ከመምህር አሠምሬ ሣህሉ
ሰሞኑን በምድራችን የሆነውንና በወገኖቻችን ላይ፣ እየሆነ ያለውን ነገር ከዓይን እማኞችና ከሰቆቃው በተረፉ ዜጎች ሲነገር ስንሰማ፣ መከራና አበሳ መፈጠርን የሚያስጠላና ሰው የመሆንን ትርጉም የሚያሳጣ ተግባር ሁሉ አንገሽጋሽ ነው። ለዚህም ነው፤ በርእሱ ላይ እንደገለጥኩት ምድሪቱ ታጥባ እንድትጠራ ቄደር ያስፈልገናል ያልኩት።
ገና ገና የእነዚህ ነገሮች አመጣጥ ያስፈራቸው ቀደምት ፀሐፍት ሁሉ ይህንን ጥያቄ አቅርበው ነበረና፤ ምን ስሁት ነገር ተገኘብንና ነው አንዴ ጸበል፣ አንዴ መድህን ያስፈልገናል፤ እያልክ የምትጽፈው፣ ሲሉ ይወዘግቧቸው፣ ይጎነትሏቸውና ያብጠለጥሏቸው አንዳንዴም ሥራ ስፍራቸው ድረስ በመምጣት ዕቃ ይገለባብጡባቸው እንደነበረ ይታወቃል።
አንዳንዶቹንም ባልዋሉበት አውለው፣ ባልሄዱበት አስኪደው፣ ከብዕር በቀር የቦንብና ፈንጂን ቅርጽና አሰራር በፎቶ ካልሆነ የማያውቁትን ሰዎች፣ በቦንብ ማፈንዳትና በሀገር ማፍረስ በብሔር ጠልነት ወይ ብሔርን ከብሔር በማጣላት ክስ በመክሰስ፣ ዕድሜ ልክና አስራ ምናምን ዓመታት ባሉበትም በሌሉበትም ይፈርዱባቸው ነበረ፤ እነ እንቶኔ ጁንታ።
ለማንኛውም ይህ ገዳይ ኢ-ፍትሐዊና ስግብግብ አስተሳሰብ ከምድራችን እንዲጠፋ አሁንም ቄደር ያስፈልገናል። በየትኛውም የሀገራችን ክፍል ሰርተን እንድንገባ ቄደር ያስፈልገናል፤ የፍቅር ቄደር፣ የመያያዝ ቄደር፣ የልብ ለልብ የመግባባት ቄደር በአንደበትም በመንፈስም መረጨት አለበት።
አሜሪካ ባርነት ይቅርና አይቅር በሚሉ ሰሜንና ደቡባውያን መካከል ግጭት ተቀስቅሶባት በነበሩት ዓመታት ሀገሪቱን የመራው ፕሬዚዳንት አብረሐም ሊንከን፣ ለአሜሪካውያን መጪ መሪዎች ሁሉ ያሳሰበው መልዕክት «በጸብ ያልተገነባችውን ሀገራችንን በፍቅር እናቆማታለን እንጂ በእብሪት አናፈርሳትም፤ ምክንያቱም በሕገ-መንግሥታችን መግቢያ ላይ በፍቅር ያቆምነውን ሕገ መንግሥት በፍቅር እና በመስዋእትነት እንጠብቀዋለን፤» ነው የሚለው ብሏቸው ነበረ።
እናም በመስዋእትነት ጠብቆ የዛሬዋን አሜሪካ ለትውልዱ ሁሉ አስረከበ እንጂ፤ ሀገሪቱን ለጥቂት የባሪያ ንግድ አራማጅ ክፉዎች፣ ስግብግብና በታኝ አሳቢዎች አልተዋትም። ያ፣ የመግባቢያ ሰነድ ወደሕይወትና የፍቅር ቄደር ተለውጦ አሜሪካንን አቁሟታል፤ እንጂ አልበተናትም። ለዚህም ሊንከን ራሱ ሕይወቱን ሲገብርላት፣ አሜሪካ ግን አልተበተነችም፤ ምክንያቱም ሕግ እና ሥርዓት ጠንክሮ ከግለሰቦች በላይ ገዝፎ ቀጠለ እንጂ አልሟሟም።
ሀገርን እኔ ካልመራኋት ከቶውንም፣ ሀገር አትሁን ብሎ ለሚዝት ጉጅሌ ኃይል፣ ፈቃድ ትተዋለችን? ከቶውንም የማይታሰብ ነገር ነው።
ሲጀመርም የዜግነት ፖለቲካ አብዛኛው ለሚባል የሕዝብ ቁጥር (ለኦሮሞና አማራ) ያዳላል፤ ከሚል የትንሽነት ክፉ ፍራቻና መደምደሚያ፣ የተነሳ ምድሪቱን በጥቃቅን የቋንቋ አስተዳደሮች ከፍሎና ሌላውን ነባር ነዋሪ (አንዳንዱ እስከ አራትና አምስት ትውልድ የኖረን) ባይተዋር አድርጎ የሚያስር የተከፋፈሉ አስተዳደሮች በየስፍራው ፈልፍሎ ያቆየው ቡድን፤ የከፋፈላቸውንም እንኳን ለራሱ እንዲመቹና ለራሳቸው እንዳይሆኑ፣ በፈቃዱ እንጂ በፈቃዳቸው እንዳይኖሩ አድርጎ ጠርንፎ ለሰላሳ ዓመታት ገደማ ሲያድፋፋቸው እና ሲቆርጥ ሲቀጥላቸው ቆይቶ አቅም አጥቶ፣ ማጣፊያው ሲያጥረው፣ «ሊጨፈልቋችሁና በባርነት አገዛዝ ስር ሊከትቷችሁ ነውና ፤ ኑ እና ጩኸቴን ተጋሩኝ» የሚል የረፈደ ሰዓት ዋይታ ማሰማቱ አስገራሚ ነው።
በሌላ አባባል እኔ ስገዛችሁ፣ ስነዳችሁና ስፈልጣችሁ ልክ ነው፤ በእኩል ስትቀመጡ ወይም እንቀመጥ «ስትሉኝ» ግን አያምርም፤ በመረጥኩላችሁ እንጂ በመረጥኩት መንገድም ልመራ ልስተዳደር ብሎ ማለት፣ ልክ አይደለም፤ ብሎ የሚያሟርትን የበሰበሰና ተነቅሎ የተንገዋለለን፣ የቀደመ ክፉ አገዛዝ ለመመለስ መጣጣር ነው።
ይህም ደግሞ ወንዝን ወደ መጣበት ከፍታ ሽቅብ እንደ ማስኬድ መሆኑን ሲረዱ፣ እብሪታዊ እርምጃ ወደመውሰድና ሀገርን ወደምስቅልቅል ለመክተት የሚጋብዝ ክፋትን እንደ አማራጭ መጠቀምን መረጡ፤ ይህ አርዮሳዊ ክህደት ነው።
እውነት ነው፤ የማጅራት መቺ ትንሽ የለውም፤ እውነት ነው፤ የክፉ ትንሽ የለውም፣ እውነት ነው፤ የአድፋጭ ደካማ የለውም። ያውም እርሱ ጠላት ነው፤ መመታት አለበት፤ መወጋት እና መሽመድመድ አለበት፤ ብሎ ያሴረና በሌላ በኩል ደግሞ እርሱን ያመነው ኃይል፣ በእንቅልፍ ላይ በሆነበት ምሽግ፣ ሁሉን ለወገኑ ትቶ በድካም ባንቀላፋበት ምድር የተነሳው አድፍጦ መቺ ኃይል አይናቅም። ይህንን የራስም ሆነ በቅርብ በሚያውቁት ሰው ላይ በደረሰ የደፈጣ ጥቃት ያውቁታል።
በዚህ ጊዜ ደግሞ ከተመቺው ይልቅ ለመቺው ሁሉም ነገር ሰርግና ምላሽ እንደሚሆንለት አይጠረጠርም።
መሣሪያውን ነጥቀው ለጥቃት የመልሶ ማጥቃትም ሆነ የመከላከል አቅሙን አዳክሞና የመሣሪያ ግምጃ ቤቱን ሰው አንድም አጭበርብሮ፣ ካለዚያም በኃይል አስረው ካስወገዱ በኋላ፣ በድፍረት ፍላጎትን መፈፀም እንግዳና የሚያሳዝን አሰቃቂ እርምጃ ነው፤ በራሱ።
ከሁሉም ከሁሉም ግን አሰቃቂውና ግራ አጋቢው ነገር ሳይወድ ይሁን ተገድዶ እጅ የሰጠን «ጠላት ያልሆነን ጠላት» የተባለን፣ ኃይል ከ40 እና 50 ኪሎ ሜትር በላይ እጁን አስሮ ረዥም መንገድ በጨለማ በእግር ካስኬዱት በኋላ ከግራና ቀኝ በጥይት ተኩስ አዋክቦ ጎዳናው ላይ ራሱን ለማስመለጥ ሲተኛ፣ በ «ሲኖ ትራክ» የጭነት መኪና በሕይወት እያለ እርቃኑን መደፍጠጥ ምን የሚሉት ጭካኔ ነው። ይህ ኃይል የወራሪ ኃይል ሰራዊት ነውን? ይህ ኃይል ግፍ የፈፀመ የሌላ ሀገር ዜጋ የሆነ ወታደር ነውን? ማነውስ? ጭካኔውንስ ምን ስም ይሰጡታል? ቢሆንስ ደግሞ፣ ከዛሬ 130 ዓመታት በፊት በአድዋ ውጊያ የተማረኩትን የጣሊያንን ሰራዊት አባላት የምኒልክ ጦር የያዘበት አያያዝ፣ በሰብዓዊነቱ በስንት ጣዕሙ ከእናንተ ተሻለ። እንዴት ከ130 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ከነበረና «ጨካኝ ነው፤»
እያላችሁ ከምትከስሱት የምኒልክ ጦር ይልቅ ራሳችሁን አላዋረዳችሁምን? ከእነርሱ የተማራኪ ሰብዓዊ አያያዝ እንዴት አንሳችሁ ተገኛችሁ? ኋላ ቀርነታችሁ ከዚያን ጊዜው የምኒልክ ጦር ማነሱን አልተረዳችሁትምን ? ምኒልክንስ የመውቀሻ ሞራልስ አላችሁን? እነዚህ ሰዎች እኮ፣ እንደ ኦሽዊትዝ የጋዝ ቻምበር አላሰናዱም ነበር እንጂ፣ ቢኖራቸው ኖሮ፣ በጋዝ አሰቃይቶ ወደሚገድለው መጋዘን ሰራዊቱን ይከቱት እንደነበረ አይጠረጠርም።
«የኛዎቹ» ገልቱ ጁንታዎች፣ ዕድሉን አላገኙም እንጂ፣ የማይካድራውንም፤ የሁመራውንም፣ የሰራዊታችንንም እና ሌላ ሌላውንም ሁሉ ድምጽ አልባ ምስኪን፣ ሁሉ ምስክር አልባ በሆነ ሁኔታ በመፍጀት የዕልቂት አምሮት መወጫ ጭዳ ከማድረግ አይመለሱም፤ ነበረ። ሰራዊታችንም የተረፈው ለጥቂት ነው።
ምክንያቱም «የኛዎቹ» አረመኔዎች፣ ከዚህ በመለስ አለ፤ የተባለውን የጭካኔ በትር ሁሉ ተቃዋሚዬ በሚሉትና በጠረጠሩት ኢትዮጵያዊ ኃይል ላይ ሁሉ በነበረው የአገዛዝ ዘመናቸው ሁሉ አሳርፈዋልና።
ፖሊሱ እነርሱ፣ አቃቤ ሕግ እነርሱ፣ መርማሪ እነርሱ፣ ደህንነት (ስሙ ሲገርም ሕዝብ በጨጓራው የሚቆርብበትን ቤት ደግሞ ፣ «የሕዝብ ደህንነት» መስሪያ ቤት ብለው ይጠሩታል ፤ ሆ!?) ምስክር እነርሱ፣ ዳኛ እነርሱ መሆናቸው ሳያንስ ፣ ወህኒ ቤቱና ያልታወቁት ሕግ አልባ እስር ቤቶቻቸውም የእነርሱ የግፍ ወፍጯቸው ሆኖ ማገልገሉ የማይካድ እውነት ነው።
ወህኒ ውስጥ እንደ አደገኛ አውሬ እጅ ከወርች ማሰሩ፣ ውሃ በኮዳ በወንድ ልጅ ብልትና በሴት ልጅ ጡት ላይ ማንጠልጠሉ፣ አካልን መጥበሱ፣ (በታሳሪው አካል ላይ የህወሓት ዓርማ ይሆን የሚጠበሰው?) አካል ማጉደሉ፣ ከሀገር አውጥቶ ያልታሰበ በረሃ ላይ መጣሉ (በጣም ሲያዝኑ የሚያደርጉት እርምጃ ነው፤ እርሱንም) ከሀገር ውጪም አፍኖ ማምጣቱ፣ አንዱ የተነኮላቸው ሲመስላቸው ቤተሰቡን ሁሉ ከሥራና ከኑሮ ማፈናቀላቸው…ገድሎና ደብዛ አጥፍቶ አብሮ አፋላጊ ሆኖ መገኘት፣ የእነርሱ መለያ ባህሪ የሆነበትና ዛሬ ድረስ ቤተሰቦች በይመጣል ተስፋ ተሰንቅረው መቅረታቸው ሲታሰብ «ፍጥረታቸው» ይዘገንናል። ለእነርሱ ግን ይህ አደራረግ ጠላትን ያለምስክር ማጥፋት መሆኑ ነው።
(በቱርክ፣ የካሾጊን ግድያና የምስጢሩን መገለጥ ስናየው፣ ተዳፍኖ የሚቀር አንዳችም ወንጀል በምድር ላይ እንደሌለ እንረዳለን። )
ይህንንና መሰል ግፎች የሰማና እጅግ አዝኖ፣ ልቡ የተነካ በሚሊዮን የሚቆጠር ሰው ማቅረብ የሚቀልለውን ያህል፤ አበጀህ ብሎ የሚያንቆለጳጵሳቸው አይገኝም፤ ከተገኘም አንድም አባሪ ተባባሪ ካለዚያም ደጋፊያቸው የሆነ ግብረ-በላ በላኤ-ሰብ ብቻ ነው።
ይህንን ሲያደርጉ የኖሩት የእኛ ናዚዎች ምን ይከብዳቸዋል፣ ወንጀል መክሰሳቸው ሴራ ቁርስ ምሣቸው ነው።
የጋዝ ቻምበሩ እንኳን ያልነበራቸው እንጂ፤ ይህንን ከማድረግ መች ይመለሱ ነበረ። ምንስ ያቅታቸውና ሰራዊታችንን ይምሩት ነበረ።
የገፈቱ ቀማሾች ምን አዲስ ነገር አለና ትቆጫበራለህ ብለው ሊያጣጥሉብኝ ያስቡ ይሆናል፤ እኔን የሚያሳስበኝ መከራና ጭካኔ ልክ እንደ እንቅልፍ ተጋቢዎች ናቸውና ይህ የአረመኔነት መንፈሳቸው ወደትውልዱ ተላልፎ ግድያና ወገንን አበሳ ማሳየት እንደ ዘበት የሚፈፀም ተራ ነገር እንዳይሆን ለማሳሰብ ወድጄ ነው።
ለዚህ ነው፤ ወደኋላ ሁሉ መለስ ብለን፣ አርባጉጉና በደኖ ሳይረሱ፣ የጂማው ጭፍጨፋ፣ የሀረርጌው የሚሊዮኖች መፈናቀል ፣ የመተከሉ የማያባራ ዘር ተኮር አበሣ፣ በሠነድ ተሰንዶ ለትውልድ መማሪያነት መቀመጥ ይገባዋል።
የሚቀጥለው ትውልድማ በፍጹም «ጎመን በጤና» ባይ ሆኖ መብቱን ለጨፍላቂዎች አስረክቦ መኖር የለበትም። የሚቀጥለው ትውልድ ወጣትና ሕፃን መገደል፣ መሰቀል፣ መቃጠልና በ«ሢኖ ትራክ» መጨፍለቅን ለባለስልጣን የተሰጠ ወግ አድርጎ ማየትና፣ እንደ ተገቢ ቅጣት የሚያስብ ሆኖ መኖር ከቶውንም አይገባውም።
ስለዚህ ምን ይደረግ ትሉኝ ይሆናል፤ እኔ እንዲህ እላለሁ። የማህበረሰብ የግንባታ መሠረት የሆነው ቤተሰብ አጠንክሮ በዚህና መሰል በሆኑ ጠቃሚ፣ እውነተኛና ገንቢ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገርና እውነት እውነቷን ለቤተሰቡ አባላት ለመንገር ማመንታት የለበትም።
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ልጆቹን ስለ ሌላው የሰው ልጅ ሊነገር የሚገባውን መልካምነት ሁሉ፣ በከበሬታና በሥነ- ምግባር ማስተማርና ማሳየት ይገባዋል።
ዓለም በልዩ ልዩ የሐሳቦች፣ የዘር፣ የእምነት፣ የአስተምህሮና የባህል ልዩነት ውስጥ ያለና በዚህም ተግባብቶ ባልተጻፈ ወግና ደንብ የሚኖር መሆኑን መንገር፣ ማሳወቅና ሲቻልም ወስዶ ማሳየት አለበት። ይህም ብቻ አይደለም፤ የእኛ ብቻ የሚባልም ነገር በቤተሰብም ሆነ በሀገር ደረጃ የሌለ መሆኑን ማወቅ አለባቸው።
የእኛ ብቻ ትምህርት ቤት፣ የእኛ ብቻ ከተማ፣ የእኛ ብቻ ሐውልት፣ የእኛ ብቻ ሆስፒታል፣ የእኛ ብቻ ሰፈርና መንደርም የሌለ መሆኑን ልጆች ማወቅና በዚህም ነፀብራቅ ውስጥ መኖር እንደሚገባቸው ማወቅ ይኖርባቸዋል።
ባልጠበበ አስተሳሰብ ውስጥ፣ ባልጠበበ አደራረግ፣ ባልጠበበ ዕይታና ማጠቃለያ ውስጥ እንዲመላለሱ መርዳት ይገባል። ምድር ሁሉ የእነርሱና የሰው ልጆች ሁሉ መኖሪያ፣ ማደሪያና መበልፀጊያ ስፍራ እንጂ መሳደጃ፣ መታሰሪያና መንገላቻ እንዳልሆነች መረዳት ይገባቸዋል። ለዚህም ከቤቶቻችን ጀምሮ ፣ ትምህርት ቤቶቻችን ፣ ገጠርና ከተሞቻችን እና ሀገራችንም የፈውስ ውኃ መረጨት አለባቸው።
ለዚህም በአንድ ቤት ውስጥ አባት ኦርቶዶክስ፣ ሚስት ፕሮቴስታንት፣ ልጅ የጂሖቫ ምስክር፣ ሴት ልጅ ደግሞ በወደደችው ልጅ ሳቢያ ሙስሊም ሆና ግን ሁሉም ተቀባብለው የሚኖሩበት ቤት እንዳለና መኖርም እንደሚቻል ማሳየት እንጂ «ምን ሲደረግ እኔ ቤት ጆቫ ይገባል፤ …. ወይም «የባሃይ (ባሃውላ ) እምነት ተከታይ በቤቴ ውስጥ ሊከሰት ይችላል፤» ብሎ መገበዝ የማይገባ መሆኑን ማሳየት፣ መቀበልና መተግበር ያስፈልጋል። ዓለም ሰፊ ናት፤ በዚህ ስፋቷ፣ ዕድሎችና አጋጣሚዎቿም እንዲሁ ብዙ ናቸውና። እነዚህን ልዩነቶች በፍቅር ፀበል ተረጭተን መፈወስና መቀበል ይገባናል።
የማንቀበለው ልዩነት ግን አለ፤ ሰው ወድዶ እና አመልክቶ ያልተቀበለውን ዘር፣ ቀለምና መልክ የማንጓጠጫ አድርጎ መጠቀምን፣ በግፍ ንብረትን መቀማትን፣ ያለፍትህ አደባባይ መብት ማጣትን፣ በየትኛው የሀገሪቱ ስርጓጉጥ ውስጥ ሰርቶ መኖርን መጋፋትን፣ በሐሳቡና በአተያዩ ሳቢያ መገለልን፣ በወንጀል መተባበርን፣ የሕዝብ ንብረት መዝረፍን፣ ቤትን የማፍረስን፣ ወዘተ…. ሐሳብ ያለመቀበል የመለየት መብት አለን። እንዳስፈላጊነቱ ፍትህን መጠየቅ ተገቢ የመሆኑን ያህል ይህንን መብት ማሳጣት ግን ከቶውንም ሊቋቋሙት እና ሊተዉት የማይገባ እውነት መሆኑን ማስተማር ይገባል።
ከዚሁ ጋርም የትምህርት ሥርዓታችንን መፈተሽና በአግባቡ ማደራጀት የተገባ ነው። ጀርመኖች፣ «የነፃነትና የረሐብ» ጊዜያቸውን ትውልዱ እንዲያውቀው አድርገው እንደሚያስተምሩት ሁሉ፣ አይሪሾች (The potato plague) «የድንች ቸነፈር» የተባለ ዘመናቸውን ከትውልዱ አይደብቁም፤ በዚህም ሳቢያ ትውልድ ለዳግመኛ ረሐብ እንዳይጋለጥ፣ ያስጠነቅቁታል።
እኛም ይህንን የማይካድራና ሁመራ ግፍ በሥነ-ልቡናም ሆነ በሲቪክስና በታሪክ ትምህርቶች ውስጥ አስገብተን፣ ትውልዱ ዳግመኛ እጁን በወገኑ ላይ እንዳያነሳ ማድረግ ይኖርብናል።
የሃይማኖት ተቋማትም ድርሻ ከዚሁ ጋር የማይናቅ መሆኑን ማሳየት መልካም ነው። ከዚህ በፊት የተሰሩትን የጥላቻ ሐውልቶች ከማፍረስም ይልቅ ሕዝብን ከሕዝብ ለማናጨት ታስበው የተሰሩ የክፋት ምልክቶች በመሆናቸው፤ በጉልህ እና በደማቁ፣ «ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማጋጨትና ዘላለማዊ ፀብ ለመፍጠር በህወሓት የተሰራ አጥፊ ሐውልት»፤ ተብሎ በላዩ ላይ መጻፍ፣ ትውልድ በተመሳሳይ መንገድ የክፋትና የጥፋት ሐውልት ላለማቆም እንዲችል በሚገባ ያስተምራል፤ ብዬ አስባለሁ።
የምናስተምረው አድራጊዎቹን ጭራቆች አድርጎ ለመሳል ሳይሆን የታሪካችን ስብራት ተደርጎ የሚቀርብበት ሁኔታ በሥርዓት ታስቦበት መሰናዳት ስላለበት ነው። እንዲህም ስናደርግ ልጆች ለሌላ ቋንቋ፣ ለሌላ ባህል ለሌላ ዝማሬም ሆነ ተረታ ተረቶች አክብሮትና ፍቅር እንዲኖራቸው በማድረግ ማሳደጉ ሳይዘነጋ ነው።
የጥቂት አጥፊዎች መልክና ተግባር ጀርመኖችን ሁሉ እንዳላስወነጀለ እንዲሁ የጥቂት አጥፊ ወገኖችን ጭካኔ የሕዝቡ፣ ወይም የጎሳው ወይም የብሔሩ ጥፋት እንደሆነ አድርጎ መተረክ እርባና የለውም። ስለዚህም፣ የፍቅርና መተሳሰብ ቄደሩ በትምህርት ሥርዓታችንና ዲስኩሮቻችን ሁሉ ውስጥ መረጨት ይገባዋል። በዚህም ሁላችንም እንረሰርሳለን!
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13/2013