ኃይለማርያም ወንድሙ
ሥራ ላይ ለረጅም ጊዜ ተሳትፏል፡፡ እናቱ የቀለም ትምህርት ያልቆጠረች ብትሆንም አስኳላ ገብቶ እንዲጎብዝ ትደግፈው ነበር። ልጇን በማበርታቷም ደስተኛ ነበረች። “አንድ ቀን ይሳካልኻል” እያለች ሁሌም የሞራል ስንቅ ትሆነው ነበር። ይህ ሰው የአሁኑ የትወና ባለሙያ ማሩ እንዳለ ነው፡፡ የዛሬው የዝነኞች እረፍት ውሎ እንግዳችን።
ከልጅነቱ አንስቶ በትወና ሙያ ሲሳተፍ ቆይቷል። በሰፈር የወጣቶች ክበባትና የአደባባይ ድራማዎችን ከልጅነቱ አንስቶ ይሳተፍ ነበር፡፡ በትምህርት ቤቶች በሚኒሚዲያ ውስጥ አቃቂ ጨርቃ ጨርቅ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት (ኢንዶ) ድራማዎች ላይ ይሰራ ነበር። ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሲገባ በሚኒ ሚዲያ ክበቡ የአሁኑን ማንነቱን የቀረፁ ድራማዎች ላይ ተሳትፏል፡፡
እነዚህ ድራማዎች ለትወና ሙያው ጥሩ አስተዋፅኦ አድርገውለታል፡፡ በቤተሰብ መምሪያ፣ በቀይ መስቀል በተለያዩ ክበባት ድራማ በመስራት በሚሳተፍበት ጊዜ ህዝብን ሊያስተምሩ የሚችሉ ስራዎችን መስራቱን ያስታውሳል፡፡ ለምሳሌ ቤተሰብ መምሪያ ስለወሊድ ቁጥጥር፣ ስለ ኮንዶም አጠቃቀም ስለተለያዩ ነገሮች የሚያስተምሩ ድራማዎችን ሰርቷል፡፡
ስለሁኔታው መለስ ብሎ ሲያስታውስ ዓላማ ነበረኝ፤ ላስተምረው የምትችለው ማኅበረሰብ አለ። ያንን ማኅበረሰብ ደግሞ ማስተማር ግዴታዬ ነው። በወቅቱ ጥሩ ሥራ ሰርተናል በማለት ይገልፃል፡፡
ተዋናይ ማሩ በበርካታ ፊልሞችና ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ ሰርቷል፡፡ ለአብነት ያህልም ፋና ላይ ይተላለፍ በነበረው “ትርታ” በሚለው ድራማ የተወሰነ ክፍል ላይ ሠርቷል፡፡ አሁን በኢቢኤስ እየተላለፈ ባለው “የእግር እሳት” ድራማ ላይ እየሠራ ነው።
ሌላው ፊልሞች ላይ ነው የትወና ብቃቱን ያሳየው። እርሱ የሚቆጭበት በአግባቡ ያልታየ ፊልም እንዳለም ያነሳል። አስተማሪ የሆነውን ቁም ነገር ያለውን ሰው እንደማይመለከተው ጠቅሶ፣ ማህበረሰቡ ቀልድ ነገር መመልከት እንደሚወድ ይናገራል፡፡ የፊልምባለሙያዎችም ያስተማሩት ይሄንን መሆኑን ይገልጻል ፡፡
በብዛት ፊልሞችን መመልከት ቢቻል ሁሉም መቼታቸው ይለያይ እንጂ ተመሳሳይ መሆናቸውን ያብራራል፡፡ ገፀ ባህርዮቹም ተመሳሳይ ናቸው። እሱ የሰራቸውና የተሳተፈባቸው ፊልሞች ግን ኮስተር ባሉ /ሲሪየስ/ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩሩ ይጠቅሳል፡፡
ይህንንም ሣልሳዊ የሚባለውን ፊልም በመጥቀስ ያብራራል፡፡ የዚህ ፊልም ደራሲ ፊልሙ በሀገር ውስጥ ለጥቂት ጊዜ ከታየ በኋላ ወደ ካናዳ ይዞት ይወጣል። ጥሩ ድራማ ነበር፡፡ ለዲቪዲ ለሲዲ አልሰጥም ብሎ ይዞት ወጣ። “ሣልሳዊ” ነዳጅ ኢትዮጵያ ማውጣት እንደምትፈልግና የተለያዩ ሀይሎች ደግሞ እንዳታወጣ እንደሚፈልጉ ያመለክታል፡፡ ፊልሙ የተሠራው 2002 ዓ.ም አካባቢ ነው፡፡ ፖለቲካዊ ኪን ነው፡፡
በዚህ ፊልም ላይ ተሳትፏል፡፡ ሆኖም ወደ ህዝብ ባለመድረሱ ማዘኑን ይገልፃል፡፡ ከደራሲው ጋራ ግንኙነት ስለሌለን ስለአለበት ሁኔታ አላቅም ሲል በቁጭት ይናገራል፡፡
ሌላው “አታመልጭኝም” በሚለው ፊልም ላይ ሰርቷል፡፡ የኛ ሀገር ፊልሞች ሲሠሩ ህንፃ በመምረጥ ላይ በብዛት የሚሰሩት የሚለው ተዋናይ ማሩ ፣”አዱኛ” ግን ታሪክ የለወጠ ነው ይላል፡፡ ሲኒማው በ2007 ሲኒማ ላይ ነበረ፡፡ አንድ ትንሽ ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ሰባተኛ አካባቢ ነው የተሠራው ሲል ያብራራል፡፡
ተዋናዩ በሬዲዮ ድራማዎች እና በቴሌቪዥን ችሎት ሳምንታዊ ድራማዎች ላይ መስራቱንም ያመለክታል፤ ድራማዎቹ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መዝናኛ መተላለፋቸውንም ይጠቁማል፡፡ ሚዲያዎቻችን ድራማዎችንና ፊልሞች በማሳየት እየተፎካከሩ መሆናቸውን ይገልጻል፡፡ ለእዚህም ፋና፣ ዋልታና ኢቢኤስን ይጠቅሳል፡፡ እሱም ዋልታ ላይ በቅርቡ አየር በአየር የሚሄድ ትወና እየሠራ መሆኑን ተናግሮ፣ ሁሉም ሚዲያዎች እየተፎካከሩ መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ ኢቢ ኤስና ፋና ቃናን በደንብ ተገዳድረውታል ይላል፡፡
“በየሚዲያው ፊልሞችና ድራማዎቹ መታየታቸው ውድድር እንጂ ያስከተለው አሉታዊ ተጽእኖ የለም” የሚለው ተዋናዩ፣ ያንን ተፎካክሮ ጥሶ በማለፍ የቱርኩን ተዋናይ በመያዬ መገዳደር የማንችል የኛ የፊልምኑ ላይ ነው? በማለት ውድድር ያለበት ሙያ እድገት እንደሚያሳይ ይናገራል። የኢትዮጵያ ተውኔት ቆንጆ ነው፤ ፀሐፌ ተውኔቶቹም አቅም አላቸው፤ ችግሩ በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥኑና ተመሳሳይ ሰዎች ማሳየታቸው ላይ ነው በማለትም መሻሻል ስላለባቸው ጉዳዮች አስተያየቱን ይሰጣል፡፡ አንድ ቦታ ክፉ ገፀ ባህሪ ከሠራው ለሌላ ክፉ ፊልም ወይም ድራማ ያው ሰው ይመለመላል ሲል ገንቢ ትችት ይሰነዝራል፡፡
ለሙያዬ በጣም ትልቅ ዋጋ ከፍያለሁ የሚለው ተዋናይ ማሩ፤ ዘርፉ ለእንዲህ አይነት ሰዎች ክብር እንደማይሰጥ ይናገራል፡፡ “ትክክለኛ ሙያተኛ ሳይሆን ክብር የሚሰጠው የገንዘብ አቅም ያለው ነው፡፡ ክብር ሲሰጥ የሚስተዋለው ካለሙያው መጥቶ ቦታውን ለሚይዝ ዓይነት ሰው ነው፡፡ በዚህም ብዙ የሙያ ሰዎች ተደብቀዋል” ይላል፡፡
የእረፍት ውሎ
ተዋናይ ማሩ የእረፍት ጊዜውን በአብዛኛው የሚያሳልፈው በቤቱ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ቤት መቆየት በጣም ያስደስተዋል። ቴሌቪዥን በማየት፣ ጋዜጦችና መፃፍ በማንበብ እንዲሁም በመፃፍ የእረፍት ጊዜዬን ማሳለፍ እወዳለሁ ይላል፡፡
ፊልም ሲያይ ከመዝናናት ባሻገር ትምህርት እቀስምበታለሁ ያለው ተዋናዩ፣ ገጸባህሪያት እንዴት እንደሚተውኑ እመርበታለሁ ሲል ይገልጻል፡፡ መጻህፍት ሲያነብም ገጸባህሪያቱ እንዴት እንደተሳሉ እንደሚመለከት፣ በመካከላቸው ያለው ገጭት አጓጊ ከሆነ ወደፊት እንዴት መጻፍ አለብኝ በሚል ራሴን እንዳይ ይረዳኛል ብሏል፡፡ ሌሎችም የእረፍት ጊዜያቸውን በመጠጥ ቤት ከሚያሳልፉ ወደጥበቡ ዞር በማለት ራሳቸውን ቢያስተምሩ ጥሩ ነው ሲልም ይመክራል፡፡
ስክሪፕቶች እና ግጥሞችን እፅፋለሁ የሚለው ተዋናዩ፣ ብዙ ሥራዎች በእጁ ላይ እንደሚገኙ ነገር ግን ለህዝብ አሳትሞ እንዳላደረሳቸው ይናገራል፡፡ ስራዎቹ ለህትመት ያልበቁበት ምክንያት ደግሞ በአቅም ማጣት መሆኑን ያነሳል፡፡
“ለሙያው ስትሠራ ብዙውን ጊዜ ፋይናንስ ላይ ትኩረት አትሰጥም፤ ሰውም ቁም ነገር ያለው ነገር አይፈልግም” የሚለው ተዋናዩ አንድ ዘፋኝ የኔን ግጥም በነፃ ብሰጠው አይሰራም “አበድኩልሽ ሞትኩልሽ” የሚሉ ተራ ግጥሞችን
ግን ቢሰራ ግን አድማጭ እንደሚያገኝ ነው የሚናገረው። ከ100 በላይ የዘፈን ግጥሞች እንዳሉት ተናግሮ ፣ ወደ አራት መጽሐፍ የሚጠጉ የግጥም መድብሎች ማዘጋጀቱን ነግሮናል፡፡ እነዚህን ስራዎች የሚሰራቸው በእረፍት ግዜው ነው። ያለውን ትርፍ ግዜ በዚህ መልኩ ማሳለፉ እንደሚያስደስተው ነው የሚገልፀው።
እንደ መውጫ
ተዋናዩ በመጨረሻ መልዕክቱ ላይ ቢሆን ብሎ የሚያስበውን ምክረ ሃሳብ ለመገናኛ ብዙሃን ይሰጣል። በፊልም ሙያ ላይ “ሁሉም ነገር አንድ ዘውግ ላይ አንድ ቦይ ውስጥ መፍሰስ የለበትም” ያለው ተዋናዩ፣ ህይወት አንድ ሺ መንገዶች ስላሏት ይህን አይነት ፍልስፍና መከተል ይኖርብናል ይላል።
ለዚህ ደግሞ ጠንካራ ተቺ መገናኛ ብዙሃን ሊፈጠሩ እንደሚገባ ያነሳል። በተለይ መገናኛ ብዙሃኑ የተደበቁ የኪነጥበብ ሰዎችን ፈልጎ ማግኘት መቻልና ዘርፉን ተቀላቅለው አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ መደረግ እንዳለበት በመግለፅ ሃሳቡን ይቋጫል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 11/2013