አዲስ አበባ፡- የጀርመን መንግሥት ለዘርፉ የሚያደርገው ድጋፍ በስልጠና ጥራቱ ላይ ከፍተኛ አዎንታዊ አስተዋፅዖ ማበርከቱን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተሻለ በሬቻ ትናንት የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ተቋሙን በጎበኙበት ወቅት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የጀርመን መንግሥት ኢንስቲትዩቱን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍን ሲደግፍ ረዘም ያለ ጊዜ አስቆጥሯል፡፡ ኢንስቲትዩቱም ከተቋቋመበት 2003 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ድጋፎቹን አግኝቷል፡፡ በገንዘብ ቢተመን ከ60 ሚሊየን ዩሮ በላይ ድጋፍ ያገኘ ሲሆን፤ ይህም በስልጠና ጥራቱ ላይ ውጤት እንዳስገኘ በዕለት ተዕለት ተግባርና ውጤት ታይቷል፡፡
ዋነኛ ትኩረቱ አቅም ግንባታ የሆነው ድጋፉ በሰው ኃይል፣ በአመራርና በመምህራን አቅም ግንባታ ላይ ይሰራል፡፡ በዚህም ለመምህራኑ የተለያዩ ስልጠናዎችን የመስጠት፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮን የመቀመር እንዲሁም ስርዓት በመዘርጋት አቅም ግንባታውን ለማሳካት የሚያከናውናቸው ተግባራት ተጠቃሽ ሲሆኑ፤ አስፈላጊ ግብዓቶች እንዲሟሉ ድጋፍ ማድረግም ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫው ነው፡፡
የአቅም ግንባታ ሥራው የሚመራው በጀርመኑ ድርጅት ጂአይዜድ ሲሆን፤ የግብዓት ድጋፉ ደግሞ ኬኤፍደብሊው በሚባለው የጀርመን ኢንቨስትመንት ባንክ የሚደረግ ነው፡፡ ባንኩ መሳሪያዎችን፣ አስፈላጊ ግብዓቶችንና ተሽከርካሪዎችን ላለፉት ዓመታት ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ሲደግፍ ቆይቷል፡፡ በዚህም ተቋሙ በአውሮፓ ደረጃ ግብዓቶች የተሟሉለት ተቋም ሆኗል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ፤ ፕሬዚዳንቱ በይፋዊ የሥራ ጉብኝታቸው ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርና ፕሬዚዳንት ጋር የመከሩ በመሆኑ በሥራው ላይ የተሻለ ውጤት እንደሚጠብቁ ዕምነታቸውን ገልፀዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና መምህራንና አመራሮችን የሚያፈራ በመሆኑም በዘርፉ የሚስተዋሉ የአመለካከት ክፍተቶችን ለማቃለል በዋናነት ገጽታውን ለመገንባት የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመተግበር አቅዷል፡፡ ለዚህ የሚረዳውን ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡
ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት የገቡት ኢትዮጵያ የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር፤ በኢንስቲትዩቱ በተመለከቱት ሥራ ተደስተው ድጋፉ ትክክለኛ ቦታ ላይ መዋሉን አረጋግጠዋል፡፡ ለጀርመን የኢኮኖሚ ጥንካሬ ትልቅ መሠረት ሆኖ የሚነሳው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈል መንግሥታቸው ይሰራል፡፡ ለዓመታት በዘለቀው ስኬታማ ተግባራት መነሻም የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ወደፊት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ቃላቸውን በመስጠት፤ ግንኙነቱ በአሁኑ ወቅት ካለበት ወደተሻለ ደረጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡
የሁለቱ አገራት የልማት አጋርነት እአአ 1964 የጀመረ ሲሆን፤ በነበረው ቆይታም 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዩሮ ጀርመን ለኢትዮጵያ አበርክታለች፡፡ ባለፈው ዓመትም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፉን በመደገፍ በኢኮኖሚው ውጤት ለማምጣት ተጨማሪ የ210 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ ማድረጓ ታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 22/2011
ፍዮሪ ተወልደ