አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማት በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ብዙኃን የኅብረተሰብ ክፍሎች ዋነኛ መተዳደሪያቸው እየሆኑ ነው። ተቋማቱ የቁጠባና የብድር አገልግሎቶችን መስጠት ከጀመሩበት ከአስራ ዘጠኝ ሰማኒያዎቹ ዓመታት ወዲህ በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ከእጅ ወደ አፍ ከሆነው የአኗኗር ዘይቤ በመላቀቅም ላይ ናቸው። ራስን ቤተሰብንና አካባቢን መለወጥ ወደሚያስችልበት ደረጃ እየተሸጋገሩ ስለመሆናቸው በየአካባቢዎቹ የሚታዩ አብነቶች ማሳያዎች ናቸው።
ተቋማቱ በነዚህም ጥረቶቻቸው ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ግለሰባዊና ቤተሰባዊ የአኗኗር ዘይቤ መቀየር ብቻ ሳይሆን ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የሚካሄደውን ጉዞ ለማሳካትም አስተዋጿቸው ከፍ እያለ መጥቷል። ይህ መሆኑ በራሱ በአነስተኛ ካፒታል ለሚንቀሳቀሱ ታታሪዎች የሥራ ባህል ለማሳደግም ሆነ ልማታዊ የሥራ መስኮች እንዲፈጥሩ አማራጭ መንገድ ሆኖላቸዋል።
እዚህ ላይ ከአነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ሀገራዊ ተልዕኮና ጠቀሜታ አንፃር በዋነኛነት ጎልቶ እየታየ ያለው ለኅብረተሰቡ የቁጠባን ባህል እያስተማሩ የሚገኙ መሆናቸው ነው።
የሚፈለገው ደረጃ ደርሷል ባይባልም እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቤት ለቤት በመዘዋወር፣ የፊት ለፊትና የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች በመስራት፣ በመገናኛ ብዙኃን፣ በማስታወቂያዎችና በስፖንሰርሺፕ አግባቦች ስለ አገልግሎቶቹ እና ምርቶቹ አስፈላጊነትና ጠቀሜታዎቹ ተከታታይነት ያላቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት ይከናወናሉ።
የእነዚሁ የፋይናንስ አገልግሎቶች ተጠቃሚዎችም እንደየሀገሮቹ ታሪካዊና ነባራዊ ሁኔታ በተለያዩ ምክንያቶች (በትምህርት ወደኋላ በመቅረት፣ መንገዶች ባለመስፋፋት፣ መብራት ባለመኖር፣ መንግሥታት አናሳ ትኩረት በመስጠት፣ ባህላዊና ሥነልቦናዊ ተጽዕኖዎች መንሰራፋት፣ እንደየትምህርት ደረጃቸውና እንደየአቅማቸው ሥራ ላይ የሚቀጠሩበት ዕድል ያለመመቻቸት … ወዘተ) በድህነት አረንቋ ውስጥ እንዲማቀቁ አድርጓቸዋል።
በዚህ ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ችግር ለዘመናት የምግብ ዋስትና ችግራቸውን እንኳን ሳያረጋግጡ እየማቀቁ የሚኖሩ ሀገሮች በ21ኛ ክፍለ ዘመንም ቢሆን በአብዛኛው ከሰሀራ በታች የሚገኙ ሀገራት መሆናቸው ነው። እነዚህም ሀገሮች ድህነትን በመቅረፍ እንቅስቃሴያቸው አርአያ ለመሆን ብርቱ ጥረት ከማድረግ ይልቅ ብስለት በሌለው ፖለቲካ እየተመሩና እየተወዛገቡ የግለሰቦችን ወይም የጥቂት ቡድኖችን የስልጣን ዕድሜ እያራዘሙ ይኖራሉ።
በዚህም ኋላቀር ባህላዊና ሥነልቦናዊ አስተዳደራቸው ሳቢያ የዜጎቻቸውን ዘርፈ-ብዙ ማህበራዊ ሕይወት ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር ካለመቻላቸውም ባሻገር እየተተራመሱ ባሉበት ይዳክራሉ።
ለሕዝቡ ከድህነት ያለመውጣት በርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶችን ማቅረብ የሚቻል ቢሆንም በዋነኛነት ከነባራዊ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሁኔታ ጋር አብረው የማይዛመዱ የእርስ በእርስ ግጭቶች መበራከት፣ የውጭ ኃይሎች ለስትራቴጂያዊ ጥቅማቸው ሲሉ የእጅ አዙር ጦርነቶችን ማስኬድ፣ አብዘኛዎቹ ምርቶቻቸው የግብርና ውጤቶች መሆንና ይህም ግብርና በመስኖ ሳይሆን በዝናብ ምርት ጥገኛ መሆን፣ መንግሥታትም በበኩላቸው እነዚህን ችግሮች ለመፍታት አዳዲስ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በየጊዜው ማሻሻል ያለመቻል፣ … ይጠቀሳሉ።
በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ከአርባ በላይ የመንግሥት፣ የግልና፣ የአክሲዮኖች አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማት እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ። ከነዚህም ተቋማት አብዘኛዎቹና ብዙኃን የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚያገለግሉት በመንግሥትና በሕዝብ ባለቤትነት ስር ያሉ ናቸው። እንደሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ከአስራ ዘጠኝ ሰማኒያዎቹ ዓመታት በኋላ ከተቋቋሙት መካከል ግዙፎቹና የተሻለ አቅም አላቸው የሚባሉትም የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም፣ የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም፣ ደደቢት ብድርና ቁጠባ ተቋም፣አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም እንዲሁም የደቡቡ ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ናቸው። እነዚህም አምስቱ ግዙፍ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የየራሳቸው መልካም ተመክሮዎች ያሏቸው ሲሆን ይህ አጭር ቅኝት የሚያተኩረው ግን በኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ተመክሮዎች ላይ ነው።
ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በ1989 ዓ.ም የተቋቋመ የብድርና ቁጠባ ፋይናንስ አገልግሎቶችን የሚሰጥና ከተመሠረተ ሃያ አራት ዓመታትን ያስቆጠረ ተቋም ነው። ተቋሙ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመሠረተው በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት በሚገኙና በወቅቱ የምግብ ዋስትና ችግር በነበረባቸው አራት ወረዳዎች ነበር።
እነዚህም ወረዳዎች በሀዲያ ዞን ባደዋቾ፣ በጉራጌ ዞን ቸሃ፣ በወላይታ ዞን ዳሞት ወይዴና በከምባታ ጠምባሮ ዞን የኦሞ ሽለቆ ወረዳዎች ናቸው። ተቋሙ ሲመሠረት አምስት መስራች የአክሲዮን ባለቤቶች እንደነበሩ ሲታወቅ አምስት መቶ ሺህ ብር የተከፈለና ሁለት ሚሊዮን ብር የተፈረመ መነሻ ከፒታልን ታሳቢ ያደረገ ነበር።
ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ የተቋሙን ተልዕኮና ራዕይ በቁርጠኝነት የሚያሳልጡና ሕዝባዊና መንግሥታዊ አገልግሎቶችን የሚሰጡ 19 ዲስትሪክቶችና 223 ቅርጫፎች አሉት። እነዚህም አደረጃጀቶች እንደ ቀድሞው በደቡብ ክልል ብቻ የሚገኙ ሳይሆኑ በአዲሱ የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጭምር የተደራጁ ናቸው።
ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ለብዙኃን የኅብረተሰብ ክፍል የቁጠባ ባህል በማስተማርና የብድር አገልግሎት በመስጠትም በሁለቱም ክልሎችና በየክልሎቹ በሚገኙ የከተማ አስተዳደሮች ለሚኖሩ በአነስተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ባለውለታ ነው ማለት ይቻላል።
በሁለቱም ክልሎች በተደራጁ ከአራት ሺህ በላይ ቀበሌዎች በሁሉም ተደራሽ በመሆን ያስቆጥባል፣ ያበድራል፣ ማበደር ብቻ ሳይሆን የተበደሩትን ገንዘብ ዕዳ ሳይሆንባቸው ወይም ውዝፍ ውስጥ ሳይገቡ እንዲመልሱ ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል። ከመበደራቸው አስቀድሞ የተበደሩትን ገንዘብ ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውንና አካባቢያቸውን በተጨባጭ መለወጥ በሚያስችላቸው ልማት እንዲያውሉም ከላይ በተጠቀሱት መንገዶች ተገቢውን ግንዛቤ ያስጨብጣል።
በወልደ አማኑኤል ጉድሶ (ሀዋሳ)
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2013