ግርማ መንግሥቴ
ህይወት እንደ ወንዝ ውሃ አይደለም። አባጣ ጎርባጣ የበዛበት እንጂ፣ ዝም ብሎ አይወርድም፤ ወይም አይፈስም። ይህ ለሁሉም ነው። በትምህርትም ይሁን በንግድ፤ በግብርናም ይሁን በትዳር አለም … በሁሉም ዘርፍ ህይወት ከፈተና ነፃ ሆና አታውቅም። በመሆኑም ትልቁ ነገር ይዞ ወይም ሆኖ መገኘት ነው እንደሚባለው ፈተናውን መጥላት ወይም አለመፈተን ሳይሆን ፈተናውን ማለፍ ነው የሚጠበቀው።
ይህን ስንል በየትኛውም የህይወት መስመር ነውና ሁላችንንም ይመለከታል። ይመልከት እንጂ አንዳንዶቻችን ላይ ፈተና ከእነ ልጅ ልጆቹ ሊመጣ ይችላል። ላያስችል አይሰጥምና እናልፈዋለን። ከእነዚህ የህይወት መስመሮች አንዱ ደግሞ የጎዳና ህይወት፤ ወይም ጎዳና ተዳዳሪነት ነው።
ጎዳና ተዳዳሪነት፣ ወይም የጎዳና ህይወት ምንም አይነት ማብራሪያ ሳያስፈልገው ክብደቱም ሆነ አስቸጋሪነቱ ይታወቃል። በአንድ ወቅት “ጎዳና ነው ቤቴ” የሚል ሙዚቃ ተለቅቆ በተከታታይ ሲሰማ ነበር። በወቅቱ ሙዚቃው ከሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር በተውጣጡ ልጆች የተሰራ መሆኑ የተነገረለት (ዮዲት በምትባል ልጅ የተዜመ) ይህ ሙዚቃ ከቋጠራቸው ስንኞች መካከል፤
ጎዳና ነው ቤቴ
እራብ ጎረቤቴ
ችግር ጎረቤቴ
የላስቲኳ ቤቴ
ጎዳና ጎዳና ጎዳና . . .
ማሙሽ እና ሚሚ ቪላ ቤት አላችሁ
የኔማ ጎጆዬን ኑ ማ ላሳያችሁ
አንሶላ ብርድ ልብስ የሌለባት
የኔማ ጎጆዬ ካርቶኔ ናት . . . .
****************
ባይሆንልኝ እንጂ ከሞቀ ቤት መኖር
ከወላጆቼ ጋር እውል አድር ነበር፡፡
ጎዳና ነው ቤቴ ጎዳና ነው ቤቴ
የተወለድኩበት ኑሮዬና እድገቴ፡፡
ጎዳና ጎዳና ርስቴ ጎዳና
ልብሴ ነፋስ ሲሆን ቀለቤ ልመና፡፡
የሚሉት ስንኞች በተለያዩና ጉዳዩን በሚመለከቱ ስራዎች ወይም መድረኮች ተደጋግመው የሚጠቀሱለት ዜማ ሲሆን፤ አጠቃላይ ዜማውም የችግሩን ግዝፈትና የተቸጋሪው ሰቆቃ ከፍ አድርጎ ከመግለፅ ባለፈ እንከን የሚወጣለት አይደለም። ከጥበብ ስራዎች አላማና ፋይዳ መካከልም የዚሁ አይነት ማህበራዊ አገልግሎትን ማንሳትና በሚያስተምርና በሚያስተባብር መልኩ ማቅረብ ነውና ትያትር ቤቱም ሆነ ድምፃዊቷ ሊመሰገኑ ይገባል።
የጎዳና ተዳዳሪነትና የጎዳና ህይወት ላይ ላዩን ይህንን ይመስላል፤ ጠለቅ ብለው ካዩት ደግሞ (የተጋፈጡት እንደሚናገሩት) መሪር ነው። ስቃይና መከራ አብረውት አሉ። ከብርዱ ጀምሮ፣ የሰው ፊትን አክሎ፣ ጤናንና ማህበራዊ ህይወትን አናግቶና የወደ ፊት ህይወትን እስከማጨለም ድረስ ይዘልቃል። ከላይ እንዳልነው ፈተናው ብዙ ሲሆን መፍትሄው ደግሞ አንድ ነው – ፈተናውን ማለፍ!!!
ምናልባት ፈተናውን ማለፍ ሲባል ቀላል ይመስላል፤ ግን አይደለም። በርካታ ተባባሪዎችን ይፈልጋል። በተለይም በጎ አድራጎት ግለሰቦችንና ድርጅቶችን። እንደ አብዛኛዎቹ ድጋፍና እርዳታ ፈላጊዎች እናውራ በማለት እንጂ እራሳቸው በራሳቸው ከችግሩ አረንቋ የወጡ የጎዳና ተዳዳሪዎችም ሆኑ ሌሎች የሉም ማለት አይደለም፤ ሞልተዋል። የዛሬው ጉዳያችን እነሱ ባለመሆናቸው ስለ እነሱ አናወራም እንጂ ከራሳቸውም አልፈው ለሌሎች የተረፉም ቁጥራቸው ብዙ ነው።
ባልታሰበና ባልተጠበቀ ሁኔታ ወደ ጎዳና ህይወት የወጣችው ወጣት እመቤት ከበደ የዛሬዋ የዚህ አምድ እንግዳችን ነች። የትውልድ እና እድገት አካባቢዋ ሚዛን ቴፒ ሲሆን ድንገት ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ለጎዳና ህይወትና ፕላስቲክ ቤት ተዳርጋ ቆይታለች። በእዛው ህይወት ውስጥም ሆና ሁለት ልጆችን አፍርታለች።
እመቤት ሁለቱን ልጆቿን የወለደችው የትዳር ጓዴ ካለችው ባለቤቷ (እሱም ጎዳና ተዳዳሪ ነው) ሁለተኛው ልጃቸው በጣም እየታመመ ማሳከሚያ በማጣታቸው፤ ባለቤቷም ምንም አይነት ገንዘብ ማግኘት ባለ መቻሉ ተበሳጭቶ ብን ብሎ ጠፋ። በዚህም ምክንያት የጎዳና ህይወትን ከሁለት ህፃናት ልጆቿ ጋር ተጋፈጠችው። የትንሹ ልጇም ህመም ከእለት ወደ እለት እየከፋ እንጂ እየተሻለው ሊመጣ አልቻለም።
ሁሉም ነገር ሰማይ በላይዋ የተደፋ ያህል ሆነባት። በዚህ አይነት መሪር ሁኔታ ውስጥ ነው እንግዲህ የቀበሌ አመራሮች (ይመስሉኛል ትላለች) እየዞሩ ጎዳና ተዳዳሪዎችን መመዝገብ ጀመሩ። እመቤትም የመመዝገብ እድሉን አገኘች። ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከሚገኘው “መሰረት የሰብአዊ አገልግሎት ድርጅት” እንድትገባ ተደረገ፤ ገባች። አሁን እሷም ልጆቿም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ትናገራለች። (እኛም ተመልክተናል።)
“መሰረት የሰብአዊ አገልግሎት ድርጅት” በመገኘት እመቤትን ያነጋገርናት ሲሆን ሁሉ ነገሯ በከፍተኛ የደስታ ስሜት ውስጥ ነበር። ወዟ ግጥም እንዳለ ነው። “እዚህ ስመጣ እኔ እንደዚህ አልነበርኩም። እዚህ ነው የኔም የልጆቼም ህይወት የተለወጠው።” የምትለው የ27 አመቷ እመቤት በአሁኑ ሰአት እሷ ብቻ ሳትሆን ልጇም “ከዛ ሌት ተቀን ከሚያሰቃየው ህመሙ ተሽሎት በጥሩ ሁኔታ ላይ” እንደሚገኝም ትናገራለች።
ወደ “መሰረት የሰብአዊ አገልግሎት ድርጅት” ከገባች በኋላ ያለውን አጠቃላይ ሰብአዊ አገልግሎት በተመለከተም “ሁሉም ነገር በጣም ጥሩ ነው። እሷም (የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ መሰረት አዛገ) ምርጥና እሩህሩህ እናት ነች። ምንም የጎደለብን ነገር የለም። በቀን ሶስቴ ጥሩ ጥሩ ምግብ እንመገባለን። ዛሬ የበላነውን ነገ አንደግምም። ሌላ ነው የሚቀርብልን።
ለልጆቻችን ጭምር መክሰስ ሁሉ ይቀርባል። ህክምና ይከታተላሉ። ስልጠና ይሰጣል። ንፅህናችንን በተመለከተ ምንም አይነት ችግር የለም። ሁሉ ነገር የተሟላ ነው።” በማለት ነበር የመለሰችልን። (እኛም ተዟዙረን እንደተመለከትነው ሁሉም ነገር ፅድት ያለና ንፅህናን ለመጠበቅ የተመቻቸ ሁኔታ ነው ያለው።)
በሰብአዊ አገልግሎት መስጫው ድርጅት አስፈላጊውን ድጋፍና እርዳታ ከነ ልጆቿ እያገኘች ያለችው እመቤት ከድርጅቱ እያገኘች ያለችውን ድጋፍ ስትነግረንም በዚህ ብቻ አላበቃችም። የስልጠና እድል መኖርንም ነው የነገረችን፤ ድርጅቱ እየከፈለ፣ የሚቻለውንም በራሱ በተቋሙ በማሰልጠን ላይ እንደሚገኝም ትናገራለች፤ እኛም ተዟዙረን እንደተመለከትነው በድርጅቱ ውስጥ ልብስ ስፌት፣ ስፌት (ሌማት፣ መሶብ፣ ሰፌድ . . .) እና ሌሎች ስልጠናዎችም ይሰጣሉ።
“አሁን እኔ መንጃ ፍቃድ ለማውጣት ሾፌርነት እየሰለጠንኩ ነው ያለሁት። የንድፈ ሀሳብ ትምህርቱን ጨርሼ ወደ ተግባር ልምምዱ ገብቻለሁ። በጣም ደስተኛ ሆኜ ነው ስልጠናውን እየተከታተልኩ ያለሁት።
በጥሩ ሁኔታም እንደማጠናቅቅ እርግጠኛ ነኝ።” በማለት የድርጅቱን ድጋፍ፣ እንክብካቤና ያጋጠማትን እድል የምትናገረው እመቤት ከበደ፤ ድርጅቱ በርካታ ስልጠናዎችን የሚሰጥ ሲሆን መንጃ ፍቃድ ለማውጣት በስልጠና ላይ የሚገኙት፣ እሷን ጨምሮ 16 መሆናቸውንም ገልፃልናለች።
“ሹፍርናን እንዴት መረጥሽው?” በማለት ላቀረብንላት ጥያቄም “ሹፍርናን እወደዋለሁ፤ በፊትም ሚዛን ቴፒ እያለሁ ባጃጅ እነዳ ስለነበር አሁንም ስሜቴና ፍላጎቴ ወደ እዚሁ ሾፌርነቱ ስለሆነ ነው ይህንን የመረጥኩት” በማለት መልሳልናለች።
“የወደፊት እቅድሽስ?” ላልናትም “የወደፊት እቅዴ በሰለጠንኩበት ሙያ (ሾፌርነት) በመሰማራት እራሴንና ህዝብን ማገልገል ነው የምፈልገው። ልጆቼም የኔ አይነት እድል እንዳይገጥማቸው በእንክብካቤ በመያዝ ማስተማርና ለጥሩ ደረጃ ማብቃት እፈልጋለሁና ዋናዎቹ እቅዶቼ እነዚህ ናቸው።
ከእግዚአብሄር ጋር እኔም ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሼ እንደኔ ጎዳና የወጡትን በምችለው አቅምና ባለኝ ሁሉ መርዳትም እፈልጋለሁ። ይህን የምለው ደግሞ ችግሩን በሚገባ ስለማውቀውና ስላሳለፍኩትም ነው።” ያለችን።
“ሰው መቼም ወዶ ወደ ጎዳና አይወጣም” የምትለው እመቤት የጎዳና ህይወት እጅግ አስከፊና መራር እንደሆነም ነው ወደ ኋላ እያሰበች በሀዘን የምትናገረው። አሁንም በጎዳና ላይ ያሉትን ስታስታውሳቸውና ስታስባቸው ህይወታቸው ያስጨንቃታል። እሷን የገጠማትን አይነት እድል እንዲገጥማቸውም ትመኝላቸዋለች።
“ይብዙልን”
“ይብዙልን” የእመቤት ቃል ነው። ቃሉን ያመጣችበት ዋና ምክንያትም እሷ ያገኘችውን እድል ሌሎችም እንዲገጥማቸው በመመኘት ነው።
እንደሚታወቀው በሀገራችን በርካታ የጎዳና ተዳዳሪዎች አሉ። እነዚህን ሁሉ በአንድ አካል አስተናጋጅነት ተገቢውን ድጋፍና እንክብካቤ እንዲያገኙ ማድረግ አይቻልም። ይህን ማድረግ እንዲቻል ከተፈለገ አድራጊ/ፈፃሚ ሰብአዊና በጎ አድራጊ ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የዛኑ ያህል ሊኖሩ፤ በአግባቡም አገልግሎቱን ሊሰጡ ይገባል።
እመቤትም የምትለው ይህንኑ ነው። እመቤት በቅርብ የምታውቃቸውን የጎዳና ተዳዳሪዎች ህይወት ስትገልፀው በከፍተኛ ደረጃ አስቸጋሪ ነው። በመሆኑም ችግሩ ውስጥ ያሉ ወገኖች ከዚህ አይነቱ ህይወት ሊወጡ ይገባል። ይህ ደግሞ ሊሆንና ሊሳካ የሚችለው እናታችንን ወይዘሮ መሰረትን አይነት ሰዎችና ድርጅቶቻቸው ሲበረክቱ፤ ሲበዙ ነው ባይ ናት።
ሁሉም የጎዳና ተዳዳሪዎች ድጋፍና እርዳታ ፈላጊዎች ናቸው። ይህንን ድጋፍና እርዳታ ካገኙ ደግሞ ሁሉም መለወጥና የተሻለ መስራት፣ የተሻለ ህይወት መምራት የሚችሉ ናቸው። ይህ እንዲሆን ደግሞ “መሰረት የሰብአዊ አገልግሎት ድርጅት”ን የመሳሰሉ ተቋማት በብዛት ሊኖሩ ይገባል በማለትም እመቤት ሀሳቧን ትገልፃለች።
“ሌላ አስተያየት ወይም የምትይው ካለሽ?” ብለናትም “ያለኝ አንድ ሃሳብ ነው። እሱም የመጠለያ ማለትም ቤት ጉዳይ ነው። አዲስ አበባ የቤት ጉዳይ በጣም ችግር ነው። አሁን እኔን ከወዲሁ በጣም የሚያሳስበኝ የመኖሪያ ቤት ጉዳይ ነው።
ከዚህ ስወጣ ወዴት ነው የምሄደው? እኔም ልጆቼም ተመልሰን እንደ ገና አፈር ልንመስል ነው ማለት ነው? በመንጃ ፍቃዴ አማካኝነት ስራ ልይዝ እችላለሁ። ግን በአዲስ አበባ የቤት ኪራይን እንዴት እችለዋለሁ? ስለዚህ መንግስት ወይም ቀበሌ አንዲት ጠባብ ቤት ቢፈልግልን በቃ ሌላ ምንም አልፈልግም። ይህንን ብቻ ነው የማስቸግረው።” በማለት የወደፊት ስጋቷን ተናግራለች።
እኛም “መሰረት የሰብአዊ አገልግሎት ድርጅት” እያደረገ ያለውን ሰብአዊ ተግባርና እየተወጣ ያለውን አገራዊ ኃላፊነት እያደነቅን፤ ሌሎችም የእሱን አርአያነት እንዲከተሉ እያሳሰብን፤ ለእመቤት ከበደ እና ለልጆቿም የተሻለ ህይወት እየተመኘን ጽሁፋችንን እናጠቃልላለን።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2013