(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ) gechoseni@gmail.com
የሀገር አራራይ፤
የሀገራችን ፈተና አቤት አባዛዙ! የዘመናት ጉዞዋም እንዲሁ በመደነቃቀፍ የተሞላ ስለመሆኑ ምስክር መፈለግም ሆነ ተጠቃሽ ታሪክ ማሰስ የሚያስልግ አይመስለኝም፡፡ ሌላ ዋቢ ሳያሻ እኛው ልጆቿ ተብዬዎች ገበናችንን መዘክዘክ እንችላለን፡፡ እንዲያው ለነገሩ ለዕውቀትም ይሁን ለጸሎት እኛን መሰል የመከራ ማራገፊያ ብጤ ሀገራትን “እነ እከሌም አሉ!” ብለን መጠቋቋም እንችል ይሆን? ይህ ድምዳሜ ጨለምተኛ የሚያሰኝ ሳይሆን ለጨለማችን ምክንያቱን እንድናስስ የሚቆሰቁስ ማስታወሻ እንደሆነ አምናለሁ፤ ላፍታታው፡፡
“ለችግር የጣፈው ቢነግድ አይተርፈው!” ይላሉ ቀደምቶቹ ብሂለኞች፡፡ እውነት ነው፤ አንዱን ተራራ ስንወጣ ሌላ የአረንቋ ሸለቆ ይፈትነናል፣ እርሱን ስናልፍ ሌላ ስርጓጉጥ ያደነቃቅፈናል፣ ቁልቁለቱን ወርደን ሳናጋምስ የተራራ ግርዶሽ ከፊታችን ተገሽሮ ያቅራራብናል፡፡ እንዲሁ ታሪካችንን “በጥቁር ቀለም” እንደከተብን ሀገሬ ምን ያህል ታሪካዊ መስቀል እንደተኮሰች ለመወሰን ያዳግታል፡፡ ትናንትም ሆነ ዛሬ ነግቶ በመሸ ቁጥር “ነገ ደግሞ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን?” እየተባባልን እንደቆዘምን ልጆችና የልጅ ልጆች ወልደንና አሳድገን ለምንጅላትነት ወግ ደርሰናል፡፡ “አደራረሳችን” መድረስ ከተባለ በሀገራችን ሲዘመር የኖረው የአራራይ ዜማ ደጋግሞ ለእምባ መዋጮ ዳርጎናል፡፡
ሀገሬን እያንገዳገዷት ያሉት የፈተና ዓይነቶች በመልክም ሆነ በግዝፈታቸው ከአሁን ቀደምቶቹ የከፉ ብቻ ሳይሆኑ በአቻነት የሚጠቀስላቸውን መሰሎችን ለመጠቆምም ያዳግታል፡፡ የዥንጉርጉርነታቸው ቀለማት በርከት ያሉ ቢሆንም ወቅታዊ ችግሮቻችንን እያቧደንንና እየነጠልን የቅኝት ያህል እንፈትሻቸዋለን፡፡ ቅኝታችን መልክና ደርዝ እንዲኖረውም በሶስት ጎራ ከፍሎ መመልከቱ የተሻለ መስሎ ታይቶኛል፡፡
ቀዳማይ – አንገት ያስደፉን የውስጥ ገመናዎቻችን፤
ሀ – የብዙ ሀገራት ታሪክ የሚያስተምረን የወራሪዎች ጦርና የጦር ወሬ ተዘውትሮ የሚያጋጥመው ከውጭ ጠላቶች እንጂ ከራስ ጓዳ በተነሱ ሀገር በቀል ጀብደኞች እንዳይደለ ያስገነዝበናል፡፡ በቤተሰብ ላይ የወረራ ዘመቻ ተከፈተ የሚል ዜና የተሰማው ምናልባትም በእኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ለራሳችን ማፈሪያ፣ ለሌሎች ሀገራትም መጠቋቆሚያ የሆነው ይህ ክስተት ከተፈጸመ ገና የአረሩ ሽታ ከአየሩ ላይ አልጠፋም፡፡ ያሳዝናል፡፡እንደ ዋርካ የገዘፈን የሀገር መድኅን የመከላከያ ሠራዊት ከራሱ አካል በተነጠለ ቅርንጫፍ ተወጋ፣ ተወረረ፣ ተማረከ፣ ተገደለ፣ ተሰቃየ ማለት ለተናጋሪውም ሆነ ለሰሚው ግራ ሊያጋባ ይችላል፡፡ አዎን የተፈጸመው በእኛው ምድር በትህነግ ከሃዲያን አማካይነት ነው፡፡ ክህደቱ በቀናት ዕድሜ የመከነና የተቀለበሰ ቢሆንም ጥሎብን ያለፈው ጠባሳ ግን እንዲህ በቀላሉ ይሽራል ተብሎ አይገመትም፡፡ ከሰብዓዊ ጉዳቱ፣ ከኢኮኖሚው ውድመት፣ ከማሕበራዊ ቀውሱ በማይተናነስ ሁኔታ በሕዝባችን ላይ ያሳረፈው የሕሊና ቁስል ሙሉ ለሙሉ ለመፈወስ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ የሥነ ልቦና ቀውሱ የሚነካካው ብዙ አካላትን ነው፡፡ ከግለሰቦችና ከቡድኖች ጉዳት ባሻገር የሕዝብ ለሕዝብ ጤናማ ወንድማዊ/ እህታዊ ግንኙነት ላይ ያጠላውን ጥላ ለመግፈፍም ጊዜ ይጠይቃል፡፡
በመከላከያ ሠራዊታችን፣ በአማራና በአፋር የቃል ኪዳን ጓዶች ውስጥ የተዳፈነው የቁጭትና የእልህ ወላፈን ተንኖ እስኪጠፋ ድረስ መታገስ ብቻም ሳይሆን ብዙ የፈውስ ሥራዎች ሊሠሩ ግድ ይላል፡፡ የፈራረሰውንና የወደመውን የሀገር ሀብት አቧራ አራግፎ እንዲያንሰራራ ለማድረግም ለዓመታት ትዕግሥት የታከለበት ቀጠሮ መያዝ ያስፈልጋል፡፡ የቀጠሮው ርዝመት እንዲያጥርና ፈውሳችን እንዲፈጥን ካስፈለገ ግን ወሳኞቹ እኛ ዜጎች ስለሆንን አጀንዳው በእጃችን ላይ ነው፡፡ እንዴታውን ላብራራ፡፡
“በከፍታ ሥልጣን ላይ ያለህ መንግሥታችን ሆይ! መከራችንን አቅልልልን! አበሳችንን አንከባልልን! ክፉዎችንም አስወግድልን! ወደ መሰል ፈተና እንዳንገባም በብርታትህ ጠብቀን፣ ደግፈን! አሜን!” እያልን እንደ ሰርክ ጸሎት የፖለቲካ መሪዎችን መማጸን ብቻ ሳይሆን ዜጎችም ከአቅማችን ቋት ቆንጥረን እጃችንንና ፈቃዳችንን ልንዘረጋ ይገባል፡፡ በግልጽ ቋንቋ መናገር ካስፈለገ ዜጎች ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ዛሬና አሁን በሥነ ልቦና የፈውስ ርብርቡ ላይ በቀዳሚ ሠልፈኛነት ለጥሪው ምላሽ ሊሰጡ ይገባል፡፡ እርግጥ ነው ተስፋና እምነታቸው የተሸረሸረ ብዙ ዜጎች ውስጣቸው በባዶነትና በስቅቅ ተሞልቶ “የመኖርና ያለመኖር” ተቃርኖ ውስጥ ወድቀው እያቃሰቱ መመልከት ከዜግነት ግዴታ ጎን ለጎን ሰብዕናንም ይፈታተናል፡፡
በሀገር ተስፋ እንደማይቆረጥ፣ በወቅት ወለድ ወጀቦች ከመናወጥ ባሻገር የደመቀ ብርሃን እንደሚጠብቀን በግማሽ ልብ ለሚያነክሱ ዜጎች አስረግጠን ልናጽናናቸው ይገባል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ የቢሮክራሲው ገደኞች ሕዝብን አያጎሳቁሉ፡፡ ነጋዴዎች የጉስቁልና መቃብር እየቆፈሩ በስግብግብነት አይስከሩ፡፡ እንዲያገለግሉን ታክሳችንን ሆጨጭ አድርገን የሾምናቸው “ምን ግዱዎች” በሕዝብ ስሜት ከማላገጥ ራሳቸውን ያቅቡ፣ የሥልጣን አብሾ አናታቸው ላይ የወጣው ፖለቲከኞችና “የማሕበረሰብ አንቂ ተብዬ” ወበከንቱዎች ከማላገጥ አደብ ይግዙ፡፡ ለበጎ ተግባር ተሰጥተናል የሚሉ የተራድኦ ድርጅቶች በሕዝብ መከራ ለመክበር አያልሙ፡፡ የሚዲያና የኪነ ጥበባት ባለሙያዎች በዚህ ፈታኝ ወቅት ወገባቸውን ታጥቀው የስጋታችንንና የፍርሃታችንን ቀበቶ በማስፈታት ያጀግኑን፡፡ ሌሎችን በይደር የቤት ሥራ አቆይቻቸዋለሁ፡፡
ለ – የገዳዮች ቀስት ይሰበር፤
ሀገሬ የተከናነበችውን የሀዘን ማቅ ከላዩዋ ላይ አውልቃ ፀአዳ ሸማ እንድትጎናጸፍ የዜጎች ሁሉ የሰርክ ጸሎት እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ጸሎታችን ወደ ጸባኦት ፈጥኖ እንዳይገሰግስ ሰማያቱን የዘጋው ኃይል የንጹሐን የደም ጩኸት ሳይሆን እንደማይቀር አምናለሁ፡፡ ከፖለቲካችን የቆሻሻ ክምር ውስጥ እየተነነ ከል የሚያስለብሰን የጨካኞች ግፍ እስካልቆመ ድረስ የካህናትና የሼኮች ምልጃ፣ የሕዝብ ምህላና እግዚኦታ ወደ ፈጣሪ መንበር ስለመድረሱ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡
ቀን ቀን ስለ ሰላም እየሰበኩ “አራዊቶች በሚፈነጩበት የሌሊት ክፍለ ጊዜ” ደግሞ ሰይፍና ቀስት የሚመዙት “የዲያቢሎስ ዘመዶች” ተለይተው ለፍርድ እስካልቀረቡ ድረስ “የእርስ በእርስ ግጭት” በሚል የሚሞካሸው ዘር ተኮር የደም ጥማተኞች ሴራ ማባሪያ ላይኖረው ይችላል፡፡
የአንዳንድ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የደላሎች አንደበት ማር እንደሚያንጠባጥብ እንኳን ለእኛ ለዜጎች ለእነርሱ ለራሳቸውም ይጠፋቸዋል ተብሎ አይገመትም፡፡ ዘርና ብሔር እየተለየ እንደ ተራ የዒላማ መፈተኛ የሚፈሰው የንፁሃን ደም በምድራዊ ሕግ ብቻ ሳይሆን በመለኮት ችሎት ፊትም እንደሚገትር ገዳዮች እንዴት ጠፋቸው? አስገዳዮችስ ለምን ጨለመባቸው? ተባባሪዎቻቸውስ እንደምን ተሰወረባቸው? እያልኩ እጠይቃለሁ፡፡
አንድ ሰው የንፁሃንን ደም አፍስሶ እንዴት በግፍ የቆሸሸውን ጭንቅላቱን ትራስ ላይ አሳርፎ እንቅልፍ ይናፍቃል? በእጁ ላይ የፈሰሰው ደምስ እየተንጠባጠበ እንዴት እንጀራ ቆርሶ ወደ አፉ ይልካል? ሁኔታውን ሲያስቡት ያሳምማል፣ ሲያውጠነጥኑትም ስሜትን አንዝሮ ያስለቅሳል፡፡
ዜጎች ሆይ! እንደ ኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ከጥሻ ጥሻ፣ ከቦታ ቦታ፣ ከክልል ክልል እየተሽሎከለኩ የንፁሃን ዜጎችን ደም ለማፍሰስ የሚሸምቁትን ጨካኞች በፍትሕ ፊት ለመገተር እንደምን ተሳነን? በግሌ “የመንግሥት ያለህ!” በሚል የተናጥልና የቡድን ጩኸት ብቻ መፍትሔ ማምጣት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ የጩኸታችንን ቅኝት አስተካክለን “የሕዝብ ያለህ!” ብለን ልንጠራራና የግፈኞቹን እጅ ጨምድደን ከፍርድ ሸንጎ ፊት ልንገትራቸው ግድ ነው፡፡ “በሕግ አምላክ!” የሚለው መማጸኛ አቅም ከድቶት የሚልፈሰፈስ ከሆነም “በሕዝብ አምላክ!” ብለን እርስ በእርስ ዘብ ልንቋቋም ይገባል፡፡
ሐ – ቤትኛው ወረርሽኝ፤
የኮቪድ ተስቦ ከትናንቱ በከፋ ሁኔታ ዛሬ በሕዝባችን ውስጥ ደንገላሳ እየረገጠ ብዙዎችን ለህልፈት፣ በርካቶችንም በአልጋ ላይ ጥሎ እየፋነነብን እንዳለ ቤታችን ምስክር ነው፡፡ ከዛሬ ነገ ይደርስልን ይሆን ወይ? እያልን
የምንፅናናበት “የክትባት ዜናም” የተስፋው ብልጭታ ቢኖርም ለተግባራዊነቱ ግን ድህነታችን ሳያዘገይብን እንደማይቀር ጠርጥረናል፡፡ እኛ ስንዘናጋ ወረርሽኙ እየተበረታታ እነሆ ሰደዱ ተቀጣጥሎ “ስንት ሰው በኮቪድ ተያዘ? ስንት ሰውስ ሞተ?” የሚሉ መርዶዎችን ከማስተናገድ እፎይ ያልንበትን ቀን አናስታውስም፡፡ የጤና ባለሙያዎቻችንን ተማጽኖና ምክር “አሜን!” ብለን እስካልተገበርን ድረስ “ኡኡታችንና ስቅቃችን!” ከቀን ወደ ቀን እየበረታ መሄዱ አይቀርምና ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ ይህም የዜጎች ኃላፊነት ነው፡፡
ካልዓይ – የውጭ ተግዳሮቶች፤
የውስጥ ተግዳሮቶቻችንን ተረባርበን የመመከቱን ፍልሚያ ገና በአሸናፊነት ሳንወጣ ሌሎች በርካታ ባዕዳን ወለድ ችግሮች እንደተጋፈጡን እያደመጥንና እያስተዋልን ነው፡፡ ያለመታደል ሆኖ ጂኦግራፊው ባጎራበተን ቀጣና ውስጥ የታከኩን አንዳንድ ጎረቤት ሀገራት ከበረከትነት ይልቅ “መርገምት” መሆናቸውን በፖለቲካ ዓይናፋርነት ብናድበሰብሰውም ነበር ታሪካችን ፍርጥርጡን እንደሚያወጣ ልንዘነጋ አይገባም፡፡ በሀገራችን ጉዳይ እንቅልፍ አልባዎቹ የፈርኦን ልጆች የእርጥባን እጃቸውን እየዘረጉ “ጃስ” የሚሏቸው ተላላኪዎቻቸው የሚያደርሱት ጥፋት ከጥንቱ የተለየ አይደለም፡፡ ዛሬም እየተገበሩት ያለው ያንኑ የእውር ድንበር ሴራቸውን ነው፡፡
ከወደ ምዕራቡ ዓለም የተዘረጋው የጀብደኞች ሴራም እንዲሁ ጉዳቱ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ገና ለገና ሞሶባችን ላይ ጉርሻ መወርወራቸው እንደ ትልቅ ውለታ እየተቆጠረ በውስጥ ጉዳያችን ላይ እጃቸውን እየዘረጉ ካልፈተፈትን እያሉ ማቅራራት ለዜጎችም ሆነ ለሉዓላዊነታችን ክብር አይመጥንም፡፡ ባዋቀሯቸው አንዳንድ የተራድኦ ተቋማትና “አይዟችሁ” እያሉ የልብ ልብ በሰጧቸው የብዙኃን መገናኛዎች አማካይነትም የክፋት አሲዳቸውን በአየሩ ላይ እየነሰነሱ መበከሉን ተያይዘውታል፡፡ ለእነዚህ አምባገነን ኃይላት የምክቶሽ ሚናውን መጫወት ያለባቸው በዋነኛነት የዲያስፖራው ማሕበረሰብና ምሁራን ናቸው፡፡ የምሁራን “ዝም አይነቅዝም” ፍልስፍና ወይንም “መንግሥት እንደ ብጤቱ ይወጣው!” ይሉት እምነት ለ“እናት ሀገር ጥሪው” ምላሽ ሊሆን አይችልም፡፡
ሣልሳይ – የእናት ጡት ነካሽ ውጭ አደሮች ተግዳሮት፤
በየሀገራቱ ከተበተኑት ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መካከል ብዙዎቹ በሀገር ፍቅር ነደው ለሕዝብ ፍቅር የተሰጡ መሆናቸው ሃሳብ ብቻ ሳይሆን ግብራቸው ጭምር ዋስ ጠበቃ ሆኖ ይቆምላቸዋል፡፡ በአንጻሩም ፖለቲካው በዘራው የእንክርዳድ ማሳ ውስጥ መሽገው በሀገርና በሕዝብ ጥላቻ የሰከሩ ጥቂት “ጉድ ፈላብን ባዮች” በማሕበራዊ ሚዲያና በሥልጡን ሀገራት አደባባዮች ላይ እየፈነጩ የሚያስተላልፉትን በመርዝ የተለወሰ ቅስቀሳ እያደመጥንና እያስተዋልን ዓመታት አስቆጥረናል፡፡ እነዚህ በተበላሸ የፖለቲካ ኮሲ ላይ የተፈለፈሉ ፀረ ሀገር እፉኝቶች በዓለም አቀፉ ሕግጋት በተደነገጉትም ሆነ የኢንተርፖል ፖሊስ በሚተዳደርበት ደንብና ሥርዓት መሠረት ልካቸውን እንዲያውቁ መደረጉ ጊዜ የማይሰጠው የመንግሥት የቤት ሊሆን ይገባል፡፡ በዚህ ጉዳይ የዜጎች ግፊት ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡
የሀገር ኤሎሄ በርክቷል፡፡ የጎልጎታው ጉዞም ሀገሬን የከበዳት ይመስላል፡፡ ዜጎች ሆይ! መስቀልና ሚስማር አዘጋጅተው ቤዛዊት ሀገራችንን ከግራና ከቀኝ ሊቸነክሯት የሚጥሩትን የሄሮዶቱስ፣ የጲላጦስና የይሁዳ የመንፈስ እጆች ተባብረን በመጠፈር ባዘጋጁት “የሃማ” መስቀያ ላይ ራሳቸው ዋንጫውን እንዲጎነጩ የዜጎች ሕዝባዊ ፍርድ ፈጥኖ ሊወጣባቸው ይገባል፡፡ ሰላም ይሁን!