መምህር አሰምሬ ሳህሉ
ሰሞኑን እያየነውና እየኖርነው ያለው እውነት አስገራሚ፣ አሳዛኝ ፣ አስደንጋጭና የሚያስቆጣም ነው። ከሰሜን ዕዝ የግፍ ጭፍጨፋ በኋላ ይኸው ጆሯችን በጨካኙና አቻየለሽ በሆነና ለግፉ ቃል ባጣሁለት፣ የትህነግ ቡድን ትዕዛዝና ባቋቋሙት “ሣምሪ” በተባለ ቡድን የተፈጸመውን አመጻዊ ድርጊት እየኖርነው ነው።
በማይካድራ የግፉዓኑ ሞት ቁጥር ከ1ሺ1መቶ መብለጡ እየተነገረን ነው።፣ በሁመራና ቃፍታ ደግሞ ሌላ የጅምላ ግድያና ግፍ መፈፀሙን መረጃና ማስረጃዎች እየወጡ ነው። የህውሓት ጁንታ ቡድን የፈጸማቸው የግፍ ግድያዎች በቀጣይ ጸሃይ እየሞቃቸው ሲወጡ ገና ብዙ ጉድ እንደምንሰማ ስሜቴ ይነግረኛል።
በኢትዮጵያ የርእሰ-መንግስትነት ስልጣንን፣ ለማስ መለስ ፈልጋችሁ የማትወዱትን ህዝብ ለመምራት የቋመጣችሁት እንደምንድነው? ይህንን የሁከትና የግፍ አዝመራስ በማጨድ ከመቀሌ አዲስ አበባ የመግቢያው መንገድ ይቀናልናል ብላችሁ ታምኑ ነበርን? ወይስ ፈረንጆቹ ፈራሽ መንግስት (Failed states) ብለው ከጠሯቸው ዝርዝር ውስጥ ያለውን ግምታቸውን በማጽናት ለመሸለም ፈልጋችሁ ነው፤ ይህንን ያደረጋችሁት።
መቼም ለኖቤል ሰላም መታጨትም ሆነ መሸለም ለእናንተ ሱሚ ነውና። ለመሆኑ ምን መልካም ቁመና፣ አለኝ ብለሽ ነው የተወዳደርሽው ብለው ጋዜጠኞች የጠየቋት አንዲት ሴት፤ ከቆንጆዎቹ ባልበልጥም እንኳን በአስቀያሚዎቹ ውድድር ላሸንፍ ብዬ ነው፤ አለች፤ አሉ።
ባለፈው ጽሑፌ ማመልከት እንደሞከርኩት፣ ይህች ሐገር፣ እናንተም እኛም ሣንፈጠር የነበረችና ወደፊትም የምትኖር የመንግስትነት ታሪኳም በሺህ የሚቆጠር ዓመታትን የዘለቀ ነው። እንደሰራናት እናፈርሳታለን፤ ይሉት ብሂልን ከደደቢት አስቀያሚ ዋሻ መዛግብታችሁ ውስጥ ካልሆነ የትም ቦታ አታገኙትም።
በቀደም “… የደበደባችሁትና አስራችሁ የገደላችሁት፣ በመብረቃዊ ምት በ45 ደቂቃ ድራሹን አጠፋነው” ያላችሁትን የሰሜን እዝን አካሄድ፣ እንዴት አያችሁት…? እንኳንም አያችሁት። አፈር አስገባነው ስትሉ አፈር ልሶ ተነስቶ መጥቶ፣ እናንተን ቀጥቅጦ ከያዛችሁት እርድ ውስጥ እየፈነቃቀለ አፈር ሲያስገባችሁ ምን አላችሁት።
ይህ ጦር፣ የኢትዮጵያ ተምሳሌት ጦር ነው፤ ይህ ጦር የሐገሬ ወድቆ መነሳት ምልክት ነው፤ ይህ የምድር ጦር የዛለ የሐገር ፍቅር ብርታት ማሳያ ነው። ኢትዮጵያ ወደቀች ሲሉ እየተነሳች፣ ደከመች ሲሉ እየበረታች፣ አለቀላት ስትባል እያንሰራራችና እየታደሰች እንደ እናንተ ዓይነቱ ፀረ-ሐገር ካንሰራዊ አስተሳሰብ ቆርጦ ሊጥላት ሲሞክር ህዳሴን እያገኘች የተጓዘች ታሪካዊት ሐገር ነች።
ጣሊያን በእዚሁ ምድር ላይ ደጋግሞ ገብቶ፣ በቅድም አያቶቻችን ብርቱ ትግል በግራካሶ፣ በመቀሌና በአድዋ የሽንፈት ጽዋን ጠጥቶ ከመመለሱ በፊት የናቀው፣ የጠላው፣ የተጣላው ከነዋሪው ህዝብና ባህል ጋር ነበረ።
ለዚህ ታሪክ ምስክር ነው። ያኔም ሲሞቱላት በወኔ ነበረ። በኋላም ከ40ዓመት በኋላ ተመልሶ ሲመጣ ከባዱ ውጊያ የገጠመው በዚያው መሬት ነበረ። ሁልጊዜ እሳት የማያጣው የነደደ አልበርድበት ያለ መሆኑ ከውጭ ወራሪዎች ጋር መሆኑ የአልበገር ባይነት ወኔው ግማድ ምልክት ነው።
ለዚህም ከቦረና እስከ ወላኢታ፣ ከጋምቤላ እስከ አሳይኢታ፤ ከደወሌ እስከ ሺኒሌ፤ ከሸዋ ምድር እስከ ጎንደር፤ ከወሎ እስከ መቀሌ የተጠራራው የወገን ሃይል ማይጨው ላይ ተሰብስቦ ነበር፤ በምድር ውጊያ ምድሪቱ ለጠላት እንዳትገዛ አድርጎ በኋላ በአየር ላይ የተበለጠው።
ይህንን ስለማታውቁት አይደለም፤ አሁን ማንሳቴ የአያት ቅድም አያቶቻችን ተጋድሎ ውጤት፣ ሐገርን ለማቆየት እንጂ ሐገር ለማጥፋትና መንግስት አልባ ሐገር ለማቆየት አልነበረም። እናንተ ግን “ሁሉንም ወይም ምንም” የተባለ መርህ አስቀምጣችሁ፤ ለእናንተ (ለዚህ ጥቂት ቁጥር ላለው አተራማሽ) ቡድናችሁ ፍላጎት እና ስግብግብነት ያልተመቸች ሐገር ትበታተን ብላችሁ ወሰናችሁ።
ነገር ግን የኢትዮጵያ አምላክ ወዴት ሄዶ? ታክቶት ለመናፈስ ወደ “ቫኬሽን” ሽርሽር የወጣ፤ መሰላችሁ ወይስ ያንቀላፋ ? ጠባቂ አምላኳ ምንጊዜም ሙሴ ማውጣት፣ ብርቱ ደቀ-መዝሙር መስራት አይታክተውም እና ጣልናቸው፤ አበቃላቸው፣ አወደምናቸው ያላችኋቸው ብርቱዎች ተነስተው ወደመቃብራችሁ አፋጥነዋችኋል።
እናንተ ሰው በቁም ትቀብሩ እንደነበረ፣ የራሳችሁ ድርሳናት ምስክሮች ናቸው፤ እናንተ ያለፍርድ ወይም በ“ Kangaroo Court” የይስሙላ ፍርድ ሸንጎ ስንታ-ስንት የሀገር ልጅ ማጥፋታችሁ የተገለጠ ሐቅ ነው።
ከወራት በፊት እንኳን በተቃዋሚዎቻችሁ ላይ ስለወሰዳችኋቸው ገራርና መራር፣ እርምጃዎች እስቲ ጥቂት እንነጋገር፤ ካለ፣ ከአንድ የዩ-ቲዩብ ጠያቂ፣ ላቀረበላቸው ጥያቄ፣ አቦይ ስብሐት ፣ “ለጋራ ግንባር የጠራችኋቸውን የ“ግንባር ገድሊ ትግራይ”ን ታጋዮች ከመግደል በመለስ ማሰርና መበተን ስትችሉ፣ ለምን እንዲያ አደረጋችሁባቸው?” ተብለው ሲጠየቁ ሰውየው፣ ፈርጠም ብለው የመለሱት ፤ “ጠላት እኮ ናቸው፤ ጠላትህን ደግሞ ያለምስክር እዚያው ጭጭ ታደርገዋለህ እንጂ ጊዜ አትሰጠውም፤” ሲሉ ነው፤ የተናገሩት።
ግፍና ግድያ የኖራችሁበት፣ ዛሬም ያለጸጸት የምትኮሩበት፣ ከሰብዓዊነት ያፈነገጠው ማንነታችሁ ነጸብራቅ ሆኖ ነው፤ የታየኝ። ይህ ለሁሉም ባለህሊና ሰው እንዲህ ይመስለኛል።
እንዲህ ያለውን የጭካኔ እርምጃ ወስዶ ደግሞ ለመኩራራት ከጎማ የተሰራ ህሊናና ከብረት የደደረ ልብ ያስፈልጋል። ይሄ ደግሞ እናንተ ዘንድ በሽበሽ ነው። ዛሬ ደግሞ ለእናንተ ጊዜ ተሰጥቷችሁ “እጅዎን በሰላም ይስጡና በፍትሕ አደባባይ ይቅረቡ” ተብላችኋል። በሌላው ላይ ከሚጨክን እጅ፣ ወደ ህግ እጅ መምጣት የሚያዋጣ ነው።
ፍርሐታችሁን ዋጥ አድርጋችሁ፣ ለእውነት አንዴ ጨከን በሉ፤ ለእውነት እንደመጨከን ያለ ትልቅነት ደግሞ የለም። ይዋል ይደር እንጂ እጅ መስጠታችሁ አይቀርም፤ ወይም ከየዋሁ የኢትዮጵያ ህዝብና ከሰራዊቱ አታመልጡም።
የማይካድራው ገርሞን ሳናበቃ በሁመራ ሲቪሎች፣ ላይ ተመሳሳይ ጭካኔ የተሞላው ጥቃትና ሰለባ በመፍጠር፣ ከሰባ በላይ የጅምላ ጉድጓዶች፣ መገኘት የፍጥረታችሁን እንግዳነት አጉልቶ ያወጣ፣ ከአንድ ክር የተፈተላችሁ እንስሳዊ ባህሪያችሁ ከሰብዓዊነት ይልቅ በብዙ እጥፍ የገነነባችሁ የሐገር እርግማኖች መሆናችሁን ያሳየ ነው።
እኔ የምለው፣ ይህች ሐገር፣ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ካሳለፈችው የደም አበላ ጉዞ ውስጥ ካለፈው መማር የምትችሉበት ሰፊ እድል ያላችሁ እናንተ፣ በ1967 ዓ.ም በቆማችሁበት ነጥብ ላይ ተቸንክራችሁ የቀራችሁበት ምክንያት ምንድነው? የማይደግፈኝ ሁሉ ጠላቴ ነው፤ የማይመቸኝ ሁሉ መጥፋት አለበት ማለት ልበ-ስውርነት እንጂ ሌላ ምን ስም ይሰጠዋል። ምክንያቱም ሁልጊዜ፣ ምናልባትም ለእናንተ ዘላለም በአጥፊነት እንዘልቃለን ብላችሁ ከሆነ እንደማትችሉ ማወቅ አለባችሁ።
መቼም ፖለቲካ ደም ካልፈሰሰበት፣ ፖለቲካ ማሳደድ ከሌለበት፣ ፖለቲካ ማኮላሸት ከሌለበት፣ ፖለቲካ ደብዛ ማጥፋትና ለፍለጋ አብሮ መውጣት ከሌለበት አያስኬድም፤ አትሉንም። እናንተና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ ቡድኖችን፣ የመላእክት ስብስቦች ናችሁ ብዬ በየዋህነት እየጠየቅኳችሁ አይደለም። ፖለቲካ መጠላለፍና መዘላለፍ ሊኖርበት መወነጃጀልና መካካድ ሊታይበት ይችላል።
ይህ በሰለጠኑት ሐገራት ጭምር የሚታይ እውነት ነው፤ ነገር ግን እንዲህ እንደ እናንተ በማጥፋት መደርጀት፣ ደም በማፍሰስ የደም ገንቦ መምሰል ግን የትም የለም። የወገኖቻችንን ደም አፍስሳችሁ አፍስሳችሁ አልጠነፍፍ ያለውን ደም ማድረቅ ሲገባችሁ ትኩስ ደም ፍለጋ በስተርጅና መናወዝን ግን ምን የሚሉት አባዜ ነው፤ ያሰኛል።
የሶቪየቱ መሪ ጆሴፍ ስታሊን (ዘመዳችሁ ሳይሆን አይቀርም)፣ የሞስኮ ከተማ ኮሚኒስት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ የነበረው ኪሮቭን በስብሰባ ላይ፣ በሐሳብ ሳይግባቡ የእለቱ አጀንዳ ይቋጫል። በዚህ ክፉኛ የተቆጣውና ጨካኙ ስታሊን የደህንነት ኃላፊውን “ያጎዳን“ ይጠራውና፤ ኪሮቭን እንዲገድል ያዘዋል።
እንደወትሮው ትእዛዙን የሚፈጽመው ያጎዳም፣ ኪሮቭ ለሌላ ስራ ከከተማ ሲወጣ ከመኪና የተገለበጠ አስመስሎ እንዲሞት ያደርገዋል፤ በቀብሩ ላይም ተገኝቶ ስታሊን ጥሩ ጓዳዊ ንግግር ያደርጋል። ይህ ቀን እንደማንኛውም ቀን ሰኞ ማክሰኞ ሆኖ አለፈ።
ከሁለት ወራት በኋላም ያጎዳን ይጠራውና እንትናንም እንዲሁ አጥፋው፤ ካለው በኋላ ኪሮቭንም መምታት እንዳትረሣ ሲለው፣ ባለፈው ጊዜ እርምጃ ወስጄ አንተም ቀብሩ ላይ ተገኝተህ ነበረ እኮ፤ ጓድ ስታሊን፤ ብሎ ሲያስታውሰው “እንደገና ግደለው” ሲል ነው ትእዛዝ የሰጠው። ገድለው እንደገና የሚገድሉ፣ አጥፍተው እንደገና ማጥፋት ሱሳቸው የሆኑ ሰዎች ፍጻሜያቸው አሳዛኝ ነው።
ስታሊንም እንዲሁ ነው፤ የሆነው። ማን ምን እንዳደረገው ባይታወቅም ሶቪየት ህብረት ግን በአንድ ማለዳ ላይ ጠረጴዛው ላይ ድፍት ያለና በደም አበላ የተነከረ ዮሴፍ ስታሊንን ቢሮው ውስጥ አገኘች። ወዲያው የደህንነት አማካሪውና የግድያ ክንዱ ያጎዳ መጥቶ ጤነኛ ሰው ከሰላሳ ደቂቃ በፊት ጥዬ ወጥቼ ስመለስ እንዴት ሞተ ትሉኛላችሁ ብሎ ሲገስል፤ “ደም ብዛት!” አሉትና፣ አንተም ደም ብዛት ሳይይዝህ አይ ላይመለስ ሸኙት። የክፉዎች ፍጻሜ አያምርም። እናንተ ግን፣ ፍጻሜያችሁን አሳምሩ።
የእልህኛነታችሁ ጥግ ራስን ብቻ ከማየት የሚመነጭ ስግብግብነት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። በ1987 ዓ.ም አንድ በአካባቢያችን በህይወት ይኖሩ የነበሩ፣ የምናውቃቸው የተከበሩ አዛውንትን (ሰላማዊ እረፍት ይሁንላቸውና) “ጋሼ በላይ ” አልኳቸው ፤ (ስማቸው የተለወጠ)፣ “አሁን እንግዲህ ጦርነቱ አብቅቷል ፤ ስልጣን የያዙት የእናንተው ልጆች ናቸው፤ እርስዎ ደግሞ ነጋዴ ነዎት እና በዚህም በዚያም ብለው ንግድዎን ማስፋፋት ነው፤” አልኳቸው።
የለኮሱትን አዲስ ሲጋራ መኮስተሪያው ላይ አስቀምጠው፣ “መምህር ባለጊዜ ሁን እያልከኝ ነው?” አሉና፤ “ስማ የሰሜንን ሰው ጠባይ ጠንቅቄ አውቀዋለሁ፤ ወደላይ በደረጃ ድንገት ከፍ ከፍ ሲል፤ በሚስት ላይ ሌላ ሚስት ፣ በማኪና ላይ ሌላ ማኪና (እንደ አነጋገራቸው መጻፌ ነው) በሐብት ላይ ሌላ ሐብት መጨመር ይፈልጋል። ግን አሉኝ፤ ይህ በአግባቡ ሲሆን መልካም ነው፤ ነገር ግን … በጥድፊያና በስግብግብነት ሲፈፀም ግን አደገኛ ነው። በሚቀጥለው አስር ዓመት ውስጥ ዘመዶቼን ካየህ በኋላ፣ ቃሌን ታዘብ፤ እንዲያውም አምስት ዓመት ይበቃል፤” አሉኝ ።
«እንዴት እንዲህ አሉ፤ ጋሼ »
“የእኔ ዘመዶች አሉ፤ …የእኔ ዘመዶች ይሉኝታ ቢሶች፣ ስግብግቦችና ጨካኞች ናቸው። በተለይ ሁኔታው የፈቀደ ከመሰላቸው ምንም ዓይነት ግፍ ከመፈፀም ወደኋላ አይሉም፤ ታየዋለህ፤” አሉና አዲስ ሲጋራ ለኮሱ።
1993 ዓ.ም ላይ በህወሓት ውስጥ “ሕንፍሽፍሽ” (ክፍፍል)፣ ሲነሳ 17 ለ13 ድምጽ የተሸነፈው ወገን፣ ለድርጅታችን ህልውና ስንል፣ ህግ ማፍረስ ልንገደድ ነው፤ ብሎ (ብዙ ድምጽ ማግኘት አፈር ድሜ በላ) በይሉኝታ ቢስነት ከ17 ድምጽ ሁለቱን በማስኮብለል 15 ያህሉን አባላት ለእስር፣ ለስደት፣ ለእንግልትና ከስራ በማፈናቀል ጭምር ጭካኔውን አሳየ። ከጫካው ጊዜ የሚለየው ግድያ አለመፈፀሙ ብቻ ነው።
ከዚያም በአስረኛው ዓመት ላይ ማለትም በ1997 ዓ.ም የሆነውን ሁላችንም ስለምናውቅ ደግሜ አልተነትነውም ። ግን ይሉኝታ ቢስነት፣ ጭካኔና ስግብግብነት አካል ገዝተው ግዘፍ ነስተው፤ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ተንሰራፉ።
የእርዳታ ድርጅታችን ነው፤ የተባለው “ትእምት” ተብሎ የተመሰረተው ኩባንያቸው በውስጡ ያቀፋቸው 30 ምናምን ድርጅቶች ሁሉ የሚያፈሩት ሐብት እጅግ ጥቂት ለሆኑት ስራ አስፈጻሚዎች ከፍም ሲል ለአንድ ሰው ጥቅምና ስርወ-ቤተሰብ ትሩፋቱን የሚያፈስስ የአውራ ስግብግብ ንብረት መሆኑ ታወቀ።
ከደም ደግሞ ወደ ደመወዝ ብናልፍ እንዲሁ ሆናችሁ ነው፤ የተገኛችሁት። አሁን በቀደም ለትግራይ ባንኮች በመንግስት የተላከውን 1.3 ቢሊዮን ብር ቅርምቻ ወደጎን ትተን፣ ሱዳን ላይ፣ የሱዳን ጉምሩክ በፍተሻው፣ “የሣምሪ” (ኢንተርሐምዌይ ማለት ይሻለናል)፤ የሚሊሻ አለቃ የሆነ ሰው፣ ሲያዝ በኢትዮጵያ ሲመነዘር ወደአራት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ዘጠና ሚሊዮን ዶላር በእጁ ላይ የመገኘቱን ዜና ስሰማ ወደልቤ ወዲያው የመጣው የሁለት ታላላቅ ከተሞች (ድሬዳዋና ሀዋሳ) የዓመት የሥራ ማስኬጃና ደመወዝ በጀት፣ ወይም የ20 ሁሉን ያሟሉ የአዳዲስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታና ቁሳቁስ ማሟያ፣ ወይም ከሞጆ ሐዋሳ የፈጣን አስፋልት ስራ መንገድ ማሰሪያ የሚያህል ገንዘብ በአንድ ስግብግብ ሽፍታ እጅ መያዙ አስገርሞኛል።
እጅግ ተገርሜ፣ ለመሆኑ ይህችን ሐገር ደሃ ናት፤ የምትሉ ሰዎች እውነት ኢትዮጵያ ደሃ ናትን? ብዬ መጠየቄ አልቀረም። ይህንን ሁሉ ዘርፈውን ይህንን ሁሉ አድርገውን፣ ህዝቡም ከ110 ሚሊዮን አለመጉደሉ፣ እኛም በልተን ማደራችን ድንቅ ነው፤ የሆነብኝ፤ ስለዚህም ድሃ አይደለንም፤ እላለሁ።
የሆነው ሆነና መንግስት እንደተለመደው በሆደ ሰፊነት እጃችሁን እንድትሰጡ፣ ከሶስት ሰባ ሁለት ሰዓት የጊዜ ገደብ የበለጠ ቀናትን በጥንቃቄ ጨምሮ እያያችሁ ነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብም በየበዓቱ ሆኖ እየታዘበ፤ ነው።
ለመሆኑ ጉድጓዱ ከዚህ እስከ የት ይደርስ ይሆን? ቀጥለናል ያላችሁት ትግል የትግራይን ህዝብ ነው የግብጽን ህዝብ ያካተተ ነው? መቼም አሁን ለዚህ መሰል ጥያቄ መልስ ለመስጠት የምትችሉበት ቦታ እና ጊዜ ላይ ባትሆኑም ታሪክና ጊዜ መልሱን ይሰጠናል። ቸር ከርመን፣ እናንተንም በአምባር አጊጣችሁ ያሳየናል፤ ብለን እናምናለን። እባካችሁ መብሰላችሁ ላይቀር ማገዶ አታስፈጁ።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 20/2013