አንተነህ ቸሬ
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት) በአገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ የፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በአገር ላይ ክህደት የፈፀመውን የህ.ወ.ሓ.ትን ቡድን ‹‹ጁንታ›› ብለው መጥራታቸውን ተከትሎ ምሁራንን ጨምሮ ጋዜጠኞችና መላው ሕዝብ ህ.ወ.ሓ.ትን ‹‹ጁንታ›› በማለት ሲገልፀውና ሲጠራው ተስተውሏል።
ይሁን እንጂ ህ.ወ.ሓ.ት ከሰራው ወንጀልና ከፈፀመው ክህደት አንፃር ‹‹ጁንታ›› ተብሎ መጠራቱ/መገለፁ የቡድኑን ነውርና ኃጢዓት ማሳነስ እንደሆነ ታዝበናል። የ‹‹ጁንታ››ን ትርጉም በመጠኑም ቢሆን በማብራራትና ህ.ወ.ሓ.ት የፈፀመውን ክህደት ከግምት ውስጥ በማስገባት ‹‹ህ.ወ.ሓ.ት እና ‹ጁንታ›ነት ምንና ምን ናቸው?›› ለሚለው ጥያቄ አጭር ትዝብቴን ለማስረዳት እሞክራለሁ።
‹‹ጁንታ›› ምንድን ነው?
የሕግ እና የፖለቲካ መዝገበ ቃላት ‹‹ጁንታ›› የሚለውን ቃል ‹‹መንግሥትን በኃይል ገልብጦ ስልጣን የያዘ ቡድን። የጥቂት ወታደራዊ ግለሰቦች ስብስብ። ለጋራ ዓላማ የተሰባሰቡ አካላት ቡድን። በጦር አዛዦች ኮሚቴ የሚመራ መንግሥት። በሕጋዊ ምርጫ ሳይሆን በኃይል ስልጣን የጨበጠ የጥቂት ወታደራዊ ግለሰቦች ቡድን … ›› ብለው ይተረጉሙታል።
የቃሉ መነሻ ከአውሮፓዊቷ ስፔን በአገሬው ቋንቋ ሲነበብም ‹‹ሁንታ›› የሚል ድምፀት አለው። የ‹‹ጁንታ›› መነሻ በ1800 ዓ.ም ስፔናውያን የናፖሊዮንን ወራሪ ጦር ለመመከት ራሳቸውን ካደራጁበት የታሪክ አጋጣሚ ጋር የተቆራኘ እንደሆነም የታሪክ ማስታወሻች ይጠቁማሉ።
‹‹ጁንታ››ዎች በአብዛኛው ስልጣን የሚጨብጡት በመፈንቅለ መንግሥት ነው። በአምባገነናዊ አሰራራቸው ይታወቃሉ። በዓለም ታሪክ ‹‹ጁንታ›› ተብለው የተሰየሙ መንግሥታትና ቡድኖች በተለያዩ አገራት በተለያዩ ጊዜያት ስልጣን ይዘው ታይተዋል። የአርጀንቲና። የቦሊቪያ። የብራዚል። የግብጽ። ኤል-ሳልቫዶር። የፊጂ። የግሪክ። የጆርጂያ። የናይጀሪያ። የፔሩ።
የፖላንድና የሌሎች በርካታ አገሮች ወታደራዊ ቡድኖች ከ‹‹ጁንታ››ዎች መካከል ይጠቀሳሉ። ኢትዮጵያም በዘመነ ደርግ በ‹‹ጁንታ›› ተገዝታለች። በአጠቃላይ ‹‹ጁንታ›› ጠቅለል ተደርጎ ሲታይ በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን የጨበጠ የወታደራዊ መኮንኖች ስብስብና አምባገነናዊ አስተዳደር ነው።
‹‹ጁንታ››ነት እና ህ.ወ.ሓ.ት
ህ.ወ.ሓ.ት የፌደራል መንግሥቱ አድራጊ ፈጣሪ በነበረበት ወቅት የፈፀመውን ምዝበራ። የሰብዓዊ መብት ጥሰት። አፈና … ለጊዜው እንተወውና በቅርቡ በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ከፈፀማቸውና ለመስማትና ለማመን ከሚከብዱ አሰቃቂና አሳዛኝ ድርጊቶች መካከል ጥቂቶቹን እንመልከት።
በቅድሚያ ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ በሰራዊቱ ላይ ስለተፈፀመው ክህደት ከተናገሩት እናስቀድም … ‹‹ … በሰራዊቱ ውስጥ ያሉ ትግርኛ ተናጋሪ አባላት ሰራዊቱን ለማፍረስ ካቀደው አካል ጋር በተቀናጀ መልኩ እንዲሰሩ ተልዕኮ ተሰጥቷቸዋል። አንደኛው ተልዕኮ በሰራዊቱ ውስጥ በመሆን ሰራዊቱን የማፍረስ ስራ መስራት ነው።
ሁለተኛው ከሰራዊቱ ወጥቶ ሰራዊቱን የመውጋት ነው። ሦስተኛው ሰራዊቱ እጅ እንዲሰጥ ማድረግ ነው። በውስጥ የራሳቸውን ሰዎች አሰማርተው የሰራዊቱን መገናኛ/ሬዲዮውን (Chain of Command) እነርሱ በሚፈልጉት መልኩ በሙሉ ወደ እነርሱ አዞሩት።
የመከላከያ መገናኛ ዋና መምሪያ ኃላፊ የእነርሱ ሰው ነው። የሰሜን ዕዝ ባለባቸው አካባቢዎች ሁሉ የነበረውን የመከላከያን የሬዲዮ ፕሮግራም እነርሱ በሚያውቁት መንገድ ፕሮግራም እንዲሆን ተደረገ። ሬዲዮ ፕሮግራም ሲደረግ የሚያጠራጥር ነገር የለውም። በወታደሮች መካከል መተማመን እንጂ መጠራጠር አይኖርም … የሰራዊቱ ራሽንና ደመወዝ ሲገባ ኦፕሬሽኑ ተጀመረ።
ኦፕሬሽኑ ማታ ሊጀመር በዚያው ዕለት። ቀን ላይ ለሰራዊቱ አዛዦች ግብዣ አድርገው በመጨረሻ የሚፈልጓቸውን አዛዦች አፍነው አስቀሩ … ራሽኑንና ብሩን ወስደው ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ብለው ላሰለጠኗቸው አደሉ። የሬዲዮ ግንኙነቱ ስለተቆረጠ የሰራዊቱ አዛዦች እርስ በእርስ መገናኘት አልቻሉም። ይህ ደግሞ የሠራዊቱ ዋና ምሰሶ የሆነውን ተዋህዶ መስራትን ከጥቅም ውጭ አደረገው።
ሻለቃዎችን ከበው ‹እጃችሁን ስጡ፤ ጠመንጃችሁን እንጂ እናንተን አንፈልግም፤ የእኛ መንግሥት የተመረጠ መንግሥት ነው፤ የአዲስ አበባ መንግሥት የተመረጠ መንግሥት ስላልሆነ ፈርሷል› የሚል ማስፈራሪያ አስተላለፉ። ወታደሮቹ ያለምግብና ውሃ ለሦስት ቀናት ቆዩ … ወታደሮቹ ‹አገር ጠብቅበት የተባልኩትን መሳሪያ ለማንም አልሰጥም› ብለው ተዋጉ።
መሳሪያ ሰጥቶ ወደፈለገበት ለመሄድ ዝግጁ የሆነ ወታደር አልነበረም። ጀግና ሰራዊት ተፈጥሯል …
በብዙ ቦታዎች ውጊያዎች ነበሩ። በውጊያው ላይ የተሳተፉትና ሰራዊቱን የወጉት ልዩ ኃይል። ሚሊሻ። ከሰራዊቱ ጋር ዩኒፎርምና መለዮ ለብሰው፤ የመለዮውን ቃል ኪዳን የካዱ ትግርኛ ተናጋሪ የሆኑ የሰራዊቱ አባላትና የኦነግ ወታደሮች ናቸው … የሰሜን እዝ አዛዦችን ግብዣ ጋብዘው። ለ21 ዓመታት አብረው የኖሩትን። ጉርሻ አጉርሰው ሲያበቁ ከግብዣው ሲወጡ እጃቸው ላይ ካቴና ያስገቡ ፍጡሮች ‹የሰሜን እዝ ከእኛ ጋር ተባብሯል› ብለው አስነገሩ …
በኮማንድ ውስጥ አፍኖ ለመውሰድ ማን አማራ ነው። ማን ኦሮሞ ነው … የሚለውን ነገር ለይተዋል። ማን ጠንካራ ነው። ማን ለስላሳ ነው የሚለውንም ለይተዋል። ማን ማንን ይይዛል የሚባለውም ነገር ተለይቷል …
የ20ኛ ክፍለ ጦር አራተኛ ብርጌድ ድጋፍ ሰጪ ብርጌድ ነው። ትጥቁ ሞርታሮች። ሮኬቶች። መድፎችና አየር መቃወሚያዎች ናቸው። ውጊያው ሲጀመር ብርጌዱን የወጉት የብርጌዱ አባላት የሚያውቋቸው ሚሊሻዎች ናቸው። የተሰውትን የመከላከያ አባላት ልብሳቸውን አውልቀው። ራቁታቸውን አድርገው ሬሳቸውን ፀሐይ ላይ አሰጡት … ሬሳቸው ፈንድቶ የአሞራና የጅብ ሲሳይ ነው የሆነው።
ለ21 ዓመታት ያህል በአንድ ጉድጓድ አብሮ የኖረን። እርሻ ያረሰን። እህል ያጨደን። ትምህርት ቤት የሰራን። አንበጣ የተከላከለን … ሰራዊት ሬሳውን ጅብ አስበሉት። ከገደሉ በኋላ ልብሳቸውን አውልቀው ሬሳቸው ላይ እያጨበጨቡ ጨፈሩበት። የእነርሱን ወገን ሬሳ አንስተው ሲቀብሩ የአገር ጋሻ የሆነውን የመከላከያ ሰራዊት ሬሳ ላይ ግን ጨፈሩበት። ተዋግቶ የገደለ ሰው በጀግንነት የተዋጋን ሬሳ አንስቶ ይቀብራል። እነዚህ ሰዎች ግን ተዋግተውና ገድለው አያውቁም ማለት ነው።
ለ21 ዓመታት ያህል ትግራይ ለኖረው ለሰሜን ዕዝ የሰጡት ክብርና ምላሽ ይህ ነው። ሬሳው ላይ የጨፈረው ይፈር እንጂ ወታደሩ የተሰዋው ለአገሩ በጀግንነት ስለተሰዋ እኛ እንኮራበታለን። ወራዳው ጀግናውን ያልቀበረው ነው …
አፍነው የያዟቸውን ዩኒፎርማቸውን አስወልቀው ነው ወደ ሻዕቢያ ሂዱ ያሏቸው። ራቁታቸውን! በዓይኔ በብረቷ ነው ያየኋቸው! ህሊና ያላቸው ሰዎች ግን ልብስ አለበሷቸው። ጠላት ብለን የተዋጋናቸው የኤርትራ ወታደሮች ልብስ አለበሷቸው። ሰራዊቱ ወገኔ ብሎ የሞተላቸው አካላት ግን ራቁቱን ሰደዱት። ስለዚህ በቁማችንም ሞተንም ከባንዳዎችና ከማፍያዎች ያተረፍነው ክብራችን ይህ ነው … ››
ይህን የሌተናል ጀኔራል ባጫ ምስክርነትና ገለፃ ይዘን ተነግሮ የማይዘለቀው ክህደት ሰላባ ከሆኑ ወታደሮች መካከል ጥቂቶቹ የተናገሩትን ደግሞ እንመልከት …
‹‹ … የህ.ወ.ሓ.ት ሚሊሻና ልዩ ኃይሎች የጋንታ አመራሩን በፊታችን ገደሉት።
ከገደሉት በኋላ አስፋልት ላይ ሲጎትቱት ነበር። የቲም አዛዦቻችን ተመቱ። ከምሽጉ ውስጥ የቀረሁት እኔ ብቻ ነበርኩ። ስናይፐር ሳይቀር ጠምደው ስለነበር እየተኮሱብኝ ነበር። ከሞትኩም ልሙት ብዬ ወደ ጓደኞቼ ሄድኩ። ወደ ጓደኞቼ ሄጄ ስንዋጋ ከቆየን በኋላ ጥይት ሲያልቅብን እጅ ሰጠን።
የነበረን መሳሪያ ክላሽ ብቻ ነበር። ሁላችንም ታሰርን። የወር አበባ ሕመም በሚያሰቃየን ወቅት የንጽሕና መጠበቂያ እንድናገኝ አሳሪዎቻችንን እንዲተባበሩን ስንጠይቃቸው ‹ሂጂ ወደዚያ!› እያሉ በጥፊ ይመቱን ነበር …››
***
‹‹ … ቤት ውስጥ ተቀምጬ ነበር። ሕጻኑም ተኝቶ ነበር። ቤቴ ላይ ጥይት ተኮሱብኝ። ‹ውጪ› ተባልኩኝ። ሕፃን ይዤ አልወጣም አልኩኝ። በመጨረሻም ገና ስድስት ወር የሆነው ህፃን ይዤ ምሽግ ውስጥ ገባሁ። ለሕፃን እንኳ ርህራሄ አልነበራቸውም … እጅ የሰጡ አመራሮችም በአሰቃቂ ሁኔታ ተደብድበዋል። አንዱ አመራር እጁ ተቆርጧል። በተለይ አማራንና ኦሮሞን እዚያው ነው ያስቀሯቸው። ‹እነሱን አንለቅም፤ እንገድላለን› አሉ።
የታፈኑ የደቡብ ሰዎች ዓይናቸው ላይ በርበሬ ይጨምሩባቸው ነበር። በረሃብም የሞቱ አሉ። ይህ ሁሉ ስቃይ ነበር … ››
***
‹‹ … ምግብ የለም። ከስሚንቶና ወንበር ላይ አስተኝተውንና አስቀምጠውን ያድራሉ። ልብሳችንን። ገንዘባችንን። ስልካችንን። ልብሳችንን። ዶክሜንቶቻችንን። የባንክ ደብተራችንንና የኤቲኤም ካርዳችንን ወስደውታል። ብዙ ሰዎች ሞተዋል … አንዱ ሰው እጅ ከሰጠ በኋላ በታንክ ረግጠውታል። ሲገድሉ ብሔር እየመረጡ ነበር፤ በተለይ ትኩረታቸው ኦሮሞና አማራ ላይ ነበር። ሬሳቸውን አሞራ በልቶታል። መትረፍ የሚችሉ ቁስለኞችም ሞተዋል …››
ከላይ የተጠቀሱት የሦስት ግለሰቦች ንግግሮች በሴት የመከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ አባላት ላይ የተፈፀሙ ግፎች መሆናቸውን ልብ በሉ! ከክህደቱ ማሳያዎች ጥቂት እንጨምር …
***‹‹ … ታግተን 40 ኪሎ ሜትር በእግራችን እንደተጓዝን ምሽት ሆነ። 1200 የምንሆን ሰዎች ሻንጣ ተሸክመን እየተጓዝን ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ሲሆን የትግራይ ልዩ ኃይል የጫነ ሲኖትራክ መኪና ከኋላችን መጣ። ከመንገድ እንዳንወጣ ታዘዝን። ሲኖትራኩ በእግሩ የሚጓዘውን ወታደር እየገጨና እየገደለ ሄደ። እኔም እግሬ ተሰብሮ ጉድጓድ ውስጥ ገባሁ … አጨዳ ውለን 11 ሰዓት ነበር የገባነው። ‹ተሃድሶ› ተብለን ተጠርተን ነው የታገትነውና የተገደልነው። ሕፃን የያዘች የወታደር ሚስት እንዲሁም የ12 ዓመት ታዳጊም ተገድለዋል። ለሕዝባችን ነበር ስንታገል የነበረው። እንዲህ ዓይነት ነገር ይፈፀምብናል ብለን አልጠበቅንም። የሰው ልጅ የሆነ ፍጡር ይህን አያደርግም … ››
***‹‹ … በዙሪያችን ታንክና ብሬን ተጠምዶ ነበር። እኛ የነበረችን አንድ አየር መቃወሚያ ብቻ ነበረች … ከሽራሮ ጀምሮ በአክሱም። ኣቢይ ዓዲና ሌሎች ቦታዎች እየወሰዱን የእኛ ጦር ሲደርስባቸው በእግራችን ሲያስጉዙን ቆዩ።
ከግራም ከቀኝም ተራራ የሆነና ከፊት ለፊት ድልድይ ያለው ቦታ ስንደርስ በሲኖትራክና በከባድ መሳሪያ መምታት ጀመሩ። ሲኖትራኩ ወርውሮኝ ጓደኛዬ ከጎማው ስር አውጥቶኝ ነው የተረፍኩት …››
***‹‹ … የእኛው የራሳችን ኮሎኔል የነበረ ሰው ነው ቄስ መስሎ መጥቶ አፈና የፈፀመብን … በእግራችን ስንጓዝ ከፊት ለፊት ተኩስ ከፈቱብን። እንዳንመታ ብለን መሬት ላይ ስንተኛ ሲኖትራክ ከኋላ መጥቶ በላያችን ላይ ሄደብን።
ከሲኖትራኩ ለማምለጥ እየተንከባለሉ የሄዱትን በጥይት ጨረሷቸው። አማራ። ኦሮሞ። ደቡብ ብለው ወታደሩን በብሔር እየለዩ ሲመድቡ ነበር። እኛ ግን ‹ሁላችንም አንድ ነን፤ ኢትዮጵያውያን ነን› ብለናቸው ነበር …››
***ታግተው የነበሩት የሰሜን እዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል አዳምነህ መንግሥቴ በበኩላቸው ‹‹ … እናትና አባትህ ይክዱኛል ብለህ በማትጠብቅበት አይነት ሁኔታ ውስጥ በሰራዊቱ ላይ ክህደት ተፈጽሟል። ቤታችን ነው፤ ሰላም ነው ባልንበት ቦታ በተደራጀ ኃይል አፈና ተካሂዶብናል። የአፈናው ጊዜ በሙሉ በርካታ ውጣ ውረዶች ያሉት ነው፤ ያለእረፍት በቀንም በሌሊትም ረጅም የእግር ጉዞዎች ነበሩ። ስሜቱን መግለጽ ያጥረኛል … ›› ብለዋል።
***
በህ.ወ.ሓ.ት እንደተፈፀመ ስለተረጋገጠውና ዓለም ሁሉ ስላወገዘው የማይካድራ። ሁመራና አካባቢው ጭፍጨፋ መዘርዘር የሚቻል ስላልሆነ አስታውሶ ማለፍን ብቻ መርጫለሁ። ሕፃናትን ለጦርነት ማሰለፉን። አደንዛዥ እፅ ማዘዋወሩን። የውሸትና የጥላቻ መረጃን በገፍ ማሰራጨቱን … ስንደምርበት ‹‹ህወሓትን ‹ጁንታ› ብቻ ብሎ መግለፅ ቀልድ ነው›› ብሎ መሞገት የዋህ አያሰኝም።
ከዚህ በተጨማሪ ህ.ወ.ሓ.ት በትግራይ ክልል በሚገኙ አገራዊ መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ውድመትና ዝርፊያ ፈፅሟል። መንገዶችን ቆፍሯል፤ ድልድዮችን ሰባብሯል። በታሪካዊቷ አክሱም ከተማ የሚገኘውን አውሮፕላን ማረፊያ ግሬደር አፈራርሶት ሸሽቷል።
በመብራትና በቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ላይ ያደረሰው ውድመትም ትግራይ ለሳምንታት በጨለማ እንድትዋጥና ከስልክና ከበይነ መረብ ግንኙነት ውጭ እንድትሆን አድርጓታል። ቡድኑ በትግራይ ክልል ባሉ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ የነበሩ የሕግ ታራሚዎችን ሰብስቦ በመቀሌ ከተማ ውስጥ በመልቀቅ ዝርፊያ እንዲፈጸም ማድረጉም ተቆጥሮ ከማያልቀው ወንጀሉ ላይ ተጨምሮ ይመዝገብ።
የህ.ወ.ሓ.ትን ወንጀልና ክህደት ለመግለፅ ቃላት እንኳ ራሳቸው አቅም ያጥራቸዋል። የኢትዮጵያን። በተለይም የትግራይን። ሕዝብ ከጠላት በሚጠብቀውና ለትግራይ ሕዝብ ብዙ ውለታ በዋለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ አሰቃቂ ጥቃት ሰንዝሮ የክፍለ ዘመኑን ዋነኛ ክህደት የፈፀመውን ቡድን በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ከጨበጠ የወታደራዊ መኮንኖች ስብስብና አምባገነናዊ አስተዳደር ጋር ማመሳሰል ያስተዛዝባል! የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አማካሪ የሆኑት ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ህ.ወ.ሓ.ት ስለፈፀመው ክህደት በፌስቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ።
‹‹ኢትዮጵያ ከዘመነ ኦሪት ጀምሮ ያደረገችውን ጦርነት በታሪክ አንብቤያለሁ። የኢትዮጵያ ሠራዊት በገዛ ወገኑ የተዋረደበት። የሰሞኑን ዓይነት ግፍ ግን አላጋጠመኝም። በቅርቡ በዝርዝር እንሰማውና እናየው ይሆናል።
ሰይጣን በስንት ጣዕሙ።›› ብለው ነበር። ‹‹የህ.ወ.ሓ.ት ግፍና ክህደት በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ከጨበጡ ወታደራዊ መኮንኖችም በባሰ ሁኔታ ሰይጣንንም ያስመሰግናል›› ብሎ ማመንና ‹‹ከህ.ወ.ሓ.ት’ማ። ጁንታዎች በስንት ጣዕማቸው!›› ብሎ መናገር መሳሳት ይሆን?!
ከሰይጣን የባሰውን ህ.ወ.ሓ.ት.ን። ‹‹ጁንታ›› በማለት
ከሃዲነቱንና ወንጀለኛነቱን አናሳንስለት!
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 12/2013