ከመምህር አሰምሬ ሣህሉ
በሕይወት ውስጥ ጥያቄ አንስተን መልስ የማናገኝላቸው ወይም ጊዜ ራሱ መልስ የሚሰጥባቸው በርካታ ጥያቄዎች መኖራቸው እሙን ነው። «እንዴት ተፈጠርን?» ለሚለው ጥያቄ አንድም ሁለትም መልስ መስጠት የሚቻል ቢሆንም፣ ለምን ተፈጠርን? እንዴት እንኖራለን? ከሚሉት መሠረታዊ ጥያቄዎቻችን ሌላ ማህበራዊ ግንኙነቶቻችንን የተመለከቱ፣ ኢኮኖሚያዊ መሠረታችንን የሚነኩ፣ ፖለቲካዊ አካሄዳችንን የሚዳስሱ በርካታ ጥያቄዎች እናነሳለን።
የበርካታዎቹ ጥያቄዎቻችን መነሻና መድረሻ በእነዚህ በሦስቱ ዓውዶች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ቢሆንም እንደኛ በሦስተኛው ዓለም ለሚኖር ሰው (ሕዝብ) ደግሞ የጥያቄዎቻችን ማጠንጠኛ ደግሞ፣ ፖለቲካው ወይም ላዕላይ መዋቅሩና እርሱን በሚዘውረው አካል ላይ ያተኩራሉ። ጥያቄውም ጤናማ ይመስለኛል።
እናም እንዲህ እንላለን፣ ማን ያስተዳድረን? በምን ያስተዳድረን? እንዴት ያስተዳድረን? ሕገ- መንግሥቱ ምን ይላል? የላዕላይና ታህታይ መዋቅሩ መስተጋብር ሲታይ ምን መልክ አለው? የታህታይ መዋቅሩ አሠራር ሲፈተሽስ ምንን ያሳያል? ቢሮክራሲው እንዴት ተቀላጥፎ ይስራ? ቀላል ጥያቄዎችን አካብዶ ያለመፈጸም አሰራራችንን እንዴት እናስኪደው? በማንኛውም መስክ የአመለካከት ስንኩልነትን እንዴት እናስወግድ? እንዲህም ማለት በሕዝብ ብዛትም ይሁን በመሬት ስፋት፣ የትምክህት ምክንያት አድርጎ የማየትን፣ በስፋትም ሆነ በሕዝብ ቁጥር ማነስን ደግሞ የመጨቆን ምክንያት አድርጎ የማቅረብን ከሳሽነትና ወንጃይነት፣ ቀድሞ በመታገልም ሆነ ኋላ ከመቀላቀል አንጻር ራስን ግንባር ቀደም አድርጎ የማየት ግብዝ አስተሳሰባችንን እንዴት እናርመው? ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚገኙ ከኢኮኖሚም ሆነ ፖለቲካዊ ወንጀል ጋር ተያይዘው የሚገኙ ጥፋቶችን የምናርምበት መንገድ ምን ይሁን? ወዘተ… ብለን መጠየቅና ለእነዚህም መዋቅራዊና ነቢባዊ የሆኑ ጊዜያዊ ምላሾች መስጠት ይቻላል።
የመልሳችን ቁምነገር፣ በሬዲዮም ሆነ በቴሌቪዥን፣ ወይም በአደባባዮች ላይ፣ በቃል መነገሩ አይደለም፣ ቁምነገሩ በስብሰባ አዳራሾች የሚወራውን ማድመጡም ሆነ መደመጡ አይደለም። ቁምነገሩ፣ መሬት ላይ ወርዶ የሚሰራው ሥራ ከሚነገረው ጋር አልጣጣምም፤ ብሎ ማስቸገሩ ነው።
ይህን ለማድረግ ያለመቻል ልምሻችንን የምናክመው እንዴት ነው? ይህንን ቃልን ከተግባር ጋር ያለማዋሃድ ሰንካላነታችንን የምናቃነው እንዴት ነው? ይህ ስህተታችንን ከመቀበል የሚጀምር ይመስለኛል። የሚሰራውን ሥራ እና የምንደርስበትን ግብ፣ በገንዘብ፣ በጊዜና በሰው ኃይል ማቀድና ለትክክለኛ ተፈጻሚነቱ መትጋት የተገባ ነው።
እዚህ ላይ ልናነሳቸው፣ የሚገቡን ታላላቅ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ቀውስ ጥያቄዎቻችንን ማንሳት ከቶውንም አይቸግርም። የብዙዎቹ ጥያቄዎቻችንን መልስ ግን ተጠቅልሎ፣ የምናገኘው በፖለቲካዊ እሳቤዎቻችን ውስጥ መሆኑ ነው፤ ችግሩ። ስለዚህም ነው፤ አንዱን የማህበራዊ ፍትህ መዛባት ጥያቄ ስናነሳ ክሩ ተጠንጥኖ የሚገኘው ፖለቲካው ላይ ነው። ማህበራዊና ፖለቲካዊ ወይም ኢኮኖሚና ፖለቲካው መተሳሰራቸው ባልከፋ፤ ነገርግን ፖለቲካው ለኢኮኖሚያዊው ፍትህም ሆነ ለማህበራዊ ፍትሁ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ አሳሪ መሆኑ ነው።
ሥራ ለመወዳደር ስትሄድ ሥራውን ትችላለህ ወይ ሳይሆን የትውልድ ሐረግ ቆጠራው አያራምድህም፤ ይህንንም በክልል ሕገ-መንግሥታት ላይ ተጠንቅሮ ታገኘዋለህ። እርሱም ባልከፋ ብለህ ስትተወው እንኳን፣ አንዳንድ ስፍራ (ቤኒሻንጉልን ይመለከቷል) መኖርም ትከለከላለህ።
እኛ ኢትዮጵያውያን እንዳለመታደል ሆኖ እስካሁን በነበሩት ዘመኖቻችን በድምጽ ብልጫ የራሳችንን መንግሥት፣ ራሳችን መስርተን አናውቅም፤ ስለዚህም ራሱን የሾመው መንግሥት የሰጠንን መተዳደሪያ ተቀብለን፣ የሰፈረልንን የ«ዴሞክራሲ» መቁነን (ዴሞክራሲ ከተባለም) ተካፍለን፣ ያዘጋጀውን ፀበል ቀምሰንና አጽድቀንለት፣ ተመረጡ የተባሉትንም ያለማንገራገር ተቀብለንለት ለመኖር ብንወስንም እንኳን አኗኗራችንንና መኖርን ራሱን የሚወስኑልን ገዢዎቻችን ናቸው።
እንዲያውም አንድ ጊዜ፤ አንዱ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን፣ አቶ በረከት ስምኦን ይመስሉኛል፤ (ለመታረም ዝግጁ ነኝ) «የኢትዮጵያ ሕዝብ ተኛ ስንለው የሚተኛልን፤ ተነስ ስንለው የሚነሳልን ሕዝብ ነው፤ ችግሩ ያለው ከእኛ የአፈጻጸም ሂደት እንጂ ሕዝቡ ምን ያድርግ?» ሲሉ መናገራቸውን አስታውሳለሁ። ልክ እንደ ለማዳ እንስሳ፣ ጭቆናን አለማምደውን መኖር የሚቻለው በጭቆና መንገድ ብቻ እንደሆነ እንድናስብ አድርገውናል።
እውነት ነው፤ እነርሱስ ምን ያድርጉ… ? ያደረጉንን ሁሉ እየተደረግን፣ «ወድዳ እንደገባች ሚስት» «ወድደሽ ገብተሻልና (መድፋት የሚለው ቃል ፀያፍ ቢሆንብኝ ነው) ቢረግጡሽ አይክፋሽ፤» የሆንን መጠጊያ-አልባ ዜጎች አድርገው አኑረውናል። እርግጠኛ ነኝ፣ «ጋሽ በረከት» እና ጁንታ አጋሮቻቸው በወቅቱም ቢሆን ለእኛ አዝነውልን ሳይሆን፣ ይህንን ሕዝብ የበለጠ ተገዢና የበለጠ አጎንባሽ ለማድረግ ከዚህ የተሻለ የማስጎብደጃ «ስልት ወዲህ በሉኝ» ለማለት ይመስላል እንጂ፣ የነፃነት ሽቱ ሊያርከፈክፉብን ከቴም አስበው እንዳልሆነ ግልፅ ነው።
ነገር ነገር ያነሳዋልና፣ አንድ ጊዜ የየክልሉን የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎችና ምክትል ኃላፊዎች ደብረ ዘይት ላይ ጠርተው፣ «ሚዲያን ስለመቆጣጠር» (Managing the outlets of media) ላይ ራሳቸው ስልጠናውን ይሰጣሉ፤ አሁን አሜሪካ በዲቪ የገባ፣ የደቡብ ክልል የማስታወቂያ ባህልና ቱሪዝም በኋላ የኮሚኒኬሽን ምክትል ኃላፊ የነበረ ሰው፣ በስልጠናው የሚና ጨዋታ (Role Play) ላይ ምሳሌ ይሆንንና መድረኩ ላይ ተጠርቶ ይቀመጣል።
አቶ በረከት፣ አንተ የቢሮ ኃላፊ ነህ፤ እንበል ይላሉ። የቢቢሲ ጋዜጠኛ በአካባቢው ስለተነሳ ወረርሽኝ ወይም ድርቅ መዘገብ ፈልጓል፤ ስምዎንና ማዕረግዎን ጠየቀ፤ እንበል ከዚያ በኋላም ፤…«ክቡርነትዎ በደቡብ ወላይታ፣ ካምባታና ሐዲያ እንዲሁም በጌዴኦ ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች ድርቅ ምን ያህል ጉዳት አደረሰ፣ ምንያህልስ ሰው ለድርቁ ተጋልጧል ብለው ያስባሉ? ተያይዞ ስለተነሳውስ ወረርሽኝ ምን የሚሉን ነገር አለ፤» ይልሃል። ምን መልስ ትሰጣለህ? ሹሙም ደንገጥ ብሎ፣ «እግዚአብሔርን እስካሁን አልሰማሁም፤ አሁን ነው፤ ያወቅኩት። ሰው ሞቷል ፤ እንዴ?» ይላል፤ በቅንነት።
አቶ በረከትም በቁጣ ግለው፣ (ስንት ነገር አስተምረን እንችላለን? ከሚል ግብዝነት ጋር፣) ስለአካባቢህ ምንም እውቀት እንደሌለህ ያሳያል፤ ይልና ይሄኔ ጋዜጠኛው «በጌዴኦ በኮሌራ ስላለቁት አምስት መቶ ሕፃናት፣ መድኃኒትና አልባሳት ስለሚያስፈልጋቸው ሰዎችስ ምንም የሚሉት ነገር የለም?» ሲልህ …. (አላስጨረሳቸውም ፤ ሹሙ።)
«እዝጌርን ምንም አላውቅም፤ እውነቴን ነው…» ሲል ግራ ግብት ያላቸው፣ አቶ በረከት፣ ከቆይታ በኋላ፣ (ሰዉ በሳቅ እያውካካ ነው) በል እኔ የደቡብ ቢሮ የኮሚኒኬሽን ኃላፊ ሆኜ፣ ጠያቂ (ቢቢሲ) አንተ ሆነህ፣ ጥያቄዎች ታቀርብልኛለህ፤ አሁን የቢቢሲ ጋዜጠኛ ነህ እንበልና፣ በቅድሚያ ጥያቄህ ላይ ስምና የሥራ ኃላፊነቴን በመጠየቅ ትጀምራለህ….ይለዋል።
እኔ?
አዎ አንተ!?
አቶ በረከትን ልጠይቅ?
አዎ! (በስጨት ያሉ ይመስላሉ፤ በሌላ በኩል ጨዋ በመሆኑ ደስተኛ ሳይሆኑ አይቀሩም፤ እንደልብ ይጋልቡታላ)
እሺ፤ አለና፤ አቶ በረከት ስምዎንና የሥራ ኃላፊነትዎን? ቢነግሩኝ ይላል፤ (በድንጋጤ)
ጥቂት አቀርቅረው እንደወትሮው ቆዩና፣ እባክህ አንድ ሌላ ሰው ወደ መድረክ ይምጣና «ሮል ፕሌዩ» ይቀጥል፤ ሲሉ ይናገሩና የሰውየው ትርዒት በዚሁ ይቋጫል። በነገራችን ላይ እንዲህ በአሠራርም ሆነ በአደራረግም ግራ ግብት የሚላቸውን ሰዎች ያለችሎታቸው በብሔር ማንነት ቁና ብቻ እንዲቀመጡ የማድረግ ውጤት ነው፤ አፈጻጸሙን ሁሉ ግራ አጋቢ ሲያደርገው የኖረው።
እና ለምንድነው፣ ይሄንን ሰው የሚመስሉና ሌሎችን ይህንን የመሳሰሉ፣ ሰዎችን የ15 እና 20 ሚሊዮን ሕዝብ ውክልና ላይ ፊጥ እንዲሉ የሚያደርጉት? የሚሉ ጥያቄዎች አእምሯችንን ያስጨንቁታል። ትልልቅ ቦታ ላይ ትልልቅ ግራ-ገብ ሰዎችን አስቀምጠው ትልቅ ቀውስ ሲፈጥሩ ነው፤ የኖሩት። እናም በቀኑ መጨረሻ፣ «የደቡብ ሰው የዋህ ነው፤» ይባልልኛል። የማይፈለግ ሰው፣ በተፈላጊ ስፍራ ላይ አስቀምጠው፣ የማይፈለግ ሥራ በማሰራት የራሳቸውን ፍላጎትና አጀንዳ ያስፈጽሙበት ይሆናል እንጂ፣ መቼም ለሀገር ጥቅም ብለው ይህንን አያደርጉም።
እነዚህ እውነትን የማይገነዘቡ፤ በራሳቸው እምነት የሌላቸው የተሰጣቸውን ብቻ በሙሌት የሚዘረግፉ ለምን የማይሉ፣ «አሜን ብቻ» የሚሉ፣ የራሳቸው የእጅ ሥራ ውጤቶችን ሾመው ነው፤ ሀገሪቱን እንደጎልፍ ሜዳ ሲጫወቱባት የኖሩት፤ እነ «ጁንታታት!»።
«ለምን» ባይነት ከአመፀኛነት የሚቆጠርበት ጊዜ ነበረና፤ ለምን ባዮች አንድም ሹመታቸው የዛፍ ላይ እንቅልፍ ይሆንባቸዋል፤ ወይም የፈጠራ ክስ ይዘጋጅላቸዋል። ያኔውኑ፣ ግን «ለምን» የሚሉ ሰዎችን ቢያበረታቱና መቀባበል በመሐላቸው የነገሰ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን የሆነው ሁሉ ባልሆነና የተፈጠሩባቸው እንቆቅልሾች ቋጠሮ በተፈታም ነበረ።
ሆኖም የድሮዎቹ ገዢዎቻችን በፍጥረታቸው ለውጥ የማይወዱ፣ ለውጠኛን የሚገድሉና ልዩ ልዩ ታርጋ በመለጠፍ ራሳቸውን ንጹህና ጽዱቅ አድርገው ማሳየት የሚወድዱ ግብዞች ነበሩና፤ ይኸው ባህሪያቸው ይዟቸው መቀመቅ ከተታቸው።
«የቀነቀነኝን ሊቀናቀን ብሎ፣
ማረፍ ይመረጣል ቀንቅኖና ጥሎ።» (ያልታተመ) ብለው እንደ እኩይ ገጸ ባህሪ፣ በእውኑ ዓለም መጫወት ይመርጣሉ እንጂ፤ ተፎካካሪ ሐሳብ ለማነፅ ከቶውንም አይጠቀሙበትም።
እኛ አሁን ከዚህ መማር አይገባንምን? ይገባናል፤ ብዬ አምናለሁ። በአሰራሮች ላይ፣ በአወቃቀር ላይ፣ በአደረጃጀት ላይ፣ «ለምን?» ማለት ይገባናል፤ በሕግ ጉዳዮች ላይ ለምን ባይ መሆን ይገባናል፤ አለበለዚያ ስለመገልበጥ አለቃ ሲያወራ፣ «ስንት ጊዜ እንገልበጥልህ» ብለን፣ የምንጠይቅ ምስኪኖች እንሆንና ከሥራ እና ከተጠየቃዊ አካሄድ ይልቅ ስሜት ዳኛ ሆኖ በሰፈር፣ በእድር፣ በመስሪያ ቤት፣ በቀበሌና በክልል አለፍም ሲል በሀገር ደረጃ አምባገነንነትን አለምላሚዎችና ተንከባካቢዎች እንሆናለን። «ከአንድ ጁንታ ተገላግለን ሌላ ጁንታ ወደ ማፍራት»….ና አዕላፍ አድርባዮች ወደ መፈልፈያ ጎርፍ ውስጥ ገብተን እንድንደፈቅ ምክንያት እንሆናለን።
እንደምታውቁት፣ አድርባዮች ከመፍራታቸው ብዛት የተነሳ፣ ጨለማ የሚገስሱትን፣ ለፍትህ የሚሟገቱትን ደፋርና ጀግና የሆኑ ተፋላሚዎችን የሚያስፈራሩ ቡከኖች ናቸው። ይህ በሁሉም የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ያለ የሚኖርና ሥራንና ግንባታን፣ ምርትንና መታደስን፣ እድገትንና ለውጥን፣ ከሁሉም በላይ ለሀገርና ለሕዝብ የሚበጁ ራዕይ ያነገቡ ባለራዕዮችን የሚያስጨነግፉ ሾተላዮች ናቸው፤ አድርባዮች።
እነዚህ ሰዎች፣ ፍቅራቸው ሆዳቸውና አጉራሻቸው እንጂ፣ እውነትም እምነትም የላቸውም። የሚያምኑበት አቋም ስለሌላቸው በማናቸውም ጊዜ ከአንዱ ጠርዝ ወደሌላው ጠርዝ ለመዝለል ወይም ለመስፈንጠር አይቸግራቸውም፤ የሚያዳምጡት ጥቅማቸውን ብቻ ነው። ስግብግቦችና ክፉዎች ናቸው።
«እነዚህ አካላት ባሳለፍናቸው 45 ዓመታት ውስጥ ለስንቶቹ ሕይወት ማጣት ምክንያት ሆነው ይሆን?» ብዬ እጠይቅና ልቤ በሐዘን ይሞላል። በየጥቃቅኑ የአስተሳሰብ ልዩነት፣ ተቸካይ ፣ አድሃሪ፣ ቀኝ ዘመም፣ ግራ ዘመም ፣ ትምክህተኛ፣ ጠባብ፣ ፀረ ሰማእታት፣ ወዘተ… እያሉና እያስባሉ፣ በየሥፍራው እየመቱ ያስቀሯቸውን ኢትዮጵያውያን ወገኖቼን የትምታ እጠይቅና፣ የረባ የቀብር ሥፍራ ሳይደረግላቸው በየፈፋው የአሞራ እራት ሆነው የቀሩትን ማን ያስታውሳቸዋል…? እላለሁ። ለእነዚህ ምውታን መገደል ምክንያት ተደርጎ ትግሉና ደርግ ሰበብ እየተደረጉ ቆይተዋል፣ አሁን ግን እውነቱ በይፋ መገለጥ አለበት። ተገልጦም ማስተማሪያ ሊሆን ይገባዋል።
ካበለዚያ፣ «እስካልተገለጠበት ድረስ ሌብነትም ሥራ ነው፤» እንደተባለው ሁሉ እስካልተጋለጡ ድረስ ነፍሰ ገዳይነትም ሙያ ነው፤ ተብሎ እንዳይወደስ ስጋት አለብኝ። እና በእነዚህ ዘመናት ያልተመለሱ ጥያቄዎቻችን መልስ እንዲያገኙ መንግሥት ከነባሩ ሰውና ከአካባቢው እውነተኛ ሰዎች ጋር በመሆን፣ ተገቢውን ጥናት በማድረግ እንዲያከናውኑት እንፈልጋለን። እነዚህ ጥያቄዎች እንዲህ ይቅረቡ እንጂ፣ የብዙ ተብሰልሳይ ኢትዮጵያውያን ጥያቄዎች መሆናቸውን አልጠራጠርም።
እነዚህን ጉድለቶቻችንንና ያልተመለሱ ጥያቄዎቻችንን ይዘን፣ ወደ መንፈሳዊና አካላዊ ልዕልናና ወደኢኮኖሚ ብልጽግና በቀላሉ መጓዝ ከቶ አይሆንልንም፤ ቢሆንልንም ሁሌ በልባችን ያንን ያልተሞላ ክፍተት ይዘን ማዝገማችን አይቀርም። ነገር በሆዱ የያዘ ደግሞ ይንፏቀቅ እንደሆን እንጂ፣ አይራመድም። በቅጡ እንድንራመድ ለጥያቄዎቻን መልስ እንሻለን። ሻሎም!!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2013