መላኩ ኤሮሴ
ሀገራት በህዋ ያላቸው የሳተላይት ብዛት የጥንካሬያቸው እና የኢኮኖሚ አቅማቸው አመላካች ተደርጎ እየተወሰደ ነው። እንደ ከዚህ ቀደሙ የሀገራት ልዕለ ሀያልነት ማሳያ ከወታደራዊ አቅም ባሻገር በህዋ ያላቸው የሳተላይት ብዛት እየሆነ መጥቷል። ይህንንም ተከትሎ በህዋ ዘርፍ የሚደረጉ ምርምሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፉ መጥተዋል።
ሳተላይት ለሀገራት የተለያዩ ጥቅሞችን ያስገኛል። ሀገራት የሳተላይት ባለቤት መሆናቸው የተለያዩ መረጃዎችን እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። ሳተላይቶች ከሚሰጧቸው ግልጋሎቶች መካከል የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አንዱ ነው። በተጨሪም የአየር ሁኔታ መረጃዎች፣ የደህንነት እና የሳይንሳዊ ምርምሮች ላይ ያለውን የመረጃ ክፍተት መሙላት የሚያስችሉ ሳተላይቶች ናቸው።
ከዚህ ቀደም ሳተላይት ካላቸው ሀገራት መረጃ በመግዛት ይጠቀሙ የነበሩ ሀገራት በራሳቸው የሳተላይት ባለቤት ሲሆኑ ደግሞ መረጃ ለመግዛት የሚያወጡትን ወጪ ይቀንስላቸዋል። የተለያዩ ሳይንሳዊ ምርምሮችን ለማካሄድ እንዲሁም በይነመረብ (የኢንተርኔት) እና መሰል አገልግሎቶችን ለህብረተሰባቸው ተደራሽ እንዲያደርጉና ለሌሎችም ግልጋሎቶች ለማዋል ያግዛቸዋል።
ኢትዮጵያም የህዋ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት ያለውን ጠቃሜታ በመገንዘብ እየሰራች ትገኛለች። በ2012 ዓ.ም ታኅሳስ ወር የመጀመሪያውን የመሬት ምልከታ ሳተላይት ወደ ህዋ ማምጠቋ የሚታወስ ሲሆን ወደ ህዋ ዘርፍ ለመሰማራት እየተንቀሳቀሱ ካሉ ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት አንዷ አድርጓታል።
የኢትዮጵያ ስም በህዋ ሳይንስ መነሳቱ በበርካታ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ከፍተኛ ደስታን የፈጠረ ነበር። ሀገሪቱ ወደ ከፍታ መንደርደር መጀመሯን አመላካች ተደርጎ ተወስዷል። ሳተላይቷ ለግብርና፣ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ ለገጠር እና ለከተማ መሬት እንዲሁም ለውሃ ሀብት አስተዳደር፣ ለማዕድን ስራ፣ የተፈጥሮ አደጋ ክስተቶችን ለመተንበይና ለመሰል አገልግሎቶች ሊውሉ የሚችሉ የሳተላይት መረጃዎችን እየላከች ትገኛለች።
አምና የመጠቀችው የመሬት ምልከታ ሳተላይት ከየካቲት 2012 ዓ.ም ጀምሮ መረጃዎችን የማቀበል ስራ እንደጀመረች የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታውቋል። የኢንስትቲዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ እንደተናገሩት፤ ሀገሪቱ የራሷ ሳተላይት ባለቤት መሆኗ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አስገኝቶላታል። ሀገሪቱ የላከችው የመጀመሪያው ሳተላይት የዘርፉን አቅም እንድትገነባ እድል ፈጥሮላታል።
የመጀመሪያዋን ሳተላይቷን ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ያለ እንከን በህዋ ማቆየቷ ሀገሪቷ በዘርፉ አቅም እንደፈጠረች ማሳያ ነው የሚሉት አቶ አብዲሳ፤ ዘርፉ ለሀገሪቱ አዲስ ቢሆንም ባለሙያዎቹ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ መስክ ላይ ሰርተው ባያውቁም በራስ አቅም ሳተላይቷን አንድ አመት ያለምንም እክል ማቆየት መቻል ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።
እንደ አቶ አብዲሳ ማብራሪያ ሁለተኛው እና ትልቁ ስኬት ሀገሪቷ የመጀመሪያዋን ሳተላይት በማምጠቋ በወጣቶች እና በታዳጊዎች ላይ መነሳሳትን ፈጥሯል። ይህም ወደፊት አቅም ያላቸው በርካታ ታዳጊ ወጣቶች እንዲፈጠሩ እድል ይፈጥራል።
ኢትዮጵያ በህዋ ዘርፍ ላይ ትኩረት ማድረጓ ታዳጊዎችና ወጣቶች በህዋ ሳይንስ ትምህርት በብዛትና በጥራት ተምረው እንዲመረቁ፣ የምርምር ስራዎችን በስፋት እንዲያከናውኑ፣ የህዋ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲስፋፉና የሳተላይት መፈብረኪያዎች እንዲቋቋሙ እድል ይፈጥራል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።
ሳተላይት ማምጠቅ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የሀገራት ተሰሚነት ከፍ ይላል። ኢትዮጵያም ሳተላይት ማምጠቅ መጀመሯ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስፔስን ለሰላም ለማዋል በተሰኘው ኤጀንሲ አባል እንድትሆን አስችሏታል። ይህም ተሰሚነቷን ከፍ እንደሚያደርግ አቶ አብዲሳ ተናግረዋል።
ሳተላይቱ የሚልካቸውን መረጃዎች ለጥቅም ከማዋል አንጻር ኢንስትቲዩቱ ከተቋማት ጋር እየሰራ ነው ያሉት አቶ አብዲሳ፤ ከሳተላይቱ የሚገኙ መረጃዎችን የምርምር ስራዎች ላይ ለተሰማሩት ዩኒቨርሲቲዎችም ማቅረቡንም ጠቁመዋል።
እንደ አቶ አብዲሳ ማብራሪያ ከሳተላይቷ የሚላኩ መረጃዎች አጠቃቀም ላይ በሚፈለገው ልክ ባለመሆኑ ሥራ ይጠበቃል። በሀገር ውስጥ ያሉ ተቋማት የመረጃ አጠቃቀም ስርዓት ክፍተት አለበት። የሳተላይት መረጃ አጠቃቀም ስርዓትም በአግባቡ አልተበጀም። ሀገሪቷ የራሷ ሳተላይት እያላት አሁንም ተቋማት የሳተላይት መረጃዎችን ከውጭ ሀገራት በመግዛት በመጠቀም ላይ ናቸው።
የሳተላይት መረጃ አጠቃቀም ዙሪያ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማሟላት ሀገሪቷ ከራሷ ሳተላይት የምታገኛቸውን መረጃዎች ጥቅም ላይ ማዋል የምትችልበትን ሁኔታዎችን የማመቻቸት ስራ ትኩረት የሚያሻው እንደሆነ ግንዛቤ ተይዟል።
በቅርቡ ደግሞ ሁለተኛውን የመሬት ምልከታ ኢቲ ስማርት አር ኤስ ኤስ (ET-Smart-RSS) የተባለች 2ኛ የመሬት ምልከታ ሳተላይቷን ኢትዮጵያ አምጥቃለች። ስምንት ነጥብ 9 ኪሎ ግራም ክብደት ያላት ይህቺ ሳተላይት ተልዕኮዋ ከመጀመሪያው ሳተላይት ጋር ተመሳሳይ ነው።
ሳተላይቷ ለግብርና፣ ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና አስተዳደር፣ ለገጠር እና ለከተማ መሬት አስተዳደር፣ ለውሃ ሀብት አስተዳደር፣ ለማዕድን ስራ፣ የተፈጥሮ አደጋ ክስተቶችን ለመተንበይና ለመሰል አገልግሎቶች ሊውሉ የሚችሉ የሳተላይት መረጃዎችን ትልካለች ተብሎ ይጠበቃል።
እንደ ኢትዮጵያ በግብርና ላይ የተሰማራ ህዝብ ቁጥር ከ80 በመቶ በላይ በሆነባት ሀገር የአየር ንብረት ሁኔታን፣ የጎርፍ፣ እሳተ ጎሞራ፣ እንዲሁም የአውሎ ነፋስ ሁኔታዎችን መከታተልና ማወቅ አስፈላጊ በመሆኑ፣ ቀድሞ የአየር ሁኔታውንና የሙቀት መጠኑን መረዳት አስፈላጊ ነው። ይህንን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ በሳተላይት በመሆኑ ፋይዳው የላቀ ነው።
ሀገሪቱ ተጨማሪ ሳተላይቶችን ወደ ህዋ ለመላክ በትኩረት እየሰራች ሲሆን፣ በቀጣይ 10 ዓመታት ውስጥ ሀገሪቱ ሶስት ሳተላይቶች ይኖራታል። ኢትዮጵያ የዛሬ ዓመት ካመጠቀችው ሳተላይት በተጨማሪ በቀጣይ 10 ዓመታት የኮሙዩኒኬሽን ሳተላይትን ጨምሮ ሶስት ሳተላይቶች ይኖራሉ።
በዚሁ መሠረትም ሁለት የምድር ምልከታ እና አንድ የኮሙዩኒኬሽንና ብሮድካስት ሳተላይት ይመጥቃሉ ብለዋል። በቀጣይ ዓመታት ወደ ህዋ ይመጥቃል ተብሎ የሚጠበቀው ሳተላይት የኮሙዩኒኬሽን ሳተላይት በኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ የሚስተዋሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎበታል።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ይሹሩን አለማየሁ እንደሚሉት፤ የመጀመሪየዋ ሳተላይት እና በቅርቡ ወደ ህዋ የተላከችው ሁለተኛዋ ሳተላይት ዓላማቸው ተመሳሳይ ነው። ሁለቱም የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች ቢሆኑም በሁለቱ ሳተላይቶች መካከል የሪዞሊዩሽን እና የቴክኖሎጂ ልዩነቶች አሏቸው።
ሁለተኛዋ ሳተላይት ከመጀመሪያዋ ሳተላይት በሪዞሊዩሽን የተሻለች መሆኗን ያብራሩት ዶክተር ይሽሩን፤ በ2012 ዓ.ም የተላከችው ሳተላይት ሪዞሊዩሽን 13 ነጥብ 75 ሜትር ሲሆን፣ የሁለተኛው ሳተላይት ሪዞሊዩሽን ግን 5 ነጥብ 4 መሆኑን አብራርተዋል። የመጀመሪያው ሳተላይት ነጥብ 75 በላይ ስፋት ያላቸውን ነገሮችን በደንብ ማየት ይችላል።
ሁለተኛው ግን ከ5 ነጥብ 4 ሜትር ያነሱ ነገሮችንም በደንብ ማየት ይችላል። ስለዚህ ሁለተኛው ሳተላይት ከመጀመሪያው ሳተላይት ከእጥፍ በላይ የተሻለ የምስል ጥራት ይኖረዋል። በመሆኑም ትንንሽ ቁሶችን እና ጠባብ አካባቢዎችን ጭምር ለመመልከት ያስችላል ብለዋል።
እንደ ዶክተር ይሽሩን ማብራሪያ፤ በ2012 ዓ.ም የተላከው ማይክሮ ሳተላይት ሲሆን በቅርቡ የተላከው ደግሞ ናኖ ሳተላይት ነው። ከ1 እስከ 10 ኪሎ ግራም መካከል ያሉ ሳተላይቶች ናኖ ሳተላይት ይባላሉ። ከ10 ኪሎ ግራም እስከ 100 ኪሎ ግራም ያሉት ማይክሮ ሳተላይት ይባላሉ። ናኖ ሳተላይት በመጠን ትንሽ ሳተላይት ሆና የዘመኑን የረቀቀ ቴክኖሎጂ የያዘ በመሆኑ የተሻለ ጥራት ያለው ምስል መላክ ያስችላል።
የመጀመሪያው ሳተላይት ሲገነባ ኢትዮጵያዊያን የሳተላይት ግንባታም ሆነ መረጃ የመቀበል ክህሎት አልነበራቸውም የዲዛይን፣ የሳተላይት መረጃን በአግባቡ መጠቀም፣ ማዕከሉን መቆጠጠር ፣ የሳተላይቶችን ጤንነት የመጠበቅ አቅም ከዚህ በፊት አልነበረም። የመጀመሪያ ሳተላይት ሲገነባ ኢትዮጵያዊያን ሲማሩ ስለነበር ሳተላይቱ ከተላከ በኋላ የሳተላይት መረጃ መቀበል እና የሳተላይት መረጃ መቀበያ ጣቢያ መቆጣጠር፣ ሲበላሽም የመጠገን አቅም መገንባት ተችሏል።
ኢትዮጵያዊያን ከመጀመሪያው ሳተላይት ባገኙት ልምድ ሁለተኛው ሳተላይት ላይ የመጀመሪያ ዲዛይን ለመሥራት በቅተዋል። ዋናውን ዲዛይን እና ሳተላይቱን የማምረት ስራ ከውጭ ዜጎች ጋር አብረው ለመስራት ዕቅድ ቢያዝም ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በመከሰቱ ምክንያት በሥራው ቦታ ባይገኙም ባሉበት ሆነው በበይነመረብ በታገዘ ሥራውን ለመሥራት ችለዋል። የመጀመሪያዋ እና በቅርቡ የተላከችው ሳተላይት አንድ ላይ ሲጣመሩ የተሻለ የመሬት ምልከታ አገልግሎት ማግኘት እንደሚቻል ይጠበቃል።
ሁለተኛዋ ሳተላይት በቅርቡ መምጠቋን ተከትሎ በተደረገው መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስትር ዲኤታ ዶክተር ያኒያ ሳኢድ እንደተናገሩት፤ መንግስት የሀገሪቷን ከፍታ ለማረጋገጥ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ላይ ይገኛል።
ለብልጽግና ጉዞ ስኬት የቴክኖሎጂ እና የኢኖቬሽን ልማት የሚኖረውን አይተኬ ሚና በጥልቀት በመገንዘብ በረጅም ጊዜ ስትራቴጂክ እቅድ ውስጥ ከወሳኝ ጉዳዮች አንዱ መደረጉንና በተለይም በህዋ ሳይንስ ላይ ልዩ ትኩረት መሠጠቱን አመልክተዋል።
የህዋ ሳይንስ ለተፈጥሮ ሀብት አስተዳደርና ልማት፣ ለመሰረተ ልማት ግንባታና ክትትል፣ ለአየር ንብረት ለውጥና ለተፈጥሮ አደጋ ቁጥጥር ከሚኖረው ፋይዳ ባሻገር ለስራ እድል ፈጠራ እና ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ሰፊ መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር መሆኑ ግምት ውስጥ መግባቱንና መንግስትም ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 20/2013