ዳግም ከበደ
ግርርርር…አንበል!
ከሰውነታቸው የጎደለ ነገር ይታየኛል። ምን አለፋችሁ በመንጋ ያስባሉ፣ በመንጋ ይፈፅማሉ። ሚዛናዊነት በራስ የመቆም ፍላጎት ፍፁም አይታይባቸውም። ሲንጫጩ አንድ ላይ ነው። ድምፃቸው ይረብሻል። ከመካከላቸው አንዱ ሃሳብ ካፈለቀ የሁሉም ገዢ መመሪያ ይሆናል። ትክክለኝነቱ አይረጋገጥም።
አንድ ጊዜ እንኳን መልሰው ሊያስቡትና ሊመዝኑት አይሹም። ግርርርር….ብለው ይሄዳሉ፤ ግርርርር … ብለው ያስባሉ፤ አረ ሲበሉም ግርርርርርር ብለው ነው። ለውሳኔ የፈጠኑ ናቸው፤ ይጨንቃሉ።
ይሄ በሽታ መቼ እንደያዛቸው በውል አይታወቅም። እነሱም አይጨነቁበትም። መታመምህን ካላወቅክ በሽታው በየት በኩል ሊያሳስብህ ይችላል? በፍፁም! እነዚህ ሰዎች አደገኞች ናቸው። ምክንያቱ ደግሞ ግልፅ ነው። የተደመረ ሃይል አላቸው። ሊያጠቁህ ከፈለጉ ይዘምቱብሃል። እውነትህ እስክታሸንፍ ብዙ ርቀት ጥለውህ ይጓዛሉ። ለጊዜውም ቢሆን ጥፋቱ የከፋ ይሆናል።
ብቻቸውን መቆም የማይችሉት ፅናት፣ እውነት፣ እውቀት የመሳሰሉት ነገሮች ስለሌሏቸው ነው። በተናጠል ቆመው ምንም ማሳካት አይችሉም። ለምን? ስንፍና አንዱ ምክንያት ነው። ሌላኛው ስግብግብነት ነው። እንደ ጆፌ አሞራ ያገኙትን ተቧጭቀውና ተናጥቀው ይበላሉ አሊያም ይሻማሉ።
በራሳቸው መቆም ባለመቻላቸው ምክንያት ፍላጎታቸውን የሚያሳኩበት ጎጥ፣ ቡድን፣ ዘር፣ ብሄር አሊያም አንዳች ጥጋት ፈልገው ነው፤ እዛ ውስጥ ይወሸቃሉ። ለአትክልቶች መለምለም ለም አፈር ምቹ እንደሆነው ሁሉ፣ ለነዚህ መንጋዎች በጎጥ ውስጥ በዘር ስብስብ ውስጥ መፋፋት የተለመደ ነው። አሳውን ከባህር ውስጥ ስታወጣው ትንፋሽ አጥሮት እንደሚሞተው ሁሉ እነርሱም ከዘውጌያቸው ስታወጣቸው የሚገቡበት ነው የሚጠፋቸው።
ብቻቸውን መፍጠር ያልቻሉትን ተፅእኖ እነርሱን ከመሳሰሉ ሰዎች ጋር በጋራ ለማሳካት ይጥራሉ። በተናጠል ያጡትን ሃብት በቡድን በዘረፋ ያግበሰብሳሉ። ተናግረው ማሳመን ካልቻሉ ሆሆሆሆ ብለው የተናጋሪውን ድምፅ ለማጥፋት ይጥራሉ። የሚያሳዝነው ለጊዜውም ቢሆን ይሳካላቸዋል።
ንፁሃን ላይ እጃቸው ይበረታል። ጭካኔ መገለጫቸው ነው። ለማጥቃት ደካሞችን ይፈልጋሉ። ምክንያቱም በጠንካሮች ሁሌም ተሸናፊ ናቸው። ሃሳብ የለሽ ናቸው፤ ማጥፋት እንጂ ማልማት የማያውቁም።
አስገራሚው ነገር ለማልማትና ለመልካም ነገር በቡድን ከሚሰባሰቡት ይልቅ ለጥፋት በመንጋ የሚከማቹት አንድነትንና ህብረትን የመፍጠር ሃይላቸው እጅጉን የተቃና ነው። በፍጥነት አንድ ይሆናሉ። እንደ አንበጣ ከፊታቸው ያለውን ሁሉ ያግበሰብሳሉ። ሃሳባቸውን በግዳጅ ለመጫን ቅንጣት አያቅማሙም። ይሳካላቸዋል።
ግን ለምን? ሳይንሱ ለነዚህ መሰል ስብስቦች ስያሜ አላጣላቸውም። ባህሪያቸው በእጅጉ ስለሚያስገርምና ጥፋቱም ላቅ ያለ ስለሆነ የሰው ልጅ በደረሰበት የስልጣኔ ደረጃ ልክ ይህን ቡድናዊ መንፈስ ለማከም ጥረት አድርጓል፤አሁንም እያደረገ ነው።
ለመግደል፣ ለመቀማትና ባጠቃላይ በመንጋ (pack mentality) ውሳኔዎችን ለማሳለፍ በምክንያታዊነት (by the capacity of consciously making sense of things) ነገሮችን ማጤን አይፈልጉም። አረ እንዲያውም ለሰከንድ ስለጉዳዩ አያስተውሉም። እንዲያው በደፈናው ግርርርርርር…! ነው ስራቸው።
ምክንያታዊነት (Reasoning) ለሰው ልጆች ብቻ የተቸረ ፀጋ ነው። ማመዛዘን የማስተዋል ውሳኔዎችን በትክክለኛው መንገድ ያለምንም ተፅእኖ በራስ ተነሳሽነት (the ability of the mind to reach correct conclusions individually and intellectually) የመድረስ ጉዳይ ነው። ምክንያታዊነት ሃሳብን ማግበስበስና መዋጥ፤ እርሱን ተከትሎ ደግሞ ከፊት ለፊት ያለውን ሁሉ እየደረማመሱ የልብ ፍላጎት ማሳካትን አይጨምርም።
ይልቁኑ በምክንያት አምኖ በዙሪያው ካለ ሰው በተለየ መንገድ ክፉና ደጉን መለየት ነው። አንድ በግ ለምለም ሳር አይታ ስትንቀዠቀዥ ወደ ገደሉ ገብታ ለጓደኞቿም ጭምር ጦስ እንደምትሆነው ሁሉ፣ የፊቱን ሳያጤን መንጋን ተከትሎ የሚሄድ ሰው ውጤቱ ገደል ከመግባት የሚብስ አጋጣሚ ጋር ያፋጥጠዋል። የማን እንደሆነ በማይታወቅ ሃሳብ ተጠልፎ በዚያ ውስጥ መዳከር የግሪሳ (Herd mentality) በሽታ ነው። ወጥመድ ውስጥ ከመውደቅም አይተናነስም።
የሰው ልጅ (ለምን?) የሚለውን የሁል ጊዜ ምክንያታዊ ጥያቄ ተሸክሞ ነው የሚዞረው። ሆሆሆሆ ብለው ለሁሉም ነገር የጅምላ ድምዳሜ ላይ የሚደርሱ ሰዎች ግን ይሄን ውድ ሰዋዊ የሆነውን ስጦታ ቀረጣጥፈው በልተውታል። የሰውነት ልክ የሆነውን ባህሪ ኮትኩቶ ከማሳደግ ይልቅ በውስጣቸው የተቀበረውን አውሬ ይቀሰቅሱታል።
ሁሌም ለመፍረድ ዝግጁ ናቸው። ለመወሰንም እንደዚያው። በዚህ የመንጋ ስብስብ ውስጥ ግን ከሁሉም በላይ በተለየ መንገድ ተጠቃሚ የሚሆን እኩይ አላማን ያነገበ ይኖራል። የዚህን ሰው ዓላማ ያለምንም ጥያቄ ሳያቅማሙ ሳይቀንሱ ሳይጨምሩ ይተገብሩታል። ግደሉ ካለ ግርርርርር…፣ስም አጥፉም ከሆነ ግርርርርርር…። ምክንያቱም ለምን የሚለው አመክንዮ የሚፈልገው የአእምሯቸው ክፍል በአለማመዛዘን ተጠፍሯል።
ዓለም አሁን ላላት ድንቅ ለውጥ ግለሰቦች ያላቸው ሚና ከምንም ጋር የሚነጻጸር አይደለም። እነዚህ ግለሰቦች ዙሪያ ገባቸውን በማስተዋላቸው፤ አዳዲስ ነገር የመፍጠር ጉጉት ስላላቸው ተፈጥሯዊ ስጦታ የሆነውን ስል የማሰላሰል አቅማቸውን አቀናጅተው እጅግ ግሩም የሆኑ የስልጣኔ ፈርጆችን አሳይተውናል።
ሳይኮሎጂስቱ በጉስታፍ ሊ ቦን Gustave Le Bon (the Crowd: A Study of the Popular Mind) በሚል ርስእ ላይ ተመስርቶ እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ1895 በፃፈው ፅሁፍ ለአለም ስልጣኔ መሰረት የሆኑት ወደፊትም የሚሆኑት ግለሰቦች እንደሆኑ ያስቀምጣል።
በተቃራኒው ደግሞ ቡድኖች ለጥፋት እንጂ ለመልካም ነገር ያላቸው ሚና አነስተኛ እንደሆነ ይናገራል። በዚህ ፅሁፍ ላይ በግርድፉ የተነሳው ሃሳብ በሰውዬው ቀጥታ ቋንቋ ሲቀመጥ (Civilizations as yet have only been created and directed by a mall intellectual aristocracy, never by crowds)። ኸረ እንደውም (Crowds are only powerful for destruction) በማለት ያለምክንያት ግርርርርር… የሚል ቡድን ለጥፋት እንጂ ለልማት እንደማይሆን ያስቀምጣል። ስልጣኔ ሁሌም እንቅፋት ሲገጥመው ለዚህ ውድቀትና ማቆልቆል ምክንያት የሚሆኑት የመንጋ ስብስብ ከሰዋዊ ተፈጥሮ ለማፈንገጥ በሚጥሩት አማካኝነት መሆኑን When the structure of a civilization is rotten, it is always the masses that bring about its downfall በማለት ይገልፀዋል፤
እዚህም በአገሬ ለመገንባት ሳይሆን ለማፍረስ ቅርብ የሆነ ግርርር ያለ ቡድናዊ ስብስብ ይታየኛል። ለጥፋት አሰፍስፏል። ሰው የሆነ ሰው እንዴት ያለምንም መነሻና ምክንያት ለማውደም ለረብሻ ዝግጁ ይሆናል። ይገርማል!! ግርርርር የማለት መንፈስ።
ከቡድንና የጎጥ ሃሳብ መውጣት ግላዊ ማንነታችንን ብቻ ሳይሆን የሚቀይርልን በእኛ የተሳሳተ ውሳኔ ተመርተው ወደ ገደሉ ጥልቅ የሚገቡትን አላዋቂዎችንም ጭምር ነው። ታዲያ የሚሻለን እያንዳንዱ ድርጊት ይዞት የሚመጣውን ውጤት መዝነን መወሰን ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ውሳኔያችንን በተፅእኖ ውስጥ የሚከቱ ማናቸውንም ቡድናዊ ሃሳቦች ማስወገድ አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም እኛ ከሌሎች ጋር የምንጋራው ምክንያታዊ ሃሳብ እንጂ ምክንያታዊነታችንን ራሱን የሚመዝንልን ጭንቅላት አይደለም። ስለዚህ ምን ይሻላል? የሚሻለውማ ቀላል ነው። እርሱም ግርርርርር አለማለት ብቻ ነው!
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 20/2013