በእምነት
ሞት፣ ሰቆቃ፣ ሃዘን፣ ከል መልበስ እስከመቼስ ነው? ማንስ ነው ይህንን የግፍ ግፍ ማስቆም የሚችለው? በመተከል ላይ ያለው ግፍ “የአካባቢ ግጭት” ተብሎ ይሆናል፤ ግን አሁን ከዛ አልፏል? መቼስ ነው እዛ ያለው ሰው በላ አረመኔ ወንበዴ “ጁንታ” ተብሎ ተጠርቶ ብቻ የሚያበቃው፤ የማያዳግም እርምጃስ የሚወሰድበት መቼ ይሆን? መቼስ ነው የጁንታውን ቡድን ድባቅ የመታንባቸውን ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ልከን ይህንን ሰው በላ ደምስሰን የመተከልን እናቶችና አባቶች እንዲሁም ህፃናት ነፃ የምናወጣው? ለእኔ ጥያቄ ሆኖብኛል።
እንደዚህ አይነት ለማሰብ እንኳ የሚሰቀጥጥ የግፍ አገዳደል በንፁህ ኢትዮጵያውያን ላይ ሲደርስ እንደ ዜጋ እንደ መንግስት ምን እያሰብን ይሆን? እናቶች በቀስት ሰውነታቸው ተወጋግቶና አንጀታቸው በስለት ተዘርግፎ መሬት እንደምንም ሲወድቁ ህጻናት በማያውቁት ባልኖሩበት ሀጢያት ፍዳቸውን ሲበሉና እዚህም እዚያም የስቃይ ድምጽን ሲያሰሙ ስለምን ዝምታንና ትእግስትን መምረጡ አስፈለገ ? ወይስ ይህ ገዳይ ቡድን የማይታይ፣ የማይጨበጥ መንፈስ ነው?
የህወሓትን ጁንታ ቡድን በሶስት ሳምንት ጦርነት እንዳልነበር ያደረገ መከላከያ ሰራዊታችን እነዛ ዘመናዊ ድሮንና ሌሎቹም የጦር መሳሪያዎች፤ ጦርና ቀስት እንዲሁም ቢላዋ ይዞ ምስኪኖችን የሚጨፈጭፈውን የጫካ አውሬ የሚያድኑትና የእጁን የሚሰጡት መቼ ይሆን? ወይስ ከዚህ በላይ ምን ያህል ሞትና እልቂት ሲከሰት ነው የሚጠበቀው? በእውነት መንግስት ይህንን ነገር ሊያስብበት፤ ሊያስብብት ብቻም ሳይሆን ምንም ጊዜ ሳያባክን ፊቱን ወደ መተከል ወንበዴዎች ማዞር አለበት።
በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድተው ወደስፍራው በማቅናት የህዝቡን፣ የተበዳዩንና የሟቹን ተወካዮች ማነጋገራቸው እንደ አንድ እርምጃ ሊወሰድ የሚችል ነው። ነገር ግን የእርሳቸውን እግር ተከትሎ የተፈጸመው ዘግናኝ ጭፍጨፋ በእውነት አሳፉሪ ከመሆኑም በላይ የንቀቱንም ጥግ ያሳየበት ነው፤ ለእኔ። በመሆኑም ጉዳዩ በዝምታ ሊታለፍ የሚገባው አይደለም ።
እርስዎ መተከል ላይ ተወካዮቻቸውን ስላነጋገሩላቸው ሞት የቀረላቸው የመሰላቸው ስለጉብኝትዎም የእግዚአብሔርን ስም ጠርተው ያመሰገኑት የሃይማኖት አባቶችና እናቶች ዛሬም የእርስዎን እርዳታ መፈለጋቸው ግልጽ ነው። በስፍራው ያሉም አመራሮች በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው እልቂት ሊቆጫቸው እንደ ሰውም ሊያሳዝናቸው በተገባ ነበር። ግን ደግሞ እነሱም የጉዳዩ ተባባሪ እስኪመስሉ ድረስ ችግሩን በዝምታ እያለፉት ነው። ለዚህ ማሳያው ደግሞ የአማራ መገናኛ ብዙሀን ለመተከል ኮማንድ ፖስት መሪው ኮሎኔል አያሌው በየነ ስለ ጉዳዩ ጥያቄ አቅርቦላቸው የሰጡትን ምላሽ በተመለከተ እንዲህ አቅርቦ ነበር።
ጋዜጠኛ፦ “የመተከልን እልቂት ለምን ወታደሮቹ ማስቆም አልቻሉም?”
የመተከል ኮማንድ ፖስት መሪው ኮሎኔል አያሌው በየነ፦ “እኔን አይመለከተኝም ሂዳችሁ የመንግስት አካልን ጠይቁ”
ጋዜጠኛ፦ “ማንን እንጠይቅ?”
ኮሎኔል አያሌው ፦ ” ሌላ ስራ አለብኝ” ብለው ስልኩን ጠረቀሙት።
ኮሎኔል አያሌው የዜጎችን ህይወት ከመታደግ በላይ ምን ዓይነት ስራ አጣድፏቸው ይሆን? የመንግስት አካል ጠይቁ ማለትስ ትርጉሙ ምንድን ነው? ከሳቸው በላይ የመንግስት አካልስ ማነው? በጣም ያሳዝናል፤ ያሳፍራል። ምናልባት ብናገር ለእኔም ደህንነት እሰጋለሁ ብለው ይሆናል፤ ነገር ግን እርሳቸው አንድ ሰው ናቸው፤ ሞት እንኳን ቢመጣ ለህዝባቸው ወግነው ቢሞቱ ክብር ጀግንነት ነው፤ ታሪክም ሰውም አምላክም ሁሉም ያስባቸዋል።
እንዲህ ግን እኔ ላይ መጥፎ ነገር ከሚደርስ እናቶች ይታረዱ፤ ህጻናት ይለቁ፤ ብሎ ጉዳዩን እርሳቸው መንግስት ላሉትና በውል ላልገለጹት አካል መስጠት አሳፋሪ ነው። እኔ እርሳቸውን ብሆን ይህንን ያህል እራሴን ከህዝቤ ካስቀደምኩ ሀላፊነቱንም እለቃለሁ የምመክራቸውም ይህንኑ ነው።
የመተከል ኮማንድ ፖስት መሪዎችስ ስራቸው ምንድን ነው? ወይስ ጉዳዩ ከአቅማቸው በላይ ነው? ከሆነም አሳውቀው አቅም ያለው እንዲመጣላቸው አመልክተው ከስፍራው ዞር ማለት ነው፤ አልያ ግን እነሱ እያሉ ንጹሃን በግፍ እንዴት ይለቁ ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው በጻፉት መልዕክትም “በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል የተፈጠረውን ችግር ከመሠረቱ ለመፍታት መንግስት አስፈላጊውን የተቀናጀ ኃይል እንዲሠማራ አድርጓል” ብለዋል ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ውስጥ በዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ጭፍጨፋ እጅግ አሳዛኝ ሆኗል ፤ በወገኖቻችን ላይ በተፈጸመው ኢሰብአዊ ተግባር በእጅጉ አዝኛለሁ፤ ችግሩን በተለያየ መንገድ ለመፍታት የተደረገው ጥረት የሚፈለገውን ውጤት እንዳላመጣም የጠላቶቻችን ዓላማ በጁንታው ላይ የሠነዘርነውን ብርቱ ኃይል ለመበተን ነው ይህ ግን የሚሳካ አይደለም፤ ካሉ በኋላ መንግሥት ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት አስፈላጊውን የተቀናጀ ኃይል እንዲሠማራ አድርጓል፤ የሚፈለገውን ውጤት ለማግኘት ሁሉም እንደ ከዚህ ቀደሙ በትኩረትና በኅብረት እንዲሠራ ጥሪ በማቅረብም አጠቃለዋል”።
አዎ እርሳቸው እንዳሉት ጁንታው ቡድን ላይ የተወሰደውን የተቀናጀ የተናበበ ሁሉም አመራር እንዲሁም ዜጋ “ሆ” ብሎ እንደተነሳበት አይነት ቆራጥ እርምጃ የመውሰጃ ጊዜው አሁን ነው። ይህንን ሰው በላ የጫካ አውሬ አፈር ማብላት ካልተቻለ ግን መዘዙ ከመተከል አልፎ ለሌላውም ማህበረሰብ መድረሱ አይቀርም። ያን ጊዜ ደግሞ አገራችን ጠላቶቻችን እንደሚመኟት አይነት ትሆናለችና እርምጃው ዛሬውኑ ይጀምር። አበቃሁ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 18/2013