ዳግም ከበደ
በሀገራችን የሥነ ጥበብ ትምህርት ታሪክ ቀድመው የሚጠቀሱት አለ ፈለገሰላም ኅሩይ ናቸው። ዘመኑም በ1951ዓ.ም።በወቅቱ ውጭ ሀገር ተምረው የሚመለሱ ምሩቃን ንጉሱን እጅ መነሳት ይጠበቅባቸዋል። እጅ ሲነሱም መሻታቸውን እንዲናገሩ እድል ይሰጣቸዋል። እናም አለ ፈለገሰላም መሻታቸውን ‹‹በአገራችን የሥዕል ትምህርት ቤት እንዲከፈትና የኔም ተግባር በሚከፈተው የሥዕል ትምህርት ቤት ማስተማር እንዲሆን እፈልጋለሁ››ሲሉ አቅርበዋል።
በወቅቱ በትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ቢመደቡም ትምህርት ቤቱን የመክፈት ርዕያቸውን ለመጀመር የመንግሥትን ውሳኔ አልጠበቁም። የትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተር በነበሩት አቶ ከበደ ሚካኤል እገዛና ድጋፍ ማስተማሩን ተያያዙት። ካስተማሩዋቸው ተማሪዎች የተሻሉትን ስራዎች በመምረጥ በተዘጋጀው ዐውደ ርዕይ ትምህርት ቤት የመመሥረት ርዕያቸው ዕውን የሚሆንበት አጋጣሚ ተፈጠረላቸው።
ለዐውደ ርዕዩ ታዳሚዎች ባደረጉት ንግግር ‹‹በአገራችን የሥነ ጥበብ ተግባር ብዙ ነበር፤ የአክሱም ሐውልቶችን ያነፁ፣ ላሊበላን የቀረፁ፣ በጎንደርና ጎጃም ሥዕልን የሠሩ አሁን የሉም፤ ብቅ አላሉም፤ በኛ ጊዜ መጥፋት የለባቸውም፤ ነፍስ እንዲዘሩ መደረግ አለበት። ወደ ነበርንበት ትልቅ ተግባር በዓላማ መጓዝ አለብን፤›› በማለት ጥሪ አቀረቡ።
በዐውደ ርዕዩ ከቀረቡት ሥዕሎች ብዙዎቹ ተሸጡላቸው።‹‹በራሴ ጥረት ይችህን ገንዘብ አግኝቻለሁ፤ ተማሪ ቤት ይስሩልን›› በማለት ንጉሱን በመጠየቃቸው ሐምሌ 16 ቀን 1950 ዓ.ም. ትምህርት ቤቱ ተመርቆ ተከፈተ። ንጉሱም ያስገነዘቡት ዐቢይ ነጥብ፣ ‹‹በሥነ ጥበብ ታላቅ ሙያ ያላቸው ወጣቶች ሁሉ ጥንታዊውን አሠራር ሳይለቁ ከዘመናዊው ጋር እያዋሐዱ እንዲሄዱ››የሚለው ነበር። ሃሳባቸውም ይሄው ነበርና እስከ ህልፈተ ህይወታቸው ደረስ ቃላቸውን ጠብቀው ሰሩ። በርግጥም ታሪክን፣ ባህልን እንዲሁም ስልጣኔን ለማስቀጠል ከተፈለገ የስነጥበብ ትምህርት ቤቶች ሚና ተወዳዳሪ እንደማይገኝለት ልብ ይሏል።
ይህ ታሪክ ከተፈጠረ ከ45ዓመታት በኋላ ዓላማውን አንድ ያመሳሰለ የስነጥበብ ትምህርት ቤት በ1995ዓ.ም ተመሰረተ በአዲስ አበባ ተመሰረተ።
ወደ እዚህ ትምህርት ቤት ግቢ ሲዘልቁ ጥበብ እየተሸመነበት ለመሆኑ ጠያቂ አያስፈልግዎትም።ለ18 ዓመታት በኪራይ የተያዘው ግቢ የወጣቶች መዝናኛ ማዕከል ይመስላል። የሙዚቃ ተማሪዎች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ይቀልጻሉ፤ የስዕል ተማሪዎች ደግሞ ካንቫሳቸው ላይ አፍጥጠው በቀለም ይተነፍሳሉ፤ የውዝዋዜ ተማሪዎቹም እስከ ላንቃው በተለቀቀው ሙዚቃ ይውረገረጋሉ፤ ይጨፍራሉ፤ ለግላጋዎቹ ቆነጃጅትም ሰበር ሰካ እያሉ አረማመዳቸውን ያሰማመራሉ።ውስጣዊና ውጫዊ ውበታቸው ጎልቶ እንዲወጣ ባለባበስና ባረማመድ ሳይንስ ተፈጥሯዊ ውበታቸውን ይገራሉ። በርግጥም ግቢው ቤተ-ውበትና ቤተ-ጥበብ እንደሆነ ክዋኔዎቹ መስካሪዎች ናቸው።
አቢሲኒያ የስነ ጥበብና የሞዴሊንግ ማሰልጠኛ ተቋም ይሰኛል። የምስረታ አላማው የስነጥበብ ፍላጎት ኖሯቸው ወደ መደበኛው የስነጥበብ ትምህርት ቤቶች ለመግባት ያልቻሉ፤ ተሰጥኦዋቸውን ማውጣት እድል ያላገኙ ወጣቶች፤ የአጫጭር ስልጠና ወስደው ወደ ሙያው እንዲገቡ እድል መፍጠር ታስቦ የተቋቋመ ቤተ ጥበብ ነው።
አቢሲኒያ የስነጥበብ እና የሞዴሊንግ ማሰልጠኛ ተቋም በ18 ዓመታት ቆይታው በንድፍና ቀለም ቅብ፣በቅርጻቅርጽ፣ በቴአትር፣ በባህላዊ ሙዚቃ መሳሪያዎች ክራርና መሰንቆ፣ በዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች በጊታርና በኪቦርድ፤ በድምጽ አወጣጥ፣ በባህላዊ ውዝዋዜ፣ በዘመናዊ ዳንስ እና በሞዴሊንግ በመደበኛና በአጫጭር ኮርሶች ተሰጥኦ ያላቸውንና ትምህርት ሚኒስቴር በሚያወጣው መቁረጫ ነጥብ መሰረት ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል።
በእስካሁኑ ጉዞ ከአስር ሺ በላይ ጠቢባን ወደ ሙያው እንዲቀላቀሉ ምክንያት ሆኗል። የጥበብ ተሰጥኦ ኖሯቸው መክፈል የማይችሉት አይጨከንባቸውም። በነጻ እንዲማሩ እድል ይሰጣቸዋል። በያዝነው ዓመት ብቻ ከ30 በላይ በነጻ የሚማሩ ወጣቶችን ተቀብሏል።
ተቋሙ በስእል ውበት የጀመረውን ትምህርት በሞዴሊንግ ዘርፍ በማስተማር አጠናክሮታል። የሞዴሊንግ ሙያ በርካታ ዘርፎች አሉት። ተፈጥሯዊ ስጦታን ተመልካችን በሚስብ መልኩ አድምቆ ማሳየት አንዱ ነው።
በሀገራችን የሞዴሊንግ ትምህርት በዘመናዊ መንገድ መሰጠት ከጀመረ ረጅም ጊዜ ባያስቆጥርም ጥቂት የማይባሉ ሞዴሎች በራሳቸው ጥረት ወደ እውቅናው ማማ ላይ ወጥተዋል።በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገራቸውን ስም እስከ ማስጠራት የደረሱም አሉ
በአቢሲኒያ ስነጥበብ ትምህርት ቤት ተምረው በተለያዩ ፊልሞችና ማስታወቂያዎች ላይ የምናያቸውም ብዙ ናቸው።
የሥነጥበብና የሞዴሊንግ ትምህርቶች ከማስተማሪያ ባለፈ ለመለማመጃ ሰፋ ያለቦታ ይፈልጋሉ።ይሁን እንጂ በግለሰብ ቤት ተከራይቶ ትምህርት መስጠት ስራውን አስቸጋሪ አድርጎታል። የኪራይ ዋጋ በየጊዜው መጨመርን ተቋቁሞ ትምህርቱን ማስቀጠሉ ፈታኝ እንደሚሆን አይካድም። እዚህ ላይ ነው የመንግስት ድጋፍ ወሳኝ የሚሆነው። በተለይም ቦታ ከሊዝ ነጻ የሚያገኙበት፣ወይም ደግሞ በቅርስነት የተመዘገቡ ቦታዎችን ይዘታቸውን ሳይለቁ ታድሰው እንዲጠቀሙበት ቢደረግ ዘርፉን ለማገዝ ያስችላል።
“ለአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ቅርስ የሆኑ ቤቶችን ባሉበት ሁኔታ አድሶ ለመጠቀም ጥያቄ አቅርበን ነበር።ብዙ ተመላልሰን ነበር፤ የመጣ ውጤት ግን የለም። አሁንም ሳንሰለች ጥያቄያችንን እያቀረብን ነው።”የሚሉት ወይዘሮ ገነት የሚጠብቁትን ምላሽ እንዳላገኙ ያመለክታሉ።
እንደሚታወቀው ስነ ጥበባት የአካባቢውን ማህበረሰብ አስተሳሰብ በማልማት ረገድ ያላቸውን ሚና ከምንም ነገር ጋር አይነጻጸርም። ይሁን እንጅ በታዳጊ ሀገራት በሚጠበቀው ልክ ሚናቸውን ተወጥተዋል ለማለት በሚያስደፍርበት ደረጃ ላይ ግን እይደሉም። እንደ አሜሪካ ባሉት ያደጉ ሀገራት ለትርፍ ያልተቋቋመና የኪነጥበብ ዘርፉን የሚደግፍ ኢንሸቲቭ አላቸው።
ተቋማቱ የሙያ ድጋፍ ከመስጠት ባለፈ፤ የግሉን ዘርፍ ከመንግስት የጥበብ ተቋማት ጋር ያስተሳስራሉ።ከያኔዎችን በማበረታታት የፈጠራ ስራ ሀሳባቸውን ለልማት እንዲውሉ ያነሳሳሉ፣ የስነጥበብ ተቋማትን ያግዛሉያስፋፋሉ፤ ፈጠራዎች በኢንዱስትሪ ዘርፎች እንዲታገዙ ያደርጋሉ።
መንግስት ስነ ጥበብን መደገፍ እንዳለበት ሁሉም አስተሳሰቦች የሚስማሙበት ቢሆንም በሀገራችን ያለው እውነት ግን ከዚህ የተለየ ነው።መንግስት ከስነጥበብ የሚጠብቀው ለሁለንተናዊ ልማት ላይ በሚኖረው አስተሳሰብ በመንግስት መዋቅር የወጣ አይደለም። በበጀት ከሚደግፋቸውና በመንግስት ስር ከሚተዳደሩት የስነጥበብ ትምህርት ቤቶች ውጭ በግል የሚንቀሳቀሱትን የሚደግፍበት አሰራር የለውም።
በራሱ ጥረት ሚናውን ለመወጣት የሚተጋው አቢሲኒያ የስነጥበብ ትምህርት ቤት ኮቪድ የፈጠረውን ተጽእኖ ተቋቁሞ ከ7 ወራት በኋላ ዳግም ወደስራ ተመልሷል። በዚህ ውጣ ውረድ ውስጥ የሚያበረታው ነገር የተማሪዎቹ ስኬት መሆኑን የሚያስታውሱት ወይዘሮ ገነት፤ “ከኛ ትምህርት ቤት ተመርቀው ትምህርታቸውን ቀጥለው እስከ ዩኒቨርሲቲ የገቡና መምህር የሆኑም አሉ። ቴአትር ቤቶች የተቀጠሩ፤ በሞዴሊንግ ሰልጥነው ፊልሞች ላይ በመሳተፍ እውቅናን አትርፈዋል። ሙዚቀኞቹም የራሳቸውን ሙዚቃ ሰርተው ሰናገኛቸው እርካታችን እሱ ነው።››ሲሉ ያብራራሉ።
የተሻለ ቦታና ድጋፍ ብናገኝ ከዚህ በላይ መስራት እንደምንችል አረጋግጠናል ያሉት ወይዘሮ ገነት፣ ከአልባሌ ቦታ ርቀው በስነምግባር ጎልብተው እርስ በርሳቸው እየተዝናኑ የሚማሩበት ቦታ በመሆኑ እጅግ በጣም ያኮራናል።በተለያዩ በሱስና በተለያዩ ጫናዎች ውስጥ የነበሩ ወጣቶች እንደ ጥበብ ህክምና (አርት ቴራፒ) የሚጠቀሙበት አሉ።የነሱ ህይወት ተቀይሮ ማየት በራሱ ስኬት ነው።” በማለት ስኬታቸውን ይገልጻሉ።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19/2013