በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
( ክፍል አንድ )
ከሀዲውና እፉኝቱ የትህነግ ቡድን ቆስቁሶ በጋየበት የሕግ የበላይነትና የህልውና ዘመቻ ህዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም በአንጸባራቂ ድል መጠናቀቁን ተከትሎ ቀጣዮቹ የፍልሚያ ግንባሮች የሚዲያና የትግራዋይን ልብና አመለካከት ከትህነግ ቡድን የፈጠራ ትርክት ነጻ ማውጣት ( Wining hearts and minds) መሆኑን የሚተነትኑ ሁለት መጣጥፎችን በዚሁ ጋዜጣ አስነብቤ ነበር።
እንዳልሁት የኢፌዴሪ መንግስትና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የትግራዋይን ልብ በተግባር እየተገለጠ ባለ እውነተኛ ወገናዊ ፍቅርና ተግባር የመማረኩንና የማማለሉን ልምምድ ተያይዘውታል። ልብንና አመለካከትን ማሸነፍ ትዕግስት ፣ ወጥነትና ቀጣይነት ያለው ጥረት ስለሚሻ ጊዜ ይፈልጋል።
አጀማመሩ ተስፋ ሰጭ ስለመሆኑ ግን አበክሮ መናገር ይቻላል። ከአብራኩ በወጡ ሀቀኛ ልጆች መተዳደር መጀመሩ፤ የመልሶ ግንባታ ሒደቱን እየተሳለጠ መሆኑ እና የመከላከያ ሰራዊቱ የቀበሮ ምሽግ አጋሮችን በክህደት ቢያጣም በጥብቅ ዲሲፕሊን ሕዝባዊነቱን ማረጋገጡ ፤ የትህነግ ቡድን ሲነዛው የኖረ የጥላቻ፣ የመለያየትና የመጠራጠር መርዝን እያረከሰው ይገኛል።
ከአቦይ ስብሀት ቤተሰብ መሆን ሳይጠበቅባቸው ፍትሐዊ ተጠቃሚ ሲሆኑ ከአንድ ለአምስት ጥርነፋ ነጻ ወጥተው ህይወትን ሲያጣጥሙ ልባቸውን መስጠታቸው አይቀርምና። የትግራዋይ ልብና አስተሳሰብ በለውጥ ኃይሉ የተማለለ እለት መወድስ ቅኔ ባይኖረኝም መወድስ ወግ ይዤ እንደምመለስ ቃል እየገባሁ ወደ ሁለተኛው የሚዲያ አውደ ግንባር ልለፍ።
ከሀዲውና አረመኔው ትህነግ ከትግራዋይ ልቦና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማስጣል ለ46 አመታት መዋቅራዊና ተቋማዊ በሆነ አግባብ ሌት ተቀን እንደሰራው ሁሉ በተቀረው የሀገራችን ክፍልም ለ30 አመታት ይሄንኑ እኩይ አላማ ተግብሯል። ለዚህ ይረዳው ዘንድ በትውልድ ቅብብሎሽ ደም ፣ ላብና ሀብት የተገነቡ ተቋማትን አፍርሷል።
የደህንነትና የጸጥታ ፣ የሀይማኖት ፣ የፍትሕ ፣ የትምህርት ፣ የመገናኛ ብዙኃን ፣ ወዘተረፈ ተቋማትን በቁማቸው እርቃናቸውን አስቀርቷል። አኮስምኗል። ለዚህ ነው ትውልድና ታሪክ ይቅር ለማይለው ለጥቅምት 24ቱ የክፍለ ዘመኑ ታላቅ ክህደት ዝግጅት የጀመረው ከውልደቱ ከየካቲት 1967 ዓ.ም ጀምሮ ነው የምለው።
ከትግራዋይ ልብ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ለመፋቅ እንደጣረው ለከፋፍሎ መግዛት እንዲያመቸው በቀረጸው አስመሳይና የሞግዚት ፌደራሊዝም ልዩነትን ፣ ጥላቻንና መጠራጠርን ዘርቷል።
የሀገሪቱን ጦርና ደህንነት በተነ፤ ከ40 በላይ የአአዩ መምህራን በማባረር በልሒቃንና በዩኒቨርሲቲዎች ላይ የበቀል በትሩን አሳረፈ ፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሞጋች እንዳይሆኑ 70/30 በሚል ሰበብ የሶሻል ሳይንስ ትምህርቶችን አዳከመ መጨረሻ ላይም ዘጋ ፣ መገናኛ ብዙኃን በአብዮታዊ ዴሞክራሲ እና በልማታዊ ጋዜጠኝነት ቅኝት በካድሬ እንዲሞሉ በማድረግ እኔን ጨምሮ አዝማሪና አጨብጫቢ አድርጓቸው ዛሬ ቃለ መጠየቅ እንኳ በቅጡ የሚያደርግ ፣ የቀጥታ ስርጭት የሚመራ፣ ርዕሰ አንቀጽ የሚጽፍ ፣ ሰበር ዜናን የሚወስን የአርትኦት ኮሚቴ አባል ጠፍቶ በትዕዛዝ ዜና የሚሰብር ሆኖት አርፏል። በየቀኑ ሰበር ዜና ቢኖርም “ ሰበር ዜና “ ለማለት ትዕዛዝ ይጠብቃል።
ከጥቅምት 24 ወዲህ ሲሰባበሩ የነበሩ ዜናዎችን እያስታወሳችሁ ሰሞነኛውን ጥልቅ ዝምታ ልብ ይሏል። በመተከል ዞን ማንነትን ኢላማ ያደረገው ጭፍጨፋ፣ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢጋድ ስብሰባ፣ ኬንያንና ሶማሊያን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት መምጣትና የተቋረጠ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለመጀመር መወሰናቸው፣ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አዲስ አበባ መምጣት፣ ከመተከል ዞን ነዋሪዎች ጋር መወያየታቸው፣ የሰምሀል መለስ ዜናዊ መታሰር፣ ወዘተረፈ ሰበር ዜናዎች ሆነው መዘገብና ከተለያየ አቅጣጫና አውድ አንጻር ተከታታይ ትንተናዎችና ማብራሪያዎች ሊደረግባቸው ሲገባ በነጠላና ግልብ ዜና ታልፈዋል። ከሀዲው ትህነግ ተቋማትን ምን ያህል ጸጉራም ውሻ አድርጓቸው እንደሄደ የመገናኛ ብዙኃን ጥሩ ማሳያዎች ናቸው።
ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አስጥሎ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግራዋይ (አደይ ትግራይ)ን፣ እምነትን አስከድቶ አብዮታዊ ዲሞክራሲን፣ በአጽሚ በቅልጺሚን፣ የሀገሪቱን የትምህርት ጥራት አሽቆልቁሎ ቃላሚኖንና ልጆቹን ደግሞ በአውሮፓና በአሜሪካ የሚያስተምር ፣ የሀገሪቱን መከላከያ በቁሙ አፍርሶ ከቀላል እስከ ከባድ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀ 200ሺህ ልዩ ኃይል ሚሊሻ የገነባ ፣ የሀገር ኢኮኖሚን እየዘረፈና እያሻጠረ ትእምት ( EFFORT) የተባለ ባለብዙ ቢሊዮን ዶላር የዘረፋ ኢምፓየር የገነባ ጉድ ነው። ባለፉት ጥቂት አመታት ብቻ ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከጭፍራዎቹ ጋር በመሆን ወደ ውጭ ያሸሸ ደመ ጠጭ መዥገር ነው።
የዛሬው መጣጥፌ ትኩረት ወደ ሆነው መገናኛ ብዙኃን ስንሻገር የሀገሪቱን ሚዲያ ሲያዘምርና ሲያስጨበጭብ ኖሮ የራሱን መደበኛና ማህበራዊ ሚዲያ ግን በአራት ትላልቅ ዘርፎች አደራጅቷል። እርሱም ፦ 1ኛ . መደበኛ ሚዲያ 2ኛ. ማህበራዊ ሚዲያ 3ኛ.አለማቀፍ ሚዲያና ተቋማት 4ኛ.ስፒን ዶክተርሰና ሎቢስትስ ናቸው። የመጀመሪያው ማለትም እነ ትግራይ ቴሌቪዥንን ፣ ድምጺ ወያኔን፣ ወይንን ፣ ትግራይ ሚዲያ ሀውስን (TMH)፣ ትግራይ ፈርስትን ፣ አይጋ ፎረምን ፣ ትግራይ ፕሬስን ፣ ቮይስ ኦፍ ትግራይ ፣ ትግራይ ኦን ላይንና አውራምባ ታይምስ የሚያካትት ሲሆን ሁለተኛው ዲጂታል ወያኔ አካልና ምን አልባት በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የዲጂታል ጭፍራ ያለው ሲሆን በአንድ ለአምስትና በአንድ ለሀያ ተደራጅቶ በማህበራዊ ሚዲያ በተለይ በፌስ ቡክ ፣ በቲዊተር ፣ በዩቲውብ፣ በቴሌግራም፣ ወዘተረፈ የተዛባ መረጃን ፣ ውሸትን፣ ጥላቻን ፣ ልዩነትን ፣ መጠራጠርን ፣ ሴራን ፣ ወዘተረፈ የሚነዛ ተከፋይና ምንደኛ ስብስብ ሲሆን፤ ሶስተኛው አለማቀፍ ሚዲያውን የተዛባ መረጃ የሚመግብ ምድብተኛ ነው ። አራተኛውና ሶስተኛው ምድብተኛ ተመጋጋቢ ናቸው። በዚህ ምድብ ነጮች ስፒን ዶክተርስና ሎቢስትስ ( spin doctors & lobbyist ) የሚሏቸው ሲሆን አላማቸው እንደቅደም ተከተላቸው አንድን ርዕሰ ጉዳይ እነሱ ከሚፈልጉት አቅጣጫ አንጻር እንዲተረጎምና እንዲበየን ጥረት ማድረግ ሲሆን ሎቢስቶች ደግሞ ከፍተኛ ገንዘብ እየተከፈላቸው የመንግስት ባለስልጣናትን ፣ የምክር ቤትና የሰኔት አባላትን በማግባባትና በማባበል ከቀጠራቸው ወይም ከከፈላቸው መንግስት ወይም ቡድን ጎን ለማሰለፍ ግፊት የሚያደርጉና የሚያግባቡ ናቸው። እነዚህ አካላት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አለማቀፍ ሚዲያውንና እንደ መንግስታቱ ድርጅት ያሉ አለማቀፍ ተቋማትን የሚመግቡና ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ናቸው።
ይህ የሕዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ከፍ ሲልም የዲፕሎማሲ ቅጥልጥል በሀገር ውስጥ በጌታቸው ረዳ የሚዘወር ሲሆን የውጭው ደግሞ “ የትግራይ ወዳጅነት አገናኝ ቢሮ “( Tigray Friendship Liaison Office ) በተሰኘ ተቋም አማካኝነት በቀድሞው ዲፕሎማት ወንድሙ አሳምነው እንደሚመራ መስፍን አማን የተባሉ ጸሐፊ በፍትሕ መጽሔት ፣ 3ኛ አመት ፣ ቁ111 ፣ ታህሳስ እትም ላይ “ከወታደራዊ ሽንፈት ወደ ዲፕሎማሳያዊ ትንቅንቅ “ በሚል ርዕስ ባስነበቡን ማለፊያ መጣጥፍ ተረድተናል።
በመንግስታቱ ድርጅት የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሀኖም በጀኔቭ በመንግስታቱ ድርጅት ሕዝብ ልማት ፈንድ ባልደረባው ዶ/ር ኪዳኔ አብርሃ ከአምባሳደር ብርሀነ ገብረክርስቶስ ጋር በመቀናጀት የአውሮፓውን የዲፕሎማሲና የአለማቀፍ ሚዲያውን እጅ ለመጠምዘዝ እየተሯሯጡ ሲሆን ከአትላንቲክ ማዶ በአሜሪካ ያለው ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ለአምባሳደር ፍስሐ አስግዶም በአደራ መሰጠቱን እኝሁ ጸሐፊ ጠቁመዋል ።
የቀድሞው ታጋይ ሙሉጌታ ገብረህይወት ( ጫልቱ ) ከመለስ ዜናዊ ወዳጅ አሌክስ ዲወል ጋር በመሆን የትህነግን አርባ ለማሳመር ላይ ታች እያሉ ይገኛሉ። የኦባማ የብሔራዊ ደህንነት የቀድሞ አማካሪና የአዲሱ የባይደን አስተዳደር ተሿሚ ሱዛን ራይስ ፣ የአሜሪካ የልማት ተራድኦ (ዩኤስኤይድ) ዳይሬክተር ጌይል ስሚዝ ፣ የሒውማን ራይትስ ዋች ኃላፊ ኬኔትስ ሮዝ ከእነ የማነ ኪዳኔ ( ጀማይካ )ጋር በመሆን አለማቀፍ ሚዲያውንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ስራ ተጠምደዋል። በትግራይ ክልል የተካሄደውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከዘር ማጥፋትና ማጽዳት ጋር ለማጣረስ ላይ ታች የሚለው ሌላው ዶ/ር መሀሪ ታደለ ነው።
በዚያ ሰሞን በማህበራዊ ሚዲያው ስለትህነግ ሽንጡን ይዞ ሲሟገት የነበረው ማርቲን ፕላውት ፤ የቢቢሲ የአፍሪካ አርታኢ ዊል ሮስ ቢቢሲ አማርኛንና ትግረኛን በትህነግ ካድሬዎችና ደጋፊዎች በመሙላት እና ኖርዌያዊው ሸተል ትሮንቮል እንደነ ቢቢሲ ባሉ አለማቀፍ ሚዲያዎች በመቅረብ ለከሀዲው ትህነግ በመወገን የተዛባና የሐሰት መረጃ በመንዛት ሊታደጉት ብዙ እየደከሙ ነው።
ስታሊን ገብረስላሴ ( ስምን መልዓክ ያወጣዋል እንዲሉ፤ ጆሴፍ ስታሊን በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሶቪየት ዜጎችን የጨፈጨፈ ሰው በላ ገዥ ነው፤)፣ አሉላ ሰለሞንና ዳንኤል ብርሀኔና ሌሎች የትግራይ ሚዲያ ሀውስ ሰዎች ደግሞ የሀገር ቤቱንና የውጭውን የትህነግን የፕሮፓጋንዳ ማሽን መካኒኮች ናቸው። የትግራይ ጦርነት ባህላዊ ጨዋታው ነው። ትግራዋይ ሁሉ ትህነግ ነው ሲሉ ካለማፈራቸው ባሻገር በሀገሪቱ ከተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች ጀርባ እጃቸው እንዳለበት አይካድም።
ከፍ ብዬ የጠቃቀስኋቸው የቀድሞ ታጋዮች ፣ አምባሳደሮች፣ በአለማቀፍ ተቋማት የሚሰሩ ፣ የውጭ ሀገር ዜጎች ፣ አክቲቪስቶች በመማጸኛ ከተማው መሽጎ ከነበረው ከሀዲው የትህነግ ስብስብ እና አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ሀገሪቱ ካሰማራቸው ጭፍራዎቹ ጋር በመቀናጀትና በመናበብ የፈጠራ ትርክታቸውን ከመለፈፋቸው ባሻገር የተዛባና ሐሰተኛ መረጃ በመደበኛውና በማህበራዊ ሚዲያው በመንዛት ሀገራችንን በጦር መፍታት ቢሳናቸው በወሬ ለመፍታት ሌት ተቀን እየተረባረቡ ነው።
የትህነግን ሞት ለማሳመር እየባዘኑና እየተሯሯጡ ነው ። በተወሰነ ደረጃ አለማቀፍ ሚዲያውንና ተቋማትን ማደናገርና ከጎናቸው ማሰለፍ ችለዋል። ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ ትግራዋይንና የተቀረውን ዜጋ ዛሬ ድረስ በተሳሳተና በሀሰተኛ መረጃ እያደናገሩት ነው ። የተሳሳተና የተዛባ መረጃ ምን ማለት ነው ? እንዴት መከላከል ይቻላል ? በለውጡ በተለይ በሕግ ማስከበሩ ዘመቻ ሰሞናት ለምን በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር ቻለ ? ዛሬ ላይስ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? ለሚሉ ጥያቄዎች በክፍል ሁለት እመለስበታለሁ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በሀቀኛና ጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!!
አሜን።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 18/2013