‹‹መልክ ስጠኝ እንጂ ሙያ ከጎረቤቴ እማራለሁ›› የሚል አባባል አለ። ተፈጥሮን መቀየር አይቻልም እንጂ ከዚያ በታች የሆነውን ነገር ሁሉ መለወጥ፣ ማስተካከልና ማረም ይቻላል ለማለት ነው ቅኔው። ሙያ ባልችል፣ ባጠፋ፣ ብሳሳት ከአዋቂዎች ተምሬ አስተካክላለሁ፤ እስተካከላለሁ። እውቀት የሚገኘው እስከ ዕለተ ሞት ድረስ ነው ለማለት ነው።
እውነት ነው የሰው ልጅ ከእናቱ ሆድ ተምሮ አይወጣም፤ ማንኛውንም ነገር የሚያውቀው ከሌሎች አይቶና ተምሮ ነው። ከሰለጠኑ አለማት ተመክሮ፣ ከመጽሐፍት ንባብ ደግሞ ከትምህርት ነው። ሌላው ደግሞ ዕድሜም አስተማሪ ነው ከስህተትም ያስተምራል። አንዳንድ ሰዎች ወይም ፖለቲከኞች ደግሞ ድሮ ከሚያውቁት ወይም አጋጣሚው ከፈጠራለቸው ነገር ወጣ ብለው አያስቡም፤ አንድ ቦታ ብቻ ተቸንክረው ያንኑ ሲያላምጡ ይውላሉ፤ ይከርማሉ።
ብዙ ጊዜ «ከስህተቱ የማይማር ፈንጂ አምካኝ ብቻ ነው» ሲባልም እንሰማለን። አባባሉ የሰው ልጅ ስህተት ይሰራል፤ ከስህተቱ የማይማር ከሆነ ግን በስህተቱ ይጠፋል ለማለት የሚያገለግል እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም። ምክንያቱም ፈንጂ አምካኝ የማምከን ሥራውን በትክክል፣ በጥንቃቄ እና በእውቀት ካልፈጸመ እንዲመክን የተፈለገው ፈንጂ ፈንድቶ የአምካኙን ሕይወት ማጥፋቱ አይቀርም።ከስህተቱም ለመማር ዕድል አያገኝም። ለጽንፈኛው ጁንታ ቡድን ይሄ መገለጫው ነው።
ጁንታው ጥፋት፣ ሴራ፣ ተንኮል ሲሰራ 27 ዓመታት አሳልፏል። አንዱንም ዓመት ከስህተቱ ለመማር አልሞከረም። ይባስ ብሎ ከስህተቱ እንደማይማረው ፈንጂ አምካኝ ፈንጂ ላይ ቆሞ ግብዐተ መሬቱን አፋጠነ። በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በሰብአዊ መብት ዙሪያ ሲያደርስ ሲፈጽመው የነበረው ግፍና በደል ሀገሪቱን ወደማትወጣበት አዘቅት ለመክተት ሲፈጽማቸው የነበሩ ተግባራቱ በቃላት ሊገለፁ የማይችሉ ዘግናኝና አረመኔያዊ ጭፍጨፋዎችና የኢኮኖሚ አሻጥሮች ሀገራችንን ወደፊት ሳይሆን ወደ ኋላ ጎትቷል።
የህወሓት ጁንታ ቡድን በሀገሪቱ የተዘረጋውን ነፃና በውድድር ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለሚዲያና ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ እየተጠቀመበት በ1983ዓ.ም ወደ ሥልጣን ሲወጣ ጡንቻውን ለማፈርጠም፤ አእምሮውን በስብ ለመድፈን ያግዙኛል ብሎ በመሰረታቸው የንግድ ድርጅቶች ከፍተኛ የጁንታው አመራር እስከ ታችኛው
መዋቅር በተደራጀና በታቀደ መልኩ ሰንሰለት ዘርግተው ሀገሪቱን ሲዘርፉ እንዲሁም የዘረፉትን ከሀገር ሲያሸሹና ሕዝብና ሀገርን ሲያደኸዩ ቆይተዋል። ይሄም በሕጋዊ ነጋዴው ላይ የፈጠረው ተጽዕኖ፤ በንግድ ሚዛኑ ላይ የፈጠረው መዛባት ይሄ ነው የሚባል አይደለም። በራሳቸው ጥረት ለፍተው ተግተው ሲሰሩ የነበሩ ድርጅቶችን ሁሉ አሽመድምዶና ሁሉንም የንግድ እንቅስቃሴ ተቆጣጥሮ ከመስመር እንዲወጡ፣ ከሀገር እንዲሰደዱ አድርገዋል።
ጁንታው ቡድን በትግሉ ወቅት የተገኘን ሀብት ለትግራይ ሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች እንዲመሰረቱ አድርጌአለሁ እያለ በፓርቲ ስም ያለ ማንም ከልካይና ተመልካችን በሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ሊባል በሚችል ደረጃ የሀገሪቱን ሀብት ሲዘርፍና ሲያዘርፍ ከርሟል። በችግር ምክንያት ጡቶቿ እንደደረቁባት እናት ሀገርም ለዜጎቿ የወር ደመወዝ መክፈል እስከማትችልበት ደረጃ ድረስ እንድትደርስ አድርጓታል።
ጁንታው ቡድን በድርጅቶቹ በኩል የባንክና ኢንሹራንስ ባለቤት ነው፣ የማዳበሪያና ምርጥ ዘር፣ ብረት፣መድኃኒት አስመጪና አከፋፋይ፣ ሲሚንቶ፣ ቆርቆሮ፣ መኪና መገጣጠሚና መለዋወጫ አስመጪ ነው፣የአበባ አምራችና ላኪ፣ የከበሩ ማዕድናትና ወርቅ፣ የባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ባለቤት ነው፣ የሪል እስቴት ባለቤት ነው ምን ያልሆነው አለ! ።
የህወሓት ጁንታ ቡድን ያልሆነውን መፈለግ እንጂ በንግዱ ዘርፍ ያልተሰማራበትን ማግኘት እንዲህ ከባድ አይሆንም። ለዘመናት በንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎች አንድ ደሳሳ ጎጆ መቀለስ አቅቷቸው የጁንታው ቡድን አባላትና ተከታዮቻቸው በአንድ ሳምንት የሁለትና ሦስት ሕንፃዎች ባለቤትና አስመጪና ላኪ ዝርዝር ውስጥ ሲገቡ ማየት ለኢትዮጵያውያን ለቀባሪ እንደማርዳት ነው።
የጁንታው ቡድን አባላት በኢኮኖሚው ዘርፍ በንግድ ሥርዓት ውስጥ የፈጠሩት ቀውስ ሀገር እንዲህ በቀላሉ ትወጣዋለች ብሎ መገመት ይከብዳል። ያለ ቀረጥ ከውጭ የሚገቡ እንደልብ ሲቸበቸቡ የነበሩት የተለያዩ ምርቶች የጁንታውን አባላት ያበለጸጉ የመንግሥትን ሕግና ሥርዓት አክብረው የሰሩ ነጋዴዎችን ከውድድር ያስወጡ የሀገርን ዕድገት ቁልቁል የጎተቱ ናቸው።
አንዳንድ ምርቶች በገበያ ላይ ሲጠፉ የነእከሌ ዕቃ ስላልገባ ነው፤ እነሱ ሲለቁ ችግሩ ይፈታል ሲባል ይሰማል። ከዚያም በገበያ ላይ የምርት እጥረት እንዲከሰት፣የውጭውን እንዳይገባ፣ የሀገር ውስጥ ያለው በመጋዘን በመያዝ ዋጋ ሲሰቀል ደግሞ በውድ ዋጋ ለኅብረተሰቡ በማቅረብ በዕለታት በማይታመን ሁኔታ
ሲከብሩ፤ ሌላው የበይ ተመልካች ሆኖ አልቅሷል። ይሄው ዛሬ እንባውን የሚያብስለት ተመልካች ማግኘት ችሏል። ያም ሆኖ አሁንም የመስመር ተጫዋቾቹ ከመስመሩ ስላልጠፉ ውንብድናው ማጭበርበሩ አሁንም ገና እልባት አላገኘም። በቅርቡ በጅቡቲ ሄደው የቀሩ ከመቶ በላይ የደረቅ ጭነት ማመላለሻ መኪናዎች የዚሁ የሸፍጥ ማሳያዎች ናቸው።
እያንዳንዱን ዘርፍ በሚፈለጉ አካላት ብቻ በመቆጣጠር እየተደረገ ጥቅመኞችም ሲነቃባቸው የሚያኮርፉት ለምን ይሆን ብሎ መጠየቅና መመራመር ሳያስፈልግ ትንንሽ ምልክቶችን ብቻ ገጣጥሞ ማንበብ በቂ ይሆናል። በራሳቸው ራሳቸው የሰሩትን ሲሰሩ የኖሩትን ሁሉ በሥራቸው እየመሰከሩ ናቸው።
እጅግ የሚገርመው እና የሚደንቀው የጁንታው ቡድን አባላት ዛሬም አዙሮ የሚያይ ጭንቅላት እንዳልተፈጠረባቸው ሳሰብ ነው። የሀገሪቱን ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ ያለእውቀት ሲጫወቱበት ኖረው አሁንም አዋቂ ታዋቂ ለመሆን መሞከራቸው ነው።
ፅንፈኛው ጁንታ ቡድን ይህ ሁሉ በደል፣ ይህ ሁሉ ዘረፋ አልበቃ ብሎት ዜጎች በሀገራቸው ጥረው፣ ግረውና ለፍተው እንዳይኖሩ ለተለያዩ ብሔረሰቦች የተለያየ ታርጋ እየለጠፈ ወደ ወህኒ ሲወረውሩ፣በአደባባይ ሲረሽኑ፣ በብሔር በሃይማኖት ጭምር ሲያጋጩ፣ ሲያጋድሉና ንብረት ሲያወድሙ ቆይተዋል።
ይሄ ሁሉ አልበቃ ብሏቸው ደግሞ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የፈጸሙት አረመኔያዊ ድርጊት ለሰሚ የሚሰቀጥጥ ለተመልካች የሚዘገንን መሆኑ በተለያየ የመገናኛ ብዙሃን አይተናል። ከሰው ዘር ስለመፈጠሩ እንድንጠራጠር የሚያደርጉን ተግባራት መፈጸማቸውን ስንሰማ እውነት እነዚህ ‹‹ሰዎች›› ናቸው እንድንል አስገድዶናል።
የህወሓት ጁንታ ቡድን በስተርጅናው እንኳን ከጥፋቱ ሊማር ሲገባው ካፈርኩ አይመልሰኝ ብሎ ኢትዮጵያውያን ወደማይፈልጉት ጦርነት ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ በውጭ ወራሪ እንኳን ያልተፈጸመባቸውን ደባ ፈጽሟል። እንደ ፈንጂ አምካኝ ሁሉ ዛሬም ከስህተቱ ብቻ ሳይሆን ከድንቁርናው ሳይማር አይቀጡ አቀጣጥ እየተቀጣ ይገኛል። ሀገር ጥሎ፣ ከመኪና ወርዶ በየጉድጓዱ ተደብቋል። የጀግኖች ምሽግ ሸሽቶ በአይጦች ጉድጓድ ተሸሽጓል።
የህወሓት ጁንታ ቡድን ከአፈጣጠሩ የሚማርና ከስህተቱ የሚመለስ አለመሆኑን በርካታ አብነቶችን መግለጽ ይቻላል። ቡድኑ ከሱ በላይ አዋቂ እንደሌለ፣ እሱ ከሌለ ኢትዮጵያ እንደምትፈራርስ ይለፍፋል። ይሄ ባዶ እብሪት ባዶነትን የሚያሳይ እንጂ ኢትዮጵያ የወላድ መካን እንዳልሆነች በጀግኖቹ ልጆቿ አሳይታለች። ጁንታው ሳይኖር ሀገር እንደምትቀጥልም ተመስክሯል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2013