ለምለም መንግሥቱ
ማልደው ከቤት ሲወጡ ብርዱ ጭብጥ ቢያደርግዎትም ጤናማ የሆነ ነፋሻ ንፁሕ አየር የሚስቡበት ሰዓት በመሆኑ ይመረጣል። ለዚህም ነው ፀሐይ ከመበርታቱ በፊት የጠዋት ጉልበት የሚፈለገው። በዚህ ረገድ ማልደው ከእንቅልፋቸው የሚነሱ ሰዎች በንጹሕ አየር ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይታመናል።
ግንዛቤ መያዝ ያለበት ግን አካባቢው በተለያየ ነገር ያልተበከለ ከሆነና ንጹሕ አየርን የሚመግቡ ዛፎች ሲኖሩ ነው የማለዳ ቱሩፋቱን ተቋዳሽ መሆን የሚቻለው። በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ ማልዶ ተነስቶ ወደ ቀን ሥራው የሚሮጠው ከተሜ እንዲህ ያለውን የተፈጥሮ ፀጋ ምን ያህል አስተውሎት ይሆን ብዬ ለመቃኘት በከተማዋ ከሚገኙ አሥራ አንድ ክፍለ ከተሞች አንዱ በሆነው ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ተገኘሁ።
በክፍለከተማው ወረዳ አንድ ነዋሪ የሆኑና ማልደው በመነሳት ሻይና ብስኩት(ፓስቲ) የጎዳናውን ጥግ ይዘው ለደንበኞቻቸው ለሽያጭ በማቅረብ በገቢው የሚተዳደሩትን ወይዘሮ ሶፊያ አማንን ስለማለዳው አየር ጠየኳቸው። እርሳቸው ለደንበኞቻቸው ቶሎ ደርሰው ቁርስ ማቅረባቸውን እና ገቢ ስለማግኘታቸው እንጂ ስለማለዳው አየር ጥቅም አስተውለው አያውቁም። በጉዳዩ ላይ ጊዜ ወስደን ከተነጋገርን በኋላ ግን በአካባቢው ላይ ያስተዋሉትን ችግር ነገሩኝ።
እርሳቸው እንዳሉት፤ከቤታቸው ከንጋቱ አስራአንድ ሰዓት ተኩል ሲወጡ በጭስ የተሸፈነ አየር ነው የሚያዩት። ጎዳና የሚያፀዱ ባለሙያዎች በመጥረጊያቸው የሚያስወግዱት የቆሻሻ አቧራ ሲጨመርበት ደግሞ የበለጠ አካባቢው ይበከላል። ማለዳ የሚጠበቀውን ያህል ንጹህ አየር እንደሌለ አረጋገጡልኝ።
ወይዘሮ ሶፊያ በዕለት ኑሮ ተጠምደው ጉዳዩን ቸል ቢሉትም በተደጋጋሚ ማጋጠሙ ውሎ አድሮ ለጤና ችግር እንደሚያጋልጥ ተገንዝበዋል። እርሳቸው እንዳሉት በአካባቢው ከፍተኛ ጭስ የሚያወጡ ፋብሪካዎች ይገኛሉ። አንዱ መስታወት የሚያመርት ፋብሪካ ሲሆን፣ሌላው በቅርቡ ቆሻሻን መልሶ ለኃይል ምንጭ ለማዋል የተቋቋመው የረጲ የኃይል ማመንጫ ፋብሪካ ነው።
አነስተኛ ቢሆንም ሌሎችም በዙሪያው ያሉ ጭስ የሚያወጡ ማምረቻዎች ይገኛሉ። ጉዳት እንዳለው ቢያውቁም አካባቢያቸውን ለመቀየር አቅም ስለሌላቸው በአካባቢ ብክለት የሚፈጠረውን ተጽዕኖ ተቋቁመው ለመኖር ተገደዋል። መንግሥት ችግሩን ይፈተዋል ብለው ያምናሉ።
የሦስት ልጆች እናት የሆኑት የአካባቢው ነዋሪ ወይዘሮ ገነት ማስረሻ ከፋብሪካዎቹ የሚወጣው ጭስ በተለይ በልጆቻቸው ላይ የጤና ጉዳት ሊያስከትልባቸው ይችል ይሆናል ብለው ሰግተዋል። የጋራ መኖሪያቤት በዕጣ ደርሷቸው ኑሯቸውን በአካባቢው ከመሠረቱ ዘጠኝ ዓመት እንደሆናቸው የሚናገሩት ወይዘሮ ገነት ሦስቱንም ልጆቻቸውን የወለዱት እዛው አካባቢ በመሆኑ ጉዳቱ የከፋ ይሆናል ብለው ፈርተዋል።
ቤታቸውን ሸጠው ወደ ሌላ አካባቢ ለመሄድ ፈልገው የቤቱን ዕዳ ከፍለው ባለመጨረሳቸው ለመቀመጥ እንደተገደዱ ያስረዳሉ። አካባቢው ሰፊ ቁጥር ያለው ማህበረሰብ የሚኖርበት በመሆኑ ጉዳቱ ሳይባባስ መንግሥት መፍትሔ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
ወደተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች መውጫ በሆነው በዚህ አካባቢ በቁጥር አንድ፣ ሁለትና ሦስት ተብለው የሚጠሩ የጋራ መኖሪያቤቶች ተገንብተዋል። እያንዳንዳቸውም ከ18ሺ ያላነሰ አባወራዎች ይኖሩባቸዋል።
በማህበርና በተለያየ መንገድ የተገነቡ መኖሪያቤቶች፣ለንግድና ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎች በብዛት የሚገኝበትና ሰፊ የሰው ፍሰት ያለበት አካባቢ ነው። በአካባቢው ያለው ግዙፍ ፋብሪካ የሚወጣው አካባቢ በካይ ነገሮች መኖሩ ብዙዎችን አነጋጋሪ ሆኗል።
በድበቅ በአነስተኛ ደረጃ በማምረት ላይ ያሉ ጭምር በጭስና በድምፅ የአካባቢ ብክለት እያስከተሉባቸው መሆኑን ያነጋገርኳቸው ነዋሪዎች ያስረዳሉ። የቻይና ኩባንያ የሆነው አምራች ኢንዱስትሪ ግዙፍ በመሆኑ በማምረት ወቅት በሚፈጥረው ንቅናቄ በመኖሪያቤቶች ላይ መናጋት ይፈጥራል የሚል ሥጋት አሳድሯል።
ግዙፎቹ ኢንዱስትሪዎች ሀገራዊ ፋይዳ ያለው ምርት በማምረት፣ የሰው ኃይል በመያዝ የሥራ አጥነትን በመቀነስ አበርክቷቸው ዘርፈ ብዙ እንደሆነ ቢታወቅም ጉዳታቸው ያመዘነ መሆን የለበትም።
ተረፈምርታቸውን በአግባቡ ለማስወገድ የሚረዳ ቴክኖሎጂ መጠቀም እንዳለባቸው በተደጋጋሚ በዘርፉ ባለሙያዎች ሲነገር ቆይቷል። ታዲያ ዘላቂ መፍትሔ ሳይገኝ እስከዛሬ የዘለቀበት ምክንያቱ ምንድ ነው?
በንፋስስልክ ላፍቶ ያስተዋልኩትንና የነዋሪውን ቅሬታ ለአብነት አነሳሁ እንጂ አዲስ አበባ ከተማ ለአየርብክለት ተጋላጭነቷ ከተነገረ ሰነባብቷል። ነዋሪዎችና ኢንዱስትሪዎች ጣሪያ ተጋርተው እየኖሩባት እንዴት ለብክለት አትጋለጥ? የሚሉ ትችቶች በዝተዋል። በዚህ ረገድ ጉዳዩ የሚመለከተውን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሙላቱ ወሰኑን አነጋግረናል።
አቶ ሙላቱ በነዋሪዎቹ የተነሱትን ቅሬታዎች ይጋራሉ። ንፋስልክላፍቶ፣ ኮልፌ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ ቦሌ አካባቢ አምራችና አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች ከሚበዙባቸው የከተማዋ ስፍራዎች መካከል ቀዳሚ እና ለአካባቢ ብክለትም የበለጠ ተጋላጭ መሆናቸውን ይገልጻሉ። እርሳቸው እንዳሉት በእነዚህ አካባቢ የሚገኙት አምራች ኢንዱስትሪዎች ብናኝና ጭስ እንዲሁም ፍሳሽ ያላቸው ሲሆኑ፣ ለመተንፈሻ አካል ጤና ጠንቅ የሚያስከትሉ ናቸው።
አምራች ኢንደስትሪዎቹ ትሪትመንት ፕላንት ወይም የጉዳት መጠኑን የሚቀንስ ቴክኖሎጂ ይጠቀማሉ የሚል ግምት ቢወሰድም በክትትልና ቁጥጥር ወቅት በተደረገ የቤተሙከራ ምርመራ አብዛኞቹ ከተቀመጠው ደረጃ በታች መሆናቸው ተለይቷል። በተለይም የቆዳ አምራች ኢንዱስትሪዎች ተጠቅመው የሚያስወግዱት ፍሳሽ ለአካባቢ ጠንቅ እንደሆነ ተረጋግጧል።
ንፋስልላፍቶ ክፍለከተማ የሚገኘው መሥታወት የሚያመርተው ሀንሰን የተባለው የቻይና ፋብሪካ በምርት ሂደት በሚያወጣው ጭስ የአካባቢ ብክለት በማስከተሉ በተመሳሳይ በክትትልና ቁጥጥር ተደርሶብት ታሽጎ እንደነበርም ባለሙያው አስታውሰዋል። ችግሩን በማሳየት የአካባቢው ነዋሪዎች ግፊትም አስተዋጽኦ እንደነበረው ባለሙያው ተናግረዋል።
እንደባለሙያው ማብራሪያ ለብክለቱ መንስኤ የሆነውንና መርዛማ ጭስ የሚያስከትለውን የሚጠቀምበትን ጥሬ ዕቃ ከከምችቱ እንዲያስወግድ ነው የተደረገው። በወቅቱም ከፋብሪካው ይወጣ የነበረው ጭስ ለመተንፈሻ አካል የሚያጋልጥ ነበር። ከእርምጃው በኋላ ፋብሪካውን ቢያሻሽልም ሙሉ ለሙሉ የፀዳ ነው ለማለት ስለማያስደፍር ክትትልና ቁጥጥሩ ተጠናክሯል።
ተቋማቸው ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለማስገኘት አዋጅ ቁጥር ሦስት መቶን መሠረት አድጎ እየሠራ ቢሆንም ውጤቱ የሚታየው በሂደት በመሆኑ ከቅሬታ የፀዳ አይሆንም። ችግሩ አምራች ኢንደስትሪው ጋር በሚስተዋለው የበዛ ግዴለሽነት የሚከሰት ሲሆን፣አንዳንዶችም በቂ ግንዛቤ ካለመኖር ጋር የተፈጠረ መሆኑን ይናገራሉ።
በማስጠንቀቂያ የታለፉ፣ በገንዘብ የተቀጡ፣ ታሽገውም ለቀናት የቆዩ አምራች ኢንደስትሪዎች መኖራቸውን ገልጸውልኛል። ሆኖም ግን አስተማሪ ሆኖ ችግሩን በሚፈለገው ደረጃ ፈትቶ ውጤት ሲያመጣ አልተስተዋለም። ከባለሙያው የተገለጸውም የተቋሙ ዋና ተግባር ድጋፍ ማድረግ፣ ብክለትን መቀነስ፣ መከላከልና መቆጣጠር ነው። በዚሁ መሠረት በቅድሚያ ባለሙያዎች ተቋሙ ውስጥ በመገኘት ሙያዊ ድጋፍ ይሰጣሉ።
ይሄውም ከሀገሪቱና ከአካባቢው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በተገናዘበ የሚሰጥ ሲሆን፣የድምፅ ብክለትን ጨምሮ የብናኝ፣የጭስ፣የፍሳሽ አወጋገድን ያካትታል። በቤተሙከራም ሥራው ተፈትሾ ይረጋገጣል። እውቅና ሳይኖራቸው በሥራው ላይ የሚገኙትን በምክር ለመመለስ ጥረት ይደረጋል። ችግሮች ከታዩም እንዲስተካከል ይመከራል። ከዚህ ሁሉ ሂደት በኋላ ነው ዕርምጃው የመጨረሻ አማራጭ የሚሆነው ብለዋል።
‹‹በ1995 የወጣው የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ ላይ ከአቅም በላይ የሆኑ ድርጅቶች ወይንም ግለሰቦች በእሥራት ወይንም በገንዘብ እንዲቀጡ ተደንግጓል። ስለዚህ አንድን ድርጅት የመዝጋት፣ የማሸግ፣ ከቦታ ቦታ የማዘዋወር ሥልጣን ለኮሚሽኑ ተሰጥቷል። ኮሚሽኑ አዋጁን መሠረት አድርጎ ካልፈጸመ ያስጠይቀዋል።
ለዚህ ነው ወደ ቅጣት ዕርምጃ የምንሄደው›› በማለት ያስረዱት አቶ ሙላት፤ ዕርምጃ የተወሰደባቸው አምራች ኢንደስትሪዎች ከሥራው እንዲወጡ ሳይሆን ከስህተታቸው ታርመው ወደማምረት ተግባር እንዲገቡ
ነው የሚደረገው ብለዋል። ወደ ሥራው እንዲመለሱ ሲደረግም ዳግመኛ ስህተት እንደማይፈጽም ግዴታ መግባቱን በፊርማው ያረጋግጣል።
በክትትልና በቁጥጥር የተወሰዱት ዕርምጃዎች አብዛኞቹ አስተማሪ እንደነበሩ አቶ ሙላት ያስታውሳሉ። እርሳቸው እንዳሉት በ2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ስድስት የቆዳ ፋብሪካዎች በአንድ ጊዜ የማሸግ ዕርምጃ ተወሰደባቸው። ሁሉም የሚያስወግዱትን ፍሳሽ ቆሻሻ አክመው ባለመልቀቃቸው ነበር ዕርምጃ የተወሰደባቸው።
ችግሩ ሲጣራ የአምራች ኢንደስትሪዎቹ ብቻ አልነበረም። ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ሲባል ቅድመ ጥንቃቄው በመንግሥትም በመዘንጋቱ ጭምር ነው። ይሄ ዕርምጃ አላዋጣም አምራች ኢንደስትሪዎቹ ሳይታከም በሚያስወግዱት ፍሳሽ ሰዎች፣ እንስሳት ለጤና ጉዳት መጋለጣቸው በጥናት ተለይቶ ለመንግሥት ቀረበ።
የችግሩ ምንጭ ግራና ቀኝ ከታየ በኋላ አምራች ኢንደስትሪዎቹ ፍሳሹን አክመው እንዲያስወግዱ ተነግሯቸው ሥራ እንዲጀምሩ ተደረገ። ሁሉም የተባሉትን ቢፈጽሙም ክትትልና ቁጥጥር ግን ሊለያቸው እንደማይገባ ታምኖበታል። ከዕርምጃ በኋላ አበረታች ውጤት ተገኝቷል።
እንደ አቶ ሙላት ማብራሪያ አምራች ኢንደስትሪዎቹ በግንዛቤ እጥረትና በግዴለሽነት የአካባቢ ብክለት እየፈጠሩ ነው ቢባልም የአቅም ውስኑነቶችም አሉባቸው። የሚያስወግዱትን ፍሳሽ ቆሻሻ ለማከም የሚያገለግለው የትሪትመንት ፕላንት ግብአት ዋጋው ውድ በመሆኑ ለማሟላት ይቸገራሉ።
ወደ ማስወገድ የገነቡትም ቢሆኑ በጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ግንባታ አለማከናወናቸው፤ የኢንዱስትሪዎቹ የቦታ አቀማመጥም የራሱ አስተዋጽኦ አለው። አብዛኞቹ በመኖሪያቤቶች እና በወንዞች አካባቢዎች ነው የተቋቋሙት።
ትልቁ ችግር ከፈቃድ ሰጭውና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተናብቦ አለመሥራትና ቅድመ ጥናትም አለመከናወኑ ነው። ቀድመው የተተከሉት ኢንደስትሪዎች ጥናትን መሠረት ባደረገ አይደለም ወደ ሥራ የገቡት። ኢንደስትሪዎቹ የንግድ ፈቃድ ከኢንቨስትመንት እና ከንግድ ቢሮዎች፣ የአካባቢ ሰነዱን ደግሞ ከኤጀንሲው ነው የሚያገኙት።
ይሁን እንጂ ተቋማቱ ተናብበው በየራሳቸው የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ባለመወጣት ነው ክፍተቱ የተፈጠረው። የንግድ ህጉ የአካባቢ ተጽዕኖን ባገናዘበ ባለመከናወኑ ተጠያቂነት ላይ ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል። የኤጀንሲው ባለሙያዎች ለሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች በተደጋጋሚ አሳውቀዋል። ግን ተፈጻሚ አልሆነም።
በዶሮ እርባታ ላይ የሚፈጠረው የሥራ ዕድልም በተመሳሳይ ለአካባቢ ብክለት ችግር እየፈጠረ መሆኑንና በዚህ ረገድም የተናበበ ሥራ መሠራት እንዳለበት አቶ ሙላት ያሳስባሉ። ከዶሮ እርባታ የሚወጣው ከፍተኛ ሽታና አሲዳማነት ያለው ነገር አስቸጋሪ መሆኑንና በአሁኑ ጊዜም እርባታው ባለባቸው ስድስት አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ ብክለት መኖሩን አስረድተዋል። ችግሩን በተመለከተ ከከተማ ግብርና እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ተደርጎ መፍትሔ አልተገኘም።
አምራች ኢንደስትሪዎቹ በሚያስከትሉት የአካባቢ ብክለት የሚጎዳው ህብረተሰብ በምን መልኩ እንደሚካስና መብቱም እስከምን ድረስ እንደሆነ አቶ ሙላት ላነሳሁላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ በመመሪያ በተደገፈው አዋጅ ሦስት መቶ መሠረት ህብረተሰቡ በአካባቢው የደረሰውን ብክለት ለኤጀንሲው የማመልከት መብት አለው። ኤጀንሲው ለደረሰው ጥቆማ መልስ ካልሰጠ ያስጠይቀዋል። ኤጀንሲው ቦታው ድረስ ሄዶ የማረጋገጥ ግዴታ አለበት።
በሥራ ዕድል ፈጠራ ተብሎ የሚከናወነው ሥራም መፈተሸ አለበት የሚሉት አቶ ሙላት፣ በአንድ ወቅት ዓለምባንክ አንፎ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የዶሮ እርባታ በሚከናወንበት ቦታ የሚኖሩ ሰዎች የህክምና ማስረጃ አያይዘው ለኤጀንሲው ቅሬታ አቅርበው እንደነበር አስታውሰው፤ በወቅቱም ማድረግ የተቻለው እርባታውን ወደሌላ አካባቢ በማዘዋወር ችግራቸው መፍታት ነው። እርሳቸው እንዳሉት የአካባቢ ብክለትን ያስከተለ አስተካክሎ ወደነበረበት የመመለስ ግዴታ እንዳለበት በአዋጁ ቢቀመጥም በአዋጁ መሠረት አልተተገበረም።
አቶ ሙላት እንዳሉት በተለይ የቆዳ ፋብሪካዎችን ከከተማ ራቅ ባለ በአንድ አካባቢ እንዲሠሩ እንደሃሳብ ቢነሳም አልተተገበረም። በአዲስ አበባ ከተማ በአሁኑ ጊዜ ከአራት ሺህ በላይ አምራች እንደስትሪዎች ይገኛሉ። ሁሉም ብክለት አያስከትሉም ባይባሉም ከፍተኛ ብክለት ያስከትላሉ ተብለው የተለዩት ግን በሥራ ላይ ካሉት ከግማሽ በላይ እንደሆኑ እስታውቀዋል።
የሚያስከተሉት ጉዳትም ከፍተኛ በሚባል ደረጃ እንደሆነ ጠቁመዋል። ጉዳቱን ለመቀነስ ኤጀንሲው የሰው ኃይሉን በተሻለ በማደራጀት እና በከተማዋ በተለያየ ዘርፍ ከተደራጁ ኢንተርፕራይዞች ጋር በጋራ በመሆን በመንቀሳቀስ ከክፍለከተሞች ጋርም ጠንካራ ግንኙነት በመፍጠር ህጋዊ ያልሆኑትን አምራች ኢንደስትሪዎች በመከላከል፣ህጋዊዎቹም ቢሆኑ ብክለትን እንዲከላከሉ በማድረግ ውጤት ለማምጣት ሥራዎች ተጀምረዋል።
ልማትና አካባቢ ተጣጥሞ እንዲከናወን በዘላቂነት ግብ ተይዟል። በአምራች ኢንደስትሪዎች ለከፍተኛ የአካባቢ ብክለት እየተጋለጠች ያለችው አዲስ አበባ ከተማ እንደስሟ እንድትሆን እያስቻሏት አይደለም።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2013