አብርሃም ተወልደ
በቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ መንግስት ላይ አመጽ ተቀስቅሶ አብዮት የፈነዳው በየካቲት ወር 1966 ዓመተ ምህረት ነበር። ስልጣኑን የተቆጣጠረው ወታደራዊ መንግስት/ደርግ/ “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚለውን መፈክር በማንገብ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴን መስከረም 2 ቀን 1967 ዓመተ ምህረት ከሥልጣን ማውረዱ ይታወቃል።
አብዮቱ ከፈነዳ በሁዋላ በቁጥጥር ስር አውሏቸው የነበሩ 60 ከፍተኛ ባለስልጣናትን የረሸነው ደርግ ከአንድ ወር በኋላም “የኢትዮጵያ ኅብረተሰብአዊነት”ን ወይም “የኢትዮጵያ ሶሻሊዝም”››ን በይፋ ያወጀው ታህሳስ 11 ቀን 1967 በዛሬው እለት ነበር።
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983 በሚለው መጸሐፋቸው እንደገለጹት፤ ደርግ በታሪክ የሚታወቀው በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ብቅ ካሉት እጅግ ቀኖናዊ ማርክሳዊ መንግስታት አንዱ በመሆኑ ነው። ከስልጣን እስከተወገደበት እለት ድረስም በዚሁ ማርክሳዊ ማንነቱ ራሱን ሲያሞካሽ ቆይቷል።
መቶ አስር ግድም የሚሆኑ የደርግ አባላት በ1966 አጋማሽ ላይ አራተኛ ክፍለ ጦር መሽገው ስለአገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሲመክሩ ሳይንሳዊ ሶሻሊዝምን በኢትዮጵያ ውስጥ ሰርጎ የማስገባቱ ጉዳይ ከአብዛኞቹ ህሊና እጅግ የራቀ ነበር። መመሪያቸው ያደረጉት “ኢትዮጵያ ትቅደም” በሚለው መፈክር በመመራት አገር ወዳድነትን የሚጠብቁም ነበር።
በታህሳስ ወር በአብዛኛው የእድገት በህብረት ዘማቾችን ለማስደሰት ሲባል ወደ “ህብረተሰባዊነት” ሲጎለምስም ዓላማው “ኢትዮጵያዊ ሶሻሊዝም”ን እንጂ ሳይንሳዊ ሶሻሊዝምን ለማስረጽ አልነበረም።
ይሁንና ደርግ ፈራ ተባ ሲል የያዘው የህብረተሰባዊነት/የሲሻሊስት/ርእዮተ አለም ወደ ፊት የሚከተለውን ርእዮተ ዓለም አቅጣጫ ያመላከተ ነበር። ያንን ፈር መልቀቁ እያደር አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆ
የማይታሰብ እየሆነ መጣ። የዚህን ዋነኛ ምክንያት ለመረዳት ተማሪዎች በኢትዮጵያ አብዮት አመጣጥ እና ሂደት ላይ የነበራቸውን ወሳኝ ሚና ማጤን ያስፈልጋል።
እንደ እውነቱ ከሆነ መለዮ ለባሹ በየካቲት 1966 ህዝባዊ አመጽ ውስጥ ብቅ ያለው ባመዛኙ ከሙያው ጋር የተያያዙ ብሶቶቹን (የደምወዝ ጭማሪ የኑሮ ሁኔታ መሻሻል፤ ወዘተ) ይዞ ነው። ጥቅማቸውን አስከብረው ወደ ካምፖቻቸው ለመመለስ ሲያስቡ “ወቴ ደሞዟን አስጨምራ ወደ ካምፕ ተመለስች”የሚለው የተማሪዎች እና የሌሎች ሲቪል ወገኖች ጉንተላ እና ወቀሳ ነው መለዮ ለባሹን ወደ ፖለቲካው መድረሻ የገፋፋው። እያደርም ደርግ ስልጣን ለመያዝ ብቻ ሳይሆን በስልጣን ላይ ለመቆየት ፈለገ። እየገነነ ከመጣው ማርክሳዊ ርዕዮት ውጭ አማራጭ እንደሌለው እየተገነዘበ መጣ።
ከ1966 እስከ 1968 ድረስ ባሉት ሁለት ዓመታት ደርግ ከዚህ ርዕዮተ አለም ጋር ለመተዋወቅ ብቻንሳይሆን ከማንም ያላነሰ ክህሎት አለኝ ለማለት ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ነበረበት። ሁል ጊዜ አንድ እርምጃ ወደ ፊት ቀድሞ ከሚገኘው የግራ ክንፍ ኃይል ጋር ለማስተካከል እና ብሎም ለመሰለፍ የነበረው ትግልና ጥረት ቀላል አልነበረም። ጥረቱም ተሳክቶ በሚያዚያ 1968 ደርግ የመጨረሻውን ርዕዮተ ዓለማዊ እምርታ በማድረግ የብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮትን በመመሪያነት አወጀ።
ለእዚህ አስደናቂ የደርግ ርዕዮተ ዓለም ምቹ ሁኔታ ከፈጠሩለት መካከል አንዱ የግራ ክንፍ ተከፋፍሎ ወደ አብዮቱ መድረክ መውጣት ነው። በተለይም ከሀገር ውጭ የሚገኘው የተማሪው ንቅናቄ አካል አብዮቱ ሲፈነዳ በሁለት አክራሪ ጎራዎች ተሰልፎ ነበር። ኋላ ገሃድ እንደ ወጣው እነዚህ ሁለት ጎራዎች የኢሕአፓና የመኢሶን ድርጅቶች ተከታዮች ነበሩ። እነዚህ ህቡዕ ድርጅቶች በተማሪ ድርጅቶች ሽፋን ደጋፊዎቻቸውን ማብዛት እና ማጠናከርን ተያያዙ።
በአብዮቱ ዋዜማ ሁለቱ ጎራዎች በዓለም አቀፉ የተማሪዎች ድርጅት አወቃቀር ላይ ከፍተኛ ክርክር አድርገዋል። የኢሕአፓ ወገኖች በአዲስ መልክ የተዋቀረውን የአለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ፌዴሬሽንን ሲደግፉ፤ የመኢሶን ተከታዮች ደግሞ በቁጥጥራቸው ስር የነበረውን ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ማህበር እንዲቀጥል ይሟገት ነበር። በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር በአብዛኛው የፌዴሬሽኑና የኢሕአፓ ደጋፊ ሲሆን። በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ማህበር ደግሞ ለሁለት ተከፍሎ ነበር።
ከአብዮቱ መፈንዳት በፊት እነዚህ ልዩነቶች ከአገር ውጭ እና በተማሪ ድርጅቶች የተወሰኑ በመሆናቸው ብዙም እርባና አልነበራቸውም። አብዮቱ በየካቲት 1966 ከፈነዳ በኋላ ግን ስለ አብዮቱ ባህሪ እና ሂደቶች ቡድኖች ካላቸው አመለካከት ጋር ተቆራኙ። በተከታዮቹ ዓመታትም ልዩነቶቹ በሀገራዊ መድረክ እየጎሉ መጥተው ቀስ በቀስ ከርእዮተ ዓለማዊ ክርክር ወደ እርስ በእርስ መጠፋፋት ዘመቻ ተሸጋገሩ።
ሚያዚያ 12 ቀን 1968 ደርግ የብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮትን መመሪያው አድርጎ ሲያውጅ በግራ ክንፍ ባቡር ጋቢና ውስጥ ከመደላደልም አልፎ መሪውን ለመጨበጥ ተዘጋጀ ማለት ይቻላል። ይህ ከቻይና አብዮት የተቀሰመ ቀመር/ፎርሙላ/ በሶስተኛው አለም ሶሻሊስት ለውጥ ለማምጣት ፍቱን መሆኑ ታመነበት። መሰረታዊ ይዘቱም በወዝ አደሩ በአርሶ አደሩ እና በተራማጅ ንዑስ ከበርቴው አብዮታዊ ጥምረት የሰፊው ህዝብ ጠላቶች ተብለው የተለዩትን ፊውዳሊዝምን ኢምፔሪያሊዝምን ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝምን መደምሰስ ነው።
ይህ ዓላማም ከብዙ ውጣ ውረዶች በኋላ እውን ሆነ። ጉዳዩን ላጤነው ደርግ እውር ድንብሩን “ኢትዮጵያ ትቅደም!”ብሎ ሰኔ 1966 የተነሳው ታህሳስ 11 ያስተዋወቀው ሶሻሊዝም እዚህ ደረጃ እና ውሳኔ ላይ ለመድረስ ምን ያህል ርቀት እንደሄደ ማየት ግልጽ ነው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2013