ለምለም መንግሥቱ
እንደዛሬ በሲሚንቶ ውጤት የቤት ግንባታ ሥራ ከመስፋፋቱ በፊት የሣር ጎጆ ቤት የተለመደ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። በከተሞች ሳይቀር የሣር ቤቶች በሲሚንቶ ውጤት የተተኩት ቅርብ ከሚባል ጊዜ ወዲህ ነው። ሆኖም አሁንም በከተሞች የሣር ቤት ከመኖሪያ ቤት ይልቅ ሎጅ ለተባሉ ዘመናዊ ሆቴል ቤቶች ግንባታ እየዋለ ይገኛል።
ዛሬም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ሣርና እንጨትን እንዲሁም ጭቃን ግብዓት አድርጎ የሚገነባው የሣር ጎጆ ቤት ሙሉ ለሙሉ አልተቀየረም። በሌላ በኩል በከተሞች አካባቢ ለሚደረግ ግንባታ በአሁኑ ጊዜ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው የሲሚንቶ ግብዓት ነው። ሁሉም ግንባታ በሲሚንቶ ላይ የተመሠረተ መሆኑና ወጪ ቆጣቢና አማራጭ የግንባታ ግብዓቶች አለመኖራቸው የሲሚንቶ ፍላጎት እንዲጨምርና የዋጋ ንረትም እንዲያስከትል አድርጓል የሚሉ ወገኖች አሉ።
በጉዳዩ ላይ ሀሳባቸውን እንዲያካፍሉን የጠየቅናቸው በአዲስ አበባ ከተማ ዲዛይን ኤጀንሲ የግንባታ ክትትልና ቁጥጥር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሀብቱ ገብረማርያም፤ ወጪ ቆጣቢ ግብዓት መጠቀም ሲባል ከደረጃ በታች የሆነ ግብዓት ጥቅም ላይ ማዋል ወይንም የወረደ የቤት ግንባታ ይከናወን ማለት እንዳልሆነ ግንዛቤ መያዝ አለበት ይላሉ።
እርሳቸው እንዳሉት ደረጃቸውን የጠበቁ የአሸዋ፣ የጠጠርና የሲሚንቶ ግብዓቶች ናቸው ለቤት ግንባታ የሚውሉት። የግንባታ ግብዓት እንደሚመረጥ ሁሉ ግንባታውን የሚያከናውኑት ባለሙያዎች ወይንም ተቋራጮች ብቃታቸው ተፈትሾ ነው ሥራውን እንዲሠሩ መደረግ ያለበት። በመንግሥት የሚሠሩ እንደጋራ መኖሪያ ቤት ያሉትም ግንባታዎች በተመሳሳይ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል።
ጨረታ በማውጣት የሚወስደውን ጊዜ እና የሚወጣውንም ወጪ ለመቆጠብ በጥናት በመንግሥት እምነት ተጥሎባቸው የተለዩና የሚታወቁ ባለሙያዎች እንዲሳተፉ በማድረግ እንዲሁም ከግንባታ ጋር የሚከናወኑ መሠረተ ልማቶች ላይ የሠለጠኑ የተለያዩ ባለሙያዎችን በማሳተፍ ወጪን መቆጠብ የሚቻልበት አሠራር የተለመደ ነው። ይህን ዘዴ መከተል የቤት ግንባታውን ጥራት ያወርደዋል ማለት አይደለም።
በተደጋጋሚ የሚነሳው የሲሚንቶ እጥረትና የዋጋ ንረት ሰው ሰራሽ እንጂ እንደሀገር የጥሬ ዕቃ አቅርቦት አጋጥሞ አይደለም የሚሉት አቶ ሀብቱ ግንባታ ሲከናወን የሁሉም ግብዓት ልኬት መታወቅ እንዳለበትና ብክነትንም ማስወገድ እንደሚጠበቅ ይገልጻሉ።
እርሳቸው እንዳሉት ችግሩ በግንባታ ዘርፉ ውስጥ በአግባቡ የተዘረጋ የጥሬ ዕቃ አስተዳደር አለመዘርጋቱ ነው። በዘርፉ ባለሙያዎችን ማፍራት የተጀመረው ገና ቅርብ ጊዜ በመሆኑ ችግሮች መኖራቸው ግድ ነው። በመንግሥት በኩል የቤት ግንባታ ሥራውን በሲሚንቶ ውጤት ብቻ ከመጠቀም አግሮስቶን የተባለውን አማራጭ የግብዓት ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ተሞክሯል።
ይሁን እንጂ ቴክኖሎጂውን ጥቅም ላይ ለማዋል ሲሞከር ከቴክኖሎጂው ጋር ለመተዋወቅ የሚያግዙ ሥልጠናዎች ወይም የቴክኖሎጂ ሽግግር ባለመደረጉ በጥራት ለማምረት ባለመቻሉ ውጤታማ አልሆነም።
በሌሎች ሀገሮች ከተለመደው የግንባታ ጥሬ ዕቃ አጠቃቀም ለመውጣት ጥረቶች መኖራቸውን ተሞክሮዎች ያሳያሉ። ነገር ግን ባለሙያዎችን ማብቃት ላይ ቅድሚያ ይሰጣል። ክህሎቱ ያላቸው ሀገሮች በቀላል ግብዓት በመጠቀም ለሦስት ዓመት ብቻ የሚያገለግል ቤት ይገነባሉ። በእነርሱ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታና የግብዓት አቅርቦት ሊያከናውኑት ይችላሉ።
በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን ወደዚህ አሠራር የሚያስገባ ነገር የለም። በኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ 25 ዓመትና ከዚያ በላይ ሊቆይ የሚችል ቤት መገንባት የሚያስችል የግንባታ ግብዓት በመኖሩ ወደ አማራጭ የግንባታ ግብዓት ለመግባት የሚያስችል ነገር የለም። ወደሌሎች አማራጮች ከመሄድ ያለውን ሀብት በአግባቡ መጠቀም ላይና ያለውን ክፍተት ፈትሾ በአግባቡ መፍታት ላይ ትኩረት ማድረጉ ይመከራል።
ግንባታ ከማህበረሰብ ንቃተ ህሊና ጋርም ተያያዥነት ስላለው አማራጭ የግንባታ ግብዓት አጠቃቀም ሽግግር ውስጥ ለመግባት የማህበረሰቡም ግንዛቤ አብሮ መዳበር አለበት። ከለመደው ነገር ውስጥ ወጥቶ አዲስ ነገር ለመልመድ ጊዜ ይፈልጋል።
ቀድመው መሠራት የሚገባቸው ባለሙያዎችን ማብቃት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር አስፈላጊነቱን መረዳት ላይና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሥራዎች ከተሠሩ በኋላ ግን በሂደት አማራጮችን ማየት ይቻላል፤ አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜም ሊኖር እንደሚችል ታሳቢ ማድረጉ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ኢንስቲትዩት ኦፍ አርክቴክቸር ቢዩልዲንግ ኮንስትራክሽን አንድ ሲቲ ዲቨሎፕመንት መምህር የሆኑት ዶክተር ጥበቡ አሰፋ እንደሚሉት የቁሳቁስ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የውሃና ምግብ ፍሰት ለከተማ ወሳኝ ግብዓቶች ናቸው።
በአሁኑ ጊዜ በከተሞች 60 በመቶ የሚሆነውን ቦታ የሚወስደው የመኖሪያ ቤት ግንባታ ሲሆን ከጥሬ ዕቃነት ወደሚፈለገው ጥቅም ለመቀየር የሚወስደው ኃይል ወሳኝ በመሆኑ የአንድ ከተማ የህንፃ ግንባታ የሚለካው በኤሌክትሪክ ኃይል ፍሰቱ ነው። በመሆኑም በኤሌክትሪክ ኃይል ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ የጥሬ ዕቃውን ዋጋ ከፍም ዝቅም ያደርገዋል አልያም እጥረት እንዲከሰት ያደርጋል።
ዶክተር ጥበቡ ለአብነት እንደጠቀሱት አንድ ኪሎ ግራም አሉሚኒየም አምርቶ ጥቅም ላይ ለማዋል 57 ሜጋ ዋት ኃይል ይፈልጋል። ጥሬ ግብዓቶቹን ለመፍጨትና ለመቀጥቀጥ የሚወስደው የኤሌክትሪክ ኃይል ከፍተኛ በመሆኑ ግብዓቱ እንዲወደድ ምክንያት ይሆናል። ግብዓቱ ከሚገኝበት ጀምሮ ጥቅም ላይ ውሎ ወደ ብስባሽነት እስኪቀየር ያለው ሂደት ዑደተ ህይወት ትንተና ይሠራለታል።
በዚህ የትንተና ዘዴ እያንዳንዱ ግብዓት የፈጀው የኤሌክትሪክ ኃይልና ሌሎችም ነገሮች በደንብ ከተለዩ በኋላ ነው የግብዓቱን ዋጋ መለየት የሚቻለው። በትንተናው የዋጋ ንረትን ብቻ ሳይሆን ግብዓቱ መልሶ አካባቢ ላይ ብክለት ስለማስከተሉ መሬቱ መልሶ እህል ማብቀል ስለመቻሉ ማረጋገጥ ይቻላል።
ዶክተር ጥበቡ እንዳስረዱት እንደ ድንጋይና ጭቃ ያሉ የግንባታ ግብዓቶች በኤሌክትሪክ ኃይል በማብሰልና በመቀጥቀጥ ጥቅም ላይ የሚውሉ ባለመሆናቸው ተፈላጊ ናቸው። በአሁኑ ጊዜ በተፈጥሮ የድንጋይ ግብዓት የሚሠሩ ‹‹ግሪን ቢውልዲንግ›› ወይንም ተፈጥሯዊ ህንጻዎች በዓለም ላይ እየተለመዱ ነው።
ግብዓቶቹ የአካባቢ ብክለትን በመቀነስና ለመኖሪያም ተስማሚ በመሆናቸው ተመራጭ ናቸው። ለግንባታ ሲውሉም ለማስተካከል ካልሆነ በስተቀር ከፍተኛ የሆነ የኤሌክትሪክ ኃይል አያስፈልግም። ቤቶቹ የሚገነቡት ለእነርሱ ተብሎ በተዘጋጀ መሣሪያ ተለክቶ ነው። ለአብነት ያህልም አውስትራሊያ ሀገር ግሪን ስታር የሚባል መሣሪያ የሚጠቀሙ ሲሆን ቤቶቹም የተለያየ ደረጃ ይሰጣቸዋል።
ወጪን፣ አካባቢን፣ የሰው ልጅ ጤናን ማዕከል ያደረጉ የቤት ግንባታዎች ለማከናወን በምርምር የታገዘ የግንባታ ሥራ ማከናወን ወሳኝ ነው። ግብዓቶችን ከቦታ ቦታ ከማንቀሳቀስ በአንድ ቦታ በመገጣጠም ግንባታው የሚከናወንበት ቦታ ያለቀለት ምርት ማጓጓዝ የተሻለ ነው፤ ዋጋም ይቀንሳል።
እንዲህ ያለ ምርት ጥቅም ላይ ማዋል ሲታሰብ ግን ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆዩ መሆናቸውንና የአገልግሎት ዘመናቸው ሲያበቃ ተመልሰው ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ይሄንን በህይወት ዑደት ትንተና ማረጋገጥ ይገባል። በአሁኑ ጊዜ ለተለያየ አገልግሎት አካባቢዎች ሲፈርሱ የቤቶቹ በሮችና ሌሎች ቁሳቁሶች መልሰው ጥቅም ላይ ይውላሉ። የዘላቂነት አዋጭ የሚባለው እንዲህ ያለው አሠራር ሲተገበር ነው። ይህ ካልሆነ ግን የቆሻሻ ክምርን ማስወገድ አይቻልም፤ ብክለትም ለመከላከል ያስቸግራል።
በአንድ ወቅት ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህንፃ ኮሌጅ ውስጥ የግብዓት ምርምር ማዕከል እንደነበርና ግብዓቶችም ተመርተው ይወጡ እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር ጥበቡ አሁን ግን እየተሠራበት እንዳልሆነና ግንባታው በጥንቃቄ እየታየ ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው ያስረዳሉ። የግብዓት አቅርቦቱ ንግድ ላይ ትኩረት ያደረገ እንደሆነም ይናገራሉ።
እርሳቸው እንዳሉት የግንባታ ግብዓት የሚሸጡ ነጋዴዎች በሚበዙበት ጊዜ ደግሞ የግብዓት ዋጋ ይንራል፤ የአቅርቦት እጥረትም ያጋጥማል። የአደጉ ሀገሮች በምርምር የታገዘ ሥራ በመሥራት የተለያየ ማጣበቂያ ወይንም ማያያዣዎች ይሠራሉ። ጥንካሬው እንደተጠበቀ ሆኖ የህንፃውን ክብደት ለማቅለል ብዙ ሥራዎች በማከናወን ነዋሪው በአቅሙ ልክ ቤት ለመሥራት የሚያስችለውን ግብዓት ያቀርባሉ።
የነዋሪዎችን አቅም ያገናዘበ ግብዓት መኖር አለበት የሚሉት ዶክተር ጥበበ መንግሥት ቤት ገንብቶ ለዜጎቹ ሲያስተላልፍ የውስጥ ክፍሉን ባለቤቱ በአቅሙ በሚችለው ግብዓት ከፋፍሎ እንዲጠቀም የውስጥ ሥራውን ሊተውለት እንደሚገባ ይመክራሉ። መንግሥት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ የተጠቀማቸው አግሮስቶን የተባለው የውስጥ ቤት ማከፋፈያ ጥቅም ላይ ቢያውለውም ነዋሪው እያፈረሰ በራሱ በብሎኬት እየሠራ ይገኛል ሲሉም ተናግረዋል።
‹‹በመንግሥት ብቻ ፍላጎትን ማሟላት ስለማይቻል የቤት ግንባታው አማራጭ ሊኖራቸው ይገባል። ቀደም ሲል በአርሶ አደሩ መንደር ይሠሩ የነበሩ ቤቶች ዛሬ ጎጆ እየተባሉ በውድ ዋጋ ለአንድ ቀን በኪራይ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው። ይሄ ቤቶቹን መናፈቅ እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል።
ከተሜነት እነዚህን ሊያስቀራቸው አይገባም። በበሰለ ሣር፣ እንጨት፣ ጭቃና ተፈጥሮሯዊ ነገሮች ነው የሚሠሩት።›› በማለት ግንባታው በምርምርና ሕግ እንዲታገዝ እንዲሁም ጥቅም ላይ የሚውለው ግብዓት ወደተፈጥሯዊ ግብዓት መመለስ እንዳለበት አመልክተዋል። ኢትዮጵያ የአምቦ፣ የተከዜ፣ የላሊበላ እና ሌሎችም የድንጋይ ሀብት እንዳላትና እነዚህንም መፈተሽ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
ዶክተር ጥበቡ የግንባታ ዘርፉ በምርምር አለመታገዙ አስቆጭቷቸዋል። መንግሥት በምርምር ላይ የታገዘ ቤት ላለመሥራቱም በእርግጠኝነት ይናገራሉ። የምርምር ፖሊሲም የለም ይላሉ። እርሳቸው እንዳስረዱት ለምርምር የሚውል ገንዘብ አይመደብም። ይሄ ደግሞ ተመራማሪውን አያበረታታም። በሀገር ውስጥ በምርምር ከሚወጣው ግብዓት ከውጭ በግዥ የሚገባው በዋጋ ርካሽ ነው።
የግብዓት ንግዱ በኮሚሽን የሚሠራ በመሆኑም ምርምሩ አይበረታታም። የግብዓት ምርምር ማዕከል ደግሞ ለኬሚካልና ለተለያዩ ወጪዎች ከፍተኛ በጀት ይፈልጋል። በማዕከል ውስጥ ተማሪዎችን ያሰለጥናል። ኬሚካል ኢንጂነሪንግ የሚማሩ ተማሪዎች ለግንባታ የሚውል ጥሬ ዕቃ ማምረት የሚያስችል ምርምር እንዲያካሂዱ ወይንም ክህሎት እንዲያገኙ የሚያስችል አቅም እየተገነባ አይደለም። ከዚህ በመውጣት ችግር ፈች ምርምር የሚያካሂዱ ምሁራንን ወይንም ባለሙያዎችን ማፍራት ይገባል። አሁን በግንባታ ዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን የሚፈታ ችግር ፈች የምርምር ውጤት ይዞ የወጣ ተመራማሪ መኖሩንም ይጠራጠራሉ።
አራት ኪሎ በሚገኘው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ‹‹ማቴሪያል ሳይንስ›› የሚባል የትምህርት ክፍል መኖሩን ያስታወሱት ዶክተር ጥበቡ በዚህ ክፍል ከውጭ የሚገባ የግንባታ ግብዓትን የሚተካ ስለመሠራቱም እርግጠኛ እንዳልሆኑ ይናገራሉ። በአሁኑ ጊዜ ለወለል ንጣፍ የሚውለው ሴራሚክ የተባለው ግብዓት ከውጭ ሀገር በውድ ዋጋ ገብቶ እየተሠራ መሆኑም ይናገሩ፤ ስለዚህ በዘርፉ ያለውን ትምህርት መፈተሽ ግድ መሆኑን ያመላክታሉ።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ዋና ተግባራቸው ችግር ፈች ምርምር ማካሄድ በመሆኑ ጉዳዩ ሊጤን ይገባል የሚል እምነት አላቸው። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚከናወኑ የምርምር ሥራዎች ከመደርደሪያ ላይ ወርደው ወደተግባር መቀየር አለባቸው ተብሎ በመንግሥትም ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠው ይታወሳል።
ለምርምር የሚበጀው በጀትም እንዲሁ ትኩረት ማግኘቱን በተለያየ ጊዜ በመገናኛ ብዙሃን ጭምር ሽፋን አግኝቷል። ወደኋላ የተመለሰ ነገር ካለ ግን ሊፈተሽ ይገባል። የግንባታ ዘርፉ እንደሌሎች ሁሉ በምርምር መታገዙ ከግብዓት አቅርቦትና የዋጋ ውድነት ጋር የሚነሱ ችግሮች እንደሚፈቱ ተስፋችን ነው።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 20/2013