እኛ በአሜሪካ፣ በካናዳና በአውሮጳ የምንኖር ዲያስፖራ የትግራይ ተወላጆች በሀገራችን በተለይም የህወሓት ጁንታ በለኮሰው እሳት ሳቢያ መንግሥት እየወሰደ ያለው እልህ አስጨራሽ ሕግንና ሥርዓትን የማስከበር እርምጃን አስመልክቶ ማሕበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ተሰባስበን በመወያየት በተስማማንባቸው ሃሳቦች መሰረት የለውጡን አጋርነታችንን ለመግለፅ ከዚህ የሚከተለውን የጋራ የአቋም መግለጫ አውጥተናል።
የህወሓት መኖር ለትግራይ ሕዝብ ኪሳራ እንጂ ጥቅም አላስገኘለትም። ህወሓት የትግራይ ሕዝብን ደም፣ ጉልበትና ሀብት ለሦስት ቡድናዊ አላማዎች ተጠቅሞበታል። አንደኛ፦ የትግራይ ለጋ ወጣቶችን ከደደቢት እስከ አዲስ አበባ ቤተ መንግሥት በትረ ሥልጣን ለመጨበጥ እንደመረማመጃ አድርጎ ከተጠቀመባቸው በኋላ እንደ ሳልቫጅ ዕቃ ሜዳ ላይ እንዲወድቁ አድርጓል።
ሁለተኛ፦ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ለጋ ወጣቶች በሁለት ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ደም ለማቃባት ሲባል በኤርትራ በሳሕል በረሃዎች የአሞራ ሲሳይ እንዲሆኑ አድርጓል።
ሦስተኛ በትግራይ ሕዝብ ስም የሀገራችን አንጡራ ሀብት በጠራራ ፀሐይ ለመዝረፍ ተጠቅመውበታል። ነገር ግን ከግማሽ በላይ የትግራይ ሕዝብ እስካሁን ድረስ ከውጭ የስንዴ እርዳታ ልመና አልወጣም።
ወጣቱ ከዓረብ ሀገር ስደትና ውርደት አልዳነም። የሚበላው ይቅርና ሁሉም የትግራይ ከተሞች የሚጠጣ ንፁህ ውሃ እንኳን ማግኘት አልቻለም።
የትግራይ ሕዝብ የሚበላና የሚጠጣ ብቻ አይደለም ያጣው ሰላምም ጭምር የጠማው ሕዝብ ነው። ህወሓት ከተፈጠረ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በትግራይ ምድር ከሰባት ጊዜ በላይ ደማዊ ጦርነት ተደርጓል። አብዛኞቹ የጦርነቱ መንስኤ ደግሞ ሌላ ምስጢር የለውም:: መንስኤው በማሌሊታዊና አብዮታዊ ዴሞክራሲ የደረቀ የህወሓት ጭንቅላት ያመጣው ጣጣ ነው።
የዴሞክራሲ ሽታ የሌለው ድርጅት በዴሞክራሲ ስም ይነግዳል፤ የነፃነት ሽታ የሌለው ድርጅት ነፃ አውጪ ነኝ እያለ ሕዝብን ያታልላል፤ ራሱን አውራ ፓርቲ ነኝ ብሎ የሰየመና የደመደመ ድርጅት የብዙሃን ፓርቲ ሥርዓት አራምዳለሁ ይላል፤ ለራሱ በሕግ የማይገዛ አጉራ ዘለል የሽፍታ ቡድን የሕገ መንግሥት ጠበቃ መስሎ ለመታየት ይፈልጋል፤ ከዚህ ሁሉ የተዛባና ጦረኛ ባህሪው የተነሳ የሚፈጠሩ ግጭቶች በአፈ ሙዝ ካልሆነ በስተቀር በዴሞክራሲ አገባብ በውይይት ለመፍታት ተፈጥሮው አይፈቅድለትም። ህወሓት ከፌዴራል መንግሥት ጋር የነበረው ግጭትም በተመሳሳይ ትዕቢት፣ ንቀት፣ ድንቁርናና ጦረኛ አመለካከት የወለደው ነው።
የተከበራችሁ የመንግሥት አካላትና የሀገር መከላከያ ሰራዊት
1) መንግሥት በህወሓት ጁንታ ላይ የወሰደው ሕግን የማስከበር እርምጃ ፍትሓዊ ርቱኣዊና ተገቢ ነው የምንለው ዋና ምክንያት ድርጅቱ ባለፈው ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ሲፈፅማቸው የነበሩ ሴራዎች ምን እንደነበሩ በግልፅ ስለሚታወቁ ነው። ከዚህ በመነሳት በህወሓት ላይ የተወሰደው ወሳኝ እርምጃና የተገኘው አንፀባራቂ ድልም ከሁሉም በላይ ለትግራይ ሕዝብ ትንሳኤና እፎይታ ሲሆን ለመላ ሀገራችንና ሕዝባችን ደግሞ የአንድነታችንን ገመድ ያጠነከረ፤ የኢትዮጵያዊነታችንን ውበት ያደመቀ፤ አትንኩን ባይነታችንን ለወዳጅም ለጠላትም ትልቅ ትምህርትና መልዕክት ያስተላልፈ፤ የሰላምንና የለውጥ ተስፋችንን ጎሕ የቀደደ፤ የመከላከያ ሰራዊታችንን ጀግንነት ብቃትና ሕዝባዊ ቃል ኪዳን በተግባር ያሳየ፤ በተለይም የመንግሥታችንን የአመራር ጥበብ ትዕግስትና ብስለት የዘመናችን አስደናቂ ሥራ መሆኑን ስንገልፅ ከፍ ያለ ኩራት ይሰማናል። ይህ የተገኘው ድል ሳይደናቀፍ ትክክለኛውን መንገድ ይዞ ወደፊት እንዲራመድ ለማድረግ ከለውጥ ኃይሉ ጎን በመሰለፍ የትግል ድርሻችንን የምንወጣ መሆናችንን እንገልፃለን።
2) የሀገራችን ጋሻና መከታ የሆነውን መከላከያ ሰራዊታችን ከሁሉም ብሔር ብሔረሶቦች የተውጣጣ እንደነብር ዥንጉርጉር ያማረ ፤ የዘር አጥርና የድንበር አስተሳሰብ የሌለው የማንነታችንና የአኩሪ ታሪካችን መገለጫ መሆኑን ለወገን ብቻ ሳይሆን ለሌሎቹ ሀገራትም ጭምር ጀግንነቱን ብቃቱን በተግባር አስመስክሯል።
መከላከያ ኃይላችን ተዋጊና ዳር ድንበር ጠባቂ ብቻ ሳይሆን ሰብአዊ መብትን ተንከባካቢ፤ ግጭትን ፈቺና አስታራቂ፤ የተቸገሩትን አጋዥና የሚያረጋጋ፤ አምራችና ሀገር ገንቢም ጭምር ተልእኮ እንደነበረው ሌላውን ትተን የሰሜን ዕዝ ላለፉት በርካታ ዓመታት ለኅብረተሰቡ የሰራቸውን ውለታዎች ስናስታውስ ከትግራይ ሕዝብ በላይ ሌላ ምስክር አይኖረውም።
ይሁን እንጂ «በሬ ከአራጁ ጋር ይውላል» እንደተባለው የእናት ጡት ነካሽና ሀገር አፍራሽ የሆነውን ጁንታ በሰራዊታችን አባላት ላይ የወሰደውን አሳፋሪ እርምጃ ሕገ መንግሥቱን የሚፃረርና የክሕደት ሥራ ከመሆኑም በላይ የትግራይ ሕዝብን ጨዋነትና ኢትዮጵያዊነት ክብር የሚዳፈር ወራዳ ተግባር ስለሆነ ድርጊቱን እናወግዘዋለን። መከላኪያ ሰራዊታችን የውስጥና የውጭ ጠላቶች ሴራ ሳይበግረው ለሀገሩና ለሕዝቡ የገባውን ቃል ኪዳን በደሙ ጠብታ መስዋዕትነት በመክፈል አስደናቂ በሆነ መልኩ በአጭር ጊዜ የተጎናፀፈውን አኩሪ ድልም እናደንቃለን። ለወደፊትም ህወሓትን በአካል መቅበር ብቻ ሳይሆን ሰይጣናዊ አስተሳሰቡንና በሀገራችን የዘራውን የዘር ጥላቻም ጭምር ከአእምሯችን ተጠራርጎና ተፍቆ ከነግሳንግሱ አብሮ እስከሚቀበር ድረስ የትግል ድርሻችንን ለመወጣት ከመከላከያችን ጎን እንቆማለን።
3) የትግራይ ሕዝብን መልሶ ለማረጋጋት የሚደረገው እንቅስቃሴ ቀላል ሥራ እንደማይሆን እንገነዘባለን። ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በትግራይ ሕዝብ ስምና ደም ሲነግድ የቆየው ህወሓት ዳግም ላይመለስ ቢቀበርም «እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል» በሚል እኩይ የአጥፍቶ መጥፋት ተግባር በመነሳት የመንግሥትና የሕዝብ የልማት ተቋማትን በማፈራረስ ያደረሰው ጉዳት የሚወገዝ ነው። እነዚህ የፈራረሱ መሰረተ ልማቶች ወደ ነበሩበት ደረጃ ለመመለስ ቀላል ሥራ እንደማይሆን እንገነዘባለን።
በሀገር ውስጥና በዲያስፖራም የሚገኙ የህወሓት ቅሪቶችና ተስፋ ቆረጥ ቡድኖች እያደሩ እንደጉም የሚበኑና የሚከስሙ ቢሆኑም ልማትን በማፍረስ ብቻ አልተወሰኑም። በትግራይ መረጋጋትም እንዳይኖር በመሬት ላይ የሌለ የሐሰት መረጃ በመፈብረክ በሕዝቡ ላይ የቀቢፀ ተስፋና የሥነ ልቦና ጦርነት ሙከራ ከማድረግ ገና አላረፉም።
በመሆኑም በቅርቡ በፌዴራል መንግሥት የተሰየመው የትግራይ ከልል ጊዜያዊ አስተዳደር እስካሁን እየሰራቸው ያሉትን የማረጋጋት ሥራዎች ተስፋ ሰጪና ጥሩ ጅምር በመሆናቸው እናደንቃለን። ለበለጠ ስኬትና ተግባራዊነትም ከአዲሱ ምሕዳር ጎን ተሰልፈን አቅማችንን የፈቀደው ሁሉ ለመተባበርና አብረን ለመስራት ዝግጁ መሆናችንን በዚሁ አጋጣሚ ለመግለፅ እንወዳለን።
የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን
4) ይህ በሀገራችን ላይ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ታሪካዊና አንፀባራቂ ድል እውን ሊሆን የቻለው በሀገር ውስጥም ሆነ በዲያስፖራ የሚኖረው የሁሉም ኢትዮጵያዊ ድምር የትግል ውጤት መሆኑን በሚገባ እንገነዘባለን። ስለሆነም ሕዝባችን ላለፉት ዓሰርቱ ዓመታት ያሳለፍከው ሰቆቃና የከፈልከውን አኩሪ መስዋእትነት ለፍትሕና ለነፃነት የተከፈለ ዋጋ ነውና ትግልህ መና አልቀረም ፍሬ አፍርቷል።
የሁሉንም ችግሮች ምንጭ በመሆን በተለይም በትግራይ ሕዝብ ስምና ደም ሲነግድ የኖረው የጁንታ ቡድን በንቀት በትዕቢትና በሙስና ቁንጣን ተሸብቦ ራሱን ከሕግ፤ ከሀገርና ከሕዝብ ልዕልና በላይ በመቁጠር ወገን ከወገን ጋር በማጋጨት እንደፈለገው ሲያምስና ሲያፈርስ መቆየቱን ጥሎ ያለፈው ጥቁር ጠባሳዎች ምስክሮች ናቸው።
ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ የዚህ ሁሉ ግፍ ድምር ውጤት ዛሬ እንደ ባቢሎን ግንብ ተደርምሶ ራሱ የዘራውን መርዝ ሲያጭድ፤ ራሱ በሰራው መከራ ዋጋውን ሲያገኝ፤ ራሱ በቆፈረው ጉድጓድ ሲቀበር ማየታችን የተገኘውን ድል ድርብ ድርብርብ አድርጎታል። በመሆኑም በዚሁ አጋጣሚ ለመላው ሕዝባችንና ታጋይ ኃይሎች ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ እንላለን።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !
ታኅሣሥ 11, 2013 ዓ.ም
አዲስ ዘመን ታህሳስ 15/2013