ውብሸት ሰንደቁ
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራ በሯን ልትከፍት እየተንደረደረች ነው፡፡ ወደተግባር ሲገባ ኢንዱስትሪዎች መንግሥትን እንዲህ ወይም እንዲያ ያድርግልኝ ማለት አይችሉም፤ የሚኖረው አማራጭ በጥራትና በዋጋ ተወዳድሮ ማሸነፍ ብቻ ነው፡፡
በኢትዮጵያ በውጭና በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የተገነቡ ኢንዱስትሪዎች በተለይም የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ኢንዱስትሪዎች እዚህም እዚያም መከፈት ቢችሉም በኤክስፖርት ረገድ ያላቸው ተወዳዳሪነትና በጥራታቸው ያላቸው ተመራጭነት እምብዛም ሆኖ ይታያል፡፡
ከሰሞኑ በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኤክስፖርት ንቅናቄ መድረክ ይህንኑ ድባቴ ውስጥ የገባ አባዜን ለማንቃት ሲባል ውይይት ተካሂዶ ነበር፡፡ የንቅናቄ መድረኩ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓት ሥራዎች እንደ ሀገር ተኪ ምርቶችን በማምረት የሀገር ውስጥ የገበያ ፍላጎትን ማርካት አንዱ ኢላማው ነው፡፡ በተጨማሪም ኢንዱስትሪዎች በኤክስፖርት ሥራ ላይ ትርጉም ያለው አበርክቶ እንዲኖራቸው በማሰብ የኢንዱስትሪዎችን ግንዛቤ ለማሳደግ እና የኤክስፖርት መሰረትን ለማስፋት ያለመ ነው፡፡
ከኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ከአምስት እስከ አሥር በመቶ የሚሆነው ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ የኤክስፖርት ሥራን በተሻለ መልኩ እንዲለማመዱና ተወዳዳሪ ኢንዱስትሪዎችን ለመፍጠር እየሠራ ይገኛል። ከ2006 በጀት ዓመት ጀምሮ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ አስተዋጽኦ ማበርከት የተቻለ ሲሆን ንዑስ ዘርፉ ካለው የኢንዱስትሪ ብዛት እና ኤክስፖርት የማድረግ አቅም አንፃር ሲታይ አፈፃፀሙ ዝቅተኛ ነው፡፡ በአማካይ የምርት መጠኑ የነበረውም 19 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር በዓመት እንደሆነ ተመላክቷል፡፡
የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኬሚካልና የኬሚካል ውጤቶች እንዲሁም ብረት ነክ ያልሆኑ የኮንስትራክሽን ግብዓት አምራቾችን ሁለንተናዊ ድጋፍ ለመስጠት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 288/2005 የተቋቋመ ተቋም ነው፡፡
የኬሚካል እና ብረት ነክ ያልሆኑ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት አቅምን ለማሳደግ የሚያስችል ምርምርና ጥናትን መሠረት ያደረገ የተቀናጀ የኢንቨስትመንት፣ የግብይት እና የማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂ ድጋፍ ለልማታዊ ባለሃብቱ በመስጠት ተወዳዳሪ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ ማድረግም ዋና ዓላማው ነው፡፡ የኬሚካል እና ብረት ነክ ያልሆኑ የኮንስትራክሽን ግብዓት ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍን ለማሳደግ የሚያግዙ የጥናትና የምርምር ሥራዎችንም ያከናውናል፡፡
ይህ ተልዕኮው የመሠረታዊ ኬሚካል፣ የኬሚካል ውጤቶች እንዲሁም ብረት ነክ ያልሆኑ የግንባታ ግብዓቶች ኢንዱስትሪ አቅምን ለማሳደግ የሚያስችል ምርምርና ጥናትን መሠረት ያደረገ የተቀናጀ የኢንቨስትመንት፣ የግብይት እና የማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂ ድጋፍ ለልማታዊ ባለሀብቱ በመስጠት ተወዳዳሪ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ ማድረግ ላይ ያተኮረ ተቋም በኬሚካል፤ በኮንስትራክሽን ግብዓቶች፤ በኢንቨስትመንት፣ በግብይትና ቴክኒክ ዘርፍ አቋቁሞ እየሠራ ይገኛል፡፡
የተቋቋመበትን ዓላማ ሊያሳካ ይችል ዘንድም ኢንቨስትመንትን የመሳብ፤ የመከታተልና የመደገፍ፤ የአቅም ግንባታና የግብይት ልማት ሥራዎችን በመሥራት ላይ ነው፡፡ የግሉ ዘርፍም ከኢንስቲትዩቱ ጋር በተደራጀ መልኩ ችግሮችን ለመፍታት እና ከመንግሥት ጋር በጋራ ለመንቀሳቀስ ይችል ዘንድ ሰባት የዘርፍ ማህበራትን በማደራጀት በጋራ ሊሠሩበት የሚችሉበትን አውድ ፈጥሯል፡፡
በኬሚካል እና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ከ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊየን በላይ የአሜሪካን ዶላር ከንዑስ ዘርፉ ኢንዱስትሪዎች ለማግኘት እንደ ሀገር ግብ ተቀምጧል፡፡ ይህንን ግብ ለማሳካት በየዓመቱ በአማካኝ 120 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ከወጪ ንግድ ገቢ አፈፃፀም ማስመዝገብ ይጠበቃል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት 196 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው ምርት በኢንዱስትሪዎች ተመርቷል፡፡ ይህም በአማካይ ሲሰላ በየዓመቱ 39 ንጠብ 24 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ምርቶች ተመርተዋል ማለት ነው፡፡
በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ሲሚንቶ፣ ጅፕሰም፣ ሪሳይክልድ ፕላስቲክ፣ ፓኬጂንግ (ወረቀት/ ካርቶን)፣ ጎማ፣ ሳልፈሪክ አሲድ፣ የእንጨት ውጤቶች፣ ማርብል፣ ሴራሚክስ፣ ጠርሙስ፣ ፋይበር ግላስ፣ ወረቀት፣ ዳይፐር እና ችፕውድ የመሳሰሉት በዘርፉ የኤክስፖርት አቅም ተብለው የተለዩ ምርቶች ናቸው፡፡
ሆኖም የዘርፉ ኢንዱስትሪዎች በመንግሥት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ግብዓቶችን፣ የቴክኖሎጅ ውጤቶችን፣ የሰው ኃይል፣ ተሽከርካሪ እና መለዋወጫዎችን ከውጭ ለማስገባት የሚያስፈልጋቸው የውጭ ምንዛሬ መጠን ከፍተኛ ነው፡፡ በመንግሥት በኩል ለኢንዱስትሪዎች የሚፈቀደው የውጭ ምንዛሬ በዕርዳታ፣ በብድር እንዲሁም ከውጭ ወደ ሀገር ቤት በሚላክ ገቢ የሚሸፈን እንጂ ከወጭ ንግድ በሚገኘው ገቢ የሚሸፈነው እጅግ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ በመሆኑም ኢንዱስትሪዎች ለሀገራዊ የውጭ ንግድ ግኝት እያበረከቱት ያለው አስተዋፅኦ ደካማ ነው፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት ከውጭ ግብዓቶችንና ምርቶችን ለማስገባት የወጣ የውጭ ምንዛሬ በአጠቃላይ ለኮንስትራክሽን ግብዓቶችና የኬሚካል ውጤቶች ወደ 10 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ነው፡፡ ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ በቀጣይ አሥር ዓመታት በዚህ ዘርፍ ብቻ የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት ወደ 50 ቢሊየን የሚጠጋ ይሆናል፡፡
እንደ ሀገር ተኪ ምርቶችን በማምረት የሃገር ውስጥ የገበያ ፍላጎትን ከማርካት በተጨማሪ በኤክስፖርት ሥራ ላይም ትርጉም ያለው አበርክቶ እንዲኖረው በማሰብ ለኢንዱስትሪዎች ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሁም ከዘርፉ ዓላማዎች አንፃር የኢንዱስትሪዎችን ግንዛቤ ማሳደግ እና የኤክስፖርት መሰረትን ማስፋት አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይም በአሁኑ ጊዜ ከ5 እስከ 10 በመቶ የሚሆነውም ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ የኤክስፖርት ሥራን መለማመድ እና ተወዳዳሪ ኢንዱስትሪ ሆኖ መገኘት የግድ ነው፡፡
እስካሁን በዘርፉ ያለው የኤክስፖርት መጠን ውጤታማ አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ምክንያች ይጠቀሳሉ፡፡ ለኤክስፖርት ሥራ ግዴታ የገቡ ኢንዱስትሪዎች በገቡት የውል ግዴታ መሰረት ወደ ኤክስፖርት አለመግባታቸው፤ የምርት እና ምርታማነት በሚፈለገው መልኩ አለማደግ፤ ትርፍ ምርት በመጠንና በዓይነት ማምረት አለመቻል፤ የሀገር ውስጥ የገበያ ፍላጎት በከፍተኛ ፍጥነት ማደግ እና በአምራች ኢንዱስትሪው በኩል በውጭ ምንዛሬ ግኝቱ ላይ እኩል ድርሻ ያለመኖር ለዘርፉ ስኬት አልባነት የተዘረዘሩ መሰናክሎች ናቸው፡፡
ዘርፉ የሚመረቱ ምርቶችን ኤክስፖርት ማድረግ ምቹ ሁኔታዎችና ተግዳሮቶች ተሰባጥረው የቆሙበት እንጂ፤ መስኩ በድቅድቅ ጨለማ የተዋጠበት ሁኔታ ውስጥ አይደለም፡፡ እንደምቹ ሁኔታ ከተያዙት ውስጥ የኤክስፖርት ማበረታቻ ሥርዓት፤ ከአጎራባች አገሮች ጋር መልካም ግንኙነት፤ የሀገሪቱ ጂኦግራፊካል አቀማመጥ ለጎረቤት ሀገራት ኤክስፖርት ምቹ መሆኑ፤ መንግሥት ኤክስፖርት ለሚያደርጉ ኢንዱስትሪዎች ትኩረት መስጠቱ፤ የመሬትና የሌሎች መሰረተ ልማት አቅርቦት እና ከሌሎች አገራት ሲነፃፀር ርካሽ የኤሌክትሪክ አቅርቦት መኖሩ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
እንደ ዘርፉ ተግዳሮት የተጠቀሱት ደግሞ የኢንዱስትሪዎች ዝቅተኛ የማምረት አቅም፤ የቴክኖሎጂ ውስንነት፤ የሠለጠነ የሰው ኃይል በበቂ ሁኔታ አለመኖር፤ ጉሙሩክና ባንክ ከመሳሰሉ የመንግሥት ተቋማት ዘንድ አሰራሮች ቀልጣፋ አለመሆን፤ ኢንዱስትሪዎች በጥራትና በዋጋ ከሌሎች አገራት ጋር ተወዳዳሪ አለመሆን እንዲሁም የትራንስፖርት ዋጋ በየጊዜው መጨመር ተዘርዝረዋል፡፡
የኤክስፖርት ሥራ የውጭ ምንዛሬ የማስገኘት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ተወዳዳሪ ኢንዱስትሪን የመገንባት፣ ኢንዱስትሪዎች ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን እንዲያሟሉ ዕድል የማግኘት ጉዳይ ጭምር ነው፡፡ ኢንዱስትሪዎች እንደ ኢንዱስትሪ የመቀጠል የህልውና ጉዳይ ከኤክስፖርት ሥራ ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ነው፡፡
የዘርፉ ኢንዱስትሪዎች የአፍሪካ የንግድ ቀጠና ስምምነት ወደ ተግባር ሲገባ በዓለም አቀፍ ገበያዎች ላይ ተወዳዳሪ ምርቶችን ይዘው የማይቀርቡ ከሆነ፤ በሀገር ውስጥ ገበያ ሌሎች አቅም ያላቸው ኢንዱስትሪዎች በጥራት፣ በዋጋና በፓኬጅንግ ለሀገር ውስጥ ገበያ የተሻለ ምርት ይዘው ስለሚቀርቡ ኢንዱስትሪዎች የኤክስፖርት ሥራን የህልውና ጉዳይ አድርገው ሊወስዱት ይገባል፡፡
ለወትሮው የኤክስፖርት ልምምዳቸው እምብዛም ከመሆኑ የተነሳ ነፃ የንግድ ቀጠናው ከመከፈቱ ጋር ያለውን ተግዳሮት እንዴት መወጣት እንደሚችሉና የሚመጡ መልካም አጋጣሚዎችን እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ ከወዲሁ የሥነ ልቦና፣ የምርት ዋጋና ጥራት ተወዳዳሪነት ላይ ልምምድ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በዚህ ዙሪያ በኤክስፖርቱ ላይ ቀደም ብሎ በጥቂቱም ቢሆን ልምምድ ከነበራቸው ኢንዱስትሪዎች ነፃ ገበያው ሲከፈት በሀገር ውስጥም ይሁን በሌሎች አገራት ገበያና ጥራት ያላችሁ የተወዳዳሪነት አቅም ምን ይመስላል፤ የሚፈጠሩት ሁኔታዎች አያሰጓችሁም በሚለው ዙሪያ ጥያቄ አንስተንላቸው ነበር፡፡
ወይዘሮ ትህትና የዋሪት ፈርኒቸር ማኔጅንግ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በዋነኝነት ድርጅታቸው የሚያመርተው ፈርኒቸር ነው፡፡ በዘርፉ ከ15 ዓመት በላይ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ በፊት የምርታቸውን ብዙ ግብዓቶች ከውጭ በማስመጣት ነበር የሚሠሩት፡፡
በአሁኑ ጊዜ ወደማኑፋክቸሪንግ በጥልቀት ገብተዋል፡፡ በፊት ከሀገር ውጭ ያስመጧቸው የነበሩ የፈርነቸር ውጤቶችን ጠረጴዛ፣ ሸልፍና የመሳሰሉትን ምርቶች እዚሁ ሀገር ውስጥ ማምረት ጀምረዋል፡፡ ኤክስፖርትን ለማበረታታት የተደረገው ውይይት ጥሩ እንደሆነም ያምናሉ፡፡ “በእርግጥ ዘግይተናል፡፡”
ያሉት ወይዘሮ ትህትና እንድንወያይ ሁኔታዎች መመቻቸታቸው ጥሩ ቢሆንም ሀገሪቱ ለነፃ ገበያ በሯን ልንከፍት አጭር ጊዜ ሲቀረው አልነበረም ኤክስፖረትን የማነቃቃት ሥራ መጀመር የነበረበት ብለው እንደሚያምኑ ነግረውናል፡፡
እንደወይዘሮ ትህትና ሃሳብ ኢትዮጵያን ከውጭ ገበያ ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግ የግሉን ብቻ ሳይሆን የመንግሥትን ጠንካራ ተሳትፎ ይፈልጋል፡፡ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት በተቸገርንበት ሁኔታ ኤክስፖርት ለማድረግ ላይመች ይችላል፡፡
ስለዚህም በትክክል ኢንቨስት አድርጎ ኤክስፖርት ለማድግ ለሚሠሩ ኢንዱስትሪዎች የውጭ ምንዛሬ መፈቀድ አለበት ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ለውጭ ዜጎች የግብር አከፋፈል ላይ የሚሰጡ ትኩረቶች ትልቅ ሆነው ለሀገር ውስጥ ባለሀብቱ የሚሰጡት አናሳ ናቸው፡፡ በተለያዩ አገራት እንደሚደረገው የኤክስፖርት አቅማችን እንዲጨምር ለሀገሪቱ ዜጎችና ባለሀብቶች የሚሰጡ ትኩረቶች ሊጨምሩ ይገባል፡፡
በ2017 እና 2018 ምርቶቻቸውን ወደ ኬንያ፣ ሱዳንና ሌሎች አገራት ይዘው ሄደው ለማስተዋወቅ ሙከራ ማድረጋቸውንና በዚያች ጊዜ የፈጠሯት ዕድል ለኤክስፖርት ግንኙነት እንዲኖራቸው ዕድል ማግኘታቸውን ይናገራሉ፡፡
አሁንም ከአምስት እስከ 10 በመቶ ኤክስፖርት እንድናደርግ በሚፈለገው መሠረት መንገዶች ከተመቻቹና በቀጣናው ሰላም ካለ ያንን ማድረግ የሚያቅት አይሆንም፡፡ አክለውም ድርጅታችን ምርቶቹን የኤክስፖርት ደረጃቸውን የጠበቁ መሆን እንዲችሉ የማሽነሪም ሆነ የሰው ኃይል አሟልተን ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
አቶ አዳነ በርሄየ አዳኤል ኢንዱስትሪያል ኃ.የተ.የግ.ማ. መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ለነፃ የንግድ ቀጠና አባል አገራት በሯን የመክፈቻ ወቅቷ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ የተወዳዳሪነት ውጣ ውረድ ካልመጣብን በስተቀር በጥራት አናመርትም የሚሉት አቶ አዳነ መንግሥት ለአምራች ኢንዱትሪዎች የሚያደርገው መከላከል ይበቃናል ብዬ አምናለሁ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ይህ በሚሆንበት ጊዜ ግን የውጭ ምንዛሬ እንዲኖረን፤ የመንግሥት ፖለሲ በአግባቡ እንዲፈፀም እንዲሁም ሁኔታዎች እንዲመቻቹልን ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡ ከዚህ ውጭ የሌሎች አገራት አምራቾች ወደሀገር ውስጥ እንዲገቡ መደረጋቸው የበለጠ ተማምረውና ተወዳዳሪ ሆነው እንዲያመርቱ ዕድል ይፈጥራል፡፡
የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ባለቤቶችንና መሪዎቹን ሃሳብ መረዳት እንደሚቻለው መንግሥት ሊያሟላቸው የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎች እንዳሉና እነዚህ ሲሟሉ የኤክስፖርት ሥራው ይጀመራል፡፡
በመሆኑም የተጠቀሱት የአሠራር ሥርዓት በአግባቡ ተዘርግቶ ተፈፃሚ እንዲሆን መሥራት፤ የውጭ ምንዛሬ ለዘርፉ አሳላጮች ማመቻቸት፤ ሰላምን ማስጠበቅና የትራንስፖርት አገልግሎቶችን ማዘመን መንግሥት ትኩረቱን ሳይነቅል ከሠራባቸው በኢንዱስትሪዎቹ በኩል ያለው ተነሳሽነት ተስፋ ሰጪ ነው፡፡
ከተወዳዳሪነትና ከጥራት ሸሽቶ አሸናፊነትን መመኘትም ማግኘትም አይቻልምና መንግሥትም ሆነ የግሉ ዘርፍ ተቀናጅተው መሥራት ያለባቸው ጊዜ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 14/2013