አሸብር ኃይሉ
እንደሚታወቀው ጁንታው ህወሓት ሲፈጠር ጀምሮ ጥፋትን፣ ወንጀልን፣ ማጭበርበርን፣ መግደልን ማስገደልን ወዘተ ሰውኛ ያልሆኑ ተግባራትን እየፈጨ፣ እያቦካ፣ እየጋገረ ሲበላ የኖረ እና ከአንድ ፋብሪካ እንደ ተመረተ ምርት ራሱን አስመስሎ በፈጠራቸው አካላት እና ድርጅቶች ሀገር በማወክ ኢትዮጵያን እርቃኗን እንድትቆም አድርጎ በዓለም ፊት እንድታፍር እና አንገቷን እንድትደፋ ለማድረግ ሲታትር የኖረ በድርጊቱ ሰይጣን የሚቀናበት በመናፍስት ጥርቅም የተዋቀረ ቡድን ነው።
ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት የትግራይን ብሎም የኢትዮጵያን ሕዝቦች ኅብረተሰባዊ ሕግጋትን ለይቶ አለማወቁ እና ከጅምሩም የኢትዮጵያን ሁለተናዊ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ሁነቶችን የማያውቅ እና ለማወቅም ካለመፈለጉም ባሻገር የቱንም ያህል ቢማር የኢትዮጵያን ሕዝቦች ኅብረተሰባዊ ሕግጋት መገንዘብ የማይችል ድርጅት ነው።
ይህን ለማወቅ ያለመፈለጉ ደግሞ ዋናው ምስጢሩ የኢትዮጵያን ሁለተናዊ ማህበረሰባዊ እና ታሪካዊ ሕግጋትን በማጥፋት ሥልጣን መያዝ የፖለቲካ መርህ አድርጎ መነሳቱ ነው። በዚህም ቢያንስ እወክልሃለው ለሚለው እና የወጣበትን የትግራይን ሕዝብ እንኳን ሕዝባዊ እና ታሪካዊ ሕግጋቶችን ለይቶ የማያውቅ እና የማያከበር ድርጅት ነው።
ጁንታው ህወሓት ከአጠፋቸው ጥፋቶች፣ ከአደረሳቸው የሰው እና የንብረት ውድመት አንጻር ምንም ዓይነት ምድራዊ ተመጣጣኝ ቅጣት ይኖራል ብዬ አላስብምም። አይኖርምም። ምክንያቱም የጁንታው ጥፋት ተቆጥሮ ባያልቅም እንኳን በህወሓት አመራሮች የዓይን ምስክርነት የተነገሩትን እና አሁን በቅርቡ ጁንታው ያደረጋቸውን ሰይጣናዊ ተግባራት መመልከቱ በቂ ነው።
ለምሳሌ፡- አንድ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩ አርአያ ገብረመድህን የተባሉ ሰው ለሚዲያዎች በሰጡት ቃለ ምልልስ እንዲህ ይላሉ፡- ህወሓት ገና ጫካ በገባ በስምንት ወሩ ባዶ ስድስት የሚል መሬት ውስጥ ያለ ማሰቃያ ቦታ ፈጠረ። በዚህም መጀመሪያ ላይ ሲሰቃዩ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ናቸው።
ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት የሆነው ህወሓት ገና በ1968 ዓ.ም ጫካ ሲገባ ጀምሮ የፖለቲካው መነሻ ያደረገው የአማራ ሕዝብ ለትግራይ ሕዝብ ጠላት ነው፤ የአማራ ሕዝብ የትግራይን ሕዝብ ቅኝ ገዝቷል የሚል ነው። በዚህም የትግራይን ሕዝብ መዋሸት እና ማደናገርን ሥራዬ ብሎ ጀመረ።
ይህን ወፍራም ውሸት እና ከፋፋይ የፈጠራ ወሬ የተቃወሙ የትግራይ ተወላጆች እስከ 1973 ዓ.ም ድረስ ባዶ ስድስት በሚለው የማሰቃያ ቦታ ሌሊት እላይ እየታፈኑ እየተወሰዱ ከአዕምሮ በላይ የሆነ ዘግናኝ ተግባር ተፈፅሞባቸዋል። በዚህም እስከ ዛሬ የት እንደደረሱ የማይታወቁ የትግራይ ተወላጆች ብዛት ቤት ይቁጠራቸው።
እስከ 1973 ዓ.ም ድረስም ህወሓት የአማራን ቅኝ ገዢነትን ባልተቀበሉ የትግራይ ተወላጆች ላይ የፈፀመው ጸረ – ትግራይ እርምጃ አባቷን እና ወንድሟን ያጣች አንድ ጎልማሳ ከሁለት ሳምንት በፊት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገረችው የ12 ልጆች አባት የሆነውን አባቷን እና የ6 ልጆች አባት የሆነውን ወንድሟን ሌሊት ላይ አፍነው በመውሰድ ከአሰቃዩ በኋላ ወንድሟን ሊሞት ሲል እቤታቸው አምጥተው ሲጥሉት አባቷን ግን የት እንዳደረሱት እንደማታውቅ ተናግራለች። በዚህም ቤተሰባቸው በችግር አይሆኑ ሆኖ እንደተፈተነ ትናገራለች።
ከህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ከነበረው አርአያ ገብረመድህን መረዳት እንደሚቻለው ከመላው ትግራይ የአማራን ቅኝ ገዢነት ያልተቀበሉ እና አማራን ቅኝ ገዢ ነው ብለን አንታገለም ያሉ የትግራይ ተወላጆችን ባዶ ስድስት በሚባል የማሰቃያ ቦታ ወስዶ እንደ ማገዶ አቃጥሏል፣ በጭስ አፍኖ ገድሏል።
ይህ አልበቃው ብሎ የትግራይ ሕዝብ በርሃብ ምክንያት በመሞት እና በመኖር መካከል ሆኖ እያየ የመጣውን የምግብ እርዳታ በመሸጥ ለጦር መሣሪያ መግዣ ያደረገ፣ እንዲህ ነው ብሎ ለመግለፅ የሚያስቸግር ጸረ ትግራይ ድርጅት ነው።
ሌላው ተማሪዎችን ይቀርፃሉ ተብለው ተስፋ ተጥሎባቸው የተቀመጡ የዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ምሁራን እንኳን ሳይቀሩ ወያኔ በፈጠረው የአጥንት ቆጠራ ሴራ ተተብትበው ሀገራቸውን በሙያቸው ከመታደግ ይልቅ ኢትዮጵያውያንን በአጥንት እየቆጠሩ፤ በብሔር እየከፋፈሉ ሀገርን ለመበታተን ሲታትሩ ስታይ እና ይህ ሁሉ ሴራ የጁንታው መሆኑን ስታውቅ ለህወሓት ምን ዓይነት ምድራዊ ቅጣት ቢቀጣ ፍትሐዊ ሊሆን ይችላል የሚል ነገር አዕምሮአችን ውስጥ በመፈጠሩ አይቀሬ ነው።
በ2003/2004 ዓ.ም አካባቢ በጋምቤላ ክልል መሬታችሁን ካልሰጣችሁን በሚል በክልሉ በሚገኙ የብሔረሰቡ ተወላጆች ላይ ያደረሱት የጅምላ ጭፍጨፋ እስካሁን ድረስ በዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ በዘግናኝነቱ የሚወሳ አረመኔአዊ ጭፍጨፋ ነው።
የህወሓት ዘግናኝ ጥፋቶች ተቆጥረው ባያልቁም ብዙ ሰዎች በግልፅ የሚያውቋቸውን መመልከት ተገቢ ይመስለኛል። ከእነዚህ መካከልም በ2009 ዓ.ም አንድ የወለጋ እናት የደረሰው የሚረሳ አይመስለኝም።
እኝህ እናት አረመኔው ህወሓት ልጃቸውን ከገደለ በኋላ ከልጃቸው አስከሬን ላይ እንዲቀመጡ አደረገ። ምን የሚሉት ጭካኔ ነው። ሌላው የእሬቻ በዓል በቢሾፍቱ ሲከበር ያደረሰው እልቂት በዘግናኝነቱ መቼም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ ውስጥ ይወጣል የሚል ግምት የለኝም።
አረመኔው ህወሓት ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንድ ጊዜ ከ300 በላይ ዜጎች እስካሁን እንዴት እንደገደላቸው ባልታወቀ ምስጢር ለዓመታት የተጠራቀመ ቆሻሻ ተጭኖአቸው እንዲሞቱ አድርጓል። የእነሱ ልጆች ግን በአሜሪካ እና በአውሮፓ በቅንጦት ቤት ውስጥ እየኖሩ በቆሻሻ ላይ ዜጎች እንዳይኖሩ ማድረግ ምን የሚባል ሰይጣናዊነት ነው። በወልዲያ የጥምቀት በዓል ለማክበር በወጡ ሰዎች ላይ ደረሰው የጅምላ ጭፍጨፋ እንደዚሁ የሚረሳ አይደለም።
ሌላው እስካሁን ግርም የሚለኝ ህወሓት በፈጠረው እኔ ብቻ ልብላ ስግብግብነት ለርሀብ በመዳረጋቸው የሕይወትን ፈተና ለመቋቋም በባህር ወደ አውሮፓ ሊሻገሩ ሲሉ በሀገረ ሊቢያ የአይ ኤስ ኤስ አሸባሪ ቡድን ወንድሞቻችን በመታረዳቸው ምክንያት በአዲስ አበባ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገራችን ባህል ሙሾ ሊያወርዱ እና ነፍስ ይማር ለማለት በመስቀል አደባባይ በተሰበሰቡበት ሰዓት ሙሾ ማውረድ እንደ ወንጀል ተቆጥሮ በተሰበሰበው ኀዘንተኛ ላይ የፈጸመው ዘግናኝ አርምጃ ከማንስ አዕምሮ ሊጠፋ ይችላል?
ሃሳቡን የሚቃወሙትን በማሰርና በማሰቃየት፣ በማኮላሸት፣ ከዱር አውሬ ጋር በማሰር፣ጥፍር በመንቀል፣ የባህር ላይ ውንብድናና ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ንግድን በማጧጧፍ፣ በቅርቡ እንዳየነውም አደንዛዥ ዕጽ ለትግራይ ወጣቶች በማቅረብ ወዘተ ያልፈጸመው የወንጀል ድርጊት የለም።
ይህ አልበቃው ብሎ ጭራሽ በየትኛውም ዓለም ተደርጎ የማይታወቀውን የአንድ ሀገር የመጨረሻ አለኝታ የሆነውን፣ ሀገራችን ከማንኛውም ዓይነት ጠላት ይከላከላል ተብሎ የተቋቋመው የመከላከያ ሰራዊትን መግደል እና ማሰቃየት ምን የሚሉት ነው ?
ከላይ የተጠቀሱት እጅግ በጣም ጥቂት ወንጀሎች ብቻ እንኳን ብንመለከት ሴረኛው ህወሓት በኢትዮጵያ ላይ ለፈጸመው ነውረኛ ወንጀሉ ምንም ዓይነት ምድራዊ የሆነ ፍትሐዊ ወይም ተመጣጣኝ ቅጣት ይኖራል ብዬ አላስብም ።
በአጠቃላይ አሁን ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ህወሓት በሀገሪቱ ላይ ከፈጠረው ቀውስ ለመውጣት እጅ ለእጅ የምንያያዝበት እና የጀመርነውን ግድባችንን ግዜ ሳንሰጥ ለመጨረስ የምንኳትንበት ሊሆን ይገባል። መልዕክቴ ነው !!!
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13/2013