አስናቀ ፀጋዬ
በአማራ ብሄራዊ ክልል በርካታ የከበሩ፣ ለግንባታ፣ ለኢንዱስትሪና ጌጣ ጌጥ ስራ ግብዓት የሚውሉና የኢነርጂ ጥቅም የሚሰጡ ማዕድናት እንደሚገኙ በተለያዩ ግዜያት በተሰሩ ጥናቶች ተረጋግጧል። በክምችትና በጥቆማ ደረጃም 29 የሚሆኑና የሚታወቁ ማዕድናት በክልሉ እንዳሉ ይነገራል።ከከበሩ ማእድናት ውስጥ በዋናነት ኦፓል በክልሉ የሚገኝ ሲሆን የብረትና የከሰል ድንጋይ ማዕድናትም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ላይ ይገኛሉ። በተመሳሳይ ለኮንስትራክሽን ግብዓት የሚውሉ ማዕድናትም በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች እንደሚገኙ ከክልሉ የማዕድን ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።
የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ይታየው ተስፋሁን እንደሚገልፁት በክልሉ ከሚገኙ የማዕድን ሃብቶች ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው ኦፓል ነው። ኦፓል በምስራቅ አማራ ደላንታ፣ በምዕራብ አማራና ደቡብ ጎንደር ሶስት ወረዳዎች ላይ በስፋት ይገኛል።ማዕድኑ በተለይ በደላንታ ወረዳ የህብረተሰቡ ዋነኛ መተዳደሪያ እየሆነ መጥቷል። በመስራቅ አማራም ከአስራ ስድስት ወረዳዎች በላይ በሚሆኑ አካባቢዎች ይገኛል።
በክልሉ የሚገኘውን የኦፓል ክምችት መጠንን በትክክል ለመግለፅ ባይቻልም በተለይ በምስራቅ አማራ በስፋት የሚገኝ ሲሆን ከግዜ ወደ ግዜ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። በየወረዳው በማህበራት የተደራጁ ወጣቶችም ኦፓልን በማምረት እየተጠቀሙ ይገኛሉ። ምርቱ ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በ2012 በመጠኑ የመቀዛቀዝ ሁኔታ ያሳየ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ለአምራቾችም ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በደቡብ ወሎ ደላንታ ወረዳ ወገል ጤና ከተማ ላይ የኦፓል ገበያ ማእከል ተሰርቶ ወደ ማጠናቀቂያው ምዕራፍ ተቃርቧል። ይህም አምራቾች ምርቶቻቸውን ወጪ ሳያወጡና ለኮንትሮባንድ ንግድ በማያጋልጥ መልኩ እንዲሸጡ ያስችላቸዋል።
የኦፓል ምርት እየሰጠ ያለው ጥቅም ከፍተኛ ሲሆን በተለይ የውጪ ምንዛሬ ከማስገኘት አንፃር አስተዋፅኦው ከግዜ ወደ ግዜ እየጎላ መጥቷል። ባለፉት አስር አመታት ውስጥም 7 ሚሊዮን 500 ሺ የአሜሪካን ዶላር ወደሀገር ውስጥ ማስገባት ችሏል።ከስራ እድል ፈጠራ አኳያም ለ345 ሺ 942 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ፈጥሯል። ከሀገር ውስጥ ገቢ አኳያም 212 ሚሊዮን 989 ሺ በላይ ገቢ ተሰብስቧል።
ሃላፊው እንደሚሉት በ2013 ዓ.ም አንደኛ ሩብ አመት የኦፓል ማዕድን ሃብት በስራ እድል ፈጠራ 6 ሺ 772 ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል። ከዚህ አንፃር አጠቃላይ ከሀገር ውስጥ ገቢም ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል።ከውጪ ምንዛሬ አኳያም የክረምት ወራትን ሳይጨምር ከ104 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል።
በአጠቃላይ በሁለት አስርት አመታት ውስጥ የኦፓል ማእድን ወደ 75 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወደ ሀገር ውስጥ አስገብቷል። ይህም ማዕድኑ የውጪ ምንዛሬ ከማስገኘትና ከውጪ ሀገር የሚገቡና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ ምርቶችን በሀገር ውስጥ እንዲተኩ ከማድረግ አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው።
ይህንኑ የማዕድን ሃብት ከኢንዱስትሪ ጋር በማስተሳሰር በተገቢው ሁኔታ ተመርቶ በአግባቡ ጥቅም ላይ የሚውል ከሆነም ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ያድናል።ይህን ከማሳካት አኳያም ጅምር እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑ አሉ። ይህም የማዕድን ሀብቱን ከመጠቀም አኳያ በክልልም ሆነ በመንግስት ትኩረት ተሰጥቶ እየሰሩ እንደሆነ ያሳያል።የማዕድን ሃብቱን በስፋት መጠቀም የሚቻል ከሆነም ኢኮኖሚያዊ አበርክቶውን ማሳደግ ይቻላል።
ከኦፓል የማዕድን ሃብት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ከሚታዩ ችግሮች ውስጥ አንዱ የማምረቻ ቴክኖሎጂ እጥረት በመሆኑ ማዕድኑ በአብዛኛው የሚመረተው በባህላዊ መንገድ ነው። ከገበያ ትስስር አንፃርም አምራቾች ምርቱን የሚሸጡት ባመረቱበት አካባቢ ሳይሆን ወደ አዲስአበባ ወስደው በመሆኑ ምርቱን በከፍተኛ ደረጃ ለኮንትሮባንድ አጋልጦታል። ከአደረጃጀት አኳያም ታች ያሉትን አምራቾች የመደገፍ ክፍተት ይታያል።
እንደ ሃላፊው ማብራሪያ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ለክልሉ መንግስት በቢሮ፣ በዞንና ወረዳ ደረጃ ዘርፉ ራሱን ችሎ መደራጀት እንዳለበት በሰጠው አቅጣጫ መሰረት ጥናት ተጠንቶ ለክልሉ መንግስትና ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ቀርቧል። የገበያ ማእከሉም በዛው አካባቢ የሚገነባ ከሆነ ይህ ችግር ይፈታል ተብሎ ይታሰባል። ከፌደራል ማእድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በመሆንም አምራቾች በዘመናዊ መንገድ የሚያመርቱበትን መንገድ ማመቻቸትና ስልጠና መስጠት ያስፈልጋል።
ከገበያ ትስስር አንፃር የሚታየውን ችግር ለመፍታትም የክልሉ መንግስት በበጀተው በጀት መሰረት የገበያ ማእከል በመገንባት ላይ ይገኛል። ይህም የኮንትሮባንድ ንግዱን ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል። አምራቾችም አዲስ አበባ መምጣት ሳያስፈልጋቸው ምርታቸውን እዛው በገበያ ማእከሉ እንዲሸጡ ያስችላቸዋል። ባህላዊ አመራረትን ከማስቀረት አንፃርም ስልጠና አስፈላጊ በመሆኑ ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን እየተሰራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19/2013