መላኩ ኤሮሴ
የሀዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ የሶስት ትላልቅ መንገዶች መገናኛ ነች። የወልቂጤ ሆሳዕና፣ የቡታጅራ ሆሳዕና እንዲሁም የወላይታ ሶዶ ሆሳዕና መንገዶች በሆሳዕና እምብርት ላይ ይገናኛሉ። ሶስቱ መንገዶች በመሃል ከተማ ላይ መገናኘታቸው ከተማዋ ለትራፊክ መጨናነቅ እንዲሁም ለትራፊክ አደጋ መበራከት ዳርጓት ቆይቷል።
ይህንን የትራፊክ መጨናነቅ እና አደጋ ለመቀነስ ሶስቱ መንገዶች ከዚህ ቀደም ከሚገናኙበት የከተማ ማዕከል ወጣ ባለ ቦታ ለማገናኘትና የከተማውን የትራፊክ ፍሰት ለማሳለጥ በ2010 ዓ.ም አዲስ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ተጀምሮ ነበር።
የሆሳዕና ከተማ ዲዛይንና ግንባታ መንገድ ስራ ፕሮጀክት ተብሎ የተሰየመው አዲሱ የመንገድ ፕሮጀክት የወልቂጤ ሆሳዕና መንገድን ከከተማው ማዕከል ወጣ ብሎ ከሆሳዕና ቡታጅራ መንገድ ጋር ለማገናኘት እንዲሁም የሆሳዕና ቡታጅራ መንገድን ከሆሳዕና ወላይታ ሶዶ መንገድ ጋር ለማገናኘት ነበር የተጀመረው።
የፕሮጀክቱ ሙሉ ወጪ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ሲሆን 194 ሚሊየን 630 ሺህ ብር በጀት ተይዞለት ዮሴፍ ተከተል በተሰኘ ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ በመገንባት ላይ ይገኛል።
አምስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ሶስቱን የአስፋልት መንገዶች የሚያገናኘው የመንገድ ፕሮጀክት በአንድ አመት ከስምንት ወር ወይም በ20 ወራት ለማጠናቀቅ ታቅዶ የነበረ ሲሆን እስካሁን ድረስ ማጠናቀቅ የተቻለው 36 ነጥብ 75 በመቶ ብቻ መሆኑን በትራንስናሽል ኢንጂነር የፕሮጀክቱ ተጠሪ መሃንዲስ አቶ ይታያል በዓለም ይገልጻሉ።
በከተማ ውስጥ የሚገነባ ፕሮጀክት በመሆኑ እና የግለሰብ ቤቶች እንዲሁም የውሃ፣ የመብራት እንዲሁም የቴሌ መሰረተ ልማቶችን ማስነሳትን የሚጠይቅ መሆኑን ያብራሩት አቶ ይታያል፤ እነዚህን ቤቶችን እና መሰረተ ልማቶችን የማስነሳት ስራ እጅግ አዳጋች እንደነበር ያብራራሉ። በዚህም ምክንያት ፕሮጀክቱ መጋተቱን ይናገራሉ።
የወሰን ማስከበር ስራው እጅግ ውስብስብ እንደነበር የሚያነሱት አቶ ይታያል፤ ከግለሰቦች ባልተናነሰ መልኩ የመንግስት ተቋማት ትብብር ማነስ ለችግሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ይላሉ። ግምታቸው ከተከፈለ ረጅም ጊዜ የሆናቸው የመብራት ሀይል ቤቶችንም ለማስነሳት ከባድ ሆኖ እስካሁንም ያልፈረሱ ቤቶች አሉ። ከዚህም በተጨማሪ ቤቶቹ እንዳይፈርሱ የመንገድ ዲዛይን ይቀየር በማለት ውዝግብ እያስነሱ ነው ብለዋል።
እንደ አቶ ይታያል ማብራሪያ፤ ከዚያ በተጨማሪ አንዳንድ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መስመሮች ግምታቸው በዶላር ካልተከፈለ ተብሎ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ጋር ውዝግቦች ነበሩ። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የመንግስት ተቋም እንደመሆኑ በዶላር መክፈል አይችልም። በመሆኑም በብር እከፍላለሁ ሲል የኤሌክትሪክ ሀይል ግን በዶላር መሆን አለበት በሚል የተነሳው ውዝግብ ለመንገዱ መጓተት የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ይጠቅሳሉ።
ከከተማው ህዝብ ጋር የተፈጠረው ቅሬታ ለመንገድ ግንባታው መጓተት ሌላኛው መንስኤ ነው። ፕላኑ ተጭበርብሯል የሚል ቅሬታ ከህዝቡ ሲነሳ ነበር። 30 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው መንገድ ይገነባል ተብሎ ተጀምሮ ወደ 22 ሜትር ወርዷል በሚል የተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሰረተ ቅሬታ ነበር። ጥያቄያቸውን ይዘው እስከ ፌዴራል እንባ ጠባቂ እና የክልሉ ፕላን ኮሚሽን ድረስ ሄደዋል። ይህም የራሱ ድርሻ ነበረው። መጨረሻ ላይ ግን ችግሩ በመግባባት ተፈቷል።
የፕሮጀክቱን ዲዛይንም ግንባታውንም የሚያካሂደው ተቋራጩ በመሆኑ ዲዛይኑን እና ግንባታውን ጎን ለጎን እንዲያካሂድ ተደርጓል። ይህም ከህብረተሰቡ የሚነሳውን የመልማት ጥያቄ ቶሎ ለመመለስ ተግባራዊ የተደረገ አሰራር ቢሆንም ለመጓተቱ የራሱ ድርሻ ነበረው ብለዋል።
ተቋራጩም የራሱ የአቅም ውስንነት ችግር አለበት። የሀብት፣ የፋይናንስ፣ የማሽነሪ እና የሰው ሀይል እጥረት ችግርም ይስተዋላል። ይህም ፕሮጀክቱ በታሰበለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሌላኛው ተግዳሮት ነው።
የፕሮጀክት ማናጀሩ አቶ አክሊሉ ሺፈራው የአቶ ይታያልን ሀሳብ ያጠናክራሉ። የወሰን ማስከበር ችግር እና የኮንትራክተር አቅም ማነስ እንዲሁም የግብዓት እጥረት ለመንገድ ግንባታው መጓተት አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ከዚያ ባሻገር የኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገሪቱ መግባትን ተከትሎ ድርጅቱ በርካታ ሰራተኞችን ለመቀነስ ተገዶ እንደነበር ገልጸው፤ ይህም ለችግሩ የራሱን ድርሻ ማበርከቱን ጠቁመዋል። አካባቢው ከፍተኛ የዝናብ መጠን ያለበት መሆኑም ችግሩ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።
የመንገድ ፕሮጀክቱ በታቀደለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ በተለይም የአማካሪ ወጪው እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችል ያብራሩት አቶ ይታያል፤ ይህም መንግስትን ለተጨማሪ ወጪ ሊዳርገው እንደሚችል ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ይታያል ማብራሪያ፤ የፕሮጀክቱ መጓተት ከተማዋን ኢኮኖሚያዊ ዋጋ እያስከፈላት ነው። እስካሁን ድረስ ለመንገድ ግንባታው መፍረስ ካለባቸው ቤቶች 97 በመቶ የሚሆኑ ቤቶች ፈርሰዋል። 3 በመቶ ብቻ ባለመፍረሱ ፕሮጀክቱ ከሚጠበቀው በላይ ተጓተዋል።
ከዓመታት በፊት የፈረሱ ቤቶች የንግድ ስራቸው ተቋርጦ እንዲፈርስ ነው የተደረገው። ሰዎቹ ደግሞ ወደ ሌላ ያልለማ ቦታ ሄደው እየኖሩ ነው። ያፈረሰው 97 በመቶ የሚሆን ነዋሪ ቤቱን ቢኖርበት እና ቢዝነሱን ቢሰራበት ኖሮ ከፍተኛ ገቢ ነበር።
መንገዱ በታቀደበት ጊዜ ተጠናቆ ቢሆን ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች እንደሚኖሩት የተናገሩት አቶ ይታያል የከተማዋን ኢኮኖሚ በማነቃቃት፣ የኢንቨስትመንት ፍሰትን በማፋጠን፣ እንዲሁም የትራፊክ አደጋን በመቀነስ ከፍተኛ ሚና ይጫወት ነበር።
ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በዚህ መልኩ ሀሳባቸውን ቢሰጡንም የፕሮጀክቱ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2013