ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳታገኝ የተፈጸመባትን ኢ-ፍትሐዊ ድርጊት ካርታው ራሱ ጮኾ ይናገራል

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳይኖራት ታስቦ የተፈጸመባትን ኢ-ፍትሐዊ ድርጊት ካርታውና ከባሕር በር ያለችበት ርቀት ራሱ ጮኾ እየተናገረ ይገኛል ሲሉ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ ሀሳቡ ተስፋ ገለጹ።

አቶ ሀሳቡ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በዓለም ላይ የባሕር በር ከሌላቸው ሀገራት መካከል እንደ ኢትዮጵያ ለውቅያኖስ ቅርብ የሆነ እና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ኖሮት ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የባሕር በር ያጣ ሀገር የለም። ኢትዮጵያ በተለይም ለቀይ ባሕር ከ40 እስከ 60 ኪሎ ሜትር በሚሆን ርቀት ላይ እያለች የባሕር በር እንዳይኖራት ታስቦ የተፈጸመባትን ኢ-ፍትሐዊ ድርጊት ካርታውና ርቀቱ ራሱ ጮኾ እየተናገረ ይገኛል ሲሉ አስረድተዋል። ካርታው ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዳይኖራት ታስቦ የተፈጸመ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

የባሕር ተዋሳኝ የሆኑ ሀገራት የባሕር በር ለሌላቸው ጎረቤቶቻቸው የባሕር በር እንዲኖራቸው ይተባበራሉ ያሉት አቶ ሀሳቡ፤ ሳውዲ ዐረቢያ ለጆርዳን፣ አንጎላ ለኮንጎ፣ ሞንቴ ኔግሮ ለሰርቢያ የባሕር በር እንዲያገኙ ያደረጉትን ትብብር በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

ይህም በሀገራቱ መካከል ሰላማዊ ጉርብትና ለመፍጠርና ተደጋግፎ ለማደግ ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ግን እንዲህ ዓይነት ትብብር እንደማይታይ ጠቅሰው፤ እንዲያውም በቅርብ ያለንን ጎረቤት ሀገር በማግለል የሩቁን የመጥቀምና በር የመክፈት አዝማሚያ ይስተዋላል ነው ያሉት። ኢትዮጵያ በአሰብ ወደብ ከምትጠቀም እናንተ ብትቀመጡበት ይሻላል በሚል ኤርትራ የባሕር በር ችግር ለሌለባት ግብጽ የባሕር ጠረፍ መስጠቷ ይህንኑ እውነታ የሚያረጋግጥ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ፓናማ እና ግሪንላንድ ወደ አሜሪካ ሊጠቃለሉ ይገባል ማለታቸው የአሜሪካን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር እንደሆነ አቶ ሀሳቡ ተናግረዋል። አሜሪካ በሀገራቱ ላይ ከምታቀርበው ጥያቄ የበለጠ ኢትዮጵያ በባሕር በር ላይ የምታነሳው ጥያቄ እጅግ በጣም አሳማኝና ፍትሐዊ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የባሕር በር ጥያቄው አልተመለሰም ማለት፤ መጪው ትውልድ ህልውና የለውም ማለት ነው ያሉት አቶ ሀሳቡ፤ ዲፕሎማሲያዊና ሰላማዊ አማራጭ ተጠቅሞ የባሕር በር ባለቤት መሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር የተካለለው ኢትዮጵያና ጣሊያን በ1900፣ በ1902 እና በ1908 የተፈራረሙትን ስምምነት መነሻ አድርጎ እንደሆነ አስታውሰው፤ ሁለቱ ሀገራት በእዚያን ዘመን የተፈራረሙት ውል ጣሊያን ኢትዮጵያን በጉልበት ለማንበርከክ ውሏን ሰርዛ በመውረሯና በመሸነፏ ምክንያት ስምምነቱ ውድቅ ሆኗል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታጣ የሆነችው በተሻረ ስምምነት እንደሆነ አስረድተዋል። በወቅቱ በኢትዮጵያም በኩል የነበሩት ገዢ ኃይሎች ጸረ ኢትዮጵያ አቋም ያላቸው በመሆኑ ያለሕዝብ ውሳኔ እና ይሁንታ ኢትዮጵያን የባሕር በር አሳጥተዋታል ብለዋል።

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You