ለምለም መንግሥቱ
በመቀሌ ከተማ ለሁለት ዓመታት ያህል መሽጎ የቆየው የህውሓት ጁንታ እኩይ ተግባር በሆነ ድርጊቱ በዜጎች ላይ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት በማድረስ፣ሀገር ለመበታተንና ለማፍረስ ለዓመታት ሲንቀሳቀስ መቆየቱ ፀሐይ የሞቀው እንደሆነ ይታወቃል።የመጨረሻ የክህደት ማሳያው ደግሞ ሀገርን ከውጭ ወራሪ ኃይል የሚጠብቀውን፣ ሀገሩን፣ህዝቡንና መንግሥቱን አስቀድሞ ቤቱን ትቶ በዱር የሚያድረውን፣በልማትና በሰብዓዊ ድጋፍ የሕዝብ ወገንተኝነቱን እየተወጣ የሚገኘውን፣የሀገር ኩራት በሆነው የመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመው ጥቃት ነው።
በሴራ ፖለቲካ የተተበተበው የህወሓት ጁንታ ቡድን እኩይ ተግባር የመንግሥትን ትዕግሥት በእጅጉ የተፈታተነ እንደነበርም አይዘነጋም።ዜጎች መንግሥትን ሕግ የማስከበር አቅም እስኪጠራጠሩ ድረስ የደረሰ እንደነበርም ከዜጎች አልፎ ዓለም ያወቀው ነበር።
ከ80 በላይ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በቋንቋ፣ በባህል፣ በዘርና በኃይማኖት ሳይለያዩ «ልዩነት ውበት ነው» ብሎ ተቀብሎ አንዱ የሌላውን አክብሮና ተፈቃቅሮ የሚኖረውን ሕዝብ ለማጋጨት ያልተሞከረ ሙከራ የለም።
ሀገሪቱ ያላት መልካም የሆኑ እሴቶቹ በዓለምም በመልካም ስሟ የሚነሳውን የኢትዮጵያውያን ስም ለማጥፋት በርካታ ሴራዎች ተገምደዋል።አንዱን ብሄር ከሌላው ጋር አንድን ሃይማኖት ከአንዱ ጋር በማናከስ የስልጣን ጥሙን ለማርካት ተዘርዝረው የማያልቁ ህልቆ መሳፍርት ተንኮሎችን ሲሸርብ ኖሯል። የዚህ ሴረኛ ቡድን ግፍና በደሉ በዝቶ፤ መንግሥትም ሳይወድ ተገዶ፣የህዝብም ሮሮ በዝቶ ህግ የማስከበሩን እርምጃ ሊወስድ ችሏል።
የህግ ማስከበሩ ሂደትም ዜጎች ሳይጎዱ፣ለዓመታት የተለፋበትና የሕዝብ ሀብት የፈሰሰበት የልማት ሥራ እንዳይፈርስ ጥንቃቄ በተሞላበት የህግ ማስከበር እንቅስቃሴ በአጭር ጊዜ መከናወኑ ለህዝብ ጆሮ የደረሰ ጉዳይ ነው።ታዲያ ይህ ህዝብንም መንግሥትንም ያስቆጨ ድርጊትና ይህንኑም ተከትሎ እየተወሰደ ያለውን የህግ ማስከበር እንቅስቃሴ ዜጎች ያለመታከት የየቀኑን መረጃ ለማግኘት አይንና ጆሮአቸውን ከፍተው በንቃት ነበር የሚከታተሉት።
በጥቂት ጁንታዎች ሀገር ስትታመስና ወንድም በወንድሙ ላይ ቃታውን ሲስብ ለምን አያስጨንቅ፣የሀገሪቷ እጣ ፈንታስ ለምን አያሳስብ፣ያለጥፋቱ ደሙ በከንቱ የሚፈሰው ወገን ጉዳይ ያንገበገበው ሁሉ ያለውን ኩነት ለማወቅ መገናኛ ብዙሃንን መከታተል የዕለት ተግባሩ አድርጓል።
አንዱ ከተለያየ መገናኛ ብዙሃን የሰማውን ለወዳጁ በስልክ መረጃ እስከመስጠትና የመከታተል ልምድ የሌላቸውን ሁሉ ቀልብ የገዛው ሀገራዊ ጉዳይ ዛሬም የማወቅ ፍላጎቱ እንደቀጠለ ነው።ህግ ማስከበሩ በአጭር የተቋጨ መሆኑ ቢገለጽም ጦርነቱም ከተቋጨም በኋላም ቢሆን ዋናዎቹ ጁንታዎች ያሉበት ሁኔታ ገና ለህዝብ ይፋ ባለመሆኑ የየዕለት መረጃ መፈለጉ እንደቀጠለ ነው።
ታዲያ ይህን የህዝብ ፍላጎት የተረዱት በየማህበራዊ ድረገጾቻቸው መረጃ የሚያስተላልፉት በለስ የቀናቸው ይመስላል።ነግቶ እስኪመሽ ርዕሶቻቸው ሰበር ዜና ናቸው።የተሟላ መረጃ አግኝቶ ለህዝብ ጆሮ ለማድረስ የሚወስደውን ጊዜ ያልተረዱና ሥለመገናኛ ብዙሃን አሰራር ያልተረዱ መረጃ የተነፈጋቸው አድርገው በመቁጠር ፊታቸውን ወደነዚህ ሰበር ዜና አቅራቢዎች በማዞር እውነቱን ለመስማት ተጠምደው ይውላሉ።ግን ደግሞ መስማት የፈለጉትን ሲያጡ ይበሳጫሉ።
በተለይ ማህበራዊ ድረ ገጽን በመከታተል አንዱ የሰማውን ለሌላው በስልኩ ሲያስተላልፍ ነው የተዛባና እውነትነት የሌላው መረጃ እየተላለፈ መሆኑን የሚገነዘበው።ከማህበራዊ ድረ ገጹ ያገኘውን መረጃ መሠረት አድርጎ እንኳን ደስ አለህ፣ወይንም እንዲህ እየተፈጸመ ነው ብሎ የተናገረው ነገር ሳይሆን ሲቀር በራሱ መልሶ የሚበሳጨው ይበዛል።ታዝባችሁ ከሆነ አንዳንዶች ማህበራዊ ድረ ገጽን መሠረት አድርገው ለሌላው ሲያወሩ ሕግ በማስከበሩ ቦታ ያሉ ይመስላሉ።
ሽምቅ ውጊያ ነው።ጦርነቱ ተፋፍሟል።ከነአባባሉ ‹‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው›› ይባል የለ።እኒህ የማህበራዊ ድረ ገጽ ውጤቶች ምን ያህል ወደተሳሳተ መንገድ እንደሚመሯቸው እና አሁን ሀገሪቷን የገጠማት ችግር አንዱ በማህበራዊ ድረገጽ የሚተላለፉ ያልተረጋገጡ መረጃዎች ለመሆናቸውም ማሳያ ነው።
እንኳን ይህን ትልቅ ሀገራዊ ጉዳይ ቀርቶ በአንድ መንደር የተፈጠረ የሰላም መታወክ መረጃ አጠናቅሮ ለሕዝብ ጆሮ ለማድረስ ቀላል የሚባል ሂደት እንዳልሆነ ተከታዮቹ ቢረዱ እነርሱም የተከታይ ቁጥር ለማብዛት ለሚንቀሳቀሱ ማህበራዊ ድረገጾች ተባባሪ ባልሆኑ።አንዳንዶችም የዋህ መሆናቸው ሕግ ማስከበሩንም ቀለል አድርጎ ማየታቸው ይመስለኛል።
ሕግ የማስከበሩ እንቅስቃሴ ከውጭ ወራሪ ኃይል ጋር ሳይሆን ከጥቂት አፈንጋጮች ጋር በመሆኑ እጅግ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል።መስማት የሚፈልጉት ነገር ለማግኘት ብለው ሲከተሏቸው ነገሮችን ባልተገባ መንገድ እንዲረዱ እንደሚያደርጓቸውና ርዕስ በማስጮህ ቀልብ ለመሳብ የሚሞክሩት ማህበራዊ ድረገጾች ብዛት ያለው ተከታይ ለማፍራት የሚከተሉት ዘዴ እንደሆነ ቢረዱ ይበልጥ ይበሳጫሉ ብዬ አስባለሁ።
በቦታው ሳይገኙ በይሆናልና በስሚ ስሚ ሰበር ዜና ብሎ ለመረጃ የማይበቃ ነገር በቀላሉ ማስተላለፍ ከተቻለ ሙያው የሚጠይቅን ሥነ ምግባር ለመማር የትምህርት ቤት ደጃፍ ባልተረገጠ ነበር።በሙያው ላይም ሆኖ ትክክለኛውን መረጃ ለሕዝብ ጆሮ ለማቅረብ የብዙ ተቋማት በር ማንኳኳትም ሆነ በሥፍራው መገኘትን ባልጠየቀ ነበር።ኃላፊነት ባልተሞላበት በሞቀና በተደላደለ ቦታ ሆኖ ያውም ትልቅ ተልዕኮ ያለውን የሕግ ማስከበር በቀላሉ እነከሌ ተያዙ፣ተገደሉ የሚሉ ሙቀት የሚፈጥሩ መረጃዎችን እያራገቡ ገንዘብ ማግኘት የተለመደ ሆኗል።
ስለማህበራዊ ድረገጽ አቀራረቦች መናገር ለቀባሪው አረዱት እንደሚባለው አይነት እንዳይሆንብኝ እንጂ አሁን አሁን ብዙዎች የተረዱትና ጥቂት ብልጣብልጦች ሊከብሩበት የሚዳዱበት መንገድ መሆኑን ጸሐይ የሞቀው ሀቅ ነው።ያልተረዱ ጥቂቶች ሰበር በሚለው ውስጥ ሰምጠው እንዳይቀሩ ማስተዋል እንዲኖራቸው ፈልጌ ነው ስለ ጉዳዩ ማንሳቴ።በርግጥ ሁሉንም የሚያነሳውም ሆነ የሚጥለው ሚዛን ስላለ ሚዛኑ ሲያጋድል መውደቅ አይቀርም።
ርዕስ በማስጮህ ቀልብ ለመሳብ የሞከሩ ማህበራዊ ድረገጾች ከአጓጊነት ወደ አሰልቺነት ለመለወጥ ጊዜ አልፈጀባቸውም።የሰውን ሥነልቦና እያዩ የሚለቁት መረጃ ከእውነትነቱ ይልቅ አሳሳችነቱ እየበዛ መሰላቸትን ፈጥሯል።ከመንግሥታዊ አካል መረጃ ተነፍጎናል እያሉ ቅሬታ ሲያሰሙ የነበሩ መረጃ ፈላጊዎችም በሂደት ሚዛናዊነትን የተረዱ ይመስላሉ።ስንወቃቀስ እንደጁንታው እንዳይመሽብን የማህበራዊ ድረገጽ ሰበር መረጃ አቀባዮች ለኃላፊነት ንቁ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 14/2013