነዚህ ውስጥ መንገድና ትራንስፖርት ተጠቃሾች ናቸው። ውሃና መብራትም ሌሎቹ አስፈላጊ ጉዳዮች ሲሆኑ፣ መስመሩን መዘርጋት ብቻ ሳይሆን በቤት ውስጥ ገብቶ አገልግሎት መስጠት መቻሉም መረጋገጥ አለበት። በተመሳሳይ መልኩም የፍሳሽ መስመሮችም እንዲሁ ናቸው።
ስለዚህ እንደሚኒስቴር መስሪያ ቤታችንና እንደቢ ሯችን በቅንጅት እንዲሰራ ነው እየተደረገ ያለው፤ የተቀመጠም ስታንዳርድ አለ። በመጀመሪያም ህንጻው ከመጀመሩ አስቀድሞ የመንገድ ተደራሽነት እንዲኖረው ተደርጎ ነው ወደ ስራ የሚገባው። መንገዱን ተከትሎ ደግሞ የውሃ፣ የኤሌክትሪክና የፍሳሽ መስመሮች ቀጥሎ የሚመጡ ናቸው። እኛ እንደቢሯችን አንደኛ እነዚህን መሰረተ ልማቶች የማቀናጀት ስራ እንሰራለን።
እንዲህም ሲባል ሁሉም ቅደም ተከተላቸውን ጠብቀው እንዲሰራ ማድረግ ነው። ምክንያቱም አንዱ መጥቶ ለምሳሌ የፍሳሽ መስመሩን ሰርቶ ከሄደ በኋላ የኤሌክትሪክ መስመር የሚሰራው ደግሞ መጥቶ ያንን በመነካካት የሚሰራ ከሆነ ሁሉንም የሚያፈራርሰው ስለሚሆን የቅደም ተከተሉ ጉዳይ በትኩረት የምናየው ነገር ነው። ይህንንም በየሳይቱ በየወሩ በምናደርገው ምልከታ የምንከታተለው ነው። ከባለድርሻ አካላትም ጋር የምንሰራ ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡– የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ሲሰሩ የንግድ ቤቶችም ታሳቢ ተደርገው ነውና አካሄዱ የውጭ አገር ተሞክሮን ከግምት ያስገባ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ታደሰ፡– የቤት እድለኞች ወደቤታቸው ከገቡ በኋላ አንዱ ያስፈልጋቸዋል የሚባለው የገበያ ሁኔታ ሊመቻችላቸው ይገባል የሚል አካሄድ አለ። በየሳይቱ ደግሞ እንደሚታወቀው እየተፈጠረ ያለው ትልልቅ ከተማ ነው። ይህ ሁኔታ የሚፈጥረው ትልቅ የገበያ እድልን ነው። ስለዚህም የገበያ ማዕከል ያስፈልጋቸዋል።
ምናልባት እዚህ የገበያ ሁኔታ ላይ የእኛና የውጭ አገር ተሞክሮ ይለያያል። እኛ ዘንድ የንግድ ሱቆች እየተሰሩ ያሉት በእያንዳንዱ ህንጻ ስር ነው። የንግድ ሱቆቹም የተሰሩት መኖሪያ ቤቶቹን እንዲደጉሙ ታስቦ ነው።
ምክንያቱም ከገበያ አንጻር የንግድ ሱቆቹ በጨረታ ስለሚሸጡ በከፍተኛ ዋጋ የመሸጥ እድሉ ስላለ ገቢ የሚያስገኝ ነው የሚሆነው። ስለዚህም የንግድ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት በተጨማሪ እነሱ በመሸጣቸው የመኖሪያ ቤቶቹን ይደጉማሉና ዓላማው ይህ ነው።
ይሁንና ቅሬታ እየተሰማ ያለው ጉዳይ ነዋሪዎች ከገቡ በኋላ በሚደረጉ የንግድ እንቅስቃሴዎች ነዋሪዎችን በሚፈጠሩ የድምጽ ብክለቶች የመረበሽ ሁኔታ መስተዋሉ ላይ ነው። የጸጥታ መደፍረስ ሁኔታም እንዳለ ይነገራል።
ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ አኳያ ሲታይ የእኛ አገር ይለያል። ለምሳሌ የኮሪያን የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ብናይ አጠቃላይ ቤቶቹ ከተገነቡ በኋላ እዛው ሳይት ተደራሽ በሆነ ቦታ ላይ ራሱን የቻለ ህንጻ ይገነባል። ሁሉም ሱቆች ተሰብስበው እዛ ህንጻ (ሞል) ላይ ይሆኑና ነዋሪዎቹ ሁሉን በአንድ ለማግኘት ይችላሉ። ነዋሪው ርቆ ሳይሄድ ነገር ግን ደግሞ የንግድ ተቋማት በቅርብ ሆነው እንዳይረበሽ ተደርጎ የተሰራ ነው። በዚህ መሰረት ነው የንግድ እንቅስቃሴውና የነዋሪው መኖሪያ ተለያይቶ የተሰራ ነው።
እኔ እንደግሌ የማስበው የእኛም አገር አሰራር ወደዚህ አይነት አሰራር እንዲመጣ ነው። ምክንያቱም ነዋሪዎች አጠገባቸው ባሉ የንግድ ተቋማት ሳይረበሹ በሰላም ማረፍ አለባቸው የሚል እምነት አለኝ። አንዱ ደክሞት ሌላው ደግሞ ታሞ ሊተኛ ይችላል። ገሚሱ ደግሞ በቤቱ ጸጥታን ፈልጎ ሊሆን ይችላል።
በንግድ ተቋማቱ አማካይነት የሚረበሽ ከሆነ ሰላማዊ ኑሮ መኖር ያዳግተዋል። ነገር ግን ገበያው በአንድ ቦታ የሚሆን ከሆነ እምብዛም የድምጽ ብክለት ላያጋጥመው ይችላል። ስለዚህ የኮሪያው አይነት ተሞክሮ ተግባራዊ ቢደረግ ይመረጣል ባይ ነኝ። በአዲሱ በተሻሻለው ስትራቴጄ ውስጥ ግን ይህ ሐሳብ ተካቷል።
አዲስ ዘመን፡– የቤት ግንባታው በሚካሄድበት ጊዜ አሰሪም ተቆጣጣሪም ሆነ ሰሪ እንደሚኖር ይታወቃል፤ በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ ዘርፉ ግንባታ እንደመሆኑ ለሙስና የተጋለጠ ነው ይባላልና ይህን ከመከላከል አሊያም ከመቆጣጣር አኳያ የተሰራ ነገር ይኖር ይሆን?
አቶ ታደሰ፡- አጠቃላይ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ትልቅ ሀብት የሚንቀሳቀስበት ሲሆን፣ ከዛ ውስጥ የቤቶች ግንባታ አንዱ ነው። በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚደረገው ያለአግባብ የመጠቀም ፍላጎቱ በቤቶች ግንባታ ዘርፍም አይታይም ብሎ መደምደም አይቻልም።
በተለይ አሁን አሁን በስፋት የምናካሂዳቸው ግንባታዎች አሉና በዛ ውስጥ ደግሞ ገንቢው፣ አስገንቢውና ተቆጣጣሪው አለ፤ እንዲሁም አምራቹ አለና በሁሉም መስክ ያልተገባ ጥቅም መፈለግ ይቀራል ማለት አያስደፍርም። ስለዚህ በዋናነት የምናደርገው ነገር ቢኖር ቼክ እና ባላንስ ነው።
እየሰራን ያለነውም በዛ ነው። ተቆጣጣሪው አካል፣ ገምቢዎቹ፣ አማካሪውና አምራቾች ማለትም የጠጠር፣ የብሎኬት፣ የሲሚንቶም ሊሆን ይችላል እነዚህን ሁሉ በተቻለ መጠን አንደኛ ተቆጣጣሪው በአግባቡ መስራት ይጠበቅበታል፤ በተጨማሪም ምን እየሰራ ስለመሆኑም ይረጋገጣል። ለምሳሌ በቤቶች ግንባታ ሂደት ወቅት በፊት ወደ 500 የሚሆኑ የግንባታ ግብዓት አሉ። እነዛን የግንባታ ግብዓት ሁሉ የሚያቀርበው መንግስት ነበር።
በዚህ ነገር ላይ ጥናት ሲደረግ አንደኛ እንደተባለው ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ የመሆኑ እድል በጣም ሰፊ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከሀብት ብክነት አኳያ ሰፊ ክፍተት ነበረው።
ሶስተኛው ደግሞ ለመዝግየት አሊያም ለመጓተት የተዳረገ ነበር። ስለሆነም ይህ ነገር መጤን አለበት በሚል በከተማ እስተዳደሩና በእኛ ቢሮ በጋራ ተጠንቶ መቀየር አለበት ወደሚለው ስለተመጣ ምን መደረግ አለበት የሚለው ሲታሰብ አንደኛ መንግስትና አማካሪው ጥራት ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉና ራሱ ኮንትራክተሩ የግንባታ ግብዓቶችን ገዝቶ ማቅረብ እንዳለበት ተደርጓል። ኮንትራክተሩ ግብዓቶቹን በተቀመጠው ዲዛይን መሰረት ከገበያ ራሱ ይገዛል፤ ቀጥሎም በራሱ ይገጥማል ማለት ነው።
ስለዚህም የሙስና አሊያ የብልሹ አሰራር የማስወገጃ መንገድ አንዱ ይህ ነው። በመሆኑም ይህንን ተግባራዊ አድርገናል። ተቆጣጣሪ አካላት መቆጣጠር ያለባቸው በተቀመጠው ብዛትና በጥራት መሰረት ስለመገጠሙ በእያዳንዱ ደረጃ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ። ቢያንስ በዚህ አይነት አካሄድ ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት ተደርጓል። በመሆኑም በእኛ በኩል ሙስናውን በዚህ መንገድ ለመከላከል ጥረት እያደረግን ነው።
አዲስ ዘመን፡– የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ የቤቶች የማጠናቀቂያ ጊዜ እቅድና አፈጻጸም የተጣጣመ ያለመሆኑ ምክንያት ከምን የመነጨ ነው ይላሉ?
አቶ ታደሰ፡- ቤቶቹ ባስቀምጥነው የጊዜ ገደብና ጥራት መሰረት ተጠናቅዋል ወይ ቢባል ብዙ ጥያቄ የሚያስነሱ ነገሮች አሉ። ምክንያቱም ሲቀመጡ በትንሹ ሁለት ዓመት አሊያም 18 ዓመት ተብሎ ነው። አብዛኝዎቹ ቤቶቻችን ግን ከአምስትና ከስድስት ዓመት በላይ ጊዜ እየወሰዱ ናቸው።
ግንባታው ከተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ጋር የተጣጣመ ነው ወይ ላልሽው አይደለም ማለት ይቻላል። ለዚህ ደግሞ ብዙ ምክንያቶች ይኖራሉ። ያስቀመጥናቸው ግን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ አለመጠናቀቃቸው ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ለሁላችንም ግልጽ ነው።
ስለዚህም በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ አልተጠናቀቁም ብሎ መደምደም ይቻላል፤ ምክንያቱም ሀቁ ይኸው ስለሆነ። እኛ ካስቀምጥነው የዲዛይን ጊዜ በጣም ከሚገባው በላይ ዘግይተው ነው እየተጠናቀቁ ያሉት። ለዚህ ደግሞ ሁሉም የየራሳቸው ምክንያት ቢኖራቸውም በቂ ምክንያት ናቸው ወይም አይደሉም ብሎ መግለጽም የሚቻል ነው።
አዲስ ዘመን፡– በእስካሁኑ ሂደት በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ያጋጠሙ ተብለው በአንኳርነት የሚጠቀሱ ችግሮች የትኞቹ ናቸው? መፍትሄስ ተገኝቶላቸዋል ተብሎ ይታሰባል?
አቶ ታደሰ፡- እኛ የምናስበው አራት ትልልቅ ችግሮች አሉ ብለን ነው። የመጀመሪያው የቤት ግንባታ ገና እንደታሰበ የመሬት ዝግጅቱ ላይ ነበር ችግሩ ያለው። የመሬት ዝግጅት ሲባል ከሶስተኛ ወገን ነጻ የሆነ መሬት ቀጥታ ዛሬ ዲዛይኑና ግንባታው አልቆ በተባለው ጊዜ ውስጥ ያልቃል ተብሎ ቢታሰብም መሬት ከተዘጋጀ በኋላ ብዙ ጭቅጭቆች ይፈጠራሉ።
ለምሳሌ እዚህ ቦታ ይገነባል ይባላል ከሶስተኛ ወገን ነጻ የማድረግ እና ከይገባኛል ነጻ የማድረግ ስራዎች በጣም ጊዜ ይወስዳሉ። አንዳንዴ እንዲያውም ወደፍርድ ቤት የሚወሰድ ነገሮችም ስላሉ በቦታው ላይ ለመጀመር ብዙ ጊዜ እንቆያለን።
ሌላው ደግሞ ትልቅ ተግዳሮት እየሆነ ያለው የገንዘብ እጥረት ነው። እንደሚታወቀው ቤት መገንባት ትልቅ ገንዘብ የሚጠይቅ ነው። ይህን ገንዘብ አንደኛ በየዓመቱ በሚፈለገው መጠን መልቀቅ ሁለተኛ የተፈቀደውን ቢሆን በጊዜ ከመልቀቅ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ችግር አለ። በአንድ ሳይት ላይ ግንባታ ከሁለት ወይም ከሶስት ወር በላይ አንዳች እንቅስቃሴ ሳይኖር ይቆያል። ይህ የሚመነጨው ከገንዘብ እጥረት ጋር ተያይዞ ነው።
እስካሁን ፋይናንሱ እየተገኘ ያለው ከንግድ ባንክ ብቻ ነው። በሌሎች አገሮች ላይ በቤት ላይ የሚሳተፉ የቤት ልማት መርሃግብር የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪዎች በጣም ብዙ ናቸው። እኛ አገር ግን እንደሚታወቅ ያለው አንድ ተቋም ብቻ ነው። በአንድ ተቋም ላይ የተንጠለጠለ የቤት ልማት መርሃግብር ነው ያለው። ስለዚህ ከዚህ የተነሳ የገንዘብ ችግሩ ከፍተኛ ነው።
ሌላው ተግዳሮት ደግሞ የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀማችን አነስተኛ ነው። በአሁኑ ወቅት እኛ እየገነባን ያለነው በተለምዶ ነው። እንዲም ሲባል ሲሚንቶና ውሃ በእጅ ተቦክቶና ሌሎችም መሰል ስራዎች ጥንት በነበረው የግንባታ ሂደት የሚከናወን ነው ማለት ነው። በጥቅሉ የግንባታ ስርዓታችን ኋላቀር ነው። ቴክኖሎጂ የመጠቀም ችሎታችን ገና ነው። ሌላው ቀርቶ የግዥ ሂደታችንም ተለምዷዊ ነው።
ስለሆነም ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪያችን ላይ ቴክኖሎጂን የመጠቀሙ ነገር ብዙም የለም። ብዙ አገራት የሚጠቀሙባቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች አሉ። ለምሳሌ ለአንድ ህንጻ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ተፈብርከው ከፋብሪካ የሚወጡበት አይነት ቴክኖሎጂ አለ። ማለትም እንደ የቤት ግድግዳ፣ መስኮትና በር እዛ ፋብሪካ ውስጥ ተመርተው የሚወጡትን የሚያካትት ነው። እኛ ዘንድ እንዲህ አይነቱ ነገር ባለመኖሩ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ አጠቃቀማችን በመሆኑ ግንባታዎቻችን እየተጓተቱ ነው።
ሌላው ግንባታዎች ከተሰሩ በኋላ የመሰረተ ልማቱ በአግባቡ ካለመሰራቱ የተነሳ ነዋሪው መግባት የማይችልበት ሁኔታ ይከሰታል። ቢያንስ ውሃ፣ መንገድና መብራት ከሌለ የጋራ መኖሪያ ቤቱ ውስጥ መግባት አይታስበም። የጋራ መኖሪያ ቤቱ ደግሞ በተፈጥሮው በተለይ ያለውሃ መኖር አይቻልም።
ስለሆነም ይህ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ሌላው እንደ ተግዳሮት የሚወሰድ ነው። ለምሳሌ አንዳንድ ሳይቶች ላይ የሚታዩ ነገሮች አሉ፤ ቤቶቹ እጣ ከወጣባቸው በኋላ የመሰረተ ልማቱ ባለመሟላቱ ዜጎች ወደቤቶቹ መግባት አልቻሉም።
አዲስ ዘመን፡– በቤት ግንባታ ሂደት የውጭ አገር ተቋራጮችን ለማስገባት የታሰበ ነገር ይኖር ይሆን?
አቶ ታደሰ፡- የታሰበ ነገር አለ። እኛ አገር ችግሩ አንዱ ቴክኖሎጂ ሲሆን፣ ሁለተኛው ፋይናንስ ነው ብዬሻለሁ። ስለዚህም ፋይናንስ ያልነውን ማፈላለግ የግድ ይላል። ሁለተኛው እንዳልኩሽ የግንባታ ቴክኖሎጂንም ማፈላለግ ያስፈልጋል።
እኛ እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አንደኛ የውጭ ባለሀብቶችን በፋይናንሱም ሆነ በግንባታው በኩል እንዲሁም በቴክሎጂውም በኩል እንዲገቡ ጥረት እያደረግን ነው ያለነው። ይህም ጥረት መንገዱ በመንግስትና የግል አጋርነት (ፐብሊክ ፕራይቬት ሺፕ) አማካይ ነው። በአሁኑ ወቅትም ቅድመ ሁኔታዎችን በማጠናቀቅ ላይ እንገኛለን።
ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ከልማት ድርጅቶቻችን ጋር ጆይንት ቬንቸር እንዲሰሩ ማድረግ ነው። ለምሳሌ በቅርቡ አንድ የውጪ ድርጅትን ከቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር ያስጀመርነው ሂደት አለ፤ በአሁኑ ወቅት ግንባታ ጀምረዋል።
እንዲሁ ሌሎች የውጭ ኩባንያዎች ፋይናንስ ይዘው እንዲሁም የግንባታ ቴክኖሎጂን ይዘው የቤት ግንባታውን ለመቀላቀል ከአገር ውስጥ ኩባንያዎች ጋር ጥምረት ፈጥረው ለመስራት ፈቃደኝነታቸውን እያሳዩ ይገኛሉ። እነሱ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት እንዲሄዱና በመንግስትና የግል አጋርነት ህጉ መሰረት የምንሰራቸው ነገሮች አሉ።
በመሆኑም ከዚህ በኋላ በቤት ግንባታው ዘርፍ ያለው የመንግስት ሚና እየቀነሰ ነው የሚመጣው። በቤት ግንባታው ዘርፍ መንግስት በሚያቀርበው ዋጋ አይነት ሌሎች ኩባንያዎች ግንባታውን እንዲቀላቀሉ ለማድረግ እየተሰራ ነው። ስለዚህም የአገሪቱ ህግ በሚፈቅደው መሰረት ማለትም ልክ የኢንቨስትመንት፣ የፋይናንስና ሌሎቹም ህጎች በሚፈቅደው መሰረት የውጭ አገር ኩባንያዎቹ በግንባታው ይሳተፋሉ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡– በቅርቡ ይጸድቃል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የሪል ስቴት ጉዳይ ከምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ታደሰ፡– የሪል ስቴት ግብይትና ግመታ አዋጅ በሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ደረጃ ጉዳዩ ተጠናቋል።ጠቅላይ ዓቃቤ ህግም በረቂቁ ላይ አስተያየት ሰጥቶበታል። በአሁኑ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ጉዳዩን የሚመለከተው ዘርፍ እየተወያየበት ያለ ይመስለኛል። ቀጥሎ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊያስቀርበው የሚያስችል አጀንዳ ተቀርጾለታል። ታይቶ የሚጸድቅ ይሆናል ብለን እንጠብቃለን።
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡኝ ማብራሪያ በጣም አመሰግናለሁ።
አቶ ታደሰ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 20/2013