ሞገስ ተስፋ
ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ? ትምህርታችሁን እንዴት ጀመራችሁት? በከኮሮና ራሳችን በመጠበቅ በጥሩ ሁኔታ ጀምረነዋል እንደምትሉኝ አልጠራጠርም። እኔም የትምህርትን አጀማመር አስመልክቶ በአፄ ናኦድ ትምህርት ቤት ተገኝቼ ያነጋገርኩትን ተማሪ ሃሳብ ላካፍላችሁ። ተማሪ አማኑኤል ማሬ ይባላል።
የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ነው። ለስምንት ወራት ከትምህርት ርቄ በመቆየቴ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሮብኝ ነበር፣ አሁን ላይ ሁሉም ተማሪ የትምህርትን መጀመር በጉጉት ሲጠብቀው ስለነበር በመከፈቱ በጣም ደስታ ይሰማኛል ይላል።
ወደ ትምህርት ቤት ሲገቡ የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የሚያስችሉ የአፍና የአፍንጫ ጭንብል በማድረግ እጅን በመታጠብ ወደ መማሪያ ክፍላቸው ከገቡ በኋላም እያንዳንዱ ተማሪ ሳኒታይዘር እና አልኮል እንደሚጠቀሙ ገልፆልናል። ተማሪዎች እንዳይዘናጉ በትምህርት ቤቱ ሚኒ ሚዲያ አማካኝነት የተለያዩ
መልዕከቶችን በማዘጋጀት ሁሉም በንቃት ራሳቸውን ከቫይረሱ እንዲጠብቁ ከሰልፍ ሥነ ሥርዓት ጀምሮ በእረፍትና ምሳ ሰዓት ግንዛቤ ያገኛሉ። አስተማሪዎቻቸው የሚሰጧቸውን መመሪያዎች በመቀበል ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ በመከላከል ትምህርታቸውን በአግባቡ እየተከታተሉ እንደሆነ አማኑኤል ይናገራል።
አማኑኤል ግጥም መግጠም ይወዳል። ከሚገጥማቸው ግጠሞች ‹‹ርዕስ አልባ ጉዞ›› በተሰኘው ግጥሙ ስለኮሮና ቫይረስና ዓለም ስላለችበት ሁኔታ እንዲሁም መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች ስንኞችን ቋጥሯል።
………..
እኚህ አውሮፓውያን ሰለጠንን ብለው
ምኑንም ምኑንም እያግበሰበሱ
ይኼው ለዓለም ኮሮናን ለገሱ
አሁንም ዓለም ምንም አልመሰላት
ያ የመከራው ዘመን እስኪመጣላት
ወዳጅ ከወዳጁ ቢርቅ
ዘመድ ከዘመዱ ቢርቅ
ለአንተነው መራቁ አውቆ መጠንቀቁ
እንዋጋው አንድ ሆነን
ታጠብ የሀገሬ ሰው ጤናህን ጠብቀው
ራቅ ራቅ በል ውዱ የሀገሬ ሰው
የኮሮና ቫይረስ ህይወትህን እንዳይቀጥፈው። በማለት ሁሉም ማድረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ ተማሪ አማኑኤል ግጥሙን ይቋጫል። ተማሪ አማኑኤል ደራሲና ገጣሚ መሆንን የወደፊት ህልሙ አድርጓል። ለዚህ ደግሞ አብነት ያደረገው የሎሬት ፀጋየ ገ/መደህን ስራዎችን በማንበብ ነው።
ለዚህ ስኬቱ ዕውን መሆን ደግሞ ጠንክሮ እየተማረ ነው። ልጆች ከተማሪ አማኑኤል ግጥም ስለኮሮና ማድረግ ያለባችሁን ጥንቃቄ በመጠኑም ቢሆን እንደተረዳችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። ሳትዘናጉ በጤና ባለሙያዎች እንዲሁም በመምህሮቻችሁ የሚሰጣችሁን ምክር እየሰማችሁ ርቀታችሁን ጠብቃችሁ ትምህርታችሁን በአግባቡ ተምህራችሁ ውጤታማ እንደምትሆኑ አንጠራጠርም። ሰላም !
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2013