አብርሃም ተወልደ
የኮንታ ብሔረሰብ ሲነሳ ወጣቱን ድምጻዊ ማንሳት የግድ ይላል። ላለፉት አስራ ሰባት ዓመታት ኮንታ ብሔረሰብንና በዞኑ የሚገኙ ብርቅዬ የተፈጥሮ ሀብቶችን በየሙዚቃዎቹ እና በአገኘው መድረክ ሁሉ አስተዋውቋል፤ የስፖርት እና የሙዚቃው ሰው ወንድዬ ኮንታ፡፡
ወንድዬ ኮንታ በአሁኑ ወቅት የደቡብ ሙዚቀኞች ማህበር ሊቀመንበር ነው፡፡“ሱሩር ጋሼ” እና “ሎሜ ሎሜ” በሚሉት ስራዎቹ የኮንታን ብሄረሰብ ያስተዋወቀ ሲሆን፣ ከኮንታ ብሔረሰብ በመለስም የከንባታ ፣ወላይታ፣ ዳውሮ፣ ከፋ፣ ሸካ፣ ቤንች ማጂ ብሔረሰቦች ሙዚቃዎችን ተጫውቷል፡፡
የተገኙ ስኬቶች
“የእኔ መነሻ ሀሳብ ማንነትን ፍለጋ ነው” የሚለው ወንድዬ፣ በመጀመሪያ ሙዚቀኛው የተገኘበትን የኮንታ ብሔረሰብን ማስተዋወቅ ላይ ሰርቷል፤ የብሔረሰቡ የመጀመሪያ መዚቀኛ መሆኑን ይገልጻል። በሙዚቃው የብሔረሰቡን ቱባ ባህል ፤ ቅርስ እና ማንነት ሳይለቅ ለማሳየት ጥረት ሲያደርግ እንደቆየ ይናገራል። በዚህም ትልቅ ስኬት አግኝቷል፡፡
እንደ ሙዝቀኛው ገለጻ፤ የኮንታ አካባቢ ለአስራ ሰባት ዓመት ያቀነቀነለት የተሟገተለት ትልቅ ሀብት ነው። ለአገርም ለአካባቢውም ትልቅ ገቢ ያስገኛል ብሎ ብዙ የደከመለት ኮንታ በመንግስት ከፍተኛ ትኩረት ማግኘት ችሏል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የቦታውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በማየት ከሀገራዊ ፕሮጀክቶቻቸው መካከል አንዱ አርገውታል፡፡ወንድዬ ከዚህ በላይ ምንም ዓይነት ስኬት እንደሌለ ይናገራል፡፡
ከሙያ ባልደረቦቹ ጋር በመሆን በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች የሚገኙ ሙዚቀኞችን በማሰባሰብ እና በማስተባበር የደቡብ ሙዘቀኞች ማህበርን መስርቷል። በናይጄሪያ በተካሄደ አለም አቀፍ የሙዚቃ ውድድር ይሄው ህብረት የዋንጫ ተሸላሚ ሆኖ ተመልሷል፡፡
የእረፍት ውሎ
ሙዚቀኛ ወንድዬ የእረፍት ጊዜውን የሚያሳልፈው በአብዛኛው ሀዋሳ በሚገኘው በቀድሞ አጠራሩ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል በሚባለው እንዲሁም ፍቅር ሀይቅ ዙሪያ ባሉት የመዝናኛ ቦታዎች እንደሆነ ይናገራል፡፡ሀይቁ ዳር ቁጭ በማለት ራሱን የማዳመጫ እና ለራሱ ጊዜ የሚሰጥበት ጊዜ እንዳለው የሚገልጸው ሙዚቀኛው፣ ክራር እየተጫወተ የተለያዩ ዘፈኖችን እያንጎራጎረ ጊዜውን ያሳልፋል። በተለይም የእነ መስፍን አበበ፣የአብተው ከበደ፣ የእነ ሰለሞን ደነቀ ዜማዎችን እንዲሁም መዝሙሮችን እያቀነቀነ ራሱን ያዝናናል፡፡
በማህበራዊ ህይወትም ተገቢውን ሁሉ እንደሚያደርግ ወንድዬ ይገልጻል። ያደገበትን ማህበረሰብ በሚመለከት በህብረት ለሚደረጉ ጉዳዮች ትኩረት ይሰጣል። እነዚህ እንደ እቁብ፣ እድር …መሰል ያሉት ተቋማት ለአንድ ግለሰብ እንደ አገር ብዙ ፋይዳ እንዳላቸው ይጠቅሳል። ሙዚቀኛውም ይህን በመረዳት ለማህበራዊ ህይወት ዋጋ እንደሚሰጥ ይገልጻል፡፡
ወንድዬ ባደገበት ኮንታ ማህበረሰብ ውስጥ እንዲህ ያሉ ማህበራዊ ተቋማት በሀዘን ጊዜ ለማጽናናት በደስታ ጊዜ ለመዝናናት ብቻ አይደለም የሚውሉት ይላል። የኮንታ ማህበረሰብ ህይወት ሙዚቀኛ ወንድዬን ጨምሮ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ “በደቦ” ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ይናገራል፡፡
ማህበረሰቡ ግብርና የሚሰራው በደቦ ነው፤ ቡና የሚጠጣው፣ የበዓል ፕሮግራሞች በአጠቃላይ ማንኛውም እንቅስቃሴ የሚደረገው በደቦ ነው። ይህ ማንነት ስላሳደገው የወንድዬም ህይወት ከዚህ የተለየ አይደለም፤ ስለዚህ ወንድዬ የኮንታ ዕድር አለው፤ በዚህም በሰዎች ላይ ችግሮች ሲደርሱ በህብረት ለመፍታት ይሰራሉ።
ሀዘን ሲከሰት ያስተዛዝናሉ፤ በዚህም ይረዳዱበታል፤ በዓሎችንም በጋራ ያሳልፋሉ። እሱም በደስታ ጊዜ አብሮ በመብላት ፣በመጫወት፣ወዘተ. የራሱን የወዳጆቹን ደስታ አብሮ ያሳልፋል፡፡
ሌሎች የእረፍት ጊዜያቸውን እንዴት ያሳልፉ
ሙዚቀኛ ወንድዬ አበበ አሁን ባለው ሁኔታ ወጣቱ በምግባረ ብልሹ ሰዎች ተጽዕኖ ስር ወድቋል፡፡ይህ ሁኔታ ወጣቱን ለበጎ ከመስበሰብ ይልቅ ለጥፋት መሰብሰብ ምርጫው እንዲሆን አርጎታል። የተገነባ አገር የሚያፈርስ ትውልድ እየተፈጠረ ነው፤ትውልዱ የሚዛናዊ ህሊና ባለቤት መሆን ተስኖታል ሲል ይጠቁማል፡፡
ትውልዱ ከዚህ የተበላሸ ህይወት እንዲወጣ የእረፍት ጊዜውን ከአባቶች ጋር ማሳለፍ እንደሚገባው ወንድየ ይመክራል፤ ወጣቱ የቀለም ትምህርት ተምረዋል ያላቸውን ብቻ መከተሉ እንደጎዳው ጠቅሶ ፣ከህይወት ከተማሩት አባቶች እግር ስር ቁጭ ብሎ የእረፍት ጊዜውን በማሳለፍ ለዘመኑ የሚሆነውን እውቀት መቅሰም እንደሚኖርበት ያስገነዝባል።
ሙዚቀኛው በእያንዳንዱ የዕድሜ ክልል ጥንካሬዎችና መልካም ዕድሎች እንዳሉም ይናገራል፡፡በልጅነት ወቅት ያለው በወጣትነት ጊዜ እንዲሁም በወጣትነት ጊዜ ያለው በጎልማሳነት ጊዜ አይኖርም ይላል። በተገቢው ዕድሜ የሚገባውን መስራት ለቀሪው ዕድሜ ብዙ የቤት ስራዎችን ላለማጠራቀም እንደሚረዳም አስታውቋል፡፡
በእረፍት ጊዜያችን ለመጪው ጊዜ እና ላሉበት ሁኔታ የሚጠቅመውን በማሰብ ለግልም ለአገርም የሚበጅ ተግባር መስራት እንደሚገባ ይመክራል፡፡በእረፍት ውስጥ መሰራትም አለ፡፡ሳምንቱን በሙሉ በተለያዩ ጉዳዮች ተወጥሮ የቆየ ጉልበት ዘና ማድረግ አእምሮን ማሳረፍ እንደሚገባ አመልክቶ፣ በእረፍት ጊዜ አብረን ከምንውላቸው ሰዎች መልካም መልካሙን በመውሰድ ለቀጣይ ህይወት የሚጠቅም ስንቅን መያዝ ይቻላል ይላል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 18/2013