በእምነት
አዎ ብልጥ ሰው የሌላውን ውድቀት አይቶና ተረድቶ” አሃ “ ይህ ነገር እኔም ቤት እንዳይመጣ በማለት ትምህርት ይወስዳል፤ ሞኝ ግን እራሱ ላይ ካልደረሰ ለመማር ያለው ተነሳሽነት እጅግ የወደቀ ነው።
እንዲሁ ስታዘብ እኛ ሞኝ ነን ብልጥ እላለሁ፤ ምክንያቱም ሞኝ ሆነን እንኳን ከራሳችን አልተማርን፤ ብልጥ ሆነን ደግሞ መጥፎ ነገሮችን ቀድሞ በመረዳት እንዳይደርሱብን አላደረግን ይገርማል።
አገር ይሉትን ታላቅ ነገር ህዝብን ያህል ክቡር ፍጡር እንዲሁ በከንቱ ህይወቱ ሲያልፍ እያየን እየሰማን እኮ ነው፤ ይህ ደግሞ ለእኔ የሞኝነታችን ውጤት ይመስለኛል።በዓለማችን ላይ በመጣብን ኮሮና ቫይረስ ይሉት መዓት ተወጥረን ራሳችንን መጠበቅና መጠንቀቅ ስንችል በየቀኑ እየሞትን ነው።አዎ እየታመምን እየሞትን ለአገርና ለወገን ሸክም እያበዛን ነው።
የዛሬ ስምንት ወር ገደማ ማለትም በሽታው ወደአገራችን ገባ ሲባል ሁላችንም ደነገጥን። እንደ መዓትም ፈራነው። አብዝተንም ተጠነቀቅን።የምንችልም ቤታችን ለመቀመጥ ወሰንን።ይህ በሆነበት አገር ላይ የዛሬው መዘናጋትና በሽታውን ችላ ማለት ከምን የመጣ እንደሆነ ለመገመት ይከብዳል።
ዛሬ ሁሉም ነገር ተቀይሯል በሽታው ሲባባስ እኛ ደግሞ እኔን አይነካኝም።እስኪ ይሞክረኝ አይነት ፈሊጥ እየተጠቀምን ደረታችንን ነፍተን ወደራሳችን እየጠራነው ነው።ይህንን ተከትሎም ብዙ ወገናችን እየታመመ እየሞተ አሁን ደግሞ ይባስ ብሎም የሚታከምበት ቦታ እያጣ ስለመምጣቱ እየተነገረ ነው።
አዎ የእኛ በሽታውን መናቅ ይበለን ቢያስብለም በዚህን ፍጥነት እየጨመረ ከሄደ ግን አገር ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ እጅግ ያስፈራል።
ሰዎች ድግስ ደግሰው አብረው እየበሉ እየጠጡ ነው፤ በመንገድ ላይ ሰላምታው ተቃቅፎ መሄዱ እንደወትሮው ቀጥሏል፣ ሀዘን ቤት ቁጭ ብሎ ማስተዛዘኑ፣ ለቀብር ንቅል ብሎ መሄዱ ሁሉም አሉ። ከነእዚህ አንጻር ኮሮና ምሮናል ያስብላል።ግን ግን ለእኔ ኮሮና አልማረንም አይምረንም ።ምናልባት ጊዜ እየጠበቀልንም እንዳይሆን እሰጋለሁ።
በአንዱ እሁድ ቀን የዘመድ ድግስ ተጠርቼ ሄድኩ፤ ድግሱ ትልቅ የሚባል ነበርና ድንኳን ተደኩኖ ሙዚቃ ተከፍቶ ሰው እየበላ እየጠጣ ይዝናናል።ህጻናት አዋቂው ድግሱን በሚገባ ታድመዋል።
በዚህ መካከል ግን አንድም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ ) ጣል ያደረገ ወንድም ይሁን ሴት ወጣት ይሁን አዛውንት አለማየቴ በጣም አስገረመኝ ።ከደጋሾቹ የእኛ የታዳሚዎች መዘናጋት ይገርማል አገሬ እግዜር ይሁንሽ አልኩ።
ህዝቡ በዚህን ያህል ደረጃ ለመዘናጋቱ የመንግስትም እጅ አለበት ባይ ነኝ።እንዴት ቢባል፤ ኮሮና ገባ በተባለበት ወቅት ስብሰባዎች ሁሉ በበይነ መረብ ሆነው ነበር፤ በተቋማት በር ላይ ሰዎች እጃቸውን እንዲታጠቡ፣ ሙቀታቸውን እንዲለኩም ጥረቶች እየተደረጉም ነበር፣ መገናኛ ብዙሀኑም በተደጋጋሚ የህዝቡን ንቃተ ህሊና ሊያጎለብቱ የሚችሉ ዜናዎችና ፕሮግራሞች በመስራትም ወደር አልተገኘላቸውም ነበር፣ ዛሬ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ለመቀዛቀዛቸው ምንድን ነው ምክንያቱ? እነዚህ ሁኔታዎችስ መቀዛቀዛቸው አይደለም የችግሩ መንስኤ? ለእኔ እንደዛ ነው።
አገራችን ከኮሮና በኋላ በርካታ ፈተናዎች ተጋርጠውባት እነሱን ለማለፍ ብዙ ትግል ያደረገችበት ወቅት ነው።ይህም ቢሆን ግን ሁሉም ጦርነት ላይ አልነበረም፤ ሁሉም ፖለቲከኛም አይደለም ፤ በመሆኑም በተዋረድ ሀላፊነትን መወጣት ይገባ ነበር።
ሌላው ከሰሞኑ በቴሌቪዥን ዜና ስመለከት በጣም የገረመኝ ነገር ሁለት ትልልቅ የመንግስት ተቋማት የስራ ሃላፊዎች በመካከላቸው የስራ ስምምነት እየተፈራረሙ ነው፤ ከዛ ፊርማውን ሲለዋወጡ ይጨባበጣሉ፤ ምናልባት እነሱም አስበውት ላይሆን ይችላል ግን ደግሞ ለሚመለከታቸው የህብረተሰብ ክፍል መልዕክቱ ምንድን ነው? ለእኔ ኮሮና የለም እንደልባችሁ ተጨባበጡ ተቃቀፉ ማለት ሆኖብኛል።
ኸረ ባለስልጣናትም የምትሰሩትን የምታደርጉትን እያንዳንዱን ነገር ሌላው ላይ ምን መልዕክት ይኖረዋል የሚለውን አስቡበት።ይህ ካልሆነ ግን በዚህ ድህነታችን ላይ ኮሮና ከተባባሰ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመቱን ለእናነት እተወዋለሁ።በእኔ በኩል ግን ሞኝ እንኳን ሆነን ከሌሎች ችግር እንማር እላለሁ።
በስልጣኔ ቀዳሚ፣ በህክምና ቴክኖሎጂና በግብዓት ሙሉ የሆኑት አውሮፓና አሜሪካን በዚህ ክፉ ቫይረስ ፍዳቸውን ሲበሉ እያየን የእኛ በዚህ ልክ መዘናጋት ለጉዳዩ ጆሮ አለመስጠት የሚገርም ብቻ ሳይሆን የሚያናድድ ከማናደድም አልፎ ሰው ስለራሱ እንኳን ቢቀር ለሚወዳቸውና ለአገሩ አያስብም የሚያስብል ነው።
አሁን እንደ ቀድሞ እየኖርን ነው፤ ሰርግ፣ ማህበር፣ ልደትና ተስካር እረ ምኑ ቅጡ ሁሉንም ማህበራዊ ህይወቶቻችንን እንደ አዲስ “በአዲስ መልክ እንደሚባለው” ጀምረናል፤ ምናልባት እንደ ኢትዮጵያዊ ከእነዚህ ነገሮች ተነጥሎ መኖር ሊከብደን ይችል ይሆናል ግን በቦታው ላይ ስንገኝ እንኳን የጤና ሚኒስቴርም ሆነ የአለም ጤና ድርጅት የሚያዙትን የጥንቃቄ መንገዶች ብንተገብረው ምንድነው ችግሩ? እኔን አይነካኝም ብሎ ማለቱስ የት ያደርሳል? ቤታችን እስኪገባ ራሳችንን ወይም የምንወዳቸውን እስኪያሳጣን፤ ግዴለም ሞኝ እንኳን ሆነን እራሳችንን እንጠብቅ።
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ሰሞኑን በየዕለቱ ከ ሶስት መቶ በላይ የኮቪድ ታማሚዎች ወደ ጽኑ ህክምና እንደሚገቡና ከእነዚህም እስከ 50 የሚደርሱት የመተንፈሻ አካልን የሚረዳ ማሽን እንደሚያስፈልጋቸውም ተናግርዋል።
ይህ እንግዲህ እንደእኛ አገር አቅምና ነባራዊ ሁኔታ ኮሮና ወደ አገር ገባ ሲባል የደነገጥነውን ያህል እንኳን ባይሆን ሊያስደነግጠን በተገባ ነበር ሁኔታው ግን የተገላቢጦሽ ሆነ፤ ኸረ አንዳንዱ እንደውም ይህንን እየሰማ ኮሮና የለም “ፖለቲካ ነው” የሚል አለ፤ ግርም እኮ ነው የሚለው በራሳችን ስንቀልድ፤ እኔማ የለም የሚሉትን ስሰማ “እንደ አፋችሁ ያድርግልን “ ነው የምለው፤ ምን ይባላል ሌላ።
ጤና ሚኒስቴር ይህንን የበሽታውን መስፋፋት ተከትሎ ለስድስት ወራት የሚቆይ ኮቪድ 19ኝን የመከላከል ንቅናቄ ሊያካሂድ መሆኑን በዚሁ ቃለ ምልልስ ላይ አስታውቋል፡፡ ንቅናቄው ጥሩ ነው፤ ግን ደግሞ የሆነ ችግሩ የከፋ ሲመስለን ብቻ እየተነሳን ንቅናቄ ከማለት ይልቅ መጀመሪያ በያዝነው ልክ መሄዱ ስለሚያዋጣ አሁንም በንቅናቄው የሆነች ብልጭታ ውጤት ስትገኝ ወደመተው እንዳንሄድ እፈራለሁ።
“ከዚህ በፊት በሽታው የሚገኘው በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ነበር፤ አሁን ላይ ግን ከ900 በላይ በሚሆኑ ወረዳዎች ላይ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች እየተገኙ ነው። ከዚህ በፊት ከተመረመረው ከሶስት እስከ አራት በመቶ ብቻ ቫይረሱ የሚገኝባቸው ነበሩ፤ አሁን ግን ከ10 እስከ 15 በመቶ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከ30 እስከ 40 በመቶ እየተገኘ ነው “። ይህ ነው እንግዲህ ያለንበት ሁኔታ! እናም ወገኖቼ እራሳችንን ከሞት እንታደግ? አበቃሁ።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 20/2013