አስናቀ ፀጋዬ
በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት በግዜው ካለመመረት፣ ካለመሰብሰብና ተጓጉዞ ለህብረተሰቡ ካለመቅረብ ጋር በተያያዘ ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ ምርቶች አቅርቦት ችግር ሊያጋጥም ይችላል።በቅርቡ የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝም በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት በምርት አቅርቦት ላይ ያራሱን አሉታዊ ተፅእኖ አሳድሯል።የምርት አቅርቦት ችግሩን በማቃለልና ምርት በወቅቱ ለህብረተሰቡ እንዲደርስ በማድረግ ረገድ ታዲያ ህብረት ስራ ማህበራት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
የአማራ ክልል ህብረት ስራ ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ልጅአለም ገዳሙ እንደሚገልፁት በክልሉ ከሚገኙ ሰባ ዩኒየኖች ውስጥ 23ቱ ሁለገብ ዩኒየኖች ከመሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራትና ከአርሶ አደሮችም ጭምር በወቅቱ ሰብል ሰብስበው የምርት እጥረት በሚያጋጥምበት ወቅት ደግሞ ወደ ምርት ስብሰባ እንዲገቡ የማድረግ ስራዎችን ሰርተዋል።
የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎም 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን በጥሬ ገንዘብና በአይነት ለተጎጂዎች፣ ድጋፍ ለሚሹና የአቅም ችግር ላለባቸው ምርት ማቅረብ ችለዋል።በአሁኑ ወቅትም ህግን በማስከበር ላይ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ፣ለአማራ ሚሊሻና ልዩ ሃይል ልዩ ልዩ ምርቶችን ድጋፍ በማድረግ ከፍተኛ ስራ እየሰሩ ይገኛሉ።በፌዴራል ደረጃም ለአስቸኳይ ግዜ የተዘጋጀውን እቅድ በክልልና በዞን ደረጃ እስከ ዩኒየኖችና መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት ድረስ እንዲወርድ በማድረግ ተጨማሪ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
ሃላፊው እንደሚሉት የህብረት ስራ ማህበራት የችግር ጊዜ ደራሽ እንደመሆናቸው መጠንና ለህብረተሰቡ በገጠርም በከተማም የኑሮ ውድነት ሲያጋጥም ምርት በቅናሽ የሚያቀርቡ ናቸው።በመሆኑም በቀጣይ አሁን ካለው በተሻለና በተጠናከረ ሁኔታ እንዲሰሩና ውጤትም እንዲያመጡ፣ ህብረተሰቡም ባለቤት እንዲሆን፣ የአባላታቸውም ቁጥር አሁን ካለበት በተሻለ ሁኔታ እንዲጨምርና የካፒታልና የሰው ሃይል እንቅስቃሴያቸውም በተደራጀ መልኩ ወደተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ጠንካራ ስራዎች ይሰራሉ።
መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራትን ወደ ዩኒየኖች ዩኒየኖችን ደግሞ ወደ ፌዴሬሽን ለማሳደግም ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ የሚገኝ ሲሆን ህብረት ስራ ማህበራቱ ከባንክ የሚገኙትን ፋይናንስ ከራሳቸው እንዲያገኙ በማድረግ አቅም መፍጠር የሚቻልበትን ሁኔታም እየተመቻቸ ይገኛል።
የሀረሪ ክልል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ሃላፊ አቶ ጃፋር ሱፊያን እንደሚሉት በክልሉ ከምርት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመቅረፍ አርሶ አደሩ የሚያመርታቸውንና የኢንዱስትሪ ምርቶች አስፈላጊ የሆኑትን የመለየትና ከታች ጀምሮ ምርቶቹ ሲመጡ ከጥራትና ከዋጋ አኳያ በማነፃፀርና በማጥናት የህብረተሰቡንም የምርት ፍላጎት በመለየት የግብይት ስራዓቱን በማሳለጥ ለሸማቹ እንዲቀርቡ እየተደረገ ነው።
ሆኖም እነዚህ ስራዎችን ጅምር በመሆናቸው ማጠናከርና ማስተሳሰር እንዲሁም የግብይት ሰንሰለቱን ማሳለጥ ይገባል።
ህብረተሰቡ ደግሞ የህብረት ስራ ማህበራት አባል እንዲሆን የማድረግና አባል የሆኑትም ይበልጥ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖራቸው የማድረግ ስራም መስራት ያስፈልጋል።ካፒታል የመጨመሩ ሁኔታም ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ በህብረት ስራ ማህበራት ጠቀሜታ ዙሪያ የህብረተሰቡ አመለካከት እንዲቀየርም በስፋት መስራት ይጠይቃል።
በቀጣይም በክልሉ በስፋት የሚመረተውን የጫት ምርት አርሶ አደሩ በህብረት ስራ ማህበራት ተደራጅቶ እንዴት ወደ ገንዘብ ቀይሮ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችል ትኩረት ተደርጎ ይሰራል።በሌላ በኩል ደግሞ በክልሉ በተወሰነ ደረጃ የሚመረቱ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ገበያ ሊያገኛቸው ከሚችሉ ወቅቶች ጋራ የማስተሳሰር ስራዎች ለመስራት ታቅዷል።
አርሶ አደሩ የኢንዱስትሪ ምርቶች በከፍተኛ ደረጃ እየፈለገ መምጣቱን ተከትሎ ምርቶቹን በቀላሉና ኪሱን ሳይጎዳ ሊያገኝ የሚችልበትን ሁኔታ ለመፍጠርም እቅድ ተይዟል።እነዚህን ስራዎች መስራት ከተቻለም ህብረት ስራ ማህበራቱ የዋጋ ንብረቱን ከማረጋጋት በዘለለ በቂ ምርቶችን በማቅረብ ህብረተሰቡ የኑሮ ዘይቤው እንዲቀየር ያደርጋሉ።
የሲዳማ ክልል ህብረት ስራ ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ሃጢሶ በበኩላቸው እንደሚገልፁት ዋጋን ከማረጋጋትና ከምርት አቅርቦት ጋር በተያያዘ በክልሉ የተሰሩ ስራዎች እንዳሉ ሆነው የግብአት እጥረት በተለይም ማህበራቶች ወደ ገበያ ለማምጣት የሚያስችላቸውን በቂ ገንዘብ ያለማግኘት፣ የአካባቢ ገበያና ማህበራቱ ውል ገብተው የሚያቀርቡት ዋጋ ከፍና ዝቅ የማለት ችግሮች ይታያሉ።
ከፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ጋር በመቀናጀትና የተወሰነ ብድር በማፈላለግ በቂም ባይሆን ችግሮቹን ለመቅረፍ ጥረት ተደርጓል።በዚህም መሰረት ለሁለት ህብረት ስራ ዩኒየኖች 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ብድር እንዲያገኙ ተደርጓል።በቀጣይም ማህበራቱ ተበድረው የመመለስ አቅም ከገነቡ ሰፊ እድሎች ይኖራሉ።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ በቀጣይ ኤጀንሲው አምስት የትኩረት አቅጣጫዎችን ያስቀመጠ ሲሆን አሁን ያሉ ማህበራትን ማጠናከር በተለይም የመፈፀምና የማስፈፀም አቅማቸውን መገንባት፣ አሰራራቸውንም ማሻሻል፣ እውቀት ባላቸው ሰዎች እንዲመሩ ማድረግ፣ አጠቃላይ የውስጥ አሰራራቸውን ማሻሻልና ገቢያቸው የሚያድግበትን ሁኔታ ማመቻቸት ዋነኛና የመጀመሪያው የትኩረት አቅጣጫ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ የህብረት ስራ ማህበራት የሀገር ውስጥ የግብይትና የወጪ ንግድ ድርሻቸውን ከፍ ማድረግ ሁለተኛው የኤጀንሲው አቅጣጫ ሲሆን ይህን ማድረግ የሚቻል ከሆነም ገቢው የተሻሻለና ኑሮው የተለወጠ የህብረት ስራ አባላትን መፍጠር ያስችላል።
የአግሮ ፕሮሰሲንግ ውጤታማነትን ማሳደግም ሶስተኛው የኤጀንሲው የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ ይህም ለአግሮ ፕሮሰሲንግ የሚሆኑ ግብአቶች አባላቶች እንዲያቀርቡና እሴት ጨምረው ወደ ገበያ የሚያቀርቡበትን ሁኔታ ለማሻሻል ይረዳል።የአባላት ኑሮ በቤተሰብ ደረጃ ከማሻሻሉም በዘለለ ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ግንባታ የሚያበረክተው አስተዋፅኦም የጎላ ይሆናል።
ቁጠባና ኢንቨስትመንትን በማሳደግም በትኩረት አቅጣጫዎቹ ውስጥ ከተያዙት ውስጥ አራተኛው ሲሆን አባላት ገንዘብ እንዲቆጥቡ በማደረግ ገንዘባቸውን ኢንቨስት እንዲያደርጉም ይሰራል።ይህም ኢንቨስትመንት እንዲጨምርና በተለይ የአባላት የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል ያደርጋል።
በመጨረሻና በአምስተኛው የትኩረት አቅጣጫም ህብረት ስራ ማህበራት ህግን ተከትለው የሚሰሩ እንዲሆኑ በተለይም የማህበራት ደህንነት በኦዲት፣ በኢንስፔክሽንና በሰርተፊኬሽን እንዲጠበቅ ይደረጋል
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19/2013