መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአገሪቱ ከ50 ሚሊዮን እስከ 72 ሚሊዮን ሔክታር ሊታረስ የሚችል መሬት አለ፡፡ ሆኖም አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም አበባን ሳይጨምር እየለማ ያለው 13 ሚሊዮን ሔክታሩ ብቻ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ በገበሬ ማሳ የሚለማው 12 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሔክታር ነው፡፡ ሊታረስ ከሚችለው መሬት አንድ ሦስተኛ ያህሉ ብቻ ጥቅም ላይ ሲውል፤ ቀሪው ሥራ ላይ አልዋለም፡፡
በአገሪቱ ሳይታረስ ከሚቀረው መሬት ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ደግሞ በአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩ አካባቢ የሚገኘው ሰፊ ስፍራ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ አካባቢ የአገሪቱ ትላልቅ ወንዞች ስለሚያቋርጡት እምቅ የመስኖ ልማት ጸጋ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ ጥቅም አልዋለም፡፡ በዛው ልክ ድህነቱ፣ የምግብ ዋስትና እጦቱ፣ የአካባቢ መራቆትና የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎቹ የሚበረታው በእነዚህ አካባቢዎች ነው፡፡
መንግሥት በአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩ አካባቢዎች ያለውን የተጠራቀመ ችግር በመፍታት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት የሚኖራቸውን ጉልህ ድርሻ አሟጦ ለመጠቀም በርካታ ጥረቶች ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ከጉዳዩ ክብደት የተነሳ በሚኒስቴር ደረጃ እንዲመራ የተደረገው የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩ አካባቢዎች ልማት የሚፈለገውን መሰረታዊ ለውጥ አላመጣም፡፡ በቅርቡ ለአስራ ሰባተኛ ጊዜ የአርብቶ አደሮች ቀን ተብሎ በጂንካ እንደተከበረው አይነት የማነሳሻ መርሐ ግብሮች በክልሎችም ጭምር ቢከናወንም እንዲሁም አምና ከዓለም ባንክና ከዓለም እርሻ ልማት ፈንድ በተገኘ የ550 ሚሊዮን ዶላር ብድር በስድስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የሚከናወን የእንስሳት ሀብት ልማት ፕሮጀክት ቢነደፍምና ሌሎችም እገዛዎች ተጠናክረው ቢቀጥሉም ፍሬያቸውን አሁን ማየት አልተቻለም፡፡
የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩ አካባቢዎች እንዳላቸው እምቅ አቅም ለኢኮኖሚው እድገት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ችግሮች ተነቅሰው መፍትሄ ሊበጅላቸው ይገባል፡፡ በቅድሚያ የሁሉም ልማት መሰረት የሆነው የሰላም ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት በዘላቂነት ሊረጋገጥ ግድ ይላል፡፡ አካባቢዎቹ ሰፊ፣ ብዙ ህዝብ የማይኖርባቸውና መሰረተ ልማት በሰፊው ያልተሟላላቸው ስለሆኑ የጸጥታና ደህንነት ስጋት አያጣቸውም፡፡ ስለሆነም ከልማቱ እኩል ለሰላሙ ትኩረት ሰጥቶ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የተጠናከረ ጥበቃ ማካሄድ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ሲሆን አልሚዎችን መሳብ የአካባቢውም ኅብረተሰብ ጊዜውን ለሥራ ብቻ እንዲያውል ማድረግ ይቻላል፡፡
የቁም እንስሳት ሀብት የአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩ አካባቢዎች አንድ መገለጫ ነው፡፡ ይህ ሀብት የሚተዳደርበትና ለገበያ የሚቀርብበት መንገድ አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮቹን በሚገባ ደረጃ ተጠቃሚ አላደረገም፡፡ ስለሆነም ዘመናዊ የከብት አረባብ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ለእዚህም በአካባቢዎቹ የአርብቶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከላትን መገንባትና ማጠናከር እንዲሁም ባለሙያዎችን በበቂ መጠን ማሰልጠን ያስፈልጋል፡፡ በእዚህም የማህበረሰቡን አመለካከት መቀየርና አቅሙና ማሳደግ ይቻላል፡፡
የቁም እንስሳት ሀብት ለገበያ የሚቀርብበትን መንገድ ለማሳለጥ በቂ መሰረተ ልማት ማሟላት እንዲሁም ህገ ወጥ ሽያጭን መቆጣጠር ሊጠናከር ይገባል፡፡ የቁም እንስሳትን እሴት እየጨመሩ መላክ አገርንም ማህበረሰቡንም ተጠቃሚ ስለሚያደርግ ትኩረት ይሰጠው፡፡ በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ማበረታቻና ምቹ ሁኔታ መፍጠርም እንዲሁ፡፡
በአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩ አካባቢዎች ዘወትር በችግርነት የሚነሳውን የውሃ እጥረት ለመፍታት ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች በስፋት መቆፈር አለባቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንደ አዋሽ ያሉ የውሃ ጸጋዎችን በላቀ ሁኔታ መጠቀም ጊዜ ሊሰጠው አይገባም። አስተማማኝ የመኖ አቅርቦት እንዲኖር በአንዳንድ አካባቢዎች የተጀመረው የሳር ባንክ የማዘጋጀት መላ በሁሉም ስፍራ ሊተገበር ይገባል፡፡ የትምህርትና የጤና ተደራሽነትና ጥራትም በሁለገብ ልማታዊ እንቅስቃሴ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ ገብቶ በሰፊው ቢሰራበት የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡
በአርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩ አካባቢዎች ያለውን እምቅ አቅም ተጠቅሞ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ መንግሥት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች እና አሠራሮች ከማኅበረሰቡ ፍላጎት ጋር ማጣጣም ያስፈልጋል፡፡ የተጠቀሱት ጉዳዮች ትኩረት ተችሯቸው ሲተገበሩ የአርብቶ አደሩን አካባቢ እምቅ አቅም ለኢኮኖሚያዊ እድገት በማዋል የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፤የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበትን አማራጭ የሚያሰፋ ገቢ ማግኘት፤ ብሎም የኅብረተሰቡን ህይወት የሚቀይርና ስጋቱንም የሚያስወግድ መንገድ መቀየስ ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 21/2011