ወርቅነሽ ደምሰው
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅባቸውን ግዴታና ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገር ልማትና ሰላም ጉዳይ የሚያደርጉት ተሳትፎ ከምንጊዜውም በላይ እየጨመረ መሆኑ ይነገራል።
በዚህም አሁን ላይ በሀገራችን በተከሰተ ወቅታዊ ጉዳዮች ከሀገራቸውና ከወገኖቻቸው ጎን በመቆም አለኝታነታቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ። የዲያስፖራ ማህበረሰብ በተለይ ከለውጡ ወዲህ ከሀገራቸው ጎን ለመሰለፍ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን የሚናገሩት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ዋና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ናቸው።
ወ/ሮ ሰላማዊት እንደሚገልጹት፤ ኤጀንሲው ለዲያስፖራው ማህበረሰብ አሁን ላይ ያለውን የሀገራችን ወቅታዊ ጉዳዮች በተለይም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍሎች የተከሰተውን ሁኔታ፣ መንግሥት እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር እርምጃና ከዚህ ጋር ተያይዞ የተጎዱ ወገኖቻችን ከመደገፍ፤ የፈረሰውን መሠረተ ልማቶች ከመጠገን አኳያ በመንግሥት ሆነ በክልሉ በተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር በመከናወን ላይ ባሉ ተግባራት ዙሪያ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ መረጃ የማስተላለፍ ሥራ ሲሰራ መቆየቱ ያስረዳሉ።
በዚህም በውጭ በሚገኙ ሚሲዮኖች፣ የዲያስፖራዎች ማህበራትና የተለያዩ የዲያስፖራ ድርጅቶች በኩል መረጃው ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ ተችሏል። ለዲያስፖራው መረጃው ከደረስ በኋላ ደግሞ የመንግሥት አቋም ወይም ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን ተግባራትና እውነታውን በማብራራት ከለውጥ በፊትና በኋላ የነበረውን አጠቃላይ ሁኔታ በማስረዳት በተለያዩ አካባቢ የተለያዩ ቋንቋዎችንና የተለያዩ ሚዲያዎች በመጠቀም እንዲያስረዱ ተደርጓል።
ይህ የዲያስፖራው ማህበረሰብ ኃላፊነታቸውን በመወጣት ሀገራቸውን ያገለገሉበት አንዱ መንገድ በመሆኑ የሚያስመሰግናቸው ነው ያሉት ወ/ሮ ሰላማዊት፤ ከዚህ ባሻገር ለመከላከያ ሠራዊትና ለተጎዱ ወገኖቻችን በራሳቸው ተነሳሽነት ድጋፍ ማድረግ ይናገራሉ። በተለይ በዚህ በህግ ማስከበር እርምጃው ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለማከም የሚረዱ መድኃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶችን የጤና ሚኒስቴርና የመከላከያ ሚኒስቴር በጋራ ባወጡት ዝርዝር መሠረት በዲያስፖራው በኩል አስፈላጊ ድጋፎች እየተሰበሰቡ ነው።
በዚህም አንድ ወር ያህል ባልሟላው ጊዜ በዓይነት ሆነ በገንዘብ እስካሁን ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ ተችሏል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህንን ያህል ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉ ምንያህል በዓለም አቀፍና በሁሉም አካባቢ ያለው ዲያስፖራ ለመከላከያ ሠራዊትና በዚህ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖቹ በከፍተኛ ሁኔታ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የሚያሳይ ነው።
አሁንም ዲያስፖራው ድጋፍንና ተሳትፎ የቀጠለ ሲሆን፤ የፈረሱ መሠረተ ልማቶች መልሶ ግንባታ ላይ የሚያደርጉትን ተሳትፎ በማጠናከሩ በኃላፊነት በተሟላው ሁኔታ እየሰሩ ይገኛሉ። ዲያስፖራው አብዛኛው የሚያደርገው ተሳትፎ በራሱ ተነሳሽነት የሚሰራ በመሆኑ ለማስተባበር የሚያስቸግር አለመሆኑን ነው ዳይሬክተሯ የሚናገሩት።
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ በዲያስፖራው ማህበረሰብ የአመለካከት፣ የአስተሳሰብና የርዕዮት ዓለም ልዩነቶች ይኖራሉ። እነዚህ የሚከለከሉም ባይሆኑም፤ በተለያየ መንገድ፤ ሰልፍ በማድረግና በሌላም አግባብ ባልሆነ መንገድ ተቃውሞአቸውን የሚያሰሙ ወገኖች ቢኖሩም በቁጥር እጅግ ጥቂት ሲሆን፤ አብዛኛውን ዲያስፖራ የሚወክሉ አይደሉም። ይሁን እንጂ እነዚህ ወገኖች በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ ከጽንፈኛ ቡድን ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆኑን ይታወቃል። ለእነዚህ ወገኖች ምናልባት በቂ መረጃ ላይኖራቸው ይችላል ከሚል መነሻ መረጃዎች እንዲደርሳቸው እየተደረገ ነው።
የዲያስፖራው ማህበረሰብ ዋንኛ ሚና መሆን ያለበት ህጋዊ መንገድ በመጠቀም ወደ ሀገር ውስጥ የገንዘብ እና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግ ነው። በአብዛኛው ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚልኩት ብር እዚያው እየቀረ ለተለያየ አላማ እየዋለ ሀገር የማፍረስ፤ ወንድም እህቶቻቸው ላይ ችግር ሊፈጥር ስለሚችል በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ ቤተሰቦቻቸውን እየጎዳ መሆኑን አውቀው መጠንቀቅ ይገባል ። ስለዚህ በውጭ የሚኖር ዲያስፖራና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ለቤተሰቦቹም ሆነ ለሚፈልግ ጉዳይ ገንዘቡን ወደ ሀገሩ በሚልክበት ጊዜ ህጋዊ መንገዶችን በመጠቀም መላክ እንዳለበት መገንዘብ እንዳለባቸው ያስረዳሉ።
ሁለተኛው ደግሞ፤ ሀገራችንን ኢትዮጵያ ሰላማዊ ሀገር መሆኗን፤ ሕዝቡ ሰላምን የሚፈልግ መሆኑን መንግሥት የወሰደው የህግ ማስከበር እርምጃ በጣም ጥንቃቄ የተሞላበትና ሕዝቡን በማይጎዳ መልኩ ተልዕኮውን ማሳካቱን በዚህም ከፍተኛ ድል የተቀናጀ መሆኑ ለሚመለከታቸው ሁሉ በማስረዳት ይገባል የሚሉት ዳይሬክተሯ ፤ በየጊዜው በተለያየ ጉዳይ ውሸት የሆኑ ፕሮፖጋንዳዎች እንደሚወጡ ይናገራል።
ከኦፕሬሽኑ በፊት ሆነ በኋላ በእያንዳንዱ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ውሸት የሆኑ መረጃዎች ሲለቀቁ የቆዩ ሲሆን ፤ እነዚህ ጉዳዮች ሁል ጊዜ ከስር ከስር በመከታተል ከሀገራቸው ጎን በመቆም ውሸቱን የማጋለጥ እውነቱን የማጉላትና ዲፕሎማሲውንና አድቮከሲውን በመደገፍ የሀገራቸውን ክብር በመጠበቅ ለሀገራቸውን ክብር መቆም አለባቸው።
ዲያስፖራው በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ ታሪካዊ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፤ እስካሁን ባለው መረጃ ዲያስፖራው በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በዲፕሎማሲና በአድቮከሲ በሁሉም መስኩ በዚህ ደረጃ ተሳትፎ አድርጎ አያውቅም፣ ይሄ የመጀመሪያው ታሪካዊ ሥራ በመሆኑ በዚህ ሊኮሩ ይገባቸዋል ካሉ በኋላ ዲያስፖራው ለሚያደርጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
በአጀንሲው በዓመቱ የተያዙ በርካታ ሥራዎች መኖራቸውን የሚናገሩት ዳይሬክተሯ፤ በሀገራዊ ፕሮጀክቶች እንደ ገበታ ለሀገር ያሉ በጊዜያቸው መጠናቀቅ ያለባቸው የገንዘብ፣ የእውቀትና የዲፕሎማሲ ድጋፍ የሚፈልጉ እንዳሉ ይጠቅሳሉ።
እስካሁን ባለው ሁኔታ የሚታቀዱ የልማት ውጥኖችን ለመደገፍና ከሕዝብና ከመንግሥት ጎን ያለው የዲያስፖራው ተነሳሽነት በጣም አመርቂ መሆኑንና በቀጣይ መንግሥት የሚነድፋቸውን ዕቅዶች ለማሳካትም የጀርባ አጥንት እንደሚሆን አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 14/2013