ፍሬህይወት አወቀ
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚኖረው ህዝብ ብዛት ከሌሎች ከተሞች የላቀ እንደሆነ እማኝ ማቅረብ አያስፈልግም። በየመንገዱ እየተገፋፋ የሚተላለፈውና በየመንደሩ ያለው ነዋሪ ለዚህ ምስክር ነው። በነዋሪዎችዋ ብዛት መተንፈሻና መላወሻ ማጣቷ የሚነገርላት አዲስ አበባ ከተማ ዕለት ተዕለት እየጨመረ የመጣውን ነዋሪ የመኖሪያቤትም ሆነ ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለማሟላት አልቻለችም።
እንዲህ ያለው ችግር ወደሌሎች ከተሞችም እየተሻገረ የከተማ ኑሮን አስቸጋሪ እያደረገው ይገኛል። እንዲህ ላለው ችግር መፈጠር የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም የከተሞች አመሰራረት ትልቅ ድርሻ እንዳለው የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ከተሞች ሲመሰረቱ በወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ ሳይሆን፣ የወደፊቱንም ባገናዘበ መንገድ መሆን እንዳለበት መረጃዎች ቢያመላክቱም አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ የክልል ከተሞች ወደፊት የሚመጣውን ሰፊ የህዝብ ቁጥር ታሳቢ ያደረገና የነዋሪውን ጥያቄ መመለስ እንዲችሉ ሆነው አልተመሰረቱም።
በከተሞች በየጊዜው እየጨመረ ከሚመጣው የህዝብ ቁጥር ጋር የተጣጣመ የመኖሪያ ቤት ጥያቄ እንዴት ባለ መንገድ እየመለሱ እንደሆነ ለመዳሰስ ባደረግነው ጥረት የደብረብርሃን ከተማን ተሞክሮ ለዛሬ ይዘን ቀርበናል።
ደብረብርሃን የኢንዱሥትሪና የኢንቨሥትመንት ከተማ በመሆን በምትሰጠው አገልግሎትና በተለያዩ እንቅስቃሴዎቿ ለውጥ እያስመዘገበችና እያደገች በመሆኗ ለኑሮ ተመራጭነቷ እየጨመረ መጥቷል። የነዋሪዎችዋ ቁጥርም ዕለት ዕለት በመጨመር ላይ ይገኛል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የመኖሪያቤት ፍላጎትና የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች ጥያቄ በስፋት እየተነሳ መሆኑ ይነገራል።
የከተማ አስተዳደሩ ጥያቄዎቹን እንዴት እያስተናገደ ነው? የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን አገልግሎት ጽህፈት ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ኃይለማርያም ንጉስ ተሞክሮአቸውን አካፍለውናል።
እንደ አቶ ኃይለማርያም ማብራሪያ በከተማዋ ውስጥ የተቋቋመው አምራች ኢንደሥትሪ ዘርፍ መሥፋፋትን ተከትሎም ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሰውና ከአጎራባች ክልሎች ወደ ከተማዋ የሚመጡ የከተማዋ ነዋሪ ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል። የመኖሪያቤት ፍላጎቱም በዚያው ልክ ጨምሯል። አሁን ያለው መረጃ እንደሚያሳየው ከ190 በላይ የተደራጁ የመኖሪያ ቤት ህብረት ስራ ማህበራት ህጋዊ ሰውነትና ዕውቅና አግኝተው ቦታ እየተጠባበቁ ሲሆን፣ የ633 የመኖሪያ ቤት ህብረት ስራ ማህበራት ደግሞ የመረጃ ማጣራት ሥራ በመሰራት ላይ ይገኛል።
የማጣራቱ ሥራ በቅርብ ይጠናቀቃል። ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ለመኖሪያቤት መሥሪያ የሚውል መሬት ለማግኘት ለካሳክፍያ የሚሆን ገንዘብ የባንክ ደብተው ከፍተው ሲቆጥቡ የነበሩ ተገልጋዮች በከፊል ሲያገኙ ክፍያ ፈጽመው የሚጠባበቁም ጥቂት የሚባሉ እንዳልሆኑ ይናገራሉ ።
‹‹በማህበር ተደራጅተው ቤት ለመሥራት ጥያቄ የሚያቀርቡና የመሬት ዝግጅቱ ሊጣጣም አልቻለም። የከተማ አስተዳደሩ መዘጋጃ ቤት ትልቅ ማነቆ የሆነበት ለመኖሪያቤት መሥሪያ ቦታ ተለይቶ ካሳ ተሰጥቶአቸው ከቦታቸው እንዲነሱ የሚጠበቁ አርሶአደሮች በወቅቱ ሳይለቁ የአዝመራ ጊዜ ይደርሳል።
አዝመራውን ተሰብስቦ እስኪገባ የሚወስደው ጊዜ በመሬት ዝግጅት ላይ ከፍተኛ መጓተት በማሥከተሉ የነዋሪውን የቤት መሥሪያቦታ በሚፈለገው ፍጥነትና ጊዜ አዘጋጅቶ መሥጠት አልተቻለም›› ያሉት ሀላፊው በነዚህና በተለያየ ምክንያት ለማህበር የሚሰጠው የመኖሪያ ቤት መሥሪያ መሬት በአስተዳደር ወሰን ሥር እንዲሆን ተደርጓል። የከተማ ወሰን እየሰፋ ሲሄድ የቤት ግንባታው የገጠር ቀበሌ ማዕከላት ላይ ያርፋል።
የገጠር ቀበሌ ማዕከላት የአርሶ አደር ቦታዎች እንደመሆናቸው የካሳ ክፍያው በወቅቱ ካልተፈጸመ የመኸርና የበልግ አዝመራ ደርሶ አርሶአደሩ ወደ እርሻ ሥራ ይገባል። በዚህ ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ማህበራት፣እንዲሁም ተቋሙ ካለበት የሰራተኛና የመዋቅር ችግር አንጻር ማስተናገድ አልተቻለም። ሌላው ችግር የገበሬውን መሬት ለመጠቀም በካቢኔ ተወስኖ የማስፋፊያ ፈቃድ ይጠየቃል።
አቶ ኃይለማርያም እንዳሉት ከተማዋ በፍጥነት እያደገች በመሆኗ ለመኖሪያ ቤት፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለማህበራዊ አገልግሎት፣ ለኢንዱስትሪ ወዘተ ታስቦ የተዘጋጀው የመሬት አጠቃቀም ፍላጎቱ ሰፊ በመሆኑ ለአሥር አመት ያገለግላል የተባለው የከተማዋ መዋቅራዊ ዕቅድ ወይንም ፕላን በአራት አመት ውስጥ ተጠናቅቆ ቦታው በአሁኑ ጊዜ ሞልቷል።
ምንም እንኳን የከተማ መዋቅራዊ ፕላን የግድ በየአስር ዓመቱ የሚከለሥ ቢሆንም ከተማ አስተዳደሩ እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። ከተማው ሊሰፋ በሚችልባቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮችና መኖሪያ አካባቢዎችን በማስፋፊያ የመጠቀም አማራጮች ተወስዷል።
በዚህም ለመኖሪያ ቤት የህብረት ስራ ማህበር የሚውል 780 ሄክታር መሬት 2011 ለ 2012 ዓ.ም የክልሉ ምክር ቤት አጽድቋል። ቦታውም ከዚህ በፊት ካሳ ከፍለው መሬት ያላገኙ የወታደር መመሪያ የሚፈቅድላቸው መከላከያ፣ የጸረ ሽብር አድማ ብተና፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ ልዩ ሀይል እንዲሁም መምህራን፣ አካል ጉዳተኛና የኤች አይቪ ተጋላጮችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
ከ780 ሄክታር መሬት ላይ የቀረው 360 ሄክታር መሬት በ2013 ዓ.ም 663 ሆነው ለተደራጁ የመኖሪያ ቤት ህብረት ስራ ማህበራት ለማስተላለፍ እየተሰራ ነው። በይዞታው ላይ ከሚገኙ አርሶአደሮች ጋር በመወያየት መግባባት ላይ በመደረሱ ማህበራቱ የመኖሪያቤት መሥሪያቦታውን በቅርቡ እንደሚረከቡ ይናገራሉ።
የከተማ አስተዳደሩ በአስር ዓመት የሚከለሰውን የከተማ መዋቅራዊ ፕላን ሳይጠብቅ አማራጮችን በመውሰድ ላይ ቢሆንም በከተማዋ ያለው የመኖሪያ ቤት ፍላጎትን ማሟላት አልተቻለም። ያሉትን አማራጮች በሙሉ አቅም ለመጠቀም አስሮ የያዛቸው ጉዳይ እንዳለም አቶ ኃይለማርያም አንስተዋል።
ይህም የገበሬው የመሬት ካሳ ክፍያ ወይም የሰብል አላባ መስሪያ አዋጁ ወጥቶ ነገር ግን ማስፈጸሚያ መመሪያው ለአንድ አመት ተኩል ሳይወርድ በመዘግየቱ ነው። የገበሬውን መሬት ማስተላለፍ የሚቻለው የካሳ ክፍያ መክፈል ሲቻል ብቻ ነው። ይህን ተግባራዊ ማድረግ ባለመቻሉ ከተማ አስተዳደሩ በሙሉ አቅሙ እንዳይሰራና በከተማዋ ያለው የመኖሪያ ቤት ህብረት ስራ ማህበራት እንዲጓተት ምክንያት መሆኑነ ይገልጻሉ።
ከዚህ ውጭ በደብረብርሃን ከተማ ያለው መልካም ተሞክሮ መሬት የሚወስዱ ማህበራት በሀላፊነት እንዲወስዱ መደረጉ ነው። ዛሬ የተለያዩ ሂደቶችን አልፈው በመምጣት መሬት የሚወስዱ ማህበራት በሂደት ውስጥ ባልተገባ ውለታ አልፈው ይሆናል።
ነገር ግን ማህበሩ ቦታውን ካገኘ በኋላ ቦታውን ያገኘው በሌብነት ወይም በማጭበርበር ከሆነ እየገነባ ባለበት ሁኔታም ይሁን ገንብቶ ቢያጠናቀቅ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የገነባው ወይም የተቀበለውን ቦታ ለህዝብና ለመንግስት የሚያስረክብበት ስምምነት አለ። ለዚህም ማህበሩ አስቀድሞ የሚስማማበት ጉዳይ በመሆኑ ፈርሞ ቦታውን ይረከባል። ከተማ አስተዳደሩ በዚህ ህገ ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል ጥረት እያደረገ ይገኛል። ይህም በየትኛውም ክልል ተግባራዊ ያልሆነ ተሞክሮ መሆኑን አቶ ኃይለማርያም አንስተዋል።
እርሳቸው እንዳሉት በከተማዋ ሰፊ የሆነ የተደራጀ የማህበር ቦታ እንዳለ ሁሉ ሰፊ የሆነ የማህበራት የቤት መስሪያ የቦታ ጥያቄም አለ። በዚህ ዙሪያ ከተማው በአቅሙ እየሰራ ቢሆንም ከከተማ አስተዳደሩ አቅም በላይ በሆኑ ችግሮች በፕላን፣ በመመሪያ መጓተትና በቦታ ጥበት ምክንያት ከተማው መስጠት የሚገባውን ቦታ ሳይሰጥ ቀርቶ የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና አቅርቦቱ ሳይመጣጠን ቆይቷል።
ይሁን እንጂ በአሁን ወቅት ችግሩ እየተባባሰ ከመምጣቱ በፊት በጣም በሰፊው እየተሰራ ነው። በዘንድሮ ዓመት በእርግጠኝነት ለ633 ማህበራት እውቅና የመስጠትና ለ50 በመቶ ለሚሆኑት መሬቱን ለማስረከብ ይሰራል። ይህም በአባላት ብዛት ሲታይ ከሰባት ሺህ እስከ ስምንት ሺህ ይደርሳል። እነዚህ 633 ማህበራት ከ12ሺህ500 እስከ 13ሺህ የሚደርስ አባላት ያላቸው ናቸው። ነገር ግን ከእነዚህ መካከል በትዳር አጋር ቦታ ኖሯቸው የሚመጡ ይኖራሉና እነሱ በቀጥታ ይወጣሉ።
በከተማዋ ያለውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ከዚህም በላይ በእጥፍ ቢጨምር አሁን እጥረቱን ለመቅረፍ ከምታደርጉት ጥረት ባለፈ በቀጣይ ምን የተሻለ ዕቅድ ይዛችኋል በሚል ላነሳንላቸወ ጥያቄ በሰጡን ምላሽ፤ በከተማዋ ከገጠር በበለጠ በከተማ ያለው ፍልሰት ከፍተኛ ነው። ይህም ሲባል የራሱ ስራ ያለው፣ በንግድ ስራና በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ግለሰቦች አሉ።
እነሱን ሊመጥን የሚችል የመኖሪያ መንደሮችን መፍጠር ያስፈልጋል። ይህን ታሳቢ ያደረገ ስራ እየተሰራ በመሆኑ በቀጣይ ዘመናዊና የደብረብርሃን ከተማን ፕላን ታሳቢ ያደረገ የመኖሪያ መንደሮችን መፍጠር ነው። ለዚህም ሪልስቴት ወይንም ቤት በመገንባት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ማሳተፍ አንዱ አማራጭ ሆኗል።
ሪልስቴት ከዚህ በፊት በከተማዋ ያልነበረ ሲሆን በአሁን ወቅት ግን ስምንት ትላልቅ የሪልስቴት የግንባታ ፈቃድና ልምድ ያላቸውን ለማሳተፍ ፈቃድ ተሰጥቷል። በቅርቡም ግንባታ ይጀምራሉ። ሁለተኛው ገበሬው ከሚገባው በላይ እንዳይፈናቀል ማድረግ የሚችል ከተሜነትን መጠቀም ላይ እየተሰራ ነው። ይህም የጋራ መኖሪያ ቤት ሆኖ ከ28 እስከ 30 አባላት በጋራ እየሆኑ በሚሰጣቸው የከተማ መኖሪያ ቦታ ላይ ጥሩ የመኖሪያ መንደር በራሳቸው መገንባት እንዲችሉ ይደረጋል።
መሬት ላይ ያለውንም ለንግድ አገልግሎት መጠቀም እንዲችሉ የሚፈቅድ መመሪያ ያለው ጥናት እየተካሄደ ይገኛል። ይህም በቅርቡ ተፈጻሚ ይሆናል። እነዚህ ሁለት ተጨማሪ አማራጮችን በመጠቀም በከተማዋ የሚፈጠረውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ጥያቄ ለመመለስ ከተማ አስተዳደሩ ዝግጁነቱን እያጠናከረ ይገኛል።
ከዚህ ውጭ አንድ ሰው ከየትም ይምጣ ከየት የደብረብርሃን ከተማ ነዋሪ ስለመሆኑ መግለጫ ካለው፣ ከመጣበት አካባቢ መኖሪያ የሌለውና የመንግስት ሰራተኛ ከሆነ ቦታ የማግኘት መብት አለው። ይህም ነጋዴው ከሰራተኛው ጋር ሰራተኛውም ከነጋዴው ጋር አንድ ላይ ተደራጅቶ ሲመጣ ዓላማው ቦታ ማግኘት ስለሆነ ቦታ ያገኛል። ነገር ግን ከተማ አስተዳደሩ ትስስር ያለው ከመምህራን እና ከመከላከያ ጋር ብቻ በመሆኑ መምህራን እና መከላከያ እንደሌሎቹ ተራ ሳይጠብቁ ከሚዘጋጀው ቦታ ላይ ከ20 እስከ 30 በመቶ ቅድሚያ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
ይህንንም ከተማ አስተዳደሩ ተግባራዊ እያደረገ ነው። ለአብነትም 2011 / 2012 ዓ.ም ከ117 በላይ የመኖሪያ ቤት ህብረት ስራ ማህበራትን ማስተናገድ የተቻለ ሲሆን ከእነዚህ መካከል መከላከያና መምህራን መካተታቸውን አንስተዋል።
‹‹ደብረብርሃን ከተማ አስተማማኝ የሆነ ጸጥታ ያለባት ከተማ በመሆኗ ከፍተኛ የሆነ የኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ እየተስፋፋባት ይገኛል። በተጨማሪም ያልተገባ የአገልግሎት አካሄድን በማስቀረትና ተገልጋዩም ለሚያነሳቸው ማንኛውንም ጥያቄዎች ያለምንም ውጣ ውረድ በአጭር ጊዜ መልስ በመስጠት ቀልጣፋ አገልግሎት እየተሰጠ ነው››በማለት መልካም ሥራዎች መኖራቸውን አንስተዋል። እኛም ሥራቸውን እንዲገፉበትና ተግባራቸው ለሌሎችም አርዓያ እንዲሆን ተመኘን።
የደብረብርሀን ከተማ ነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት የተለያዩ አማራጮች ተዘጋጅተዋል፤
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2013