ኃይለማርያም ወንድሙ
በዛሬው የዘመን ጥበብ ገፅ አምዳችን ላይ አንጋፋውን የጥበብ አድባር እናስታውሳለን። እኚህ ሰው ለኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ እድገት የላቀ አሻራቸውን አሳርፈው በክብርና ሞገስ ነው ይህቺን ምድር የተሰናበቱት። ለዚህ ነው እኛም ዛሬ ጊዜ ሰጥተን የእኚህን ታላቅ ሰው ስራዎች እየዘከርን ጥቂት በትዝታ ወደኋላ ለመመለስ የወደድነው።
ሁሉም ይወዳቸዋል፤ ሁሉም ያከብራቸዋል። አንደበታቸው ጣፋጭ ነው። ንግግራቸው የሰላ። በኢትዮጵያውያን የጥበብ ባለሙያዎች ውስጥ ጉልህ ስፍራን ወስደዋል። እንደ መምህር፣ እንደ ተዋናይና እንደ አባትም ጭምር ናቸው። በፊልሞች፣ መድረክ ቲያትሮች፣ ድራማዎችና መሰል የጥበብ ስራዎች ላይ ስማቸው በጎላ ብዕር ተፅፏል። እኚህ ሰው ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ ናቸው።
የኪነጥበብ አፍቃሪያን መርዶ የሰሙበት እለት ነበር፤ ተወዳጁን አርቲስት በሞት የተነጠቁበት። ህመም አጋጥሟቸው አስር ቀናትን ብቻ በሕክምና ሲረዱ በ84 ዓመታቸው ታህሳስ 7 ቀን ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል። የቀብር ስነስርዓታቸውም ታኅሣስ 8 ቀን፣ 2013 ዓም በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡
ታላቁ ሰው ማነው?
የዘመን ጥበብ አዘጋጅ በሽኝት ስነስርዓቱ ላይ በተገኘበት ወቅት የኚህን የኪነ ጥበብ አድባርና የብዙዎች አባት የህይወት ዘመን ስራዎች ለማወቅ እድሉን አግኝቷል። የተለያዩ ምስክርነቶችም ሰምቷል። የህይወት ዘመን ስራቸውንም ከዚህ እንደሚከተለው ያስቀምጣል።
በሙያቸው በቆዩባቸው 40 ዓመታት ውስጥ በተዋናይነት፣ በጸሐፌ ተውኔትነት፣ በዳሬክተርነት፣ የቲያትር ቤት (ብሔራዊ ቲያትር) አስተዳዳሪነት እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትያትር እና ጥበባት ኮሌጅ ለበርካታ ዓመታት በመምህርነት አገልግለዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ መስከረም 17 ቀን በ1929 አም በጉሮ ጉቱ ሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት የተወለዱ ሲሆን፤ የቲያትር ሙያቸውን የጀመሩት በ1950ዎቹ ወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆነው ነው። ንጉሡ በብሔራዊ ቲያትር በወቅቱ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቲያትር ቤት ባዩት ተውኔት የተስፋዬ ገሰሰን የመድረክ ትወና አደነቁ፤ የነፃ ትምህርት ዕድል ሲያገኙ ተስፋዬ ሕግ ለመማር ቢፈልጉም ንጉሡ በኖርዝዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ቲዓትር ትምህርት ቤት ቲያትር ቢማሩ የበለጠ ውጤታማ እንደሚሆኑ ስለመከሩዋቸው በቲያትር ጥበብ የሀገሪቱ የመጀመሪያው ምሩቅ ለመሆን በቅተዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ባለዲግሪ ተዋናይ ለመሆን በቁ። በቲያትር ቤት መድረክ በተውኔትና በድርሰት በዳይሬክተርነት ከመሥራታቸው በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲ የቲያትር ጥበብ በማስተማር ብዙ ባለሙያዎችን ያፈሩ አንጋፋ የጥበብ ሰው ነበሩ።
በ1960 ዎቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱም የቲያትር ጥበቡ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሁኔታዎችን ተከትሎ ለመሳፍንቱ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ሆኖ ነበረ። በወቅቱ የመጀመሪያ የመድረክ ሥራቸው “የሺ”( በሴተኛ አዳሪነት ህይወትዋን የምትገፋና የፍቅረኛዋን ሕይወት የምታጠፋ) የተባለ በከተማ ኑሮና ሙስና ላይ ያተኮረች ገፀ ባህርይ ወክለው ተውነው ነበር፡፡
ደርግ ሥልጣን እንደያዘ በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ዋና ዳይሬክተር ሆነው አስተዳድረዋል፡፡በዓመቱ ግን በደርግ መንግሥት ዋና ዳይሬክተርነታቸው ታግዶ ሥርዓቱን በሚያብጠለጥለው “ዕቃው” በተባለው ቲያትር የአስተዳደሩን ሙስና ወክለው በመተወናቸው ወደ እስር ቤት ተወርውረዋል፡፡
ዘግይቶም ‘ደማችን ትግላችን’ የሚል ሙዚቃዊ ድራማ ላይ በትወና እና በዝግጅት የሠሩ ሲሆን በዚህም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። ከዓመት በኋላም ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ከብሔራዊ ቲያትር ቤት በሠራተኞች ተቃውሞ እንዲነሱ ሲደረጉ ተስፋዬ ገሰሰ በአዲስ ዳይሬክተርነት ተሾሙ፡፡
በወቅቱ በዳይሬክተርነት ሲመሩት የነበረው “ፀረ ኮሎኒያሊስት” የሚል ተውኔትና “ተሀድሶ” የሚል ድርሰታቸው ሥርዓቱን ይፃረራሉ በሚል ውዝግብ አስነስተው ነበር፡፡ደርግም ቁጥጥሩን በማጥበቁ ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ ከሦስት ዓመት በኋላ ከኃላፊነታቸው ተነሱ።
ቢሆንም ግን ዝናቸው በፈጠረላቸው አመቺ አጋጣሚና በከፈተላቸው ቀዳዳ ከጥቂት ጸሐፌ ተውኔትነት ጎን ሆነው ፖለቲካዊ ስሜት የነበራቸው ድርሰቶች በ1980ዎቹ ደርሰዋል። ከነዚህ መካከል “ፍርዱ ለናንተ” የተባለ ድርሰታቸው ተጠቃሽ ነው፡፡
ረዳት ፕሮፌሰሩ መተከዣ፣ አባትና ልጆች፣ ላቀችና ደስታ፣ ተሐድሶ የተሰኙ ተውኔቶችን ደርሰዋል። ሐምሌት የተባለውን የሼክስፒር ድርሰት ትያትርን ጨምሮ በርካታ ተውኔቶችን በመተረጎም፣ በመተወን እና በማዘጋጀት ለመድረክ አብቅተዋል።
የዑመር ኻያምን ልቦለዳዊ የሕይወት ታሪክና ሩብ አያቴ የትርጉም ሥራ ለአንባቢያን አድርሰዋል ። በተለይ የኢራን ጥንታዊ ገጣሚ የሆነውን መልክዐ ዑመር ኻያም ሩብ አያቶች (ባለ አራት ስንኝ ግጥሞች) መጽሐፍ ወደ አማርኛ የተረጎሙበት መንገድ ግጥሙን ትርጉም እንዳይመስል አድርገውታል፤ በዚህም ግጥሙን ቤተኛ አስመስለውታል፡፡በግጥሞቹም ላይ የሚታዩት አማርኛ ኦሮምኛን ጨምሮ የግዕዝ ቃላት የተጠቀሙበት መንገድ ግጥሙን ተወዳጅ አድርገውታል።
አርቲስቱ በተለያዩ ፊልሞችና ድራማዎች ላይ የተውኑ ሲሆን ‘ሽልንጌን’ ጨምሮ በርካታ የአጭር ልቦለድ ሥራዎችን ለአንባቢያን አበርክተዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትያትር እና ጥበባት ኮሌጅ ለበርካታ ዓመታት በመምህርነት አገልግለዋል።
በጥበብ አድባሮች አንደበት
አርቲስት ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) ከተስፋዬ ገሰሰ የቅርብ ወዳጆች አንዱ ናቸው። እኚህ ተወዳጅ የጥበቡ ዘርፍ ባለሙያ ለአስርት ዓመታትም በጥበቡ ዘርፍ አብረው መስራታቸውን አንስተው “ተስፋዬ ገሰሰ ልዩና ጨዋ ሰው ነበር” በማለት ምን አይነት ባህሪ እንደነበራቸው ይናገራሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትያትር ጥበብ መምህር ሆኖ ወደፊት ተተኪ የሆኑ ተዋንያንን ማፍራቱንም በማንሳት በግል ለኪነጥበቡ ካበረከቱት አስተዋፆኦ በላይ መጪው ትውልድ ላይ በመስራት ተጨማሪ ላቅ ያለ አበርክቶ እንደነበራቸው ይገልፃሉ። ባልደረባቸው ተስፋዬ ገሰሰ በግለሰቦችም ሆነ በአገር ላይ ብዙ ውጤቶች ያፈራ ሰው መሆኑን በማንሳትም በህልፈተ ህይወቱ እጅግ ማዘናቸውን አንስተዋል።
ሌላኛው የሙያ አጋራቸው ታላቁ የኪነ ጥበብ ባለሙያ ፀሃፊ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ ናቸው። እኚህ ሰው ስለ ታላቁ አርቲስት ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ቀድሞ በልቦናቸው የሚከሰተው በብሄራዊ ቲያትር በዳይሬክተርነት የሃላፊነት ስራቸውን ሲወጡ ያበረከቱትን አስተዋፆኦ ነው።
በተለይ በአፄ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት አርቲስቶች ቋሚ ደመወዝ ስላልነበራቸው ይህን ችግር ለመፍታት ብዙ ርቀት እንደተጓዙ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ። ጥናት በማድረግም ቋሚ ደመወዝ ተከፋይ እንዲሆኑ ማድረጋቸውን ይናገራሉ። በቲያትር ሙያ ያበረከቱት አስተዋፆም በእጅጉ የሚደነቅ መሆኑን ከማንሳት አልተቆጠቡም።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 18/2013